የአምላክ ስምና የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች
የአምላክ ስምና የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች
በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ኢየሱስና ተከታዮቹ የተነበዩለት በክርስትና እምነት ላይ የሚፈጸም ክህደት ሙሉ በሙሉ መስፋፋት ጀመረ። የአረማውያን ፍልስፍናዎችና መሠረተ ትምህርቶች ወደ ጉባኤዎች ሰርገው ገቡ። ኑፋቄና መከፋፈል አቆጠቆጠ። የቀድሞው የእምነት ንጽሕና ተበከለ። በአምላክ ስም መጠቀምም ቀረ።
ይህ የክህደት ክርስትና በየቦታው እየተስፋፋ ሲሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋዎች ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም አስፈላጊ ሆነ። ታዲያ ተርጓሚዎቹ የአምላክን ስም በየትርጉሞቻቸው ውስጥ እንዴት አስቀመጡት? አብዛኛውን ጊዜ “ጌታ” በሚለው ቃል ተክተውታል። በዚህ ዘመን በጣም እውቅ የሆነው ትርጉም ዤሮም በዘመኑ በተራ ሰዎች ይነገር ወደነበረው የላቲን ቋንቋ የተረጎመው የላቲን ቩልጌት ነበር። ዤሮም ቴትራግራማተን (የሐወሐ) የሚገኝበትን ቦታ ሁሉ ዶሚኑስ “ጌታ” በሚለው ቃል ተክቷል።
ከጊዜ በኋላ እንደ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ እና ስፓንኛ የመሳሰሉ አዳዲስ ቋንቋዎች በአውሮፓ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ አዳዲስ ቋንቋዎች እንዳይተረጎም ታከላክል ነበር። በዚህ ምክንያት በመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀሙ የነበሩት አይሁዶች የአምላክ ስም ተጽፎ የሚገኝበትን ቦታ ለማንበብ እምቢተኞች ሲሆኑ አብዛኞቹ “ክርስቲያኖች” መጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብ ያዳምጡ የነበረው በአምላክ ስም የማይጠቀመውን የላቲንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን በአምላክ ስም መጠቀም ተጀመረ። በ1278 ሬይሙንዱስ ማርቲኒ የተባለ የስፔይን መነኩሴ በጻፈው ፑጂዮ ፊዴይ (የእምነት ሳንጃ) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ሠፍሯል። ሬይሙንዱስ ማርቲኒ የአምላክን ስም የጻፈው ዮሑዋ በማለት ነበር *። ከዚያ ጥቂት ቆየት ብሎ በ1303 ፖርሼቱስ ደ ሳልቫቲቺስ ቪክቶሪያ ፖርሼቲ አድቬርሱስ ኢምፒዮስ ሄብራዮስ (ፖርሼቱ ፀረ አምላክ በሆኑት ዕብራውያን ላይ ያገኘው ድል) የተባለ መጽሐፍ ጻፈ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የአምላክን ስም የጠቀሰ ሲሆን ኢዩአህ፣ ኢዮሁዋ፣ ኢሁአህ በሚሉ የተለያዩ አጠራሮች ተጠቅሟል። ከዚያም በ1518 ፔትሩስ ጋላቲነስ ደ አርካኒስ ካቶሊኬ ቬሪታቲስ (ጽንፈ ዓለማዊውን እውነት ስለሚመለከቱ ምሥጢሮች) የተባለ መጽሐፍ ሲያዘጋጅ በመጽሐፉ ውስጥ የአምላክን ስም ኢዬሁአ በማለት ጠርቷል።
ይህ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝኛ * በዚህ እትም ላይ በጻፈው ማስታወሻ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ኢዬሆቫ የአምላክ ስም ነው። . . . ከዚህም በላይ ጌታ የሚለው ቃል በትላልቅ ፊደሎች ተጽፎ በምትመለከቱበት ቦታ ሁሉ (የህትመት ስህተት ካልኖረ በስተቀር) የገባው የዕብራይስጥ ቃል ኤዬሆቫ ነው።” የይሖዋን ስም በጥቂት ቁጥሮች ላይ የማስገባትና በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ቴትራግራማተን በሚገኝበት ቦታ ሁሉ “ጌታ” እና “አምላክ” የሚለውን ቃል የማስገባት ልማድ የመጣው ከዚህ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የገባው ዊልያም ቲንደል የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ አምስት መጻሕፍት ትርጉም ባሳተመበት በ1530 ነበር። በዚህ ትርጉም ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ኤዬሁዋ ተብሎ ይጻፍ የነበረውን የአምላክ ስም በበርካታ ቁጥሮች ላይ ያስገባ ሲሆንበ1611 በሰፊው የሚሠራበት የእንግሊዝኛ ትርጉም የሆነው ኦቶራይዝድ ቨርሽን ታተመ። በዚህ ትርጉም ውስጥ የአምላክ ስም በዋናው ጽሑፍ የሚገኝባቸው ቦታዎች አራት ናቸው። (ዘጸአት 6:3፤ መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 12:2፤ 26:4) የአምላክ ስም ምህጻረ ቃል የሆነው “ያህ” ደግሞ በመዝሙር 68:4 ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ስሙ እንደ “ያህዌ ይርኤ” ባሉት የቦታ ስሞች ተጽፎ ይገኛል። (ዘፍጥረት 22:14፤ ዘጸአት 17:15፤ መሳፍንት 6:24) ቢሆንም ተርጓሚዎቹ በአብዛኞዎቹ ቦታዎች ላይ የቲንደልን ምሳሌ በመከተል የአምላክን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” በሚሉት በትላልቅ ፊደላት በተጻፉ ቃላት ተክተዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም በአራት ጥቅሶች ላይ ሊገኝ ከቻለ ስሙ በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ጽሑፍ በሚገኝባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ጥቅሶች ላይ የማይገኝበት ምን ምክንያት አለ?
በጀርመንኛ ቋንቋም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ተፈጽሟል። ማርቲን ሉተር ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች የተረጎመውን ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ በ1534 አሳተመ። በሆነ ምክንያት የተነሣ የአምላክን ስም በትርጉሙ ውስጥ ሳያስገባ እንደ ኸር (“ጌታ”) ባሉት የማዕረግ ስሞች ተክቷል። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ በ1526 ኤርምያስ 23:1–8ን አስመርኩዞ ባሰማው ስብከት ላይ “ይህ ጌታ ይሖዋ የሚለው ስም ብቸኛ ባለንብረት እውነተኛው አምላክ ነው” ብሏል።
ሉተር በ1543 ልማዱ በሆነው ግልጽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነዚህ [አይሁዶች] ይሖዋ የሚለው ስም በአፍ የማይጠራ ስም ነው ሲሉ የሚናገሩትን አያውቁም። . . . በብዕርና ቀለም ሊጻፍ የሚችል ከሆነ በአፍ ሊጠራ የማይችልበት ምን ምክንያት አለ? በብዕርና ቀለም ከመጻፍና በአፍ ከመጥራት የትኛው የተሻለ ይሆናል? ለምን ሊጻፍ፣ ሊነበብ ወይም ሊታሰብ የማይችል ስም ነው አይባልም? ሁለመናውን በዘጸአት 6:3 ላይ ገብቷል።
ስንመለከት ነገሩ ሁሉ የተበላሸ እንደሆነ እንገነዘባለን።” ሆኖም ግን ሉተር በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ ላይ ሁኔታውን ለማስተካከል ያደረገው ነገር አልነበረም። በኋለኞቹ ዓመታት በተተረጎሙት የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ግን የአምላክ ስምበተከታዮቹ መቶ ዘመናት የተነሡ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች አንዱን ተከትለዋል። አንደኛውን አቅጣጫ የተከተሉት የአምላክን ስም ከትርጉማቸው ፈጽመው ያስወጡ ሲሆኑ ሁለተኛውን አቅጣጫ የተከተሉት ደግሞ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይሖዋ ወይም ያህዌህ የሚለውን መጠሪያ በብዛት አስገብተዋል። የአምላክን ስም ፈጽመው ያስወጡትን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንውሰድና ተርጓሚዎቻቸው ለዚህ ድርጊታቸው የሰጡትን ምክንያት እንመልከት።
ስሙን ያስወጡበት ምክንያት
ጄ ኤም ፓዊስ ስሚዝና ኤድጋር ጄ ጉድስፒድ በ1935 ባሳተሙት ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ የአምላክ ስም በሚገኝባቸው አብዛኞቹ ቦታዎች “ጌታ” እና “አምላክ” የሚሉት ቃላት በምትክነት ገብተዋል። ይህን ያደረጉበትን ምክንያት በመቅድማቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በዚህ ትርጉም ውስጥ የወግ አጥባቂ አይሁዶችን ልማድ በመከተል ‘ያህዌህ’ የሚለውን ስም በ‘ጌታ’፣ ‘ጌታ ያህዌህ’ የሚለውን ሐረግ በ‘ጌታ አምላክ’ ተክተናል። ‘ጌታ’ ወይም ‘አምላክ’ የሚለው ቃል በ‘ያህዌህ’ ምትክ የገባ ሲሆን በትላልቅ ወይም በካፒታል ሆሄያት ተጽፏል።”
ከዚያም መቅድሙ የሐወሐ የሚሉትን ሆሄያት ሲመለከቱ “ጌታ” ብለው የሚያነቡትን አይሁዳውያን ወግ በመቃረን እንዲህ ብሏል:- “ስለዚህ የበኩረ ጽሐፉን ጣዕምና ለዛ ለማግኘት
የፈለገ ሰው ጌታ ወይም አምላክ የሚሉትን ቃላት በሚመለከትበት ቦታ ሁሉ ‘ያህዌህ’ ብሎ ማንበብ ይኖርበታል!”ይህን በምናነብበት ጊዜ የበኩረ ጽሑፉን ጣዕምና ለዛ በትክክል የሚያስተላልፈው “ጌታ” ከማለት ይልቅ “ያህዌህ” ብሎ ማንበብ ከሆነ ተርጓሚዎቹ ያህዌህ የሚለውን ስም በትርጉሞቻቸው ያልተጠቀሙት ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ በአእምሮአችን ውስጥ ይነሣል። ራሳቸው እንደተናገሩት የአምላክን ስም “ጌታ” በሚለው ቃል የተኩትና የበኩረ ጽሑፉን ለዛና ጣዕም ያጠፉት ለምንድን ነው?
ተርጓሚዎቹ የአይሁዳውያንን ወግ አጥባቂ ልማድ ስለተከተልን ነው የሚል ምክንያት ይሰጣሉ። ታዲያ አንድ ክርስቲያን የእነርሱን ልማድ ቢከተል ጥሩ ይሆናልን? ኢየሱስን ያልተቀበሉትና እሱም “ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ” ሲል ያወገዘው የአይሁድ ወግ አጥባቂ ልማድ አስጠባቂ የሆኑት ፈሪሳውያን እንደነበሩ አስታውስ። (ማቴዎስ 15:6) በእውነትም እንዲህ ባለ መንገድ የአምላክን ስም በሌላ ቃል መተካት የአምላክን ቃል ኃይል ያዳ ክማል።
በ1952 በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታተመው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ሪቫይዝድ ስታንደርድ ቨርሽንም የአምላክን ስም በሌሎች ቃላት ተክቷል። ተሻሽሎ ከተዘጋጀው ከዚህ ትርጉም በፊት ታትሞ የነበረው አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን ግን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሙሉ ጅሆቫ በሚለው ስም ተጥቅሟል። ስለዚህ ይህ ትርጉም የአምላክን ስም ማስወጣቱ ከፍተኛ ለውጥ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ለውጥ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው?
በሪቫይዝድ ስታንደርድ ቨርሽን መቅድም ላይ የሚከተለውን እናነባለን:- “ኮሚቴው በሁለት ምክንያቶች የተነሣ ይበልጥ ወደተለመደው የኪንግ ጀምስ አተረጓጎም [የአምላክን ስም ማስወጣት ማለት ነው] ተመልሷል:- (1) ጅሆቫ የሚለው ስም ማንኛውንም የዕብራይስጥ አጠራር በትክክል አይወክልም። (2) አንዱንና ብቸኛውን አምላክ ከእርሱ የተለዩ መሆናቸው ሊታወቅ የሚገቡ ሌሎች አማልክት ያሉ ይመስል በተጸውኦ ስም መጥራት ገና የክርስትና ዘመን ከመጀመሩ በፊት በአይሁዳውያን ሃይማኖት የቀረ ነገር በመሆኑ ዓለም አቀፉ የክርስትና እምነትም እውነተኛውን አምላክ በስም መጥራቱ ትክክል አይሆንም።”
ታዲያ እነዚህ ጠንካራ መሠረት ያላቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ናቸውን? ቀደም ብለን እንዳብራራነው ኢየሱስ የሚለው ስም ተከታዮቹ ይጠቀሙበት የነበረውን የመጀመሪያ አጠራር በትክክል አይወክልም። ይሁን እንጂ ኮሚቴው ይህን ምክንያት አድርጎ የኢየሱስን ስም እንደ “መካከለኛ” ወይም “ክርስቶስ” ባሉት የማዕረግ ስሞች አልተካም። መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ የማዕረግ ስሞች መጠቀሙ የማይካድ ቢሆንም በኢየሱስ ስም ላይ ተጨማሪ አድርጎ እንጂ ስሙን አስወጥቶ አይደለም።
ከእውነተኛው አምላክ መለየት የሚኖርባቸው ሌሎች አማልክት ስለሌሉ በአምላክ ስም መጠቀም አያስፈልግም የሚለው ምክንያትም ቢሆን ፈጽሞ ትክክል አይደለም። በሰው ልጆች የሚመለኩ በሚልዮን የሚቆጠሩ አማልክት አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ብዙ አማልክት . . . አሉ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 8:5፤ ፊልጵስዩስ 3:19) እርግጥ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ እንደተናገረው እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ ነው። ስለዚህ በእውነተኛው አምላክ ስም መጠቀም ከሚያስገኛቸው ትላልቅ ጥቅሞች እንዱ እውነተኛውን አምላክ ከሐሰት አማልክት በሙሉ ለመለየት ማስቻሉ ነው። ከዚህም በቀር በአምላክ ስም መጠቀም ‘ትክክል ባይሆን’ ኖሮ በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ ወደ 7, 000 ጊዜ ያህል የተጠቀሰው ለምንድን ነው?
ብዙ ተርጓሚዎች በዘመናዊ አጠራሩ የሚጻፈው የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም ብለው አላሰቡም። በትርጉሞቻቸው ውስጥ አስገብተውታል። ይህን በማድረጋቸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን አምላክ በይበልጥ የሚያስከብርና ከበኩረ ጽሑፉ ጣዕምና ለዛ ጋር በይበልጥ የሚስማማ ትርጉም ለማዘጋጀት ችለዋል። የአምላክን ስም በስፋት ከሚጠቀሙ በብዛት የሚሠራባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል የቫሌራ ትርጉም (በ1602 በስፓንኛ
የተዘጋጀ)፣ የአልሜዳ ትርጉም (በ1681 በፖርቱጊዝ ቋንቋ የተዘጋጀ)፣ የመጀመሪያው የኤልበርፈልደር ትርጉም (በ1871 የታተመ የጀርመንኛ ትርጉም)፣ የአሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን (በ19 01 የታተመ የእንግሊዝኛ ትርጉም) ይገኛሉ። አንዳንድ ትርጉሞች ደግሞ፣ በተለይ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል የተባለው ትርጉም ያህዌህ በሚለው የአምላክ ስም አጠራር ከዳር እስከ ዳር ተጠቅመዋል።አሁን ደግሞ የአምላክን ስም በትርጉሞቻቸው ውስጥ ያስገቡ ተርጓሚዎች የሰጡትን ማብራሪያ እናንብብና እነርሱ የሰጡትን ምክንያት ስሙን ያስወጡት ተርጓሚዎች ከሰጡት ምክንያት ጋር እናነጻጽር።
ሌሎቹ የአምላክን ስም ያስገቡበት ምክንያት
በ1901 የታተመው የአሜሪካን ስታንደርድ ቨርሽን ተርጓሚዎች የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል:- “[ተርጓሚዎቹ] መለኮታዊው ስም እጅግ በጣም ቅዱስ በመሆኑ ምክንያት መጠራት አይገባውም የሚለው የአይሁዳውያን አጉል እምነት በእንግሊዝኛውም ሆነ በማንኛውም ሌላ ትርጉም ላይ ሊሰለጥን እንደማይገባው በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል። . . . ይህ በዘጸ. 3:14, 15 ላይ የተገለጸውና በብሉይ ኪዳን በኩረ ጽሑፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ጎልቶ የተገለጸው ይህ የመታሰቢያ ስም አምላክ ግላዊ አካል ያለው አምላክ፣ የቃል ኪዳን አምላክ፣ ራሱን ለሌሎች የሚገልጥ አምላክ፣ የሕዝቦቹ አዳኝና ወዳጅ የሆነ አምላክ መሆኑን ያመለክታል። . . . ይህ ከብዙ ቅዱሳን ነገሮች ጋር ትስስር ያለው የተጸውኦ ስም አሁን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የነበረውን አጠያያቂ ያልሆነ ቦታ አግኝቷል።”
በጀርመንኛው ኤልበርፌልደር ቢበል የመጀመሪያ ትርጉም መቅድም ላይ ደግሞ የሚከተለውን እናነባለን:- “ጅሆቫ የተባለው ይህ የእስራኤል የቃል ኪዳን አምላክ ስም አንባቢው ለበርካታ ዓመታት የለመደው ስለሆነ እንዳለ አስቀምጠነዋል።”
ዘ ባይብል ኢን ሊቪንግ ኢንግሊሽ የተባለውን ትርጉም ያዘጋጀው ስቲቨን ቲ ባይንግተን በአምላክ ስም የተጠቀመበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል:- “የስሙ አጻጻፍና አጠራር ይህን ያህል ሊያሳስቡ የሚገቡ አይደሉም። ይበልጥ ሊያሳስብ የሚገባው ይህ ስም የግል መጠሪያ ስም መሆኑን ግልጽ ማድረጉ ላይ ነው። ይህን ስም እንደ “ጌታ” ባሉት የወል ስሞች እንዲያውም የባሰውን ጠቃሽ አመልካች በተጨመረባቸው ቅጽሎች [ለምሳሌ ያህል “ዘላለማዊው”] እያልን ብንተረጉመው በትክክል ልንረዳ የማንችላቸው ብዙ ጥቅሶች አሉ።”
ጄ ቢ ሮዘርሃም የተባሉት ሌላ ተርጓሚ የሰጡትም ምክንያት ሊስተዋል የሚገባው ነው። እኚህ ተርጓሚ በትርጉማቸው ውስጥ በአምላክ ስም ቢጠቀሙም ያህዌህ የሚለውን አጠራር መርጠዋል። ይሁን እንጂ ቆየት ብለው በ1911 ባሳተሙት ስተዲስ ኢን ዘ ሳልምስ (የመዝሙራት ጥናት) በተባለው መጽሐፍ ላይ ጅሆቫ ወደሚለው አጠራር ተመልሰዋል። ለምን ተመለሱ? ምክንያታቸውን እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “ጅሆቫ— በዚህ በአሁኑ የመዝሙር ትርጉም ውስጥ ይህ የመታሰቢያው ስም (ዘጸ. 3:18) የእንግሊዝኛ አጠራር የተሠራበት ትክክለኛው አጠራር ያህዌህ ነው መባሉ ስህተት ሆኖ ስለተገኘ ሳይሆን ዋነኛው ቁምነገር የመለኮታዊው ስም በቀላሉ መታወቅ በሚኖርባቸው እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች የሕዝብ ጆሮና ዓይን የለመደውን አጠራር መጠቀም የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ብቻ ነው።”
ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች በመዝሙር 34:3 ላይ “እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፣ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ” ተብለው ተመክረዋል። ታዲያ የአምላክ ስም የማይገኝባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚያነቡ ሰዎች ይህን ምክር እንዴት ሊፈጽሙ ይችላሉ? ቢያንስ አንዳንድ ተርጓሚዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚተረጉሙበት ጊዜ የአምላክን ስም ለማስገባት የሚያስችል ድፍረት ስለኖራቸውና ስሚዝና ጉድስፒድ እንዳሉት “የበኩረ ጽሑፉ ጣዕምና ለዛ” እንዳይጠፋ የሚያደርግ እርምጃ በመውሰዳቸው ክርስቲያኖች በጣም ደስ ይላ ቸዋል።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተርጓሚዎች፣ (የአምላክን ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያስገቡት እንኳን ሳይቀሩ) “አዲስ ኪዳን” ከሚባለው የክርስትና ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አስወጥተውታል። ይህን ያደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው? የአምላክ ስም በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል ውስጥ ለመጨመር የሚያበቃ ምክንያት ይኖራልን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ከጥቂት መቶ ዘመናት በኋላ የታተሙ የዚህ መጽሐፍ ግልባጮች መለኮታዊውን ስም ጅሆቫ ብለው ጽፈዋል።
^ አን.6 ዘፍጥረት 15:2 ዘጸአት 6:3፤ 15:3፤ 17:16፤ 23:17፤ 33:19፤ 34:23፤ ዘዳግም 3:24። በተጨማሪም ቲንደል በአዲስ ኪዳን አንትወርፕ፣ 1534 መጨረሻ ላይ ባስገባቸው ትርጉሞቹ ላይ የአምላክን ስም በሕዝቅኤል 18:23 እና በ36:23 ላይ አስገብቷል።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የኦቶራይዝድ ቨርሽን ተርጓሚዎች ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ያስገቡት በአራት ቦታዎች ብቻ ሲሆን በሌሎቹ ቦታዎች አምላክ እና ጌታ በሚሉት ቃላት ተክተውታል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአምላክ ስም መጠቀም “ፈጽሞ ስህተት” ከሆነ ታዲያ በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ውስጥ ወደ 7,000 ጊዜ ያህል ተጽፎ የሚገኘው ለምንድን ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የአምላክን ስም ለማጥፋት የተደረገ ርብርቦሽ ይሆን?
በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ስም የሚገኝበት በአፍሪካንስ ቋንቋ (የዳች ዝርያ ያላቸው ደቡብ አፍሪካውያን የሚናገሩት ቋንቋ) የተዘጋጀ ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱስ የለም። ይህም የሚያስደንቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም በዚያ አገር በሚነገሩ የጎሣ ቋንቋዎች የተተረጐሙ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአምላክ ስም በሰፊው ይጠቀማሉ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እንመልከት።
ነሐሴ 24 ቀን 1878 በተደረገው የእውነተኛዎቹ አፍሪካነርስ ማኅበር (ጂ አር ኤ) ስብሰባ ላይ በአፍሪካንስ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲዘጋጅ ጠንካራ ጥያቄ ቀረበ። ጉዳዩ ከስድስት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ተነሥቶ መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች ወደ አፍሪካንስ ቋንቋ የመተርጎሙ ሥራ እንዲጀመር ተወሰነ። ይህን ሥራ የተረከቡት በትራንስቫል ግዛት የትምህርት የበላይ ተቆጣጣሪ የነበሩት ኤስ ጄ ዱ ቱዋ ነበሩ።
ለዱ ቱዋ በተጻፈው የሥራ መመሪያ ደብዳቤ ውስጥ የሚከተለው ቃል ይገኝ ነበር:- “የጌታ መጠሪያ ስም የሆነው ጅሆቫ ወይም ጃህቬ ሳይተረጎም [ጌታ ወይም አምላክ በሚሉት ቃላት ሳይተካ ማለት ነው] እንዳለ ከዳር እስከ ዳር መጻፍ ይኖርበታል።” ኤስ ጄ ዱ ቱዋ ሰባት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ወደ አፍሪካንስ ቋንቋ ተረጎሙ። በእነዚህ መጽሐፎች ሁሉ የአምላክ ስም እንዳለ ተቀምጧል።
በሌሎች የደቡብ አፍሪካ ጽሑፎችም ላይ የአምላክ ስም የገባበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ1914 በጄ ኤ ማልሄርብ የተዘጋጀው ደ ኮርት ካቴኪስሙስ (አጭሩ የእምነት ማጥኛ መጽሐፍ) የተባለ ጽሑፍ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር:- “ታላቁ የአምላክ ስም ማነው?” መልሱ “በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ጌታ በሚሉት ታላላቅ ፊደሎች የተጻፈው ጅሆቫ ነው። ይህ [ስም] ለማንም ፍጡር ተሰጥቶ የማያውቅ ነው” ይላል።
ዲ ካትኪሳሲበክ (በደቡብ አፍሪካ የዳች ሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ፌደራዊ ኮሚሽን የታተመ ካቴኪዝም ወይም የመሠረተ ትምህርት ማጥኛ መጽሐፍ) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚከተለው ጥያቄ ሠፍሯል:- “ታዲያ ይሖዋ ወይም ጌታ የሚለውን ስም ፈጽሞ መጥራት አይገባንምን? እንዲህ የሚያደርጉት አይሁዶች ናቸው። . . . የትእዛዙ ትርጉም ይህ አይደለም። . . . በከንቱ አይሁን እንጂ በስሙ መጠቀም እንችላለን።” እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዲ ሃሌ ሉያ በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ እትሞች ላይ በአንዳንዶቹ መዝሙሮች ይሖዋ የተባለው ስም ይገኝ ነበር። ይሁን እንጂ የዱ ቱዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እምብዛም ተወዳጅነት አላገኘም፤ ስለሆነም በ1916 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚሽን ተቋቁሞ መጽሐፍ ቅዱስን በአፍሪካንስ ቋንቋ የማዘጋጀቱን ሥራ እንዲከታተል ተደረገ። ይህ ኮሚሽን የአምላክን ስም ከትርጉሙ ውስጥ ማስወጣትን የሥራ መመሪያው አድርጎ ነበር። በ1971 የደቡብ አፍሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የጥቂት መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን “ረቂቅ ትርጉም” በአፍሪካንስ ቋንቋ አሳትሟል። በዚህ ትርጉም መግቢያ ላይ የአምላክ ስም ቢጠቀስም በዋናው ጽሑፍ ውስጥ ግን አንድም ጊዜ አልተጠቀሰም። በ1979ም ሌላ “የአዲስ ኪዳን” እና የመዝሙር ትርጉም ቢታተምም የአምላክ ስም እንዲወጣ ተደርጓል።
በተጨማሪም ከ1970 ወዲህ ይሖዋ የተባለው የአምላክ ስም ከዲ ሃሌ ሉያ እንዲወጣ ተደርጓል። በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ የዳች ሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያን የሚያሳ ትመው የዲ ካትኪሳሲበክ ስድስተኛ እትም የይሖዋን ስም አስወጥቷል።
ይሖዋ የሚለውን ስያሜ ለማጥፋት የሚደረገው ርብርቦሽ በመጻሕፍት ላይ ብቻ አልተወሰነም። በፓርል በሚገኝ የዳች ሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ላይ ጅሆቫ ጂሬ (“ይሖዋ ያዘጋጃል”) የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ነበር። የዚህ ቤተ ክርስቲያንና የመሠረቱ ድንጋይ ፎቶግራፍ በአፍሪካንስ ቋንቋ በተዘጋጀው የጥቅምት 22, 1974 ንቁ! መጽሔት ላይ ወጥቷል። ከዚያ ጊዜ በኋላ የመሠረቱ ድንጋይ ዲ ኸረ ዛል ፋርዚን (“ጌታ ያዘጋጃል”) የሚል ጽሑፍ በተቀረጸበት ሌላ ድንጋይ ተተክቷል። የጥቅሱ ምዕራፍና ቁጥር እንዲሁም ቀኑና ዓመቱ እንዳለ ሳይለወጥ ሲቀር ይሖዋ የሚለው ስም ግን ተቀይሯል።
በዚህ ምክንያት ብዙ የአፍሪካን ቋንቋ ተናጋሪዎች የአምላክን ስም እንዳያውቁ ተደርገዋል። ስሙን የሚያውቁ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም ቢሆኑ በስሙ ለመጠቀም አይደፍሩም። እንዲያውም አንዳንዶቹ የአምላክ ስም ጌታ ነው በማለት ሰዎች በአምላክ ስም እንዳይጠቀሙ ይከራከራሉ። እንዲያውም ይሖዋ የሚለውን ስም የፈለሰፉት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው በማለት ይከስሳሉ።
[ሥዕሎች]
በደቡብ አፍሪካ፣ በፓርል ከተማ የሚገኝ የዳች ሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ። ጅሆቫ የሚለው የአምላክ ስም በፊት በሕንፃው መሠረት ድንጋይ ላይ ተጽፎ ነበር። (ከላይ በኩል በስተቀኝ ያለውን ተመልከት።) በኋላ ግን ጽሑፉ ተቀይሯል። (ከላይ በስተግራ ያለውን ተመልከት)
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፈረንሳይ አገር በፓሪስ በሚገኘው የቅዱስ ዠነቪየቭ ቤተ መጻሕፍት (ጥራዝ 162b) በሚገኝ ፑጂዮ ፊዴይ በተባለ መጽሐፍ በ1278 (በ13ኛው ወይም በ14ኛው መቶ ዘመን እንደተጻፈ ይታሰባል) የእጅ ጽሑፍ ቅጂ ላይ የአምላክ ስም ዮሖዋ ተብሎ ተጽፏል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዊልያም ቲንደል በ1530 ባሳተማቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ትርጉሙ ውስጥ የአምላክን ስም በዘጸአት 6:3 ላይ አስገብቶአል። በዚህ ስም የተጠቀመበትን ምክንያት ስለ ትርጉሙ በጻፈው ማስታወሻ ላይ አብራርቶአል።
[ምንጭ]
(ፎቶግራፉ የተገኘው ኒው ዮርክ ከሚገኘው የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ቤተ መጻሕፍት ነው)