በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍትሕ ጥያቄዬ መልስ ያገኘበት መንገድ

የፍትሕ ጥያቄዬ መልስ ያገኘበት መንገድ

የፍትሕ ጥያቄዬ መልስ ያገኘበት መንገድ

ኡርሱላ ሜነ እንደተናገሩት

ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ሰው ፍትሕና እኩልነት በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ ሲኖር የማየት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ይህ ምኞቴ ምሥራቅ ጀርመን በኮሚኒስት ሥርዓት በምትተዳደርበት ወቅት ዘብጥያ እስከመውረድ አድርሶኛል። የሚገርመው ነገር፣ የፍትሕ ጥያቄዬ መልስ ያገኘው እስር ቤት ሳለሁ ነበር። እስቲ ይህ እንዴት እንደሆነ ላውጋችሁ።

የተወለድኩት ከ1,200 የሚበልጡ ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ ባላት ሃሌ በተባለች የጀርመን ከተማ ሲሆን ጊዜውም 1922 ነበር። ከበርሊን በስተደቡብ ምዕራብ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኘው ሃሌ የፕሮቴስታንት እምነት በጣም ከተስፋፋባቸው ጥንታዊ ቦታዎች አንዷ ነበረች። ካቴ የተባለችው እህቴ የተወለደችው በ1923 ነው። አባቴ በጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለግል ነበር። እናቴ ደግሞ በትያትር ቤት ውስጥ በድምፃዊነት ትሠራ ነበር።

ኢፍትሐዊነትን የማስወገድ ፍላጎት እንዲቀረጽብኝ ያደረገው አባቴ ነው። አባቴ ጦር ሠራዊቱን ለቆ ሲወጣ አንድ መደብር ገዝቶ ነበር። አብዛኞቹ ደንበኞቹ ድሆች ስለነበሩ ለእነሱ ካለው ርኅራኄ የተነሳ ዱቤ ይሰጣቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በጎ ምግባሩ የኋላ ኋላ ለኪሳራ ዳረገው። የአባቴ ተሞክሮ እኩልነትንና ፍትሕን ለማስፈን የሚደረገው ትግል ከሚታሰበው በላይ ከባድና ውስብስብ እንደሆነ ሊያስተምረኝ ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ በወጣትነት ዘመን ሁሉ ነገር የሚቻል ስለሚመስል ይህን ሐሳቤን ከውስጤ ማውጣት አስቸገረኝ።

እናታችን እኔንና ካቴን ሙዚቃ፣ ዘፈንና ዳንስ ስላስተማረችን የኪነ ጥበብ ክህሎትን ከእሷ መውረስ ችያለሁ። በልጅነቴ ደስተኛና ቀልጣፋ የነበርኩ ሲሆን ከእህቴ ጋር ግሩም ሕይወት አሳልፈናል፤ በ1939 ግን ሁኔታው ተለወጠ።

አስፈሪው ጊዜ ጀመረ

መደበኛ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ የባሌ ዳንስ ሥልጠና በሚሰጥ ትምህርት ቤት ገብቼ ተማርኩ፤ በተጨማሪም በዚህ ትምህርት ቤት ሳለሁ ታዋቂ የዳንስ አስተማሪ የሆነችው ሜሪ ቪግማን አውስድሩክስታንዝ የሚባለውን ስሜት ገላጭ የዳንስ ዓይነት አስተምራኛለች። ሜሪ ቪግማን፣ ስሜትን በዳንስ የመግለጽን ጥበብ በማስተዋወቅ ረገድ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት ሰዎች አንዷ ናት። በዚያ ወቅት ሥዕል መሳልም ጀመርኩ። በመሆኑም በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሳለሁ የነበረኝ ሕይወት አስደሳች ከመሆኑም በላይ በዚህ ወቅት ብዙ ነገር ተምሬያለሁ። ዳሩ ምን ያደርጋል፣ በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ሁሉ ነገር ተቀየረ። በ1941 ደግሞ ሌላ አስደንጋጭ ነገር ደረሰብኝ፤ አባቴ በሳንባ ነቀርሳ ሕይወቱ አለፈ።

ጦርነት አስፈሪ ነገር ነው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር ገና 17 ዓመቴ ቢሆንም በወቅቱ ዓለም እንዳበደ ተሰምቶኝ ነበር። ከዚህ በፊት ጤነኛ አስተሳሰብ የነበራቸው በርካታ ሰዎች የናዚን የእብደት አካሄድ ሲከተሉ ተመልክቻለሁ። ከዚያም ችጋር፣ ሞትና ጥፋት ተከተለ። ቤታችን በቦምብ በመመታቱ ክፉኛ ተጎዳ፤ እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት አያሌ የቤተሰቤ አባላት ተገደሉ።

ጦርነቱ በ1945 ባበቃበት ጊዜም እኔ፣ እናቴና ካቴ የምንኖረው በሃሌ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ እናት የነበርኩ ሲሆን ትዳሬም ውጥረት የሰፈነበት ነበር። ከባለቤቴ ጋር በመለያየቴ ለእኔም ሆነ ለልጄ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ በዳንስና በሥዕል ሙያ ተሰማራሁ።

ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን ለአራት የተከፈለ ሲሆን እኛ የነበርንባት ከተማ በሶቪየት ኅብረት ትተዳደር ነበር። በመሆኑም ሁላችንም በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ያለውን ኑሮ መልመድ ግድ ሆነብን። አብዛኛውን ጊዜ ምሥራቅ ጀርመን ተብሎ ይጠራ የነበረው እኛ ያለንበት ክፍል በ1949 የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ በመባል ራሱን የቻለ አገር ሆነ።

በኮሚኒዝም ሥርዓት የነበረው ሕይወት

በኮሚኒዝም አገዛዝ ወቅት እናቴ በመታመሟ እሷን መንከባከብ ነበረብኝ። በአካባቢያችን በሚገኝ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የቢሮ ሥራ አገኘሁ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በወቅቱ ይፈጸም የነበረውን አንዳንድ የፍትሕ መዛባት ለማጋለጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ተማሪዎች ጋር መገናኘት ጀመርኩ። ለምሳሌ አንድ ወጣት አባቱ ከዚያ ቀደም የናዚ ፓርቲ አባል ስለነበረ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዳይከታተል ተከልክሎ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ከዚህ ተማሪ ጋር ብዙ ጊዜ ሙዚቃ አብረን እንጫወት ስለነበረ በደንብ አውቀዋለሁ። ‘አባቱ በሠራው ነገር እሱ ለምን ይሠቃያል?’ ብዬ አሰብኩ። ከተማሪዎቹ ጋር የነበረኝ ግንኙነት እየጨመረ ሲመጣ ተቃውሞዬን በተግባር መግለጽ ጀመርኩ። እንዲያውም በአንድ ወቅት በአካባቢው ፍርድ ቤት ሕንፃ ላይ ከውጭ በኩል በራሪ ወረቀቶችን እስከመለጠፍ ደርሻለሁ።

የአካባቢ ሰላም አስከባሪ ኮሚቴ ውስጥ በጸሐፊነት በምሠራበት ጊዜ እንድጽፍ የምታዘዛቸው አንዳንድ ደብዳቤዎች ያበሳጩኝ ነበር። በአንድ ወቅት ኮሚቴው በምዕራብ ጀርመን በሚኖሩ አንድ አረጋዊ ሰው ላይ ጥርጣሬ በማስነሳት ፖለቲካዊ ዓላማውን ለማሳካት ስለፈለገ የኮሚኒስት ፕሮፓጋንዳ የያዘ ጽሑፍ ለእኚህ ሰው ለመላክ አስቦ ነበር። በእኚህ ሰው ላይ ሊደረግ በታሰበው ሸፍጥ በጣም ስለተናደድኩ ሊላክ የተዘጋጀውን ጥቅል ቢሮ ውስጥ ደበቅሁት። በዚህም የተነሳ ጽሑፉ ሳይላክ ቀረ።

“በክፍሉ ውስጥ ካሉት ሁሉ እጅግ አደገኛ” የሆነችው ሴት ተስፋ ሰጠችኝ

ሰኔ 1951 ሁለት ሰዎች ወደ ቢሮዬ መጡና “በቁጥጥር ሥር ውለሻል” አሉኝ። ከዚያም ሮተር ኦችሴ (ቀይ በሬ ማለት ነው) ተብሎ ወደሚጠራ እስር ቤት ወሰዱኝ። ከአንድ ዓመት በኋላ፣ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመገርሰስ በመሞከር ወንጀል ተከሰስኩ። ይህ ክስ የቀረበብኝ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን በመደገፍ ከዚያ ቀደም ወረቀት ማሰራጨቴን አንድ ተማሪ ሽታዚ ለተባሉት የደኅንነት ፖሊሶች ስለጠቆመብኝ ነው። ችሎቱ ለይስሙላ ያህል የተሰየመ ነበር፤ ምክንያቱም እኔ ያቀረብኩትን የመከላከያ ሐሳብ ማንም ከቁም ነገር አልቆጠረውም። በመሆኑም ስድስት ዓመት ተፈረደብኝ። በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት በመታመሜ ወደ እስር ቤቱ ሆስፒታል የተወሰድኩ ሲሆን በክፍሉ ውስጥ 40 የሚያህሉ ሴቶች ነበሩ። በክፍሉ ውስጥ ያየኋቸው ሰዎች በሙሉ ፍጹም ደስታ የራቃቸው መሆኑን ስመለከት ጭንቀት ያዘኝ። ከዚያም ወደ በሩ በመሄድ መዝጊያውን በእጄ ደበደብኩት።

“ምን ፈለግሽ?” በማለት ወታደሩ ጠየቀኝ።

“ከዚህ ቦታ መውጣት እፈልጋለሁ። ብትፈልጉ ብቻዬን እሰሩኝ፤ ብቻ ከዚህ ቦታ አውጡኝ!” በማለት ጮኽኩ። እሱ ግን ጥያቄዬን ከምንም አልቆጠረውም፤ ድሮስ ምን ይጠበቃል! ጥቂት እንደቆየሁ ከሌሎቹ ለየት ያለች አንዲት ሴት ተመለከትኩ። ውስጣዊ ሰላም እንዳላት ከዓይኖቿ መመልከት ይቻላል። እኔም ጎኗ ሄጄ ተቀመጥኩ።

“እኔ አጠገብ ከተቀመጥሽ መጠንቀቅ ይኖርብሻል” ስትለኝ በጣም ገረመኝ። አክላም “የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ሌሎቹ የሚያዩኝ በክፍሉ ውስጥ ካሉት ሁሉ እጅግ አደገኛ እንደሆንኩ አድርገው ነው” አለችኝ።

በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የኮሚኒስት ሥርዓት ጠላቶች ተደርገው እንደሚታዩ አላውቅም ነበር። ስለ እነሱ የማውቀው ነገር ቢኖር ሕፃን ሳለሁ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል የሚጠሩበት ስም ነው) አባቴ ጋ አዘውትረው ይመጡ እንደነበረ ነው። እንዲያውም አባቴ “እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትክክል ናቸው!” ብሎ ሲናገር ትዝ ይለኛል።

በርታ ብሩዌግሚየ የምትባለውን ይህችን ተወዳጅ ሴት ማግኘቴ እፎይታ እንዲሰማኝ ስላደረገኝ አለቀስኩ። “እባክሽ ስለ ይሖዋ ንገሪኝ” አልኳት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብረን ረጅም ሰዓት እናሳልፍ የነበረ ሲሆን በአብዛኛው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንወያይ ነበር። በርካታ ነገሮችን የተማርኩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል እውነተኛው አምላክ ይሖዋ የፍቅር፣ የፍትሕና የሰላም አምላክ ስለመሆኑ የሚናገረው ትምህርት ይገኝበታል። በተጨማሪም አምላክ ክፉና ጨካኝ የሆኑ ሰዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ሙሉ በሙሉ እንደሚያስተካክል ተማርኩ። መዝሙር 37:10, 11 “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል።

ከእስር ስለቀቅ ወደ ምዕራብ ጀርመን ሸሽቼ ሄድኩ

በእስር ቤት ከአምስት ዓመት በላይ ካሳለፍኩ በኋላ በ1956 ተለቀቅሁ። ከእስር ከተፈታሁ ከአምስት ቀን በኋላ ሃነሎርና ሳቢነ ከተባሉ ሁለት ሴት ልጆቼ ጋር ከምሥራቅ ጀርመን ሸሽቼ ወደ ምዕራብ ጀርመን ሄድኩኝ። እዚያ እያለሁ ከባለቤቴ ጋር የተፋታሁ ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደገና ተገናኘሁ። መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናሁ ስሄድ ይሖዋ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምቼ ለመኖር ብዙ ለውጦችን ማድረግ እንደሚኖርብኝ ተገነዘብኩ። እናም እነዚህን ለውጦች ሁሉ አድርጌ በ1958 ተጠመቅሁ።

ከጊዜ በኋላ ክላውስ ሜነ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር አገባሁ። እኔና ክላውስ በትዳራችን ደስተኛ የነበርን ሲሆን ቤንጃሚንና ታቢያ የሚባሉ ሁለት ልጆችም ወልደናል። ይሁንና ከ20 ዓመታት በፊት አንድ የሚያሳዝን ነገር አጋጠመኝ፤ ባለቤቴ በደረሰበት አደጋ ሳቢያ ሕይወቱ በማለፉ ውድ አጋሬን ከጎኔ አጥቻለሁ። ይሁን እንጂ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሙታን እንደገና እንደሚነሱ ስለማውቅ በትንሣኤ ተስፋ በጣም እጽናናለሁ። (ሉቃስ 23:43፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) በተጨማሪም አራቱም ልጆቼ ይሖዋን የሚያገለግሉ መሆናቸው በእጅጉ ያጽናናኛል።

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ ምክንያቱም እውነተኛ ፍትሕ ማስፈን የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ አውቄያለሁ። ይሖዋ ከሰዎች በተለየ መልኩ ያለንበትን ሁኔታ ጨምሮ የኋላ ታሪካችንን ማለትም ብዙውን ጊዜ ከሰዎች ዓይን ሊሰወሩ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ከግምት ያስገባል። ይህን ውድ እውቀት ማግኘቴ አሁንም እንኳ ሰላም ሰጥቶኛል፤ በተለይ በራሴም ሆነ በሌሎች ላይ የፍትሕ መዛባት ሲደርስ ሰላሜን ጠብቄ እንድኖር ይረዳኛል። መክብብ 5:8 “በአንድ አገር ግፍ ሲሠራና መብት በመንፈግ ፍትሕ ሲጓደል ባየህ ጊዜ አትደነቅ፤ እያንዳንዱ ገዥ የበላይ ተመልካች አለው፤ ከሁሉም በላይ የሆነ ሌላ ተመልካች ደግሞ አለ” ይላል። (የታረመው የ1980 ትርጉም) “ከሁሉም በላይ” የሆነው ፈጣሪያችን እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ዕብራውያን 4:13 “ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው” በማለት ይናገራል።

ያሳለፍኳቸውን 90 የሚያህሉ ዓመታት ወደኋላ ስመለከት

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በናዚና በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር መኖር ምን ይመስል እንደነበር ይጠይቁኛል። ሁለቱም አገዛዞች ቢሆኑ ለኑሮ የሚመቹ አልነበሩም። እንደማንኛውም ሰብዓዊ መስተዳድሮች ሁሉ የናዚና የኮሚኒስት አገዛዞችም ያረጋገጡት ነገር ቢኖር ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንደማይችሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ [ይሆናል]” በማለት በግልጽ ይናገራል።​—መክብብ 8:9

ምንም ተሞክሮ ባልነበረኝ የወጣትነት ዕድሜዬ ሰዎች ፍትሐዊ አገዛዝ ያመጣሉ ብዬ ተስፋ አደርግ ነበር። አሁን ግን የተሻለ ግንዛቤ አለኝ። እውነተኛ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ሊያመጣ የሚችለው ፈጣሪያችን ብቻ ነው፤ ይሖዋ ክፉዎችን በሙሉ በማጥፋት፣ ምንጊዜም ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም የሚያስቀድመው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርን እንዲያስተዳድር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር “ጽድቅን ወደድክ፣ ዓመፅን ጠላህ” ይላል። (ዕብራውያን 1:9) ይህን ድንቅና ፍትሐዊ የሆነ ንጉሥ እንዳውቅ ስላደረገኝ አምላክን በጣም አመሰግነዋለሁ፤ በዚህ ንጉሥ አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ!

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሴት ልጆቼ ከሃነሎርና ከሳቢነ ጋር ምዕራብ ጀርመን ከገባን በኋላ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከልጄ ከቤንጃሚንና ከባለቤቱ ከሳንድራ ጋር