የአምላክ ስምና “አዲስ ኪዳን”
የአምላክ ስምና “አዲስ ኪዳን”
የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ማለት “በብሉይ ኪዳን” ውስጥ ያለው ቦታ ፈጽሞ የማይናወጥ ነው። አይሁዳውያን ሲውል ሲያድር መለኰታዊውን ስም በአፋቸው መጥራት ቢተውም እንኳን ሃይማኖታዊ እምነታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ጥንታዊ ቅጂዎች በሚገለብጡበት ጊዜ የአምላክን ስም እንዳያስወጡ ያግዳቸው ነበር። በዚህም ምክንያት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የአምላክ ስም ከማንኛውም ስም ይበልጥ ብዙ ጊዜ ተጽፎ ሊገኝ ችሏል።
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። በራእይ መጽሐፍ (የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ) የእጅ ጽሑፍ ቅጂ ውስጥ የአምላክ ስም “ያህ” በሚለው ምህጻረ ቃል (“ሃሌ ሉያ” በሚለው ቃል ውስጥ) ተጽፎ ይገኛል። ከዚህ በቀር በአሁኑ ጊዜ በእጃችን በሚገኙት ከማቴዎስ እስከ ራእይ በሚገኙት የጥንት ግሪክኛ የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች ውስጥ የአምላክ ስም ተጽፎ አይገኝም። ታዲያ የአምላክ ስም በክርስትና ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መኖር የለበትም ማለት ነውን? እንዲህ ቢሆን ነገሩ ግራ ያጋባ ነበር። ምክንያቱም የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክ ስም ያለውን ከፍተኛ ቦታ ይገነዘቡ ነበር፤ ኢየሱስም ስለ አምላክ ስም መቀደስ እንድንጸልይ አስተምሮናል። ታዲያ የአምላክ ስም ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የጠፋው ለምንድን ነው?
ይህንን ለመረዳት በአሁኑ ጊዜ ያሉን ጥንታዊ ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች በኩረ ጽሑፎች አለመሆናቸውን ማስታወስ ይገባናል። ማቴዎስ፣ ሉቃስና ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በራሳቸው እጅ የጻፏቸው መጻሕፍት በአገልግሎት ብዛት አርጅተው ጠፍተዋል። በዚህም ምክንያት
እነዚህን መጻሕፍት መገልበጥ አስፈላጊ ሆኗል። ግልባጮቹ በሚያረጁበት ጊዜ ደግሞ ሌሎች ግልባጮች ከግልባጮቹ ተገልብጠዋል። የሚገለበጡት ቅጂዎች አገልግሎት ላይ የሚውሉ እንጂ በአንድ ቦታ ተጠብቀው የማይቀመጡ በመሆናቸው እንዲህ መደረጉ የሚጠበቅ ነገር ነው።በአሁኑ ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ግሪክኛ የክርስቲያን ጽሑፎች ጥንታዊ የእጅ ግልባጮች ይገኛል፤ ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የተገለበጡት በአራተኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ወይም ከዚያ በኋላ ነው። ይህ ደግሞ ከአራተኛው መቶ ዘመን በፊት የአምላክ ስም ከግሪክኛ የክርስቲያን ጽሑፎች ውስጥ እንዲወጣ ያደረገ ነገር ተፈጽሞ ይሆንን? የሚል ጥርጣሬ ያሳድርብናል። በእርግጥም የተፈጸመ ነገር መኖሩን እውነታዎቹ ያሳያሉ።
መለኮታዊው ስም ይገኝ ነበር
ሐዋርያው ማቴዎስ የአምላክን ስም በወንጌሉ ውስጥ አስገብቶ እንደነበረ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ለምን? ወንጌሉን በመጀመሪያ የጻፈው በዕብራይስጥ ስለነበረ ነው። በአራተኛው መቶ ዘመን የላቲን ቩልጌት ን የተረጎመው ዤሮም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሌዊ ይባል የነበረውና ከቀረጥ ሰብሳቢነት ሐዋርያ የሆነው ማቴዎስ በመጀመሪያ በይሁዳ ምድር በዕብራይስጥ ቋንቋ የክርስቶስን ወንጌል አጠናቀረ። . . . ከዚያ በኋላ ወደ ግሪክኛ የተረጎመው ማን እንደሆነ በውል አይታወቅም። የዕብራይስጡ ቅጂ ግን እስከ ዛሬ ድረስ በቂሣርያ በሚገኝ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል።”
ማቴዎስ የጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ በመሆኑ በተለይ ‘ከብሉይ ኪዳን’ ጠቅሶ በሚጽፍበት ጊዜ በአምላክ ስም አልተጠቀመም ማለት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ሁለተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጻፉት ሌሎች ጸሐፊዎች መጽሐፎቻቸውን የጻፉት ለዓለም አቀፍ አንባቢዎች ስለነበረ የጻፉበት ቋንቋ በዘመኑ ዓለም አቀፍ ቋንቋ የነበረው ግሪክኛ ነበር። በዚህም ምክንያት ከ“ብሉይ ኪዳን” በሚጠቅሱበት ጊዜ ከዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፎች ሳይሆን ከግሪክኛው ሰፕቱጀንት ትርጉም ይጠቅሱ ነበር። የማቴዎስ ወንጌልም ቢሆን ከጊዜ በኋላ ወደ ግሪክኛ ተተርጉሟል። በእነዚህ የግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ የአምላክ ስም ይገኝ ነበርን?
በኢየሱስ ዘመን ከነበረው የሰፕቱጀንት ትርጉም እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው የቆዩ በጣም ያረጁ ብጥስጣሾች ይገኛሉ፤ በእነዚህ ቅዳጆች ላይ የአምላክ ስም ተጽፎ መገኘቱም ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ተስታመንት ቲኦሎጂ (ጥራዝ 2፣ ገጽ 512) እንዲህ ይላል:- “በቅርቡ በተገኙ የጽሑፍ ማስረጃዎች ምክንያት የሰፕቱጀንት አጠናቃሪዎች የሐወሐ የሚለውን ቴትራግራማተን ኪሪዮስ እያሉ ተርጉመዋል የሚለው አስተሳሰብ እውነት መሆኑ በጣም አጠራጣሪ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ በሚገኙት እጅግ ጥንታዊ የሆኑ የሰፕቱጀንት ቅጂ ቅዳጆች ላይ በግሪክኛው ጽሑፍ መካከል ቴትራግራማተኑ በዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይታያል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን የብሉይ ኪዳን ተርጓሚዎችም ይህንኑ ልማድ ይከተሉ ነበር።” ስለዚህ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ የሚያነቡት ቅዱስ ጽሑፍ ዕብራይስጥ ወይም ግሪክኛ ቢሆን መለኮታዊውን ስም ማግኘታቸው አይቀርም ነበር።
በዚህ ምክንያት በአሜሪካ አገር የሚገኘው የጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆርጅ ሐዋርድ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “የአዲስ ኪዳኑ ቤተ ክርስቲያን ይጠቀምበትና ይጠቅሰው በነበረው በሰፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኝ በነበረበት ጊዜ ሁሉ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ቴትራግራማተንን በጥቅሶቻቸው ውስጥ ይጽፉ እንደነበረ አያጠራጥርም።” (ቢብ ሊካል አርኪዮሎጂ ሪቪው፣ መጋቢት 1978፣ ገጽ 14) ከዚህ የተለየ ነገር ለማድረግ ምን ሥልጣን ሊኖራቸው ይችላል?
የአምላክ ስም በግሪክኛ የ“ብሉይ ኪዳን” ትርጉም ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ቆይቷል። በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የመጀመሪያ አጋማሽ ወደ አይሁድ እምነት ገብቶ የነበረው አቂላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ግሪክኛ ሲተረጉም የአምላክን ስም የሚወክለውን ቴትራግራማተን በጥንታዊው የዕብራይስጥ ፊደል ጽፏል። በሦስተኛው መቶ ዘመን ደግሞ አሪገን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጣም ትክክለኛ በሆኑት የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች ውስጥ ስሙ በዛሬው ሳይሆን በጣም ጥንታዊ በሆነው የዕብራይስጥ ፈደል ተጽፎ ይገኛል።”
በአራተኛው መቶ ዘመን እንኳ ዤሮም ለመጽሐፈ
ሳሙኤልና ለመጽሐፈ ነገሥት በጻፈው መቅድም ላይ እንዲህ ብሏል:- “የአምላክን ስም ማለትም ቴትራግራማተንን [יהוה] እስከዚህ ዘመን ድረስ እንኳን በአንዳንድ የግሪክኛ ጥራዞች ውስጥ በጥንታዊ ፊደላት ተጽፎ እናገኛለን።”የመለኮታዊው ስም መወገድ
ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ይመጣል ሲል የተነበየለት ክህደት መከሰት ጀምሮ ስለነበር የአምላክም ስም በጽሑፎች ላይ ተጽፎ የሚገኝ ቢሆንም ቀስ በቀስ ከአገልግሎት ውጭ እየሆነ መጣ። (ማቴዎስ 13:24–30፤ ሥራ 20:29, 30) እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ብዙ አንባቢዎች የቴትራግራማተንን ምንነት እንኳን ፈጽመው የማያውቁ ሆኑ። ዤሮም በዘመኑ “አንዳንድ ደንቆሮዎች [ቴትራግራማተንን] በግሪክኛ መጻሕፍት ውስጥ በሚያገኙበት ጊዜ ከፊደሎቹ መመሳሰል የተነሣ ΠΙΠΙ (የግሪክኛ ፊደላት ሲሆኑ “ፒፒ” ተብለው ይነበባሉ) ብለው ያነቡ ነበር” ብሏል።
በኋለኞቹ ዘመናት በተጻፉት የሰፕቱጀንት ቅጂዎች ውስጥ የአምላክ ስም ተወግዶ እንደ “አምላክ” (ቴኦስ ) እና “ጌታ” (ኪሪዮስ ) ያሉ ቃላት ተተክተዋል። ይህን ለማለት የምንችለው የአምላክ ስም የተጻፈበት ቀደም ያለ የሰፕቱጀንት መጽሐፍ ቅዱስ ብጣሽና የአምላክ ስም የማይገኝበት ከዚሁ ብጣሽ ጋር አንድ የሆነ በኋለኞቹ ዘመናት የተገለበጠ ብጣሽ ስለምናገኝ ነው።
“በአዲስ ኪዳን” ወይም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል። ፕሮፌሰር ጆርጅ ሐዋርድ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል:- “በዕብራይስጥ ሆሄያት ይጻፍ የነበረው የአምላክ ስም በሰፕቱጀንት ውስጥ በግሪክኛ ቃላት መተካት ሲጀመር በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ የሰፕቱጀንት ጥቅሶችም ተወገደ። . . . ብዙም ሳይቆይ መለኮታዊው ስም በአንዳንድ ቃላት ላይ ተለጣፊ ሆኖ ከመግባቱና በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ ከመታወቁ በስተቀር ከአሕዛብ ቤተ ክርስቲያን እይታ ፈጽሞ ተወገደ።”
ስለዚህ አይሁዳውያን የአምላክን ስም ለመጥራት እምቢተኞች ሲሆኑ የከሐዲዋ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የግሪክኛና የሌሎች ቋንቋዎች ትርጉሞች ፈጽማ አስወጥታለች።
የስሙ አስፈላጊነት
ከጊዜ በኋላ ግን ቀደም ስንል እንደተመለከትነው መለኮታዊው ስም በብዙዎቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሞች ውስጥ ተመልሶ ሊገባ ችሏል። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችስ ውስጥስ? የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችና አጥኚዎች የአምላክ ስም ካልተጨመረባቸው ለመረዳት የሚያስቸግሩ አንዳንድ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች እንዳሉ ተገነዘቡ። የስሙ ወደ ቦታው መመለስ በመንፈስ አነሣሽነት ለተጻፈው ለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ግልጽነትና ትክክለኛ ግንዛቤ መጨመር ከፍተኛ እርዳታ አበርክቷል።
ለምሳሌ ጳውሎስ ለሮማውያን የጻፈውን ቃል በኦቶራይዝድ ቨርሽን ተጽፎ እንደሚገኘው እናንብብ:- “የጌታን ስም የሚጠራ ማንኛውም ሰው ይድናልና” ይላል። (ሮሜ 10:13) ለመዳን የምንጠራው የማንን ስም ነው? ኢየሱስ ብዙ ጊዜ “ጌታ” ተብሎ ስለተጠራና እንዲያውም አንድ ጥቅስ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን . . . ትድናላችሁ” ስለሚል ጳውሎስ እዚህ ላይ የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ነው ብለን መደምደም ይገባናልን? — ሥራ 16:31
የለም፣ እንዲህ ማለት አንችልም። በኦቶራይዝድ ቨርሽን በሮሜ 10:13 አንጻር የገባው የህዳግ ማጣቀሻ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ኢዩኤል 2:32ን ይጠቅሳል። ይህን ጥቅስ አውጥተህ ብትመለከት ጳውሎስ ለሮማውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ የኢዩኤልን ቃል በቀጥታ ጠቅሶ እንደጻፈ መገንዘብ ትችላለህ። ኢዩኤል ደግሞ በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ያለው “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ነው። (አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ) አዎን፣ ጳውሎስ የይሖዋን ስም መጥራት እንደሚገባን መናገሩ ነበር። ስለዚህ በኢየሱስ ማመን ቢኖርብንም መዳናችን ግን ለአምላክ ስም ካለን አድናቆትና ግንዛቤ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው።
ይህ ምሳሌ የአምላክ ስም ከግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በመወገዱ ምክንያት ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ማንነት እንዴት ግራ ሊጋቡ እንደቻሉ ያሳያል። ለሥላሴ መሠረተ ትምህርት መፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አያጠራጥርም!
መለኮታዊው ስም ወደ ቦታው መመለስ ይኖርበታልን?
አንድ ተርጓሚ መለኮታዊውን ስም፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሚገኙት ጥንታዊ ጽሑፎች ውስጥ የማይገኝ ሆኖ እያለ፣ በትርጉሙ ውስጥ ለማስገባት መብት ሊኖረው ይችላልን? አዎን፣ ይኖረዋል። አብዛኞቹ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጆች “ጌታ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋን እንደሚያመለክት ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል በሮቢንሰን የተዘጋጀው ኤ ግሪክ ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ተስታመንት (በ1859 የታተመ) ኪርዮስ (“ጌታ”) በሚለው ቃል ሥር “የሁሉ የበላይ የሆነ ጌታ እና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ፣ በሰፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ በዕብራይስጥ יהוה ይሖዋ ተብሎ የሚጻፈው” ማለት እንደሆነ ይገልጻል። ስለዚህ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚጠቅሱባቸው
ቦታዎች ተርጓሚው ኪርዮስ የሚለውን ቃል መለኮታዊው ስም በበኩረ ጽሑፉ ላይ ይገኝባቸው በነበሩ ቦታዎች ሁሉ “ይሖዋ” ብሎ ለመተርጎም መብት አለው።ብዙ ተርጓሚዎችም እንዲሁ አድርገዋል። ቢያንስ ከ14ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ ጊዜ ወደ ዕብራይስጥ ተተርጉመዋል። ታዲያ ተርጓሚዎቹ የአምላክ ስም የሚገኝባቸው “የብሉይ ኪዳን” ክፍሎች ‘በአዲስ ኪዳን’ ውስጥ ተጠቅሶ ሲያገኙ ምን አድርገዋል? አብዛኛውን ጊዜ የአምላክን ስም ጨምረው ለመተርጎም ተገድደዋል። በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ዕብራይስጥ ቋንቋ በተተረጎሙ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የአምላክ ስም ይገኛል።
በዘመናዊ ቋንቋ የተተረጐሙ በርካታ ትርጉሞችም፣ በተለይ ሚስዮናውያን ይገለገሉባቸው የነበሩ ትርጉሞች የእነዚህን ተርጓሚዎች ምሳሌ ተከትለዋል። በዚህም ምክንያት በብዙ የአፍሪካ፣ የእስያ፣ የአሜሪካና የፓስፊክ ደሴቶች ቋንቋዎች በተተረጎሙ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይሖዋ የሚለው ስም በብዙ ቦታዎች ስለሚገኝ አንባቢዎች በእውነተኛው አምላክና በሐሰተኞቹ አማልክት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ሊገነዘቡ ችለዋል። ስሙ በአንዳንድ የአውሮፓ ቋንቋዎች ትርጉሞችም ላይ ገብቷል።
የአምላክን ስም በጥሩ መረጃዎች በመደገፍ ቀድሞ ወደነበረው ቦታ በድፍረት ከመለሱት ትርጉሞች አንዱ ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ነው። ይህ በአሁኑ ጊዜ እንግሊዝኛን ጨምሮ በ13 የተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀው ትርጉም የአምላክ ስም የሚገኝባቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተጠቀሱባቸው የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ሁሉ የአምላክን ስም አስገብቷል። በዚህ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ የአምላክ ስም በጠቅላላው 237 ጊዜ ተጠቅሷል።
በስሙ ላይ የተነሣ ተቃውሞ
ብዙ ተርጓሚዎች የአምላክን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስገባት ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም ይህን ስም ለማስወጣት ሃይማኖታዊ ግፊት መደረጉ አላቆመም። አይሁዳውያን ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ባያስወጡትም በአፋቸው ለመጥራት አሻፈረን ብለዋል። የሁለተኛውና የሦስተኛው መቶ ዘመን ከሃዲ ክርስቲያኖች የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በሚገለብጡበት ጊዜ ስሙን ከማስወጣታቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች በሚተረጉሙበት ጊዜ አስወጥተውታል። ዘመናዊ ተርጓሚዎችም ቢሆኑ ትርጉማቸው የአምላክ ስም ወደ 7,000 ጊዜ ያህል በሚገኝበት በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም መለኮታዊውን ስም ከትርጉማቸው አውጥተዋል። (በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የ1984 እትም ላይ በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ 6,973 ጊዜ ተጠቅሷል።)
ታዲያ ይሖዋ ስሙን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያስወጡትን ሰዎች እንዴት ያያቸዋል? አንተ ደራሲ ብትሆንና አንድ ሰው ሆን ብሎ ስምህን አንተ ከደረስከው መጽሐፍ ውስጥ ጨርሶ ቢያጠፋ ስለዚያ ሰው ምን ይሰማሃል? በአጠራር ችግር በማሳበብም ሆነ የአይሁዳውያንን ወግ በመከተል የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያስወጡ ተርጓሚዎች ኢየሱስ “ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ” ያላቸውን ሰዎች ይመስላሉ። (ማቴዎስ 23:24) በእነዚህ ትናንሽ ችግሮች ተሰናክለው የመላው ጽንፈ ዓለም የበላይ የሆነውን አምላክ ስም ራሱ ካዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ በማስወጣታቸው በጣም ከባድ የሆነ ችግር ፈጥረዋል።
መዝሙራዊው “አቤቱ [አምላክ ሆይ] ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ጠላት ስምህን ሁልጊዜ ያቃልላልን?” ብሏል። — መዝሙር 74:10 አዓት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ጌታ” የሚለው “ይሖዋ” ከሚለው ስም ጋር አንድ ነውን?
አምላክ ተለይቶ የሚታወቅበትን የተጸውኦ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስወጥቶ እንደ “ጌታ” ወይም “አምላክ” ባሉት የማዕረግ ስሞች መተካት የጽሑፉን ኃይል ከማዳከሙም በላይ በብዙ መንገዶች ጎደሎ ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል ትርጉም የለሽ የቃላት ድግግሞሽ ሊያስከትል ይችላል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል በመቅድሙ ላይ እንዲህ ይላል:- “‘ያህዌህ አምላክ ነው’ ማለት ግልጽ ትርጉም ያለው አባባል ሲሆን ‘ጌታ አምላክ ነው’ ማለት ግን ትርጉም የሌለውና አስፈላጊ ያልሆነ የቃላት ድግግሞሽ ነው።”
ከዚህም በላይ ይህ ዓይነቱ መለኮታዊውን ስም በማዕረግ ስም የመተካት ተግባር ለአንዳንድ ግራ የሚያጋቡ ሐረጎች መፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ መዝሙር 8:9 በኦቶራይዝድ ትርጉም እንዲህ ይነበባል:- “አቤቱ ጌታ ጌታችን ሆይ፣ ስምህ ምንኛ በመላው ምድር ግሩም ነው!” እንዲህ ባለው ጥቅስ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም ሲጨመር የጥቅሱ ትርጉም ምን ያህል ግልጽ እንደሚሆን ማስተዋል ይቻላል። ያንግስ ሊተራል ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ሆሊ ባይብል “ጌታችን ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ በመላው ምድር ላይ ምን ያህል የተከበረ ነው!” ይላል።
በተጨማሪም ስሙን ማውጣት ግራ መጋባት ሊያስከትል ይችላል። መዝሙር 110:1 “ጌታ ጌታዬን፣ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” ይላል። (ኦቶራይዝድ ቨርሽን ) እዚህ ላይ ተናጋሪው ማነው? የሚናገረውስ ለማነው? “ይሖዋ ለጌታዬ የተናገረው ቃል ‘ጠላቶችህን የእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ይላል’ ” ተብሎ ሲተረጎም ትርጉሙ ምን ያህል ግልጽ እንደሚሆን ማስተዋል ይቻላል።— የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም
በተጨማሪም “ይሖዋ” የሚለውን ስም በ“ጌታ” መተካት አንድ በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲወገድ ምክንያት ይሆናል። እርሱም የአምላክ የተጸውኦ ስም ነው። ዘ ኢላስተረትድ ባይብል ዲክሽነሪ (ጥራዝ 1፣ ገጽ 572) “እንደ እውነቱ ከሆነ ብቸኛው የአምላክ ‘ስም’ ያህዌህ ነው” ይላል።
ዘ ኢምፐሪያል ባይብል ዲክሽነሪ (ጥራዝ 1፣ ገጽ 856) “በአምላክ” (ኤሎሂም ) እና “ይሖዋ” በሚለው መጠሪያ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “[ይሖዋ] በየትም ቦታ የእውነተኛው አምላክ የእርሱ ብቻ የግል መታወቂያ፣ የተጸውኦ ስም ሲሆን ኤሎሂም ግን ይበልጥ የወል ስምነት ባሕርይ ያለው የግዴታ ወይም ሁልጊዜ ባይሆንም አብዛኛውን ጊዜ ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ የሚያመለክት ቃል ነው።”
እንግሊዝ አገር ያለው የትሪኒቲ ኮሌጅ ርዕሰ መምህር የሆኑት ጄ ኤ ሞትየር እንዲህ በማለት ይጨምራሉ:- “በምትክነት ከሚገቡት [ጌታ ወይም አምላክ] ቃላት አልፈን የአምላክን የግልና የተጸውኦ ስም ለመመልከት ብንረሳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ማግኘት የሚገባንን ብዙ ጥቅም ሳናገኝ እንቀራለን። አምላክ ስሙን ለሕዝቦቹ ያስታወቃቸው ውስጣዊ ባሕርዩን ሊገልጻላቸው ስለፈለገ ነው።”— ኤርድማንስ ሃንድቡክ ቱ ዘ ባይብል ገጽ 157
አምላክ ተለይቶ የሚታወቅበትን የተጸውኦ ስም ተራ በሆነ የማዕረግ ስም መለወጥ ፈጽሞ አይቻልም። ማንኛውም የማዕረግ ስም የመጀመሪያው የአምላክ ስም የሚያስተላልፈውን የተሟላና የበለጸገ ትርጉም ሊያስተላልፍ አይችልም።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ይህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የተጻፈ ነው ተብሎ የሚታሰበው ዘካርያስ 8:19–21 እና 8:23 እስከ 9:4 የሚገኝበት የሰፕቱጀንት ትርጉም ቅዳጅ (በስተቀኝ) በኢየሩሳሌም በእስራኤል ቤተ መዘክር ይገኛል። የአምላክ ስም በአራት ቦታዎች ላይ የሚገኝበት ቅዳጅ ሲሆን ሦስቱ በሥዕሉ ላይ ተመልክተዋል። ከ400 ዓመት በኋላ በተጻፈው አለክሳንድሪን ማኑስክሪፕት በተባለው የሰፕቱጀንት ግልባጭ ላይ ግን (በስተግራ) በእነዚሁ ቁጥሮች ላይ የሚገኘው የአምላክ ስም ኪሪዮስ (“ጌታ”) የተባለው የግሪክኛ ቃል ምህጻረ ቃል በሆነው KY እና KC ተተክቷል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጆን ደብልዩ ዴቪስ የተባለ በ19ኛው መቶ ዘመን በቻይና ይኖር የነበረ ሚስዮናዊ የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግባት ይኖርበታል ብሎ የሚያምንበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “መንፈስ ቅዱስ በማንኛውም ሥፍራ ላይ በዕብራይስጥ ይሖዋ ካለ ተርጓሚው በእንግሊዝኛም ይሁን በቻይንኛ ይሖዋ የማይልበት ምን ምክንያት አለ? በዚህ ቦታ ይሖዋ የሚለውን አጠራር እጠቀማለሁ፣ በዚያኛው ቦታ ላይ ደግሞ ምትክ በሚሆን ሌላ ቃል እጠቀማለሁ የሚልበት ምን መብት አለው? . . . ይሖዋ በሚለው ስም መጠቀም ስህተት የሚሆንባቸው ቦታዎች አሉ የሚል ሰው ካለ ምክንያቱን ያሳየን። ማስረጃ የማቅረቡ ግዴታ የሚያርፈው በእርሱ ላይ ነው። ይህም ቀላል ሥራ አይሆንለትም፤ ምክንያቱም በትርጉሞች ውስጥ ይሖዋ በሚለው ስም መጠቀም ስህተት የሚሆንበት አንድ ቦታ እንኳን ከኖረ በኩረ ጽሑፉን በመንፈስ አነሣሽነት የጻፈው ሰው ለምን በዚህ ስም ተጠቀመ? ለሚለው ቀላል ጥያቄ መልስ መስጠት ይኖርበታል።” — ዘ ቻይኒዝ ሪከርደር ኤንድ ሚሽነሪ ጆርናል፣ ጥራዝ 7፣ ሻንጋይ፣ 1876
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም 237 ጊዜ በአምላክ ስም ተጠቅሟል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክ ስም በስፔይን አገር በሚኖርካ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ላይ
በፈረንሳይ አገር ፓሪስ አጠገብ በሚገኝ ሐውልት ላይ
በኢጣልያ አገር በፓርማ ከተማ በሚገኘው በኪየሳ ዲ ሳን ሎረንሶ