በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም የይሖዋን ተግሣጽ ተቀበል

ምንጊዜም የይሖዋን ተግሣጽ ተቀበል

“የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ።”—ምሳሌ 3:11

1. መለኮታዊ ተግሣጽ መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?

 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ሁላችንም አምላክ የሚሰጠንን ተግሣጽ እንድንቀበል የሚያነሳሳንን ጥሩ ምክንያት ገልጿል። ሰሎሞን “ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻልና” ብሏል። (ምሳሌ 3:11, 12) አዎን፣ የሰማዩ አባትህ የሚገሥጽህ ስለሚወድህ ነው።

2. “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ፍቺ ምንድን ነው? አንድ ሰው ተግሣጽን ከየት ማግኘት ይችላል?

2 “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ቅጣትን፣ እርማትን፣ መመሪያ መስጠትንና ትምህርትን ያመለክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 12:11) መለኮታዊ ተግሣጽን ተቀብሎ በሥራ ላይ ማዋል የጽድቅ ጎዳናን እንድትከተልና በዚህም የተነሳ ቅዱስ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንድትቀራረብ ይረዳሃል። (መዝሙር 99:5) ይህን መሰሉን እርማት ከእምነት አጋሮችህና በክርስቲያን ጉባኤ ከምታገኛቸው ትምህርቶች እንዲሁም የአምላክን ቃል ብሎም ‘ታማኙ መጋቢ’ የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በምታጠናበት ወቅት ልታገኝ ትችላለህ። (ሉቃስ 12:42-44) በአንድ ጉዳይ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብህ የሚጠቁም ምክር በምታገኝበት ጊዜ እጅግ አመስጋኝ ልትሆን ይገባል! ይሁንና ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ ምን ዓይነት ተግሣጽ ሊያስፈልግ ይችላል?

አንዳንዶች የሚወገዱት ለምንድን ነው?

3. አንድ ሰው የሚወገደው መቼ ነው?

3 የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ያጠናሉ። በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች በተመለከተ ትምህርት ይሰጣል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ይሖዋ ከእነርሱ ምን እንደሚጠብቅባቸው ያውቃሉ። አንድ የጉባኤ አባል የሚወገደው ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ንስሐ ሳይገባ ከቀረ ብቻ ነው።

4, 5. ውገዳን በተመለከተ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ቀርቧል? በሰውየው ላይ የተጣለው የውገዳ ውሳኔ እንዲነሳለት ለቆሮንቶስ ጉባኤ ማሳሰቢያ የተሰጠው ለምን ነበር?

4 ውገዳን በተመለከተ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ተመልከት። በአንድ ወቅት የቆሮንቶስ ጉባኤ ‘የአባቱን ሚስት በማግባት በአረማውያን ዘንድ እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ርኩሰት’ የፈጸመን ሰው በቸልታ ተመልክቶ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችን “ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን [ምናልባት] ትድን ዘንድ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ” አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 5:1-5) ኃጢአት የሠራ ሰው ሲወገድና ለሰይጣን ሲሰጥ ዳግም የሰይጣን ዓለም ክፍል ይሆናል። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ዓይነቱ እርምጃ ግለሰቡ ሊያሳድረው የሚችለውን መጥፎ ተጽዕኖ ከጉባኤው ለማስወገድ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ በጉባኤው ውስጥ አምላካዊ ባሕርያት የሚንጸባረቁበት ጥሩ “መንፈስ” እንዲሰፍን ያደርጋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:22፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11-13

5 ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ኃጢአት በፈጸመው ግለሰብ ላይ ያሳለፉትን የውገዳ ውሳኔ እንዲያነሱለት ነገራቸው። ለምን? ይህን ማድረግ ያለባቸው “ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ” መሆኑን ገልጾላቸዋል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ኃጢአተኛው ንስሐ ከመግባቱም ባሻገር በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ ሕይወት መምራት ጀምሯል። (2 ቆሮንቶስ 2:8-11) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህንን ሰው እንደገና ወደ ጉባኤው እንዲመለስ ለማድረግ ፈቃደኞች ካልሆኑ ልክ ሰይጣን እንደሚፈልገው ደግነት የጎደላቸውና ምሕረት የሌላቸው ስለሚሆኑ ዲያብሎስ ሌላ መግቢያ ቀዳዳ ያገኛል። በመሆኑም እነዚህ ክርስቲያኖች ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት የተጸጸተውን ሰው ‘ይቅር ብለውትና አጽናንተውት’ መሆን አለበት።—2 ቆሮንቶስ 2:5-7

6. ውገዳ ምን ዓላማ ያከናውናል?

6 ውገዳ ምን ዓላማ ያከናውናል? ውገዳ የይሖዋ ቅዱስ ስም ከነቀፋ ነጻ እንዲሆንና የሕዝቦቹ መልካም ስም እንዳይጎድፍ ያደርጋል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16) ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛ ከጉባኤ እንዲወገድ መደረጉ የአምላክ የአቋም ደረጃዎች እንዲከበሩና የጉባኤው መንፈሳዊ ንጽሕና ተጠብቆ እንዲኖር ይረዳል። ንስሐ ያልገባውንም ሰው ወደ አእምሮው እንዲመለስ ሊረዳው ይችላል።

ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው

7. ዳዊት ኃጢአቱን አለመናዘዙ ምን ጉዳት አስከትሎበታል?

7 ከባድ ኃጢአት ከሚፈጽሙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ እውነተኛ ንስሐ ስለሚገቡ ከጉባኤ አይወገዱም። እውነት ነው፣ ለአንዳንዶች እውነተኛ ንስሐ መግባት ቀላል ላይሆን ይችላል። መዝሙር 32ን ያቀናበረውንና የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን የዳዊትን ሁኔታ ተመልከት። ይህ መዝሙር ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ የሠራውን ኃጢአት ሳይናዘዝ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ እንደነበር ያመለክታል። የበጋ ትኩሳት አንድን ዛፍ እንደሚያደርቀው ሁሉ ዳዊትም ኃጢአት መሥራቱ ያስከተለበት ውጥረት ኃይሉን አሟጦበት ነበር። ዳዊት አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ሥቃይ የደረሰበት ቢሆንም ‘መተላለፉን በተናዘዘ ጊዜ’ ይሖዋ ‘ይቅር ብሎታል’። (መዝሙር 32:3-5) በመሆኑም “እግዚአብሔር ኃጢአቱን የማይቈጥርበት . . . ሰው፣ እርሱ ቡሩክ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 32:1, 2) የአምላክን ምሕረት ማግኘት ምንኛ ያስደስታል!

8, 9. ንስሐ መግባት የሚገለጸው እንዴት ነው? አንድ የተወገደ ሰው የውገዳ ውሳኔው እንዲነሳለት ንስሐ መግባቱ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

8 ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ኃጢአተኛ ምሕረት ለማግኘት ከፈለገ ንስሐ መግባት ይኖርበታል። ሆኖም በሠሩት ነገር ማፈርም ሆነ ምናልባት እጋለጥ ይሆናል ብሎ መስጋት ንስሐ መግባትን አያመለክትም። “ንስሐ መግባት” አንድ ሰው በሠራው መጥፎ ተግባር ተጸጽቶ “አስተሳሰቡን መለወጡን” የሚያሳይ ነው። ንስሐ የገባ ሰው ‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ ይኖረዋል፤ እንዲሁም ‘ስህተቱን ለማረም’ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።—መዝሙር 51:17፤ 2 ቆሮንቶስ 7:11 NW

9 አንድ የተወገደ ሰው ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እንደገና እንዲመለስ ንስሐ መግባቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። ግለሰቡ ተወግዶ የተወሰነ ጊዜ ስላሳለፈ ብቻ ወደ ጉባኤ እንዲመለስ ይፈቀድለታል ማለት አይደለም። ውገዳው ከመነሳቱ በፊት የልቡ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መለወጥ ይኖርበታል። የፈጸመውን ኃጢአት ክብደትና በይሖዋም ሆነ በጉባኤው ላይ ያመጣውን ነቀፌታ መገንዘብ ይገባዋል። ኃጢአት የሠራው ግለሰብ ንስሐ መግባት፣ ይቅርታ ለማግኘት ከልብ መጸለይና ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር አለበት። ይህ ሰው ወደ ጉባኤ ለመመለስ ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ ንስሐ መግባትና “የንስሓም ፍሬ” ማሳየት ይገባዋል።—የሐዋርያት ሥራ 26:20

ኃጢአትን መናዘዝ ለምን አስፈለገ?

10, 11. ኃጢአታችንን ለመደበቅ መሞከር የሌለብን ለምንድን ነው?

10 ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ‘ኃጢአቴን ለሰው ከተናገርኩ፣ የሚያሳፍሩ ጥያቄዎችን መመለስ ግድ ሊሆንብኝ ብሎም ልወገድ እችላለሁ። ዝም ካልኩ ግን ይህ ሁሉ አይደርስብኝም እንዲሁም ማንኛውም የጉባኤው አባል መቼም ቢሆን ሁኔታውን አያውቅም’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም። እነዚህ ነጥቦች ምንድን ናቸው?

11 ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር አምላክ . . . ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል” ቢሆንም ሕዝቦቹን “በመጠኑ” ከመቅጣት ወደኋላ አይልም። (ዘፀአት 34:6, 7፤ ኤርምያስ 30:11) ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ይህን ኃጢአትህን ለመደበቅ ጥረት የምታደርግ ከሆነ እንዴት የአምላክን ምሕረት ማግኘት ትችላለህ? ይሖዋ ስለሁኔታው ያውቃል፤ እንዲሁም ኃጢአትን ችላ ብሎ አያልፍም።—ምሳሌ 15:3፤ ዕንባቆም 1:13

12, 13. ኃጢአትን ለመደበቅ መሞከር ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

12 ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ መናዘዝህ ዳግም ጥሩ ሕሊና እንድታገኝ ይረዳሃል። (1 ጢሞቴዎስ 1:18-20) ኃጢአትህን ከመናዘዝ ወደኋላ የምትል ከሆነ ግን ሌሎች ኃጢአቶችን ወደመፈጸም የሚመራ የረከሰ ሕሊና እንዲኖርህ ሊያደርግ ይችላል። ኃጢአት የፈጸምከው በሌላ ሰው አሊያም በጉባኤው ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ መሆኑን ልብ በል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “የእግዚአብሔር ዙፋን በሰማይ ነው። ዐይኖቹ ሰዎችን ይመለከታሉ፤ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል።”—መዝሙር 11:4, 5

13 ይሖዋ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ሳይናዘዝ ንጹሕ በሆነው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለመኖር የሚጥርን ሰው አይባርከውም። (ያዕቆብ 4:6) በመሆኑም ኃጢአት ሠርተህ ከነበረና አሁን ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ሐቁን ከመናዘዝ ወደኋላ አትበል። ያለበለዚያ ግን ከፈጸምከው ከባድ ኃጢአት ጋር የተያያዙ ምክሮችን ባነበብክና በሰማህ ቁጥር ሕሊናህ ይወቅስሃል። ይሖዋ በንጉሥ ሳኦል ላይ እንዳደረገው መንፈሱን ቢወስድብህስ? (1 ሳሙኤል 16:14) የይሖዋ መንፈስ ከራቀህ ከዚህም የባሰ ከባድ ኃጢአት ልትፈጽም ትችላለህ።

በታማኝ ወንድሞችህ ተማመን

14. አንድ ኃጢአት የሠራ ሰው በያዕቆብ 5:14, 15 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው?

14 ታዲያ፣ አንድ ሰው ኃጢአት በመሥራቱ ከተጸጸተ ምን ማድረግ ይኖርበታል? “የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል።” (ያዕቆብ 5:14, 15) ሽማግሌዎችን ቀርቦ ማነጋገር ግለሰቡ ‘ለንስሐ የሚገባ ፍሬ ማፍራቱን’ የሚያሳይበት አንዱ መንገድ ነው። (ማቴዎስ 3:8) እነዚህ ታማኝና አፍቃሪ የሆኑ ወንዶች ‘በጌታ [በይሖዋ] ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለታል።’ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮቻቸው ልክ እረፍት እንደሚሰጥ ዘይት እውነተኛ ንስሐ የገባውን ሰው እንደሚያጽናኑት የተረጋገጠ ነው።—ኤርምያስ 8:22

15, 16. ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ በሕዝቅኤል 34:15, 16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አምላክ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

15 እረኛችን የሆነው ይሖዋ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስራኤላውያንን ከባቢሎን ምርኮ ባስለቀቃቸው እንዲሁም በ1919 መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ግዞት ነጻ ባወጣቸው ጊዜ ግሩም የሆነ ፍቅራዊ ምሳሌ ትቶልናል! (ራእይ 17:3-5፤ ገላትያ 6:16) እንዲህ በማድረግም እንደሚከተለው ሲል የገባውን ቃል ፈጽሟል:- “እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸዋለሁም . . . የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ።”—ሕዝቅኤል 34:15, 16

16 ይሖዋ ምሳሌያዊ በጎቹን ይመግባቸዋል፣ ያስመስጋቸዋል ወይም አስተማማኝ በሆነ ቦታ ያሳርፋቸዋል እንዲሁም የባዘኑትን ይፈልጋል። በተመሳሳይም ክርስቲያን እረኞች የአምላክ መንጋ በደንብ መመገቡንና ጥበቃ ማግኘቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች ከጉባኤ ርቀው የባዘኑ በጎችን ይፈልጋሉ። አምላክ ‘የተጐዱትን እንደሚጠግን’ ሁሉ የበላይ ተመልካቾችም በአንድ ሰው አነጋገር ወይም በራሳቸው አድራጎት የተጎዱ በጎችን ‘ይጠግናሉ።’ ከዚህም ባሻገር አምላክ ‘የደከሙትን እንደሚያበረታ’ ሁሉ ሽማግሌዎችም፣ ምናልባት በራሳቸው ኃጢአት ምክንያት በመንፈሳዊ የታመሙትን ይረዳሉ።

እረኞች ሌሎችን የሚረዱት እንዴት ነው?

17. ሽማግሌዎች የሚሰጡትን መንፈሳዊ እርዳታ ከመፈለግ ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?

17 ሽማግሌዎች ለሌሎች ‘በፍርሀት ምሕረት እንዲያሳዩ’ የተሰጣቸውን ምክር በደስታ ይቀበላሉ። (ይሁዳ 23) አንዳንድ ክርስቲያኖች የጾታ ብልግና በመፈጸም ከባድ ኃጢአት ሠርተዋል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ንስሐ ከገቡ መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑት ሽማግሌዎች በርኅራኄና በፍቅር እንደሚይዟቸው ሊተማመኑ ይችላሉ። ጳውሎስ ራሱን ጨምሮ እነዚህን ስለመሰሉ ወንዶች ሲናገር “ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) ስለሆነም መንፈሳዊ እርዳታቸውን ከመፈለግ ፈጽሞ ወደኋላ ማለት አይኖርብህም።

18. ሽማግሌዎች ኃጢአት የፈጸሙ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?

18 ከባድ ኃጢአት ከሠራህ በሽማግሌዎች ላይ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው? የእነዚህ ሰዎች ተቀዳሚ ኃላፊነት የአምላክን መንጋ እረኛ ሆኖ መጠበቅ ስለሆነ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:1-4) ማንኛውም አፍቃሪ እረኛ ለማገድ የማያስቸግረውንና ራሱን ችግር ውስጥ በመክተቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት የሚጮህን በግ አይመታም። በመሆኑም ሽማግሌዎች አንድ የእምነት ባልንጀራቸው ኃጢአት በሚሠራበት ወቅት ትኩረት የሚያደርጉት ወንጀል ሠርቷልና መቀጣት አለበት በሚለው ላይ ሳይሆን በተሠራው ኃጢአትና ግለሰቡ በተቻለ መጠን በመንፈሳዊ ሊያገግም በሚችልበት ሁኔታ ላይ ነው። (ያዕቆብ 5:13-20) ሽማግሌዎች በጽድቅ መፍረድና ‘ለመንጋው መራራት’ ይገባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ ኢሳይያስ 32:1, 2) እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ሽማግሌዎችም ‘ፍትሕን ማድረግ፣ ምሕረትን መውደድና በአምላክ ፊት በትሕትና መራመድ’ አለባቸው። (ሚክያስ 6:8) ‘[ከይሖዋ] የማሰማሪያ በጎች’ ሕይወትና ከሚያቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ውሳኔዎችን ስናደርግ እነዚህ ባሕርያት በእጅጉ ያስፈልጉናል።—መዝሙር 100:3

19. ክርስቲያን ሽማግሌዎች አንድን ሰው ለማስተካከል የሚጥሩት በምን ዓይነት ዝንባሌ ነው?

19 ክርስቲያን እረኞች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ሲሆኑ የመንፈሱን አመራር ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉ። አንድ ሰው ሳያስበው “በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ” መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ‘በገርነት ሊመልሱት’ መጣር ይገባቸዋል። (ገላትያ 6:1፤ የሐዋርያት ሥራ 20:28) አሳቢ የሆነ የሕክምና ባለሙያ እጁ ወይም እግሩ ላይ ስብራት ያጋጠመውን ሰው እንዳያሳምመው ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ በተገቢው ሁኔታ እንደሚጠግነው ሁሉ ሽማግሌዎችም በገርነት ሆኖም መለኮታዊውን መሥፈርት በጠበቀ መልኩ ኃጢአት የሠራውን ግለሰብ አስተሳሰብ ለማስተካከል ይጥራሉ። (ቈላስይስ 3:12) ሽማግሌዎች ምሕረት የሚያደርጉት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ተመሥርተው ጉዳዩን በጸሎት ካሰቡበት በኋላ ስለሆነ ውሳኔያቸው የአምላክን አመለካከት ያንጸባርቃል።—ማቴዎስ 18:18 NW

20. አንድ ግለሰብ ተግሣጽ እንደተሰጠው ለጉባኤው ማስታወቂያ መናገር የሚያስፈልገው መቼ ነው?

20 የተሠራው ኃጢአት በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚታወቅ ወይም ደግሞ መታወቁ የማይቀር ከሆነ የጉባኤውን ስም ከነቀፋ ለመጠበቅ ሲባል ማስታወቂያ መነገሩ ተገቢ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጉባኤው ስለ ጉዳዩ ማወቁ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማስታወቂያ ሊነገር ይችላል። በፍርድ ኮሚቴ ተግሣጽ ተሰጥቶት በመንፈሳዊ እያገገመ ያለ አንድ ግለሰብ በአካሉ ላይ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለጊዜው ከተገደበበት በማገገም ላይ ካለ ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ ንስሐ የገባ ሰው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ከመስጠት ይልቅ ለተወሰነ ጊዜ አዳማጭ ቢሆን ጠቃሚ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ሽማግሌዎች፣ ግለሰቡ ደከም ያለበትን ጎን እንዲያሻሽልና ‘በእምነት ጤናማ’ እንዲሆን ለመርዳት ሲሉ ከአንድ ክርስቲያን ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት ያደርጉ ይሆናል። (ቲቶ 2:2) ይህ ሁሉ የሚደረገው በፍቅር እንጂ ኃጢአት የሠራውን ሰው ለመቅጣት በማሰብ አይደለም።

21. አንዳንድ የኃጢአት ድርጊቶች እንዴት ሊያዙ ይችላሉ?

21 ሽማግሌዎች በተለያዩ መንገዶች መንፈሳዊ እርዳታ መስጠት ይችላሉ። ለአብነት ያህል፣ ከዚህ ቀደም የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ የነበረ አንድ ሰው ቤቱ ውስጥ ለብቻው ሳለ አንዴ ወይም ሁለቴ ከመጠን በላይ ጠጥቶ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ከረጅም ጊዜ በፊት ሲጋራ ማጨሱን ያቆመ አንድ ሰው በአንድ ወቅት ደከም በማለቱ ምክንያት ለብቻው ሆኖ አንድ ሁለቴ አጭሶ ይሆናል። ይህ ሰው ለአምላክ ጸልዮ ይቅርታ እንደተደረገለት የሚሰማው ቢሆንም እንኳ ይህ ዓይነቱ ኃጢአት ልማድ እንዳይሆንበት የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በአንድ ወይም በሁለት ሽማግሌዎች ሊያዝ ይችላል። ይሁንና ሌሎች ከግምት ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሽማግሌው ወይም ሽማግሌዎቹ ሁኔታውን ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።

መለኮታዊ ተግሣጽ መቀበላችሁን ቀጥሉ

22, 23. መለኮታዊውን ተግሣጽ መቀበልህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው?

22 እያንዳንዱ ክርስቲያን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ከፈለገ ለይሖዋ ተግሣጽ ትኩረት መስጠት አለበት። (1 ጢሞቴዎስ 5:20) በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍትንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ስታጠና የምታገኛቸውን ማስተካከያዎች ወይም የይሖዋ ሕዝቦች በሚያደርጓቸው የጉባኤ፣ የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የምትሰማቸውን ምክሮች ተግባራዊ አድርግ። ምንጊዜም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ንቁ ሁን። መለኮታዊ ተግሣጽ ኃጢአትን ለመመከት የሚያስችል ጠንካራ መንፈሳዊ ጋሻ ይሆንልሃል።

23 መለኮታዊውን ተግሣጽ መቀበልህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ ለመኖር ይረዳሃል። አንዳንዶች ከክርስቲያን ጉባኤ እንደተወገዱ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ‘ልብህን የምትጠብቅ’ እና ‘እንደ ጥበበኞች የምትኖር ከሆነ’ በአንተ ላይ እንዲህ ያለ ነገር አይደርስም። (ምሳሌ 4:23፤ ኤፌሶን 5:15) ምናልባት በአሁኑ ወቅት ተወግደህ ከሆነ ለመመለስ የሚያስችሉህን እርምጃዎች ለምን አትወስድም? አምላክ ራሳቸውን ለእርሱ የወሰኑ ሰዎች ሁሉ በታማኝነትና “በሐሤት” እንዲያመልኩት ይፈልጋል። (ዘዳግም 28:47) አንተም የይሖዋን ተግሣጽ የምትቀበል ከሆነ ለዘላለም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ።—መዝሙር 100:2