ክርስቲያኖችና መለኮታዊው ስም
ክርስቲያኖችና መለኮታዊው ስም
ወግ አጥባቂ አይሁዶች የአምላክን ስም ጮክ ብለው መጥራት ያቆሙትና በምትኩ አምላክና ሉዓላዊ ጌታ የሚሉትን የዕብራይስጥ ቃላት መጠቀም የጀመሩት መቼ እንደሆነ በእርግጠኝነት ሊናገር የሚችል ሰው የለም። አንዳንዶች የአምላክን ስም በየዕለቱ መጠቀም የቀረው ከኢየሱስ ዘመን ብዙ ቀደም ብሎ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱ በ70 እዘአ እስከጠፋበት ጊዜ ድረስ ሊቀ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ በሚያከናውናቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች፣ በተለይ በሥርየት ቀን መለኮታዊውን ስም ይጠራ እንደነበረ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ አለ። ስለሆነም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የስሙ ትክክለኛ አጠራር ይታወቅ ነበር። ምናልባት ግን ሕዝቡ በሰፊው አይጠቀሙበት ይሆናል።
አይሁዳውያን የአምላክን ስም መጥራት ያቆሙት ለምን ነበር? ምናልባት አንደኛው ምክንያት “የይሖዋን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ” ለሚለው ትእዛዝ የተሳሳተ ትርጉም መስጠታቸው ሳይሆን አይቀርም። (ዘጸአት 20:7 አዓት) እርግጥ፣ ይህ ትእዛዝ በአምላክ ስም መጠቀምን አልከለከለም። ይህ ባይሆን ኖሮ እንደ ዳዊት ያሉት የጥንት የአምላክ አገልጋዮች የአምላክን ስም ብዙ ጊዜ እየጠሩ የይሖዋን በረከት ሊያገኙ ይችሉ ነበርን? አምላክስ ስሙን ለሙሴ ያሳወቀውና ማን እንደላከው ለእስራኤላውያን እንዲናገር ያዘዘው ለምንድን ነው?—መዝሙር 18:1–3, 6, 13፤ ዘጸአት 6:2–8
በኢየሱስ ዘመን ምክንያታዊ ለሆኑት የአምላክ ትእዛዞች በጣም ምክንያታዊ ያልሆነ ትርጉም መስጠት በጣም ተስፋፍቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል የአሥርቱ ትእዛዛት አራተኛ ትእዛዝ እስራኤላውያን የእያንዳንዱን ሳምንት ሰባተኛ ቀን የዕረፍት ቀን ማለትም ሰንበት እንዲያደርጉ ያዛል። (ዘጸአት 20:8–11) ወግ አጥባቂ አይሁዶች ይህን ሕግ ከሚገባው በላይ አክርረው በሰንበት ቀን መሠራት ስለሚገባቸውና ስለማይገባቸው ጥቃቅን ነገሮች የሚገልጽ ቁጥር ሥፍር የሌለው ሕግ አውጥተዋል። የአምላክን ስም ማቃለል እንደማይገባ የተሰጠውን ምክንያታዊ ትእዛዝ እጅግ አክርረው ስሙ መጠራት እንኳን አይገባውም ያሉት በዚሁ ዓይነት መንፈስ ተነሣስተው እንደሆነ አያጠራጥርም። *
ኢየሱስና መለኮታዊው ስም
ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ወግ ተከትሎ ይሆንን? በፍጹም አልተከተለም! የአይሁዳውያንን ሰው ሠራሽ ሕግ ማፍረስና ሕይወቱን ለአደጋ ማጋለጥ ቢሆንበትም እንኳን በሰንበት ሰዎችን ከመፈወስ ወደኋላ እንዳላለ የታወቀ ነገር ነው። (ማቴዎስ 12:9–14) እንዲያውም ፈሪሳውያን ወጋቸው በመንፈስ የተጻፈውን የአምላክ ቃል የሚተላለፍ በመሆኑ አውግዟል። (ማቴዎስ 15:1–9) ስለዚህ በተለይ የኢየሱስ ስም ራሱ “ማዳን የይሖዋ ነው” ማለት መሆኑን ስንመለከት፣ የአምላክን ስም ከመጥራት ወደኋላ ብሏል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው።
ኢየሱስ በአንድ ወቅት በምኩራብ ቆሞ ከኢሳይያስ ጥቅልል አውጥቶ አንብቦ ነበር። አውጥቶ ያነበበው ጥቅስ በዛሬው ጊዜ ኢሳይያስ 61:1, 2 የምንለውን ሲሆን በዚህ ጥቅስ ላይ የአምላክ ስም ከአንድ ጊዜ በላይ ይገኛል። (ሉቃስ 4:16–21) ታዲያ በሚ ያነብበት ጊዜ መለኮታዊውን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” በሚሉ ቃላት በመተካት ሳይጠራው አልፏልን? እንዲህ እንዳላደረገ ግልጽ ነው። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነውን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ወግ ተከትሏል ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ “እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው” እንደነበረ እናነባለን። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)—ማቴዎስ 7:29
እንዲያውም ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ተከታዮቹ “ስምህ ይቀደስ” ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) በተጨማሪም ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ወደ አባቱ ሲጸልይ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። . . . ቅዱስ አባት ሆይ፣ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው” ብሏል።—ዮሐንስ 17:6, 11
ደር ናመ ጎተስ (የአምላክ ስም) የተባለው መጽሐፍ በገጽ 76 ላይ ኢየሱስ ስለ አምላክ ስም ስለተናገረበት ስለዚህ ጥቅስ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል:- “አምላክ ራሱን ለእስራኤላውያን ገለጸ ሲባል ስሙን ገለጸላቸው ማለት ነው የሚለው ለብዙ ዘመናት የቆየ የብሉይ ኪዳን ግንዛቤ እስከ መጨረሻዎቹ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች፣ እንዲያውም ለምሳሌ ያህል በዮሐንስ 17:6 ላይ “ስምህን ገለጥሁላቸው” እስከሚለው የአዲስ ኪዳን የመጨረሻ ክፍሎች ድረስ የዘለቀ የመሆኑን አስደናቂ ሐቅ መቀበል ይኖርብናል።”
አዎን፣ ኢየሱስ በተለይ የአምላክ ስም የሚገኝባቸውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል በሚጠቅስበት ጊዜ የአምላክን ስም አልተጠቀመም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም።
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች በአምላክ ስም ይጠቀሙ ነበርን? አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ኢየሱስ አዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ከሚሰብኩላቸው ሰዎች አብዛኞቹ ለአይሁዳውያን ይሖዋ በሚለው ስሙ ስለተገለጠው አምላክ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ታዲያ ክርስቲያኖች የእውነተኛውን አምላክ ማንነት ለማሳወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ጌታ ወይም አምላክ ብቻ ቢሉ በቂ ይሆናልን? አይሆንም። እነዚህ አሕዛብ የየራሳቸው አማልክትና ጌቶች ነበሩአቸው። (1 ቆሮንቶስ 8:5) ታዲያ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አምላክ ከሐሰተኞቹ አማልክት ሊለዩ የሚችሉት እንዴት ነው? የእውነተኛውን አምላክ ስም በመጠቀም ብቻ ነው።
ለምሳሌ ያህል ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ተደርጎ በነበረው የሽማግሌዎች ጉባኤ ላይ “እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ለአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደጐበኘ ስምዖን ተርኳል። ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል” ብሏል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ሥራ 15:14, 15) ሐዋርያው ጴጥሮስ በዓለ ሃምሳ (ጰንጠቆስጤ) በተባለው ቀን ባደረገው እውቅ ንግግሩ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚለውን የኢዩኤል ትንቢት በመጥቀስ አንዱን የክርስትና ዐቢይ መልእክት አመልክቷል።—ኢዩኤል 2:32 አዓት ፤ ሥራ 2:21
ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ስም አስፈላጊነት በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል። ለሮማውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህንኑ የኢዩኤል ትንቢት ከጠቀሰ በኋላ ክርስቲያን ባልደረቦቹ ሌሎች ሰዎችም መዳን እንዲችሉ ስለ አምላክ ስም ለሌሎች በመስበክ በዚህ ትንቢት ላይ ያላቸውን እምነት በተግባር እንዲያሳዩ አበረታቷል። (ሮሜ 10:13–15) ቆየት ብሎም ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:19 አዓት ) ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማለቂያ በጻፋቸው ጽሑፎች ላይ በአምላክ ስም ተጠቅሟል። “ያህን አወድሱ” የሚል ትርጉም ያለው “ሃሌ ሉያ” የሚለው ቃል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በበርካታ ቦታዎች ላይ ይገኛል።—ራእይ 19:1, 3, 4, 6
ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆኑ ተከታዮቹ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ክህደት እንደሚነሣ ተንብየው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ “በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ” ሲል ጽፎ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:1 አዓት ፤ በተጨማሪ ማቴዎስ 13:36–43፤ ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3፤ 1 ዮሐንስ 2:18, 19 ተመልከት።) እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች በትክክል ተፈጽመዋል። ይህ ክህደት ካስከተላቸው ውጤቶች አንዱ የአምላክ ስም ወደጎን ገሸሽ መደረጉ ነው። እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችና ትርጉሞች እንዲወጣ ተደርጓል! ይህ እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 አንዳንዶች ለዚህ ሌላ ምክንያት ይሰጣሉ:- የግሪ ካውያን ፍልስፍና በአይሁዶች ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር አልቀረም ይላሉ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በኖረበት ዘመን አካባቢ በእስክንድርያ ይኖር የነበረው ፊሎ የተባለ አይሁዳዊ ፈላስፋ በመለኮታዊ መንፈስ ይመራል ብሎ በሚያስበው ፕላቶ የተባለ ግሪካዊ ፈላስፋ በእጅጉ ተነክቶ ነበር። ሌክሲኮን ደስ ጁደንቱምስ (የአይሁድ እምነት መዝገበ ቃላት) “ፊሎ” በሚለው ቃል ግርጌ “ፊሎ የግሪካውያንን (የፕላቶን) ፍልስፍና ቋንቋና አስተሳሰብ አምላክ ከገለጠው የአይሁድ እምነት ጋር አዋህዷል” ካለ በኋላ “በክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባቶች ላይም ጉልህ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል” ይላል። ፊሎ አምላክ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ስለሆነ በስምም ሊጠራ አይችልም የሚል እምነት ነበረው።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ በመጠምጠሚያው ላይ “ቅድስና ለይሖዋ” የሚል የዕብራይስጥ ጽሑፍ ያለበት የአይሁድ ሊቀ ካህናት ሥዕል በቫቲካን ውስጥ ይገኛል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ በ1805 የተዘጋጀ የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚያመለክተው ኢየሱስ በምኩራብ ውስጥ የኢሳይያስን ጥቅልል በሚያነብበት ጊዜ የአምላክን ስም ጮክ ብሎ አንብቧል።—ሉቃስ 4:18, 19
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጴጥሮስና ጳውሎስ የኢዩኤልን ትንቢት በጠቀሱበት ጊዜ በአምላክ ስም ተጠቅመዋል።—ሥራ 2:21፤ ሮሜ 10:13