በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑን አረጋግጧልን?

ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑን አረጋግጧልን?

ምዕራፍ 8

ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑን አረጋግጧልን?

በ1613 ኢጣልያዊው ሳይንቲስት ጋሊሊዮ “ሌተርስ ኦን ሰንስፖትስ” የተባለ ጽሑፍ አሳትሞ ነበር። በዚህ ጽሑፉ ፀሐይ ሳትሆን በምድር ዙሪያ የምትሽከረከረው ምድር በፀሐይ ዙሪያ እንደምትሽከረከር ገልጿል። ይህን በማለቱ ብዙ ነገር የደረሰበት ሲሆን በመጨረሻ ‘በመናፍቅነት’ ተጠርጥሮ በሮማ ካቶሊክ ኢንክዊዚሽን ፊት ለጥያቄ ቀረበ። የኋላ ኋላም ሐሳቡን ‘እንዲክድ ’ አስገደዱት። ምድር በፀሐይ ዙሪያ ትሽከረከራለች የሚለው ሐሳብ እንደ መናፍቅነት የታየው ለምንድን ነበር? የጋሊሊዮ ከሳሾች ይህ ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይቃረናል በማለታቸው ነው።

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ጋሊሊዮ ምድር በፀሐይ ዙሪያ ትሽከረከራለች በማለቱ ምን አጋጥሞታል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ስናወዳድረው ምን ነገር እናስተውላለን?

በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ አይደለም የሚለው አመለካከት በሰፊው ይንጸባረቃል። አንዳንዶችም ይህን ለማረጋገጥ የጋሊሊዮን ሁኔታ እንደ ምሳሌ አድርገው ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነውን? ይህን ጥያቄ ስንመልስ መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት፣ የታሪክ፣ የጸሎት፣ የሕግ፣ የምክርና ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የያዘ መጽሐፍ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ እንደሆነ አይናገርም። የሆነ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ የሚዳስሳቸው ከሳይንስ ጋር ተዛምዶ ያላቸው ጉዳዮች ሁሉ ፍጹም ትክክለኛ ናቸው።

ፕላኔቷ ምድራችን

2. መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በሕዋ ውስጥ ያላትን አቀማመጥ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

2 ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፕላኔቷ ምድራችን ምን እንደሚል ተመልከት። በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ:- “ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፣ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል” የሚል ቃል እናነባለን። (ኢዮብ 26:​7) ይህን ሐሳብ “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል” ከሚለው የኢሳይያስ አባባል ጋር አወዳድር። (ኢሳይያስ 40:​22) “በባዶ ስፍራ” ‘አንዳች አልባ’ የተንጠለጠለች ክብ ምድር እንዳለች የተሰጠው መግለጫ ድቡልቡሏ ምድር በባዶ ሥፍራ ተንጠልጥላ የሚያሳየውን የጠፈር ተመራማሪዎች ፎቶግራፍ ያስታውሰናል።

3, 4. የምድር የውኃ ዑደት ምን ይመስላል? መጽሐፍ ቅዱስስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ይላል?

3 አስገራሚ የሆነውንም የምድር የውኃ ዑደት ተመልከት። ኮምፕተን ኢንሳይክለፒዲያ ምን ነገር እንደሚከናወን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ውኃ . . . ከውቂያኖሶች ላይ በመትነን ወደ ከባቢ አየር ይሄዳል። . . . በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ያለማቋረጥ የሚዘዋወረው አየር እርጥበት አዘል የሆነውን አየር ወደ የብስ ይወስደዋል። አየሩ ሲቀዘቅዝ ተኑ ወደ ጤዛነት ይለወጣል። እነዚህም ባብዛኛው እንደ ደመና ሆነው ይታያሉ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ የውኃ ጠብታዎች ተጠራቅመው ዝናብ ይሆናሉ። ከባቢ አየሩ በጣም ከቀዘቀዘ ደግሞ ከዝናብ ይልቅ በረዶ ይፈጠራል። በሁለቱም ሁኔታዎች ቢሆን ከውቂያኖሶች ላይ ተነስቶ በመቶዎች ብሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ የሄደው ውኃ ወደ ምድር ይወርዳል። ምድር ላይ ከወረደም በኋላ አንድ ላይ ተጠራቅሞ ላይ ላዩን በጅረት መልክ አሊያም ወደ ምድር ውስጥ ሰርጎ በመግባት ውስጥ ውስጡን ወደ ባሕር የመልስ ጉዞውን ይጀምራል።”1

4 በየብስ ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችለው ይህ አስገራሚ ሂደት ከ3,000 ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀላልና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ተገልጿል። “ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፣ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደገና ወደዚያ ይመለሳሉ።”​—⁠መክብብ 1:​7

5. መዝሙራዊው የምድርን ተራራዎች በተመለከተ የተናገረው ነገር ከዘመናዊው ሐሳብ ጋር የሚያስገርም ስምምነት ያለው ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

5 ከዚህ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተራሮች አሠራር የያዘው ጥልቅ እውቀት ነው። አንድ የስነ ምድር መማሪያ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ከቅድመ ካምብራዊ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ተራሮችን የመሥራቱና የማፍረሱ የማያቋርጥ ሂደት ቀጥሏል። . . . ተራሮች ባሕሩ ሲደርቅ አግጠው መውጣት ብቻ ሳይሆን ይታዩ የነበሩትም ከብዙ ጊዜ በኋላ በባሕር ተሸፍነው ይጠፉና እንደገና ደግሞ ብቅ ይላሉ።”2 ይህን አባባል ከሚከተለው የመዝሙራዊው አገላለጽ ጋር አወዳድር:- “በጥቅል ውኃ [ምድርን] እንደ ልብስ ከደንሃት፣ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። አንተ ወዳዘጋጀህላቸው ሥፍራ ተራሮች ወደ ላይ ወጡ ሸለቆዎችም ወደታች ወረዱ።”​—⁠መዝሙር 104:​6, 8 NW

“በመጀመሪያ”

6. የአጽናፈ ዓለሙን አጀማመር በሚመለከት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር የሚስማማ ሆኖ የተገኘው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ነው?

6 የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ቁጥር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:​1) ሳይንቲስቶች አንዳንድ ነገሮችን ማስተዋላቸው በእርግጥም ግዑዙ አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ አለው ወደሚል ጽንሰ ሐሳብ አድርሷቸዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕልውና ያገኘ ነገር ነው። ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ምንም ነገር ማወቅ አይቻልም የሚል አቋም ያላቸው የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ጃስትሮው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ዝርዝር ጉዳዮቹ ይለያዩ እንጂ በጠፈር ምርምርና በመጽሐፍ ቅዱስ የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ ነገሮች ተመሳሳይ ናቸው። ከሰው ልጅ ሕልውና በፊት ደረጃ በደረጃ የተፈጸሙት ነገሮች የጀመሩት በአንድ በተወሰነ ወቅት ላይ እንደ ብርሃን ብልጭታ በድንገትና በቅጽበት ነው።”3

7, 8. ብዙ ሳይንቲስቶች የአጽናፈ ዓለሙን አጀማመር በተመለከተ አምላክ የተጫወተውን ሚና ባይቀበሉም ምን ነገር አምነው ለመቀበል ተገድደዋል?

7 ብዙ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለሙ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ የመጣ ነገር መሆኑን ቢያምኑም ‘እግዚአብሔር ፈጠረው’ የሚለውን ሐሳብ ግን አይቀበሉም። የሆነ ሆኖ ዛሬ አንዳንዶች ከዚህ ሁሉ ነገር በስተጀርባ አንድ የማሰብ ችሎታ ያለው ኃይል እንዳለ የሚያሳዩትን ማስረጃዎች መካድ እንደማይቻል ያምናሉ። የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፍሪማን ዳይሰን እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል:- “ስለ አጽናፈ ዓለሙ ይበልጥ በተመራመርኩና ስለ ንድፉ ዝርዝር ባጠናሁ መጠን ጽንፈ ዓለሙ የሰውን ልጅ ለመቀበል አስቀድሞ ዝግጅት እንዳደረገ የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎች አገኛለሁ።”

8 ዳይሰን በመቀጠል እንዲህ ሲሉ አምነዋል:- “በአሥራ ስምንተኛው ሳይሆን በሃያኛው መቶ ዘመን አስተሳሰብና ቋንቋ የተቀረጽኩ ሳይንቲስት እንደመሆኔ መጠን የአጽናፈ ዓለሙ ንድፍ አምላክ እንዳለ ያረጋግጣል ብዬ አልናገርም። የአጽናፈ ዓለሙ ንድፍ በሥራው ወሳኝ ሚና የተጫወተ አእምሮ አለ ከሚለው መላምት ጋር የሚስማማ መሆኑን እናገራለሁ።”4 የሰጡት አስተያየት የዘመናችንን ጥርጣሬ የሞላበት አመለካከት ያጋለጠ ነው። ይሁን እንጂ ይህን የጥርጣሬ አመለካከት ወደ ጎን ብንተወው በዘመናዊው ሳይንስና “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መካከል የሚያስገርም ስምምነት እንዳለ እናስተውላለን።​—⁠ዘፍጥረት 1:​1

ጤናና ንጽሕና አጠባበቅ

9. ተላላፊ የቆዳ በሽታዎችን በሚመለከት የተሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ተግባራዊ ጥበብ የተንጸባረቀበት እንዴት ነው? (ኢዮብ 12:​9, 16)

9 መጽሐፍ ቅዱስ የሚዳስሰውን ሌላ መስክ ደግሞ ተመልከት። ጤናንና የንጽሕና አጠባበቅ ነው። አንድ እስራኤላዊ ሥጋ ደዌ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ የሚያሳድር የቆዳ ችግር ካለበት ተገልሎ እንዲቀመጥ ይደረግ ነበር። “ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር ውጭ ይሆናል።” (ዘሌዋውያን 13:​46) በበሽታው የተበከለው ልብስ ሳይቀር መቃጠል ነበረበት። (ዘሌዋውያን 13:​52) በዚያ ዘመን ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ ይህ ነበር።

10. በአንዳንድ አገሮች ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ የሚሰጠውን ምክር ቢከተሉ የሚጠቀሙት በምን መንገድ ነው?

10 ሌላው በጣም ጠቃሚ ሕግ ደግሞ የሰውን ዓይነ ምድር በተመለከተ የተሰጠው ሕግ ሲሆን ከሰፈሩ ውጭ መቀበር እንዳለበት ያዝዛል። (ዘዳግም 23:​12, 13) ይህ ሕግ እስራኤላውያንን ከብዙ በሽታዎች እንደጠበቃቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬም እንኳ ሳይቀር በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ከባድ የጤና ችግሮች የሚከሰቱት ከሰው የሚወጡ ቁሻሻዎች በአግባቡ ስለማይወገዱ ነው። በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙት ሰዎች በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ሕግ ቢታዘዙ ኖሮ ብቻ የተሻለ ጤና በኖራቸው ነበር።

11. መጽሐፍ ቅዱስ የአእምሮ ጤንነትን በተመለከተ የሚሰጠው የትኛው ምክር ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል?

11 የላቀ ደረጃ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጤና አጠባበቅ የአእምሮ ጤናን ሳይቀር የሚያካትት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ትሑት [“የተረጋጋ፣” NW] ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፤ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል” ይላል። (ምሳሌ 14:​30) በቅርብ ዓመታት የተደረጉ የሕክምና ምርምሮች አንድ ሰው ለሁኔታዎች ያለው አመለካከት በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ሲ ቢ ቶማስ ለ16 ዓመታት ያህል የእያንዳንዱን ተማሪ ስነ ልቦናዊ ባሕርይ ለበሽታ የተጋለጡባቸውን አጋጣሚዎች በማነጻጸር ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ተመራቂ ተማሪዎች ላይ ጥናት አካሂደዋል። አንድ ያስተዋሉት ነገር አለ:- ከተመራቂዎቹ መካከል ከሁሉ ይበልጥ ለበሽታ የተጋለጡት ቁጡዎችና የሆነ ችግር ሲገጥማቸው ከልክ በላይ የሚጨነቁት ሆነው ተገኝተዋል።5

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

12. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋሊሊዮ ስለ ምድር የገለጸው ጽንሰ ሐሳብ መናፍቅነት ነው ብላ የተከራከረችው ለምን ነበር?

12 መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንሳዊ መስኮች ይህን ያህል ትክክለኛ ከሆነ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በፀሐይ ዙሪያ የምትሽከረከረው ምድር ነች የሚለውን የጋሊሊዮ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም ብላ የተቃወመችው ለምንድን ነው? በወቅቱ የነበሩት መሪዎች ለአንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ከሰጡት ትርጓሜ የተነሣ ነው።6 ትክክል ነበሩን? እስቲ የጠቀሷቸውን ሁለት ጥቅሶች እንይና ትክክል ነበሩ ወይስ አልነበሩም የሚለውን ጉዳይ እንመልከት።

13, 14. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተሳሳተ መንገድ የተጠቀመችባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? አብራራ።

13 አንዱ ጥቅስ እንዲህ ይላል:- “ፀሐይ ትወጣለች፣ ፀሐይም ትገባለች፣ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኩላለች።” (መክብብ 1:​5) የቤተ ክርስቲያኒቱ አባባል “ፀሐይ ትወጣለች” እና “ፀሐይ ትገባለች” የሚሉት አገላለጾች የምትዞረው ፀሐይ እንጂ ምድር እንዳልሆነች ያሳያል የሚል ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን ፀሐይ ትወጣለች፣ ትገባለች እንላለን። ሆኖም የምትንቀሳቀሰው ምድር እንጂ ፀሐይ እንዳልሆነች አብዛኞቻችን እናውቃለን። እንዲህ ዓይነቶቹን መግለጫዎች የምንጠቀመው ለሰብዓዊ ተመልካች ፀሐይ የምትንቀሳቀስ መስላ ስለምትታይ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊም ያደረገው ከዚህ የተለየ ነገር አልነበረም።

14 ሌላው ጥቅስ ደግሞ “ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት” ይላል። (መዝሙር 104:​5) ይህ ጥቅስ ምድር ከተፈጠረች በኋላ በምንም ዓይነት መንቀሳቀስ እንደማትችል ያሳያል የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል። ከዚህ ይልቅ ግን ጥቅሱ ጠበቅ አድርጎ የሚገልጸው መንቀሳቀስ ስላለመቻሏ ሳይሆን ዘላቂነት ያላት ስለመሆኗ ነው። ሌሎቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንደሚያረጋግጡት ምድር ‘ተናውጣ’ ከሕልውና ውጭ አትሆንም ወይም አትጠፋም። (መዝሙር 37:​29፤ መክብብ 1:​4) ይህም ጥቅስ ቢሆን ምድርና ፀሐይ አንዳቸው በሌላው ዙሪያ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር ምንም ተዛምዶ የለውም። በጋሊሊዮ ዘመን ነፃ ሳይንሳዊ ውይይት እንዳይደረግ ያገደችው ቤተ ክርስቲያኒቱ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም።

ዝግመተ ለውጥና ፍጥረት

15. የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ምንድን ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረነውስ እንዴት ነው?

15 ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ዘመናዊው ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ጨርሶ ሊጣጣሙ የማይችሉበት መስክ እንዳለ ይሰማቸዋል። አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተገኙት በሚልዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከነበረች ትንሽ ሕያው ነገር እየተሻሻሉ ነው በሚለው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ያምናሉ። በአንጻሩ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ትላልቆቹ ሕያዋን ወገኖች እያንዳንዳቸው እንደተፈጠሩና ‘እንደየወገናቸው’ ብቻ እንደተራቡ ያስተምራል። ሰው “ከምድር አፈር” እንደተፈጠረም ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:​21፤ 2:​7) ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጉልህ ሳይንሳዊ ስህተት እንዳለ የሚያሳይ ነውን? እስቲ እንዲህ ብለን ከመደምደማችን በፊት ሳይንስ ከሚናገርለት ጽንሰ ሐሳብ በተቃራኒ የሚያውቀው ምን ነገር እንዳለ በጥሞና እንመርምር።

16-18. (ሀ) ቻርልስ ዳርዊን በዝግመተ ለውጥ እንዲያምን ያደረገው የትኛው የተመለከተው ነገር ነበር? (ለ) ዳርዊን በጋላፓጎስ ደሴቶች ላይ የተመለከተው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ነገር ጋር አይቃረንም ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

16 ባለፈው መቶ ዘመን የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ያስፋፋው ቻርልስ ዳርዊን ነው። ዳርዊን በፓስፊክ ጋላፓጎስ ደሴቶች ላይ በነበረበት ወቅት በተለያዩ ደሴቶች ላይ ባያቸው የተለያዩ የድንቢጥ ዝርያዎች በጣም ተደንቆ ነበር። እነዚህ ዝርያዎች በሙሉ ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ መሆን አለባቸው ብሎ አሰበ። ይህም ሁሉም ሕያዋን ነገሮች የመጡት ከመጀመሪያዋ አንዲት ትንሽ ሕያው ነገር ነው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ እንዲያስፋፋ በከፊል አስተዋጽኦ አድርጓል። ዳርዊን ትላልቅ ፍጥረታት ከትናንሽ ፍጥረታት እየተሻሻሉ እንዲመጡ የሚያደርገው ተፈጥሮ የመረጠችው ወይም በሌላ አባባል ትግሉን የተወጣው በሕይወት ለመቀጠል የመቻሉ ሁኔታ ነው ሲል ተናግሯል። ለዝግመተ ለውጥ ምስጋና ይግባውና በየብስ ላይ የሚኖሩ እንስሳት ከዓሦች፣ ወፎች ደግሞ በሆዳቸው ከሚሳቡ እንስሳት፣ ሌሎችም እንዲሁ ሊገኙ ችለዋል ብሏል።

17 እንደ እውነቱ ከሆነ ዳርዊን ርቀው በሚገኙ በእነዚያ ደሴቶች ላይ ያስተዋለው ነገር አንድ ሕያው የፍጥረት ዓይነት የተለያዩ ዝርያዎች ሊኖሩት እንደሚችል ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር አይስማማም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ሁሉም የሰው ዘሮች የተገኙት ከመጀመሪያዎቹ አንድ ባልና ሚስት ነው። (ዘፍጥረት 2:​7, 22-24) በመሆኑም እነዚያ የተለያዩ የድንቢጥ ዝርያዎች የዘር ግንዳቸው አንድ ነው መባሉ እንግዳ ነገር አይደለም። ሆኖም ድንቢጦች ድንቢጥ እንደሆኑ ቀጠሉ እንጂ ከጊዜ በኋላ ወደ ጭልፊትነት ወይም ንስርነት አልተለወጡም።

18 ዳርዊን የተመለከታቸው የተለያዩ የድንቢጥ ዝርያዎችም ሆኑ ሌሎቹ ነገሮች የሚያረጋግጡት ሕያዋን ነገሮች በሙሉ ሻርክም ሆነ የባሕር ጭላት፣ ዝሆንም ሆነ ክርክሬ ትል ሁሉም የዘር ግንዳቸው አንድ ነው የሚለውን ሐሳብ አይደለም። የሆነ ሆኖ ብዙ ሳይንቲስቶች ዝግመተ ለውጥ እንዲሁ ጽንሰ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ እውነታ መሆኑን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ጽንሰ ሐሳቡ ያሉበትን ችግሮች እያወቁም ያም ሆነ ይህ እናምንበታለን ብለው ይናገራሉ። እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ዝግመተ ለውጥ መጽሐፍ ቅዱስን ስህተት ነው እስኪያሰኝ ድረስ በተጨባጭ የተረጋገጠ ነገር መሆን አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።

በተጨባጭ የተረጋገጠ ነውን?

19. የቅሪተ አካል ማስረጃዎች የሚደግፉት ዝግመተ ለውጥን ነው ወይስ ፍጥረትን?

19 የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ትክክል መሆን አለመሆኑን እንዴት መፈተን ይቻላል? ከሁሉ ይበልጥ ቀላሉ ዘዴ ከአንዱ ዓይነት ዘር ወደ ሌላው ቀስ በቀስ ለውጥ ተካሂዶ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ቅሪት አካሎችን መመርመር ነው። ለውጥ ተካሂዷልን? ብዙ ሳይንቲስቶች በሐቀኝነት እንዳመኑት እንዲህ ዓይነት ለውጥ አልተካሄደም። ከእነዚህ ሳይንቲስቶች አንዱ የሆኑት ፍራንሲስ ሂቺንግ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በዋና ዋናዎቹ የእንስሳት ቡድኖች መካከል የሚዛመድ ነገር እንዳለ ብትፈልጉ ምንም ነገር አታገኙም።”7 ሳይንቲስቶች ቀስ በቀስ ለውጥ ይካሄዳል ለሚለው የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ አማራጭ ይሆናል ብለው ያሰቡት የቅሪት አካል ማስረጃ ይህንን ማረጋገጥ እንዳልቻለ በግልጽ ታይቷል። እንዲያውም በቅሪት አካል ፍለጋ ያልታሰቡ የእንስሳት ዓይነቶች መገኘታቸው ዝግመተ ለውጥን የሚደግፍ ሳይሆን ልዩ ፍጥረታት እንደነበሩ የሚያረጋግጥ ነው።

20. ሕያው የሆኑ ሕዋሳት የሚራቡበት መንገድ ዝግመተ ለውጥ እንዲከናወን የሚፈቅድ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

20 ከዚህም በተጨማሪ ሂቺንግ ሕያዋን ነገሮች መሰላቸውን እንዲተኩ ተደርገው እንጂ ቀስ በቀስ ወደ ሌላ ዓይነት እንዲቀየሩ ተደርገው እንዳልተዘጋጁ ገልጸዋል። እንዲህ አሉ:- “ሕያው ሕዋሳት ፍጹም መሰሎቻቸው የሆኑ ሌሎች ሕዋሳትን በማስገኘት ይባዛሉ። በዚህ ሂደት መሀል የሚኖረው ልዩነት ኢምንት ከመሆኑ የተነሳ የትኛውም ሰው ሠራሽ መሣሪያ ሊተካከለው አይችልም። በተጨማሪም ፍጥረታቱ የሚያደርጉትን ለውጥ የሚገድብ ነገር በውስጣቸው አለ። ዕጽዋት እስከ ተወሰነ መጠን ካደጉ በኋላ ከዚያ በላይ ጨርሶ አይጨምሩም። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢቀየስላቸው ትንኞች ከትንኝነት አይለወጡም።”8 ሳይንቲስቶች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ትንኞች ላይ የለውጥ ሂደት ለማካሄድ ሞክረው ወደ ሌላ ነገር እንዲለወጡ ለማድረግ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

የሕይወት አጀማመር

21. ለዝግመተ ለውጥ አማኞች ትልቅ ችግር የፈጠረባቸው ሉዊ ፓስተር የደረሰበት የትኛው መደምደሚያ ነው?

21 የዝግመተ ለውጥ አማኞች ሊመልሱት ያልቻሉት ሌላው አከራካሪ ጥያቄ ደግሞ ሕይወት የጀመረው እንዴት ነው? የሚለው ነው። ሁላችንም የተገኘነው ከእርሷ ነው የሚባልላት የመጀመሪያዋ ትንሽ ሕያው ነገር እንዴት ወደ ሕልውና መጣች? ከተወሰኑ መቶ ዘመናት በፊት ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ይህን ያህል አስቸጋሪ አይሆንም ነበር። ያኔ አብዛኞቹ ሰዎች ዝንቦች ከበሰበሰ ሥጋ ሊፈጠሩ ይችላሉ እንዲሁም አንድ ላይ የተከማቸ ቡትቶ በድንገት አይጦች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል ብለው ያስቡ ነበር። ሆኖም ከመቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ፈረንሳዊው ኬሚስት ሉዊ ፓስተር ሕይወት ሊገኝ የሚችለው ቀደም ሲል ከነበረ ሕያው ነገር ብቻ እንደሆነ በግልጽ አስረድቷል።

22, 23. እንደ ዝግመተ ለውጥ አማኞች አባባል ከሆነ ሕይወት የተገኘው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ እውነታዎቹ ምን ያሳያሉ?

22 ታዲያ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ስለ ሕይወት አመጣጥ ምን ብለው ያብራራሉ? በጣም በሰፊው የሚታወቀው ጽንሰ ሐሳብ እንደሚገልጸው ከሆነ ከብዙ ሚልዮን ዓመታት በፊት የኬሚካሎችና የኃይል በአጋጣሚ መደባለቅ ሕይወት ከመቅጽበት እንዲጀምር አስችሏል። ፓስተር ያረጋገጠው መሠረታዊ ደንብስ? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ እንዲህ ብሏል:- “ፓስተር ዛሬ ምድር ላይ ባሉት ኬሚካላዊም ሆኑ ፊዚካላዊ ሁኔታዎች ሕይወት በድንገት ሊጀምር እንደማይችል አረጋግጧል። ይሁን እንጂ በቢልዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የነበሩት ኬሚካላዊም ሆኑ ፊዚካላዊ ሁኔታዎች ዛሬ ካሉት እጅግ የተለዩ ነበሩ”!9

23 ሁኔታዎቹ ከዛሬው እጅግ የተለዩ ቢሆኑም ሕይወት በሌላቸው ነገሮችና በትንሿ ሕያው ነገር መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ማይክል ዴንተን ኢቮሉሽን​—⁠ኤ ቲዮሪ ኢን ክራይስስ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “በአንድ ሕያው ሕዋስና ሕያው ባልሆነ የረቀቀ ሁኔታ ባለው አንድ ባልጩት ወይም አንድ የበረዶ ጠጠር መካከል ልንገምተው ከምንችለው በላይ ሰፊ የሆነና እዚህ ያበቃል የማይባል ልዩነት አለ።”10 ሕይወት የሌለው ነገር እንዲሁ ድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ ሕያው ይሆናል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ‘ሕይወት የሚገኘው ከሕያዋን ነገሮች’ ነው፤ ሕይወትንም የፈጠረው አምላክ ነው የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ ከእውነታው ጋር የሚስማማ ነው።

በፍጥረት የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?

24. የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ችግሮች ቢኖሩበትም ብዙ ሳይንቲስቶች ይህን ጽንሰ ሐሳብ የሙጥኝ ያሉት ለምንድን ነው?

24 የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ችግር የሞላበት ቢሆንም ዛሬ በፍጥረት ማመን ኢ-ሳይንሳዊ እንደሆነ አልፎ ተርፎም እንደ እንግዳ ነገር ይታያል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? እንደ ፍራንሲስ ሂቺንግ ያሉት የዝግመተ ለውጥን ድክመት በሐቀኝነት የጠቆሙት ባለሙያዎች ሳይቀሩ የፍጥረትን ሐሳብ የማይቀበሉት ለምንድን ነው?11 ማይክል ዴንተን ዝግመተ ለውጥ ይህ ሁሉ ድክመት እንዳለበት ቢታወቅም ከፍጥረት ጋር ግንኙነት ያላቸው ጽንሰ ሐሳቦች “ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ጣልቃ ገብነት እንዳለ ስለሚያስተምሩ” የዝግመተ ለውጥ ትምህርት መሰጠቱን ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።12 በሌላ አባባል ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት ያጣው ፈጣሪ አለ በማለቱ ነው። ይህ ቀደም ሲል ተዓምራትን በሚመለከት ከገጠመን:- ተዓምራት ተዓምር ስለሆኑ ብቻ ሊፈጸሙ አይችሉም! ከሚለው ምክንያታዊነት የጎደለው አመለካከት የተለየ አይደለም።

25. ዝግመተ ለውጥ የሕይወትን አጀማመር በሚመለከት ከፍጥረት ሐሳብ ጋር ጎን ለጎን የሚታይ አንድ ራሱን የቻለ አማራጭ እንዳልሆነ የሚያሳየው ከሳይንስ አንጻር የተገኘበት የትኛው ድክመቱ ነው?

25 ከዚህም በላይ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ራሱ ከሳይንስ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ላይ ወድቋል። ማይክል ዴንተን ሐሳባቸውን በመቀጠል:- “[የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ] በመሠረቱ ታሪካዊ ቅንብር ስለሆነ እንደሌላው ሳይንስ በሙከራ ወይም ደግሞ አካባቢያችንን በማስተዋል ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም። . . . ከዚህም በላይ ዝግመተ ለውጥ የሕይወት አጀማመር፣ የማስተዋል ችሎታ አጀማመር የሚሉትን የመሰሉ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ተከታታይ ክስተቶችን ይዘረዝራል። እነዚህ አምሳያ የሌላቸው ክስተቶች የማይደገሙ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ሙከራ ሊካሄድባቸው አይችልም።”13 እውነታው እንደሚያሳየው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ በብዙዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ያግኝ እንጂ እንከን የሞላበት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት አጀማመር የሚሰጠውን መግለጫ ለማጣጣል የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ምክንያት አያቀርብም። ­የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ እነዚህ “የማይደገሙና” “በዓይነታቸው ልዩ” የሆኑ ክስተቶች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በዘለቁ የፍጥረት ‘ቀናት’ ውስጥ እንዴት እንደተከናወኑ የሚገልጽ ምክንያታዊ ዘገባ ያቀርባል። *

የጥፋት ውኃን በሚመለከት ምን ማለት ይቻላል?

26, 27. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውኃን በሚመለከት ምን ይላል? (ለ) የጎርፉ ውኃ በከፊል የመጣው ከየት መሆን አለበት?

26 ብዙ ሰዎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስና በዘመናዊው ሳይንስ መካከል ያለ ሌላ አለመጣጣም ነው ብለው የሚያስቡትን ነጥብ ይጠቅሳሉ። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የሰው ልጆች ክፋት እጅግ በመባባሱ አምላክ ሊያጠፋቸው እንደወሰነ እናነባለን። ይሁን እንጂ ጻድቅ ሰው የነበረውን ኖኅን በእንጨት ትልቅ መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። ከዚያም አምላክ በሰው ልጅ ላይ የጥፋትን ውኃ አወረደ። ከዚህ ጥፋት የተረፉት ኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም ለዘር የቀሩት የእንስሳት ዓይነቶች ብቻ ናቸው። የውኃው መጥለቅለቅ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ “ከሰማይም በታች ያሉ ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።”​—⁠ዘፍጥረት 7:​19

27 መላዋን ምድር የሚሸፍን ውኃ ከየት መጣ? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ መልሱን ይሰጠናል። በፍጥረት ሥራ መጀመሪያ አካባቢ የከባቢው አየር ጠፈር መልክ መልኩን ሲይዝ “ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ” ውኆች እንዲኖሩ ተደርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 1:​7፤ 2 ጴጥሮስ 3:​5) የጥፋት ውኃው በወረደ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ።” (ዘፍጥረት 7:​11) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው “ከጠፈር በላይ” የነበረው ውኃ ወርዶ መጥለቅለቅ እንዲፈጠር አድርጓል።

28. ኢየሱስን ጨምሮ የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች የጥፋት ውኃውን የተመለከቱት እንዴት ነው?

28 ዘመናዊ መማሪያ መጻሕፍት ምድር አቀፍ መጥለቅለቅ ደርሶ ነበር የሚለውን ሐሳብ ወደ ማጣጣል አዘንብለዋል። በመሆኑም የጥፋት ውኃው ታሪክ እንዲሁ ተረት ነው ወይስ በእርግጥ የተፈጸመ ነገር? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ከጥፋት ውኃው በኋላ የነበሩት የይሖዋ አምላኪዎች ይህ ታሪክ እውነተኛ መሆኑን አምነው እንደተቀበሉ ልብ ልንል ይገባል። እንደተረት አልቆጠሩትም። ይህ ነገር በእርግጥ እንደተፈጸመ ከጠቀሱት መካከል ኢሳይያስ፣ ኢየሱስ፣ ጳውሎስና ጴጥሮስ ይገኙበታል። (ኢሳይያስ 54:​9፤ ማቴዎስ 24:​37-39፤ ዕብራውያን 11:​7፤ 1 ጴጥሮስ 3:​20, 21፤ 2 ጴጥሮስ 2:​5፤ 3:​5-7) ይሁን እንጂ ይህንን ምድር አቀፍ መጥለቅለቅ በተመለከተ መልስ ሊያገኙ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ።

የጎርፉ ውኃ

29, 30. የጥፋት ውኃው ሊፈጸም የሚችል ነገር መሆኑን የሚያሳየው የትኛው የምድር ውኃ ሁኔታ ነው?

29 በመጀመሪያ ደረጃ መላዋ ምድር በውኃ ተጥለቀለቀች ማለት የማይመስል ነገር አይሆንምን? አይሆንም። እንደ እውነቱ ከሆነ አሁንም ቢሆን ምድር በተወሰነ ደረጃ እንደተጥለቀለቀች ናት ለማለት ይቻላል። ሰባ በመቶ የሚያክለው የምድር ክፍል በውኃ የተሸፈነ ሲሆን የብሱ 30 በመቶ ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ 75 በመቶ የሚያክለው ለመጠጥ የሚሆን ውኃ በበረዶ ግግሮችና በምድር ዋልታዎች በተቆለሉት በረዶዎች መልክ ተከማችቶ ይገኛል። ይህ ሁሉ በረዶ ቢቀልጥ የባሕር ወለል አሁን ካለበት እጅግ ከፍ ይል ነበር። እንደ ኒው ዮርክና ቶኪዮ ያሉት ከተሞችም ሙሉ በሙሉ በውኃ በተዋጡ ነበር።

30 ከዚህም በተጨማሪ ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል:- “የሁሉም ባሕሮች አማካይ ጥልቀት 3,790 ሜትር (12,430 ጫማ) እንደሚሆን ተገምቷል። ይህ ቁጥር ደግሞ ምድር ከባሕር ወለል በላይ ካለው አማካይ ከፍታ ማለትም ከ840 ሜትር (2,760 ጫማ) ጋር ሲወዳደር ልዩነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። አማካይ ጥልቀቱን ከእያንዳንዱ የወለል ስፋት ጋር ስናባዛው በዓለም ላይ የሚገኙት ውቅያኖሶች ይዘት ከባሕር ወለል በላይ ከሚገኘው የምድር ይዘት 11 ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ሆኖ እናገኘዋለን።”14 በመሆኑም ተራራዎች ተደልድለው የባሕሩን ውኃ የቋጠሩት ጎድጓዳ ቦታዎች ቢሞሉና ሁሉም ነገር ደልዳላ ሜዳ ቢሆን ባሕሩ መላዋን ምድር በብዙ ሺህ ሜትሮች ከፍታ ይሸፍናት ነበር።

31. (ሀ) የውኃ መጥለቅለቁ በዚያ ዘመን ደርሷል ለማለት የምንችለው ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ምድር ምን ዓይነት ሁኔታዎች ከነበሩት ነው? (ለ) ከጥፋት ውኃው በፊት ተራሮቹ ከአሁኑ ያነሱና ባሕሮቹን ያቆሩት ጎድጓዳ ቦታዎችም የዛሬውን ያክል ጥልቅ ላይሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳየው ምንድን ነው?

31 በዚያ ዘመን የጥፋት ውኃ እንዲከሰት ከጥፋቱ በፊት የነበሩት ባሕሩን ያቆሩት ጎድጓዳ ቦታዎች ጥልቀታቸው ከአሁኑ ያነሰ ተራሮቹ ደግሞ ከፍታቸው ከአሁን ዝቅ ያለ ኖሮ መሆን አለበት። ይህ ሊሆን ይችላልን? አንድ የመመሪያ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ዛሬ ለዓይን የሚያታክት ከፍታ ያላቸው ተራራዎች በአንድ ወቅት፣ ከብዙ ሚልዮን ዓመታት በፊት ማለት ነው፣ በውቅያኖሶች የተሸፈኑና በቦታቸው የተንጣለለ ሜዳ የነበረባቸው ናቸው። . . . የአሕጉሮቹ ስፍሃን (plates) መንቀሳቀስ ምድሩ፣ ችግር መቋቋም የሚችል ፍጥረት ካልሆነ በቀር ማንም የማይደፍረው እጅግ ከፍተኛ ቦታ እንዲሆን ወይም ደግሞ ከባሕር ወለል በታች በሚያስገርም ጥልቀት ወደ ውስጥ እንዲሰጥም ሊያደርገው ይችላል።”15 ተራሮችም ሆኑ ባሕሩን ያቆሩት ጎድጓዳ ቦታዎች ከፍና ዝቅ ስለሚሉ በአንድ ወቅት ተራሮቹ አሁን ያላቸውን ያህል ከፍታ እንዳልነበራቸው እንዲሁም ታላላቆቹም የባሕር ጎድጓዳ ስፍራዎች የዛሬውን ያህል ጥልቅ እንዳልነበሩ ግልጽ ነው።

32. የጥፋት ውኃው ምን ሆኖ መሆን አለበት? አብራራ።

32 ታዲያ ከጥፋት ውኃው በኋላ ጎርፉ ምን ሆነ? ወደ ባሕር ውስጥ ገብቶ መሆን አለበት። እንዴት? ሳይንቲስቶች አሕጉሮቹ የተቀመጡት እጅግ ግዙፍ በሆኑ ስፍሃኖች ላይ እንደሆነ ያምናሉ። የእነዚህ ስፍሃኖች መንቀሳቀስ በምድር ገጽ ላይ የከፍታ ልዩነት ሊያመጣ ይችላል። ዛሬ በአንዳንድ አካባቢዎች በስፍሃኖቹ ጠርዞች አካባቢ ከአሥር ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ጥልቀት ያላቸው ከውኃ ታች ያሉ ጥልቅ ሥፍራዎች ይገኛሉ።16 ምናልባትም ከጎርፉ የተነሣ ስፍሃኖቹ ሲንቀሳቀሱ የባሕሩ ወለል በመስጠሙ እነዚህ ትላልቅ ጎድጓዳ ስፍራዎች ተከፍተው ውኃው ከምድሪቷ ላይ ሊደርቅ የሚችልበት ሰፊ አጋጣሚ እንደተፈጠረ እሙን ነው። *

የጥፋት ውኃው ቅሪቶች

33, 34. (ሀ) ሳይንቲስቶች የጥፋት ውኃው እንደደረሰ የሚያሳይ ማስረጃ ሊሆን የሚችል ምን ነገር አግኝተዋል? (ለ) ሳይንቲስቶች ለማስረጃዎቹ የተሳሳተ ትርጓሜ ሰጥተው ይሆናል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናልን?

33 ታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ ተከስቶ ሊሆን እንደሚችል ከተስማማን ሳይንቲስቶች ምንም ምልክት ያላገኙት ለምንድን ነው? ለመረጃዎቹ የሚሰጡት ትርጉም ሌላ ሆኖ ነው እንጂ ሳያገኙ ቀርተው አይደለም። ለምሳሌ ያህል ተቀባይነት ያገኘው ሳይንስ በተከታታይ ጊዜ በተከሰቱት የበረዶ ዘመናት ምክንያት በምድር ላይ የሚገኙ ብዙ ቦታዎች በበረዶ ግግሮች አማካኝነት መልካቸውን ቀይረዋል በማለት ያስተምራል። ይሁን እንጂ የበረዶ ግግር ያስከተላቸው ነገሮች ናቸው የተባሉት ማስረጃዎች አንዳንድ ጊዜ በውኃ ምክንያት የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። እንግዲያው የጥፋት ውኃውን የሚያመለክቱት አንዳንድ ማስረጃዎች በስህተት የበረዶ ዘመን ተብለው ተነግረው እንደሚሆን እሙን ነው።

34 ተመሳሳይ ስህተቶች ተሠርተዋል። ሳይንቲስቶች ስለ በረዶ ዘመን የሚናገረውን ጽንሰ ሐሳብ ያዳበሩበትን ጊዜ በሚመለከት እንዲህ የሚል ነገር እናነባለን:- “የመሠረተ አሁን ፍልስፍናን በመጠቀም በስነ ምድር ታሪክ የተለያየ ወቅት ላይ የበረዶ ዘመናት እንደነበሩ ተረድተው ነበር። ይሁን እንጂ በቅርቡ በመረጃዎቹ ላይ በድጋሚ የተደረጉት ምርምሮች የበረዶ ዘመን የተባሉትን ብዙዎቹን ወቅቶች ውድቅ አድርጓቸዋል። በአንድ ወቅት የበረዶ ገፍ ክምችት የፈጠራቸው ናቸው ተብለው ይታሰቡ የነበሩት ነገሮች የጭቃ ፍስ፣ የባሕር ውስጥ መሬት መንሸራተት እንዲሁም ድብልቅልቅ ጎርፍ የፈጠራቸው መደቦች፤ ከውቅያኖሶች ጥልቅ ወለል ደቃቅ ጠጠር፣ አሸዋና ኮረት ተሸክመው የሚመጡት ድብልቅልቅ የውኃ ናዳዎች የሚፈጥሯቸው ነገሮች ናቸው የሚል አዲስ ትርጓሜ ተሰጥቷቸዋል።”18

35, 36. ከጥፋት ውኃው ጋር ሊዛመድ የሚችል ምን የቅሪተ አካልና የስነ ምድር ማስረጃ አለ? አብራራ።

35 የጥፋት ውኃው እንደተከሰተ የሚያሳይ የቅሪተ አካሎች ማስረጃም ተገኝቷል። ይኸው ግኝት እንዳስረዳው በአንድ ወቅት ረጃጅም የክራንቻ ጥርስ ያላቸው ነብሮች ሌሎች እንሰሳትን አድነው ለመብላት አውሮፓን ያስሱ ነበር፤ ዛሬ ካሉት ሁሉ ይበልጥ ረጃጅም የሆኑ ፈረሶች ሰሜን አሜሪካን አጥለቅልቀዋት የነበረ ሲሆን ዛሬ የሌሉ የዝሆን ዝርያዎች በሳይቤርያ ምግብ ፍለጋ ይንከራተቱ ነበር። ከዚያ በዓለም ዙሪያ የአጥቢ እንስሳት ዝርያ ከፍተኛ ውድመት ደረሰበት። በተመሳሳይ ወቅት ላይ ድንገተኛ የሆነ የአየር ጠባይ ለውጥም ተከስቶ ነበር። በሳይቤርያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩት እነዚህ የዝሆን ዓይነቶች ሞተው ወዲያው በበረዶ ደርቀዋል። * በቻርልስ ዳርዊን ዘመን የኖረው ታዋቂው አልፍሬድ ዋላስ እንዲህ ያለው መጠነ ሰፊ ጥፋት የደረሰው ምድር አቀፍ በሆነ አንድ እንግዳ ክስተት ምክንያት መሆን አለበት ብሏል።19 ብዙዎች ይህ ክስተት የጥፋት ውኃው መሆን አለበት ሲሉ ተከራክረዋል።

36 ቢብሊካል አርኪኦሎጂስት የተባለ መጽሔት አዘጋጅ የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ ደርሶ ነበር የሚለው ታሪክ በሰው ልጅ ባሕሎች ውስጥ በሰፊው ተሠራጭቶ የሚገኝ ወግ መሆኑን ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነው። . . . የሆነ ሆኖ በምሥራቃውያን አካባቢ ከሚገኙት ጥንታዊ ወጎች በስተጀርባ ዘመነ ዝናብ ከሚባሉት ወቅቶች በአንዱ . . . ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በእርግጥ የተከሰተ ከፍተኛ መጠን ያለው የውኃ መጥለቅለቅ ሊኖር ይችላል።”20 ዘመነ ዝናብ የሚባሉት ወቅቶች የምድር ገጽ ከአሁኑ ይበልጥ እርጥበት አዘል የነበረባቸው ጊዜያት ናቸው። በዓለም ዙሪያ ለመጠጥ የሚሆን ውኃ የሚገኝባቸው ሐይቆች ከአሁኑ ይበልጥ ሰፋፊ ነበሩ። መሬት እንደዚያ እርጥብ የነበረችው በበረዶ ዘመን መጨረሻ ላይ በዘነቡት ከባድ ዝናቦች ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በአንድ ወቅት በምድር ገጽ ላይ የነበረው ከፍተኛ እርጥበት ከውኃ መጥለቅለቁ የመጣ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የሰው ልጅ አልረሳውም

37, 38. አንድ ሳይንቲስት በማስረጃዎቹ መሠረት የጥፋት ውኃ ደርሶ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት እንዴት ነው? ይህ ነገር በትክክል እንደደረሰ እንዴት እናውቃለን?

37 የስነ ምድር ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ማካምፔል በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ታላቅ ጥፋት [የጥፋት ውኃ] እና በዝግመተ ለውጣዊው መሰረተ አሁን (evolutionary uniformitarianism) ፍልስፍና መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት በስነ ምድር ውህብ እውነተኝነት ሳይሆን ለእነዚህ ውህቦች በሚሰጠው ትርጓሜ ነው። የሚሰጠው ትርጓሜ ባብዛኛው በግለሰብ ተማሪው ሁኔታና መሆን አለበት ብሎ በሚጠብቀው ነገር ላይ የተመካ ነው።”21

38 የሰው ልጅ ፈጽሞ ያልረሳው ነገር መሆኑ የጥፋት ውኃው በእርግጥ እንደተፈጸመ የሚያሳይ ነው። እንደ አላስካና ሳውዝ ሲ ደሴቶች ያሉት ሩቅ አካባቢዎች ድረስ ስለዚህ ሁኔታ የሚናገሩ የቆዩ ተረቶች አሉ። ኮሎምበስ አሜሪካን ከመርገጡ በፊት በነበረው የአገሬው ሥልጣኔም ሆነ በአውስትራሊያ በሚገኙት የአቦርጂን ጎሳዎች ዘንድ ስለ ጥፋት ውኃ የሚገልጹ ተረቶች አሉ። አንዳንዶቹ ተረቶች በዝርዝር ጉዳያቸው እርስ በርሳቸው የሚለያዩ ይሁኑ እንጂ ምድር በውኃ ተጥለቅልቃ እንደ ነበርና በሰው ሠራሽ መርከብ ተሳፍረው ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደ ዳኑ የሚገልጸው መልእክት በሁሉም ተረቶች ውስጥ ለማለት ይቻላል ተንጸባርቆ እናገኘዋለን። ይህ ተረት ይህን ያህል በስፋት ተቀባይነት ያገኘበት ምክንያት የጥፋት ውኃው ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም። *

39. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንጂ የሰው አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ምን ተጨማሪ ማስረጃ አግኝተናል?

39 እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ይስማማል። በሁለቱ መካከል እርስ በርሱ የሚቃረን ነገር የሚገኘው የሳይንቲስቶቹ መረጃ አጠያያቂ ሲሆን ነው። እርስ በርሳቸው በሚስማሙበት ነጥብ ደግሞ ስናየው መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ፍጹም ትክክል ከመሆኑ የተነሣ መረጃው የተገኘው ከሰው በላይ የሆነ የማሰብ ችሎታ ካለው አካል መሆኑን እንድናምን ያደርገናል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በማስረጃ ከተረጋገጠ ሳይንስ ጋር ያለው ስምምነት የሰው ቃል ሳይሆን የአምላክ ቃል ለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.25 ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1985 ባዘጋጀው ሕይወት—⁠ እንዴት ተገኘ በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥና ስለ ፍጥረት ሰፋ ያለ ዝርዝር ማብራሪያ ሰፍሯል።

^ አን.32 ፐላኔት ኧርዝ​—⁠ግላሲየር የተባለው መጽሐፍ በበረዶ መልክ ያለ ውኃ የምድርን ወለል ምን ያህል እንደሚጫን ገልጿል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብሏል:- “በግሪንላንድ ያለው በረዶ ቢቀልጥ ምድሩ ከጊዜ በኋላ አሁን ካለበት 600 ሜትር ከፍ ይል ነበር።” ከዚህ አንጻር ሲታይ ድንገተኛ የሆነው ምድር አቀፍ መጥለቅለቅ በምድር ቅርፊት ላይ የከፋ ውጤት ይኖረዋል።17

^ አን.35 አንድ ግምት አምስት ሚልዮን ይሆናሉ ብሏል።

^ አን.38 ስለ ጥፋት ውኃው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 327, 328, 609-612 ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 105 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ከምድር አፈር”

“ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ” እንደዘገበው:- “በሕያዋን ነገሮች ውስጥ የሚገኙት ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ሕይወት በሌላቸው ነገሮች ውስጥም ይገኛሉ።” በሌላ አባባል ሰውን ጨምሮ ሕያዋን ነገሮች የተሠሩባቸው መሠረታዊ የሆኑት ንጥረ ነገሮች በምድር ውስጥ ይገኛሉ ማለት ነው። ይህም “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ጋር ይስማማል።”​—⁠ዘፍጥረት 2:​7

[በገጽ 107 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘በአምላክ መልክ’

አንዳንዶች በሰዎችና በአንዳንድ እንስሳት መካከል ዝምድና አለ የሚለውን አመለካከታቸውን ለማስረዳት አካላዊ መመሳሰሎችን ይጠቅሳሉ። ይሁንና የሰው ልጅ የአእምሮ ችሎታ ከየትኛውም እንስሳ እጅግ የላቀ እንደሆነ ያምናሉ። የሰው ልጅ ዕቅድ የማውጣት፣ በዙሪያው ያለውን ነገር የማደራጀት፣ ሌሎችን የማፍቀር፣ ከፍተኛ የማስተዋል ችሎታና ሕሊና ያለው እንዲሁም ስላለፈው፣ አሁን ስላለውና ወደፊት ስለሚመጣው ነገር ሊያስብ የቻለው ለምንድን ነው? ዝግመተ ለውጥ ለዚህ መልስ ሊሰጥ አይችልም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል። እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔርም መልክ ፈጠረው።” (ዘፍጥረት 1:​27) የሰውን ልጅ አእምሮአዊና ሥነ ምግባራዊ ችሎታ እንዲሁም ያሉትን ልዩ ልዩ ተሰጥኦዎች ካሰብን በእርግጥም የሰማያዊ አባቱ ነጸብራቅ መሆኑ ግልጽ ነው።

[በገጽ 99 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በሕዋ ውስጥ አንዳች አልባ እንደተንጠለጠለች የሚሰጠው መግለጫ የጠፈር ተመራማሪዎች በዓይናቸው አይተው ከተናገሩት ነገር ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነው

[በገጽ 102 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ በፀሐይ ዙሪያ የምትሽከረከረው ምድር ናት ወይም ደግሞ በምድር ዙሪያ የምትሽከረከረው ፀሐይ ነች ብሎ አይናገርም

[በገጽ 112, 113 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምድር ብትደለደልና ምንም ተራራ ወይም ጥልቅ ጉድጓድ ባይኖር ከፍተኛ ጥልቀት ባለው ውኃ ትዋጥ ነበር

[በገጽ 114 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬ ዓይነታቸው የማይገኝ የዝሆን ዝርያዎች ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በበረዶ ደርቀው ተገኝተዋል

[በገጽ 115 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉዊ ፓስተር ሕይወት ሊገኝ የሚችለው አስቀድሞ ከነበረ ሕያው አካል ብቻ መሆኑን አረጋግጧል

[በገጽ 109 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን የውኃ ዑደት በትክክል ይገልጻል