“ብሉይ ኪዳን” ምን ያህል ተዓማኒነት አለው?
ምዕራፍ 4
“ብሉይ ኪዳን” ምን ያህል ተዓማኒነት አለው?
በሚቀጥሉት ጥቂት ምዕራፎች ውስጥ የዘመናችን ተቺዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሚሰነዝሯቸው አንዳንድ ነቀፋዎች እንወያያለን። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል እንዲሁም “ሳይንሳዊ አይደለም” የሚል ነቀፋ ይሰነዝራሉ። ወደፊት እነዚህን ነጥቦች አንስተን እንወያያለን። በመጀመሪያ ግን በተደጋጋሚ የሚሰማውንና መጽሐፍ ቅዱስ የተረትና የአፈታሪክ ጥርቅም ነው የሚለውን ውንጀላ እንመርምር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቃዋሚዎች እንዲህ ላለው ትችታቸው አሳማኝ ማስረጃ አላቸውን? እስቲ በመጀመሪያ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን እየተባሉ የሚጠሩትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እንመልከት።
1, 2. የኢያሪኮ አወዳደቅ ምን ይመስል ነበር? ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄዎች ተነሥተዋል?
አንዲት የጥንት ከተማ ተከብባለች። ወራሪዎቹ የዮርዳኖስን ወንዝ አቋርጠው በመትመም ከከተማይቱ ታላላቅ ቅጥሮች ፊት ለፊት ሠፍረዋል። ይሁን እንጂ የተጠቀሙበት የጦር ስልት እጅግ እንግዳ ነበር! ወራሪው ሠራዊት በየዕለቱ ለስድስት ቀናት ከተማይቱን ሲዞራት ቆይቷል። ሠራዊቱን ያጀቡት ካህናት ከሚነፉት መለከት ሌላ የሚሰማ ድምፅ አልነበረም። ሰባተኛው ቀን በደረሰ ጊዜ ሠራዊቱ አንድም ድምፅ ሳያሰማ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞራት። ከዚያም ካህናቱ በድንገት ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው መለከታቸውን ነፉ። ዝም ብሎ የቆየው ሠራዊት በብርቱ የሰልፍ ጩኸት አካባቢውን አደበላለቀው። ከተማዋን የከበበው ቅጥር ሲደረመስ አካባቢው በአቧራ ጉም ተዋጠ፤ ከተማዋም ያለ ቅጥር ቀረች።—ኢያሱ 6:1-21
* የኢያሱ መጽሐፍም ሆነ ከእርሱ በፊት ያሉት አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከረጅም ጊዜ በፊት ተፈጽመዋል እየተባለ በሚነገርላቸውና ከብዙ መቶ ዘመን በኋላ በተጻፉ አፈታሪኮች የተሞሉ ናቸው ብለው ይናገራሉ። ብዙ አርኪኦሎጂስቶችም ይህ ነገር አልተፈጸመም በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። እንደ እነርሱ አባባል ከሆነ እስራኤላውያን ከነዓን ምድር በደረሱበት ጊዜ ኢያሪኮ የምትባል ከተማ ላትኖርም ትችላላች።
2 ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስድስተኛ መጽሐፍ የሆነው የኢያሱ መጽሐፍ ወደ 3,500 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የኢያሪኮ ከተማ አወዳደቅ የሚተርከው በዚህ መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ነገር በእርግጥ ተፈጽሟልን? ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች አፋቸውን ሞልተው አልተፈጸመም ብለው ይናገራሉ።3. መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ታሪክ እውነተኛ ነው ወይስ አይደለም ብሎ መወያየት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
3 እነዚህ ውንጀላዎች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ስታነብ ትምህርቶቹ ከታሪክ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ታስተውላለህ። አምላክ የሐሳብ ግንኙነት ያደርግ የነበረው በገሃዱ ዓለም ከነበሩ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ቤተሰቦችና ብሔራት ጋር ሲሆን ትእዛዛቱንም የሰጠው በታሪክ ለነበረ ሕዝብ ነው። የዘመናችን ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊነት ላይ የጥርጣሬ ደመና እንዲያጠላ ሲያደርጉ በመጽሐፉ መልእክት ጠቃሚነትና ተዓማኒነት ላይም ጥርጣሬ እንዲያጠላ ማድረጋቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ከሆነ ታሪኩ እምነት የሚጣልበት ሊሆን ይገባል እንጂ እንዲሁ አፈታሪክና ተረት መሆን የለበትም። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች የመጽሐፉን ታሪካዊ እውነተኝነት ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት አላቸውን?
—ምን ያህል ተጨባጭ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት4-6. አንዳንዶቹ የቬልሃውዘን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ጽንሰ ሐሳቦች ምንድን ናቸው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘረው ትችት ተጠናክሮ ብቅ ያለው በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመናት ነው። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ጀርመናዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺ ጁሊየስ ቬልሃውዘን የኢያሱን መጽሐፍ ጨምሮ የመጀመሪያዎቹ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት ታሪኮቹ ከተፈጸሙ ከአንድ ሺህ ዓመታት ገደማ በኋላ ማለትም በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ማናፈስ ጀመረ። ይሁን እንጂ ከዚያ ቀደም ብለው የተጻፉ ሐሳቦችንም እንደያዙ ተናግሯል።1 ይህ ጽንሰ ሐሳብ በ1911 በታተመው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ 11ኛ እትም ላይ የወጣ ሲሆን መጽሐፉ እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “የዘፍጥረት መጽሐፍ የተጻፈው ከግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ ሲሆን ከግዞት በኋላ ከተዘጋጁ የካህናት ጽሑፎች (ፒ) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ከዚያ ቀደም ከነበሩና በቋንቋም ይሁን በአጻጻፍ እንዲሁም በሃይማኖታዊ አቋም ከ(ፒ) ከሚለዩና የካህናት እጅ ከሌለባቸው ጽሑፎች የተቀናበረ መጽሐፍ ነው።”
5 ቬልሃውዘንና ተከታዮቹ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጀመሪያ አካባቢ ተጠቅሰው የሚገኙትን ታሪኮች በሙሉ የሚመለከቷቸው “በሆነ ወቅት ላይ እንደተፈጸሙ ታሪኮች ሳይሆን በሰፊው እውቅና እንዳገኙ የጥንት ወጎች ነው።”2 መጀመሪያ አካባቢ የሚገኙት ታሪኮች ከኋለኛው የእስራኤል ታሪክ አንጻር የተጻፉ ዘገባዎች እንደሆኑ ተደርገው ተቆጥረዋል። ለምሳሌ ያህል በያዕቆብና በዔሳው መካከል የታየው ጠላትነት በእርግጥ የተፈጸመ ነገር ሳይሆን ከጊዜ በኋላ በእስራኤል ሕዝብና በኤዶም ሰዎች መካከል የነበረውን ጠላትነት ለማንጸባረቅ የተፈጠረ ታሪክ ነው የሚል አስተያየትም ተሰንዝሯል።
6 እነዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ከዚህ አባባላቸው ጋር በመስማማት ሙሴ የቃል ኪዳኑን ታቦት ለመሥራት ምንም ዓይነት ትእዛዝ አልተቀበለም፣ የእስራኤል የአምልኮ ማዕከል የነበረ የመገናኛ
ድንኳን የሚባል ነገርም ጨርሶ አልነበረም ብለዋል። እንዲሁም የአሮን የክህነት ሥልጣን ሙሉ በሙሉ የጀመረው ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ከመጥፋቷ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ እንደሆነ ያምናሉ። እንደ እነርሱ እምነት ከሆነ ደግሞ ይህ ነገር የተከናወነው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጀመሪያ ላይ ነው።37, 8. ቬልሃውዘን ለጽንሰ ሐሳቦች ምን “ማስረጃዎች” አቅርቧል? ማስረጃዎቹስ ተቀባይነት ያላቸው ናቸውን?
7 ለዚህ አባባላቸው ያቀረቡት “ማስረጃ” ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን የመጀመሪያ መጻሕፍት ወደ ተለያዩ በርካታ መዛግብት መከፋፈል እንችላለን ይላሉ። በጥቅሉ ሲታይ ይህን ለማድረግ የሚጠቀሙበት መሠረታዊ መመሪያ የሚከተለውን ይመስላል:- አንድ ጸሐፊ ሁለቱንም መጠሪያዎች መጠቀም የማይችል ይመስል አምላክ ለሚለው ቃል (ኤሎሂም) የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል የያዘ ቁጥር ካለ ራሱን የቻለ ጸሐፊ አለው፣ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የሰፈረበት ቁጥር ካለ ደግሞ ጸሐፊው ሌላ መሆን አለበት ይላሉ።4
8 አንድ ክንውን መጽሐፉ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የተጠቀሰበት አጋጣሚ ካለ መጽሐፉን የጻፈው አንድ ሰው አይደለም ለማለት እንደ ማስረጃነት ይጠቀሙበታል። ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ሴማዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም ተመሳሳይ የድግግሞሽ ባሕርይ ይታይባቸዋል። በተጨማሪም የአጻጻፍ ስልቱ ከተቀየረ ጸሐፊው እንደተለወጠ አድርገው ያስባሉ። ይሁንና በዘመናዊ ቋንቋዎች የሚጠቀሙ ጸሐፊዎች እንኳ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ የጽሑፍ ሥራዎቻቸው ውስጥም ሆነ ስለተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲጽፉ የተለየ የአጻጻፍ ስልት ይጠቀማሉ። *
9-11. የዘመናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ያሉበት አንዳንድ ጉልህ ድክመቶች ምንድን ናቸው?
9 እነዚህን ጽንሰ ሐሳቦች የሚደግፍ ተጨባጭ ማስረጃ አለን?
በፍጹም። አንድ አስተያየት ሰጪ እንዲህ ብለዋል:- “ከሁሉ የተሻለ የሚባለው ትችት እንኳ ሳይቀር ግምታዊና ጊዜ ሊሽረው የሚችል ሲሆን በማንኛውም ጊዜ ማሻሻያ ሊደረግበት አለዚያም ስህተት መሆኑ ተረጋግጦ በሌላ ሊተካ ይችላል። ይህ ምሁራን የሚያደርጉት ሙከራ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ሙከራዎች ደግሞ ከጥርጣሬና ከመላምት ተነጥለው አያውቁም።”5 በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘረው ትችት ከልክ በላይ ‘ግምታዊና ጊዜ የሚሽረው’ ነው።10 ግሌሰን ኤል አርከር ጁንየር ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች መከራከሪያ ነጥብ ያለበትን ሌላ ድክመት ጠቁመዋል። ችግሩ “የቬልሃውዘን ትምህርት ቤት ሥራውን የጀመረው የእስራኤላውያን ሃይማኖት እንደ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ ሰዎች የፈጠሩትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ነው ብሎ ለማስረዳት ግምታዊ ሐሳብ (ይሁንና ይህን አመለካከት ለማንጸባረቅ ተጨንቀው አያውቁም) ይዞ በመነሣት ነው።”6 በሌላ አባባል ቬልሃውዘንና ተከታዮቹ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ቃል ነው ብለው ከተነሡ በኋላ እንደገና ከዚያው እየጠቀሱ አስረድተዋል።
11 በ1909 የተዘጋጀው ዘ ጁዊሽ ኢንሳክለፒዲያ የቬልሃውዘናውያን ጽንሰ ሐሳብ ያሉበትን ሁለት ተጨማሪ ድክመቶች ሲጠቁም እንዲህ ብሎ ነበር:- “ቬልሃውዘን በዘመኑ ከነበሩት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ሁሉ ገንኖ የታየባቸው የመከራከሪያ ነጥቦች በሁለት
መላምቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። የመጀመሪያው መላምት ሃይማኖታዊ ሥርዓት እየጎለበተ የሚሄደው ሃይማኖት እያደገ ሲሄድ ነው ይላል። ሁለተኛው መላምት ደግሞ ቀደምት የሆኑት ምንጮች ሁልጊዜ የሚገልጹት የሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጅምር ብቻ ነው የሚል ነው። የመጀመሪያው መላምት እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ ባሕሎች ሁኔታ ጋር አይጣጣምም። ሁለተኛውም ቢሆን በሕንድ ካሉት ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አንጻር ሲታይ ተቀባይነት የለውም።”12. ዘመናዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ከአርኪኦሎጂ አንጻር ሲታይ ምን ይመስላል?
12 ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ጽንሰ ሐሳብ ትክክል መሆን አለመሆኑን መፈተን የሚቻልበት ዘዴ ይኖራልን? ዘ ጁዊሽ ኢንሳክለፒዲያ እንዲህ በማለት ሐሳቡን ይቀጥላል:- “የቬልሃውዘን አመለካከት ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በተራ ግምገማዎች ላይ ነው ለማለት ይቻላል። በተደራጀ መልክ በሚደረግ አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ሊደገፍ ይገባል።” ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ከቬልሃውዘን ጽንሰ ሐሳቦች ጋር እየተስማሙ መጥተዋልን? ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “አርኪኦሎጂያዊ ግምገማዎች የቆዩትን ታሪካዊ ዝርዝሮች [የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች] ሳይቀር በማስረጃ እያረጋገጡና የፔንታቱች ዘገባዎች [በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ዘገባዎች] ከብዙ ጊዜ በኋላ ታስቦባቸው የተቀናበሩ ናቸው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ውድቅ እያደረጉ መጥተዋል።”
13, 14. የቬልሃውዘን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት መሠረቱ የሚዋዥቅ ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ በሰፊው ተቀባይነት ያገኘው ለምንድን ነው?
13 የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ድክመቶች እያሉበትም ዛሬ ባሉ ምሁራን ዘንድ ይህን ያህል ተቀባይነት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? እነርሱ ሊሰሙት የሚፈልጉትን ነገር ስለሚነግራቸው ነው። በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩ አንድ ምሁር እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “እኔ በበኩሌ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ ይበልጥ ለማለት እችላለሁ ይህን የቬልሃውዘንን መጽሐፍ እመርጣለሁ። ምክንያቱም ከብሉይ ኪዳን ታሪክ ጋር በተያያዘ የሚነሡት ከባድ ችግሮች የሰው
ልጅ በዝግመተ ለውጥ መገኘቱን ከሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ መልስ እንዳገኙ ይሰማኛል። ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ ከሁሉም ሃይማኖቶች ታሪክ ጋር የማጣጣም ግዴታ አለብኝ።”7 ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት በዝግመተ ለውጥ ከሚያምኑት ምሁር ሐሳብ ጋር ተጣጥሟል። ደግሞም የሁለቱም ጽንሰ ሐሳቦች ዓላማ አንድ ነው። ዝግመተ ለውጥ በአምላክ ማመን አስፈላጊ አይደለም ሲል የቬልሃውዘን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ደግሞ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው ብለው ሊያምኑ አይገባም ይላል።14 ተጨባጭ ነገር ማየት በሚሻው በዚህ 20ኛው መቶ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ሳይሆን የሰው ቃል ነው የሚለው ሐሳብ ለምሁራኑ የተስማማቸው ይመስላል። * ትንቢቶች እውነት ናቸው ብሎ ከማመን ይልቅ ከተፈጸሙ በኋላ የተጻፉ ነገሮች ናቸው ማለት ይቀላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተዓምራት የሚናገረውን ነገር እውነት ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን ብሎ ከመመርመር ይልቅ ተረት፣ አፈታሪክ ወይም የአባቶች ወግ እንደሆነ መቁጠር ይመርጣሉ። ይሁን እንጂ ይህ በመሠረተ ቢስ ጥላቻ ላይ የተመሠረተና መጽሐፍ ቅዱስ እውነት አይደለም ለማለት የሚያበቃ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ነገር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት የራሱ ብዙ ድክመቶች ያሉበት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዝራቸውም ውንጀላዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሳይችሉ ቀርተዋል።
አርኪኦሎጂ መጽሐፍ ቅዱስን ይደግፋልን?
15, 16. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውና በሕይወት እንደነበር በአርኪኦሎጂ የተረጋገጠው የትኛው የጥንት ገዥ ነው?
15 አርኪኦሎጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ይበልጥ ጠንካራ መሠረት
ያለው የጥናት መስክ ነው። አርኪኦሎጂስቶች የጥንቱን ሥልጣኔ ቅሪቶች በቁፋሮ በመፈለግ በብዙ አቅጣጫ ጥንት ስለነበሩት ሁኔታዎች ያለንን ግንዛቤ እንድናሰፋ ረድተውናል። በመሆኑም አርኪኦሎጂያዊ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናነበው ነገር ጋር ብዙ ጊዜ ስምም ሆነው መገኘታቸው ምንም አያስገርምም። ከዚህም በላይ አርኪኦሎጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰነዘርበት ነቀፋ ነፃ መሆኑን ያረጋገጠባቸውም ጊዜያት አሉ።16 ለምሳሌ ያህል የዳንኤል መጽሐፍ እንደሚገልጸው ባቢሎን በፋርስ እጅ ከመውደቋ በፊት የነበረው የመጨረሻ ገዥ ብልጣሶር የሚባል ነበር። (ዳንኤል 5:1-30) ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ብልጣሶር የሚለው ስም የተጠቀሰበት ቦታ በመጥፋቱ እንዲህ የሚባል ሰው ኖሮ አያውቅምና መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት ነው የሚል ነቀፋ ተሰነዘረ። ይሁን እንጂ በ19ኛው መቶ ዘመን በደቡባዊ ኢራቅ በነበሩ አንዳንድ ፍርስራሾች ውስጥ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው ሞላላ ሸክላዎች ተገኙ። እነዚህ ሸክላዎች ስለ ባቢሎኑ ንጉሥ ስለ ናቦኒደስ ታላቅ ልጅ ጤንነት የቀረበውን ጸሎትም ይዘው ተገኝተዋል። የልጁ ስም ማን ነበር? ብልጣሶር ነው።
17. ብልጣሶርን አብዛኞቹ የጥንት ጽሑፎች አልጋ ወራሽ ብለው ሲጠሩት መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ የሚልበትን ምክንያት እንዴት ማስረዳት እንችላለን?
17 ስለዚህ ብልጣሶር የሚባል ሰው ነበር ማለት ነው! ነገር ግን ይህ ሰው ባቢሎን በወደቀችበት ጊዜ ንጉሥ ነበር? ከዚያ ወዲያ የተገኙት አብዛኞቹ ሰነዶች የንጉሡ ልጅ ማለትም አልጋ ወራሽ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈበት “የናቦኒደስ የታሪክ ሰነድ” በመባል የሚታወቀው ሰነድ ስለ ብልጣሶር ትክክለኛ የሥልጣን ቦታ ተጨማሪ ብርሃን ፈንጥቋል። እንዲህ ይላል:- “እርሱ [ናቦኒደስ] ለታላቅ (ልጁ) ማለትም ለበኩር ልጁ ‘የጦር ሰፈሩን’ ሰጠው፤ በአገሪቱ በማንኛውም ቦታ የሚገኘው ሠራዊት በእርሱ (ቁጥጥር) ሥር እንዲውል አደረገ። (ሁሉንም ነገር) አሳልፎ ሰጠው፤ ንግሥናውንም አስረከበው።”8 በመሆኑም ብልጣሶር የንግሥና ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። በእርግጥም ንጉሥ ያሰኘው ነገር ይህ ነበር! * በብልጣሶርና በአባቱ በናቦኒደስ መካከል የነበረው ይህ ግንኙነት በባቢሎን በተደረገው የመጨረሻ የእራት ግብዣ ላይ ብልጣሶር ዳንኤልን በመንግሥቱ ሦስተኛ ገዥ ለማድረግ ቃል የገባለት ለምን እንደሆነ ይጠቁመናል። (ዳንኤል 5:16) ናቦኒደስ አንደኛ ገዥ ብልጣሶር ደግሞ ሁለተኛ ገዥ ስለነበር ነው።
ሌሎች ማጠናከሪያ ማስረጃዎች
18. የዳዊት ግዛት ያስገኘውን ሰላምና ብልጽግና በተመለከተ አርኪኦሎጂ ምን መረጃ ይሰጣል?
18 እርግጥ ብዙ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ሰሎሞን ንግሥናውን ከአባቱ ከዳዊት ከተቀበለ በኋላ እስራኤል እጅግ በልጽጋ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።” (1 ነገሥት 4:20) ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ዳዊት ያስገኘው ሰላም ብዙ አዳዲስ ከተማዎችን ለመቆርቆር በማስቻሉ በይሁዳ ግዛት በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበና ከዚያ በኋላ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ እንደነበር የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።”10
19. አርኪኦሎጂ በእስራኤልና በሞዓብ መካከል ስለተደረገው ጦርነት ምን ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል?
2 ነገሥት 3:4-27) የሚያስደንቀው በ1868 ዮርዳኖስ ውስጥ ሞሳ ራሱ ይህን ግጭት በሚመለከት ያሰፈረውን ዘገባ የያዘ አንድ ሐውልት (በላዩ ላይ የተቀረጸበት የድንጋይ ስባሪ) ተገኝቷል።
19 ከጊዜ በኋላ እስራኤልና ይሁዳ ሁለት መንግሥታት ሆኑና እስራኤል አጎራባቿን ሞዓብን ድል አደረገች። ሞዓብ በንጉሥ ሞሳ ትተዳደር በነበረበት ወቅት ግን በማመፅዋ እስራኤል ከይሁዳና ከአጎራባቿ ከኤዶም መንግሥት ጋር ኅብረት በመፍጠር በሞዓብ ላይ ዘመተች። (20. እስራኤል በአሦራውያን ስለመጥፋቷ አርኪኦሎጂ ምን ይነግረናል?
20 ከዚያም በ740 ከዘአበ አምላክ ዓመፀኛ የነበረው ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት በአሦራያውያን እጅ እንዲደመሰስ ፈቀደ። (2 ነገሥት 17:6-18) አርኪኦሎጂስትዋ ካቴሊን ኬንዮን ይህን ክስተት ስለሚዘግበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ሰው ይህ ነገር ተጋንኗል የሚል ጥርጣሬ ያድርበት ይሆናል።” ይሁን እንጂ እውነት ተጋንኗልን? እንዲህ ሲሉ አክለው ተናግረዋል:- “የእስራኤል መንግሥት መውደቁን የሚጠቁመው አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይበልጥ ግልጽ ነው ማለት ይቻላል። . . . የእስራኤል ከተሞች የሆኑት ሰማርያና ሐጾር ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውና ከዚሁ ጋር የተፈጸመው የመጊዶው ውድመት [የመጽሐፍ ቅዱስ] ጸሐፊዎች ምንም ያጋነኑት ነገር እንደሌለ የሚያሳዩ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች ናቸው።”11
21. ይሁዳ በባቢሎናውያን ሥር መውደቋን በሚመለከት አርኪኦሎጂ ምን ዝርዝር ሁኔታዎችን ገልጿል?
21 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም በኋላ ቢሆን በንጉሥ ዮአኪን ትተዳደር የነበረችው ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ተከብባ ድል እንደተደረገች ይገልጽልናል። ይህ ታሪክ አርኪኦሎጂስቶች በቁፋሮ ባገኙት የባቢሎናውያን ዜና ታሪክ ማለትም የሽብልቅ መልክ ባላቸው ፊደላት የተጻፈበት ጽላት ላይ ተመዝግቦ ተገኝቷል። በዚህ ጽላት ላይ እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን:- “የአካድ [የባቢሎን] ንጉሥ . . . የይሁዳን (ኢያሁዱን) ከተማ ከብቦ በአዳሩ ወር በሁለተኛው ቀን ከተማይቱን ተቆጣጠረ።”12 ዮአኪንም ወደ ባቢሎን ተወስዶ በግዞት ተቀመጠ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ከእስር ቤት ተፈቶ ቀለብ ይሰጠው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (2 ነገሥት 24:8-15፤ 25:27-30) “ለይሁዳ ንጉሥ ለያውኪን” ይሰጠው የነበረውን ራሽን የያዙት በባቢሎን የተገኙት የአስተዳደር ሰነዶች ይህንን ሐሳብ ይደግፋሉ።13
22, 23. በጥቅሉ ሲታይ በአርኪኦሎጂና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዘገባ መካከል ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
22 ፕሮፌሰር ዴቪድ ኖል ፍሪድማን በአርኪኦሎጂና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዘገባዎች መካከል ያለውን ዝምድና በሚመለከት እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “በጥቅሉ ሲታይ አርኪኦሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካዎችን ታሪካዊ ተቀባይነት የሚደግፍ ሆኗል። ከእምነት አባቶች አንስቶ እስከ አ[ዲስ] ኪ[ዳን] ዘመን ድረስ የተዘረዘረው ሰፊ የዘመናት ስሌት ከአርኪኦሎጂያዊው ውህብ ጋር የሚዛመድ ነው። . . . ወደፊት የሚገኙትም ነገሮች ቢሆኑ ምንም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ወይም ከሳይንስ አንጻር እንደ ታሪክ ባይታዩም የመጽሐፍ ቅዱስ ወጎች ታሪካዊ መሠረት ያላቸውና በሐቀኝነት የተላለፉ መሆናቸውን የሚሽር እንደማይሆን እሙን ነው።”
23 ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣጣል የሚያደርጉትን ጥረት በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “የዘመናችን ምሁራን ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች አዲስ መልክ ለመስጠት ያደረጓቸው ሙከራዎች—ለምሳሌ ያህል የእምነት አባቶች ዘመን የሥርወ መንግሥት መከፋፈል ያመጣው ውጤት ነው የሚለው የቬልሃውዘን አመለካከት ኖዝና ተከታዮቹ ሙሴ የሚባል ሰው ስለመኖሩና እስራኤላውያንም ከግብጽ ስለመውጣታቸው የሚገልጸውን ዘገባ ታሪካዊነት አንቀበልም ብለው የእስራኤላውያንን ታሪክ እንደ አዲስ ለማስተካከል መሞከራቸው የአርኪኦሎጂያዊ መረጃዎችንም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን ትረካዎች ሊያስተባብል አልቻለም።”14
የኢያሪኮ መውደቅ
24. መጽሐፍ ቅዱስ የኢያሪኮን አወዳደቅ በተመለከተ ምን መረጃዎችን ይሰጠናል?
24 ይህ ማለት ግን አርኪኦሎጂ በሁሉም አቅጣጫ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል ማለት ነውን? የለም፤ በርከት ያሉ ልዩነቶች አሉ። አንዱ በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተገለጸው አስገራሚው የኢያሪኮ ድል ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ኢያሱ እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ከነዓን በገባ ጊዜ ድል ያደረጋት የመጀመሪያዋ ከተማ ኢያሪኮ ናት። የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት እንደሚያሳየው ከተማዋ ድል የተደረገችው በ15ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ነው። ከተማይቱንም ከያዙ በኋላ ሙሉ በሙሉ በእሳት ስላቃጠሏት ለብዙ መቶ ዓመታት ባድማ ሆና ቆይታለች።—ኢያሱ 6:1-26፤ 1 ነገሥት 16:34
25, 26. አርኪኦሎጂስቶች በኢያሪኮ አካባቢ ባደረጉት ቁፋሮ ምን ሁለት የተለያዩ መደምደሚያዎች ላይ ደርሰዋል?
25 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ፕሮፌሰር ጆን ጋርስታንግ ኢያሪኮ የነበረችበት ቦታ ነው ተብሎ በሚታሰበው አካባቢ ቁፋሮ አካሂደው ነበር። ከተማዋ በጣም ጥንታዊ እንደነበረችና ብዙ ጊዜ ፈርሳ እንደገና እንደተገነባች ደርሰውበታል። ጋርስታንግ በከተማዋ ላይ ከደረሱት ጥፋቶች መካከል በአንደኛው ወቅት እንደ ርዕደ መሬት የመሰለ ክስተት ቅጥሮቿን እንዳፈራረሰና ከተማዋም ሙሉ በሙሉ በእሳት
እንደወደመች ተረድተዋል። ጋርስታንግ ይህ ነገር የተከናወነው በ1400 ከዘአበ ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን ግምታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ኢያሪኮ በኢያሱ መሪነት የጠፋችበት ዘመን እንደሆነ ከሚጠቁመው ጊዜ ብዙም የራቀ አይደለም።1526 ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ ሌላዋ አርኪኦሎጂስት ካቴሊን ኬንዮን በኢያሪኮ ከተማ አካባቢ ተጨማሪ ቁፋሮ አካሂደው ነበር። አርኪኦሎጂስቷ ጋርስታንግ ያገኟቸው የፈራረሱት ግንቦች የወደቁት እርሳቸው ካሰቡት ጊዜ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት ቀደም ብሎ ነው ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል። በኢያሪኮ ላይ ከባድ ጥፋት የደረሰው በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መሆኑን ገልጸው መጽሐፍ ቅዱስ ኢያሱ ምድሪቱን ወረረ በሚልበት በ15ኛው መቶ ዘመን ግን በኢያሪኮ አካባቢ ከተማ የሚባል ነገር እንዳልነበር ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ በዚሁ አካባቢ በ1325 ከዘአበ ተከስቶ ሊሆን ይችላል ስላሉት ጥፋት ከገለጹ በኋላ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ኢያሪኮ የጠፋችው በኢያሱ ወረራ ነው ከተባለ አርኪኦሎጂ ይሆናል ብሎ የሚያስበው ዓመት ይህ [1325] ነው።”16
27. በአርኪኦሎጂና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ያሉት ልዩነቶች ከልክ በላይ የማያስጨንቁን ለምንድን ነው?
27 ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷል ማለት ነውን? በፍጹም። አርኪኦሎጂ ያለፈውን ነገር እንደ መስኮት ሆኖ የሚያሳየን ቢሆንም ሁል ጊዜ ጥርት ያለ ነገር እንደማያሳየን ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ጭራሽ ጭልም ያለ ይሆናል። አንድ አስተያየት ሰጪ እንደገለጹት “የሚያሳዝነው የአርኪኦሎጂ መረጃ የተበጣጠሰ ከመሆኑ የተነሣ ውስን ነው።”17 በተለይ ደግሞ ግልጽ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ ያልተገኘላቸውን ቀደም ያሉትን የእስራኤላውያን የታሪክ ዘመናት በተመለከተ ይህ ነገር እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። የኢያሪኮ አካባቢ ክፉኛ በውኃ የተሸረሸረ በመሆኑ ስለ ከተማዋ የሚገኘው ማስረጃ ይበልጥ የተመናመነ ሆኗል።
አርኪኦሎጂ ያለበት የአቅም ገደብ
28, 29. ምሁራኑ ራሳቸው አርኪኦሎጂ ምን የአቅም ገደቦች እንዳሉበት አምነው ተቀብለዋል?
28 አርኪኦሎጂስቶች ራሳቸው ሳይንሳቸው አቅሙ ውስን እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ዮሃናን አሃሮናኒ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “ለታሪካዊ ክስተቶች ወይም ለታሪካዊ መልከዓ ምድር አቀማመጥ ወደሚሰጠው ትርጓሜ የመጣን እንደሆነ አርኪኦሎጂስቶች ትክክለኛ ሳይንስ የሚባለውን ነገር ትተው የሚመስል ታሪክ ለመፍጠር የቁጥር ግምትና መላምት ይጀምራሉ።”18 ለተለያዩ ግኝቶች ስለተሰጠው የዘመን ስያሜ ጨምረው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “በመሆኑም ሁሉም የዘመን ስያሜዎቹ ፍጹም ትክክል ካለመሆናቸውም ሌላ ደረጃው ይለያይ እንጂ አጠራጣሪ ሁኔታ እንዳላቸው ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም።” ይህን ይበሉ እንጂ በዘመን አሰያየም ረገድ የዛሬዎቹ አርኪኦሎጂስቶች ከጥንቶቹ ይበልጥ እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን አምነዋል።19
29 ዘ ወርድ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት “አርኪኦሎጂያዊው ዘዴ ትክክለኛነቱ ወይም ሳይንሳዊ እውነትነቱ ምን ያህል ነው?” የሚል ጥያቄ አንስቷል። መልሱን ሲሰጥ:- “አርኪኦሎጂስቶች ይበልጥ ትክክለኛ ነገር የሚሠሩት ለግኝቶቻቸው ትርጓሜ ሲሰጡ ሳይሆን
ግኝቶቻቸውን ቆፍረው ሲያወጡ ነው። ይሁን እንጂ ‘ቁፈራውን’ ሲያካሂዱም ቢሆን ሰው እንደመሆናቸው መጠን ያሉባቸው ድክመቶች በሚጠቀሙት ዘዴ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የምድርን ዓለቶች ወደታች ሲቆፍሩ ማስረጃዎቻቸውን ስለሚያጠፉ ምርምሩን ደግሜ ልሞክር የሚሉበት አጋጣሚ አይኖራቸውም። ይህም አርኪኦሎጂን ከሌሎቹ ሳይንሶች የተለየ ያደርገዋል። ከዚህም በላይ ደግሞ የአርኪኦሎጂ ሪፖርት ከሁሉ ይበልጥ ብዙ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ እንዲሁም እንከን የማያጣው ሥራ እንዲሆን አድርጎታል።”2030. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለአርኪኦሎጂ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?
30 አርኪኦሎጂ በጣም ጠቃሚ ሊሆን መቻሉ ባይካድም እንደሌሎቹ የሰው ልጅ ጥረቶች ሁሉ የራሱ ድክመት ይኖረዋል። አርኪኦሎጂያዊ ጽንሰ ሐሳቦችን በጉጉት ብንከታተልም ፍጹም የማይታበሉ እውነቶች አድርገን ልንመለከታቸው አይገባም። አርኪኦሎጂስቶች ስለ ግኝቶቻቸው የሚሰጡት ትርጓሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረን ቢሆን የተሳሳተው መጽሐፍ ቅዱስ ነው እንጂ አርኪኦሎጂስቶቹ ትክክል ናቸው ብሎ በችኮላ መደምደም ተገቢ አይሆንም። የሚሰጧቸው ትርጓሜዎች በየጊዜው እንደሚለዋወጡ የታወቀ ነገር ነው።
31. የኢያሪኮን መውደቅ በተመለከተ በቅርቡ የተሰነዘረው አዲስ ሐሳብ ምንድን ነው?
31 የሚያስገርመው ፕሮፌሰር ጆን ጄ ቢምሰን የኢያሪኮን ጥፋት በ1981 በድጋሚ ለማጥናት ተነስተው ነበር። ካቴሊን ኬንዮን በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ተፈጸመ ያሉትን አስከፊውን የኢያሪኮ ውድመት በሚገባ መርምረዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ አባባል ከሆነ የደረሰው ጥፋትና መጽሐፍ ቅዱስ ኢያሱ ከተማዋን እንዳጠፋ የሚሰጠው መግለጫ እርስ በርሱ የሚስማማ ከመሆኑም በተጨማሪ የከነዓን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በአጠቃላይ፣ እስራኤላውያን ከነዓንን በወረሩ ጊዜ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገርለት የምድሪቱ ገጽታ ጋር ፍጹም ስምምነት አለው። ከዚህ የተነሣ አርኪኦሎጂያዊው የዘመን ስሌት ስህተት እንደሆነ ጠቁመው በእርግጥ ከተማዋ የጠፋችው በኢያሱ ዘመን ማለትም በ15ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ እንደሚሆን ገልጸዋል።21
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ታሪክ ነው
32. በአንዳንዶቹ ምሁራን ዘንድ ምን ዓይነት ዝንባሌ ተስተውሏል?
32 ይህ፣ አርኪኦሎጂስቶች ብዙውን ጊዜ እርስ በርሳቸው በሐሳብ እንደማይጣጣሙ ያሳያል። ስለሆነም አንዳንዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲስማሙ ሌሎች ቢቃወሙት ምንም አያስገርምም። የሆነ ሆኖ አንዳንድ ምሁራን በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እንኳን ባይስማሙ በጥቅሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ይዘት ማክበር ጀምረዋል። ዊልያም ፎክስዌል ኦልብራይት ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸውን ወገኖች በመወከል እንዲህ ብለዋል:- “በአጠቃላይ ሲታይ ከእስራኤል ሃይማኖታዊ ታሪክ ጋር የተያያዙት ጥቅልም ሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ትክክለኛ መሆናቸውን እየተገነዘብን መጥተናል። . . . ለማጠቃለል ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ከዳር እስከ ዳር ትክክለኛ ሃይማኖታዊ ታሪኮችን የያዘ ሰነድ መሆኑን ዛሬ በድጋሚ አምነን ለመቀበል ችለናል።”22
33, 34. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙት ታሪክ ትክክል መሆኑን ራሳቸው የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?
33 እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የትክክለኛ ታሪክ መለያ የሆኑት ምልክቶች የሚንጸባረቅበት መጽሐፍ ነው። ከአብዛኞቹ የጥንት ተረቶችና አፈታሪኮች በተለየ መልኩ ሁኔታዎቹ የተፈጸሙበትን ትክክለኛ ጊዜና ዘመን ለይቶ ይጠቅሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ብዙዎቹን ክንውኖች በዚያ ዘመን የተዘጋጁ የጽሑፍ ማስረጃዎች ይደግፏቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስና በአንዳንድ የጥንት ጽሑፎች መካከል ልዩነት ካለ ብዙውን ጊዜ ልዩነቱ የሚፈጠረው የጥንቶቹ ገዥዎች የራሳቸውን ሽንፈት ለማስመዝገብ ስለማይፈልጉ ይልቁንም ያገኙት ስኬት ተጋንኖ እንዲታይ ለማድረግ ስለሚሹ ነው።
34 ደግሞም ከእነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል ብዙዎቹ ዘግበው የያዙት ታሪክን ሳይሆን የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳ ነው። በአንጻሩ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እምብዛም ያልተለመደ ዓይነት ግልጽነት አሳይተዋል። እንደ ሙሴና አሮን ያሉት ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው የጥንት ሰዎች ደካማና ጥሩ ጎናቸው ሁሉ ተዘርዝሯል። የታላቁ ንጉሥ የዳዊት ስህተቶች እንኳ ሳይቀሩ በሐቀኝነት ተገልጸዋል። ብሔሩ በጥቅል የፈጸማቸው ስህተቶች በተደጋጋሚ በግልጽ ሠፍረዋል። ይህ ፍጹም ግልጽነት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እውነተኛና እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ከማረጋገጥም አልፎ ኢየሱስ ወደ አምላክ በጸለየ ጊዜ “ቃልህ እውነት ነው” ሲል የተናገራቸውን ቃላት የሚያጠናክር ነው።—35. ተጨባጭ ነገር ማግኘት አለብን የሚሉት ወገኖች ምን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል? መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ለማረጋገጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚመለከቱት ነገር ምንድን ነው?
35 ኦልብራይት እንዲህ ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም አቅጣጫ ከቀደምት ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ሁሉ ልቆ ይታያል። መልእክቱ ቀላል በሆነ መንገድ የቀረበ በመሆኑና በሁሉም አገሮችና በማንኛውም ዘመን የኖሩትን ሰዎች ሁሉ የሚያቅፍ መሆኑ ከእርሱ በኋላ ከተሠሩት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ በላይ ገንኖ እንዲታይ ያደርገዋል።”23 በኋላ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ውስጥ እንደምንመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚያረጋግጠው ‘መልእክቱ የላቀ ሆኖ መገኘቱ’ እንጂ የምሁራን ምሥክርነት አይደለም። ይሁን እንጂ ተጨባጭ ነገር እንሻለን የሚሉት የዘመናችን ተመራማሪዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉት ታሪኮች እውነተኛነት የላቸውም የሚለውን ሐሳባቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ልብ ልንለው ይገባል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ግን ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ብዙ ማስረጃ ያዘሉ ናቸው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማለትም ‘አዲስ ኪዳንን’ በሚመለከትስ ተመሳሳይ ነገር ለማለት ይቻላልን? ይህንን በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 ከጸሐፊው፣ ከጽሑፉ ምንጭ እንዲሁም እያንዳንዱ መጽሐፍ ከተጠናቀረበት ጊዜ ጋር በተያያዘ የሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት “የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት” (ወይም “ከታሪክ ጋር ተዛምዶ ያለው የግምገማ ዘዴ”) በመባል ይታወቃል።
^ አን.8 ለምሳሌ ያህል እንግሊዛዊው ባለቅኔ ጆን ሚልተን ትልቅ ግምት የተሰጠውን “ፓራዳይዝ ሎስት” የተባለውን የግጥም ሥራውን የሠራበትና “ላሌግሮ” በተባለው የጽሑፍ ሥራው ውስጥ የተጠቀመበት ስልት በጣም የተለያየ ነው። ፖለቲካዊ መልእክት ያላቸውን ትራክቶቹን ያዘጋጀበት መንገድም እንዲሁ የተለየ ነበር።
^ አን.14 ዛሬ ያሉት አብዛኛዎቹ ምሁራን ተጨባጭ ነገር ካላገኘን አናምንም ወደ ማለት አዘንብለዋል። በመዝገበ ቃላት ሰፍሮ በሚገኘው ፍቺ መሠረት ራሽናሊዝም ማለት “ሃይማኖታዊ እውነትን ለመቀበል ምክንያት ካልቀረበልኝ ማለት ነው።” እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በጉዳዩ መለኮታዊ እጅ ይኖርበት ይሆናል ብለው ከማሰብ ይልቅ ሁሉንም ነገር በሰብዓዊ ዓይን ለማየት ይሞክራሉ።
^ አን.17 የሚያስገርመው በ1970ዎቹ በሰሜን ሶርያ ውስጥ የተገኘ የአንድ የጥንት ገዥ ሐውልት አንድ ገዥ ከንጉሥ ያነሰ ሥልጣን ኖሮትም ንጉሥ ተብሎ መጠራቱ እንግዳ ነገር እንዳልሆነ አረጋግጧል። ሐውልቱ የአንድ የጎዛን ገዥ ሐውልት ሲሆን በላዩ በአሦርና በአረማይክ ቋንቋ ተጽፎበታል። በአሦር ቋንቋ የሠፈረው ጽሑፍ ገዥ ብሎ ሲጠራው ተመሳሳይ ሐሳብ የቀረበበት የአረማይክ ጽሑፍ ግን ንጉሥ ብሎታል።9 በመሆኑም ብልጣሶር በኦፊሴላዊ የባቢሎን ጽሑፎች ላይ አልጋ ወራሽ ተብሎ ተጠርቶ ዳንኤል ባሰፈረው የአረማይክ ጽሑፍ ላይ ግን ንጉሥ መባሉ ምንም አያስገርምም።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 53 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከጥንቶቹ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ታሪኮች በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሙሴና ዳዊት ያሉት የተከበረ ቦታ የነበራቸው ሰዎች የሠሯቸውን ስህተቶች በግልጽ አስፍሯል
[በገጽ 44 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአርኪኦሎጂ ጥቅም
“አርኪኦሎጂ ጥንት የነበሩትን መገልገያ መሣሪያዎች፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ ግንቦችና ሕንጻዎች፣ የጦር መሣሪያዎችና ጌጣ ጌጦችን ናሙና አስገኝቷል። ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹን በዘመን ቅደም ተከተላቸው ማስቀመጥና በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኘው ሐሳብ አንጻር በእርግጠኝነት ስያሜያቸውን መስጠት ይቻላል። በዚህ መልኩ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ የጥንቱን ባሕላዊ መቼት ምንም ሳይዛባ በጽሑፍ ጠብቆ ማቆየት ችሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ የተካተቱት ዝርዝር ሁኔታዎች የአንድ ጸሐፊ ሐሳብ የወለዳቸው ግምታዊ ነገሮች አይደሉም። ይልቁንም ከተራዎቹ ጉዳዮች አንስቶ እስከ ተዓምራዊዎቹ ክስተቶች ድረስ ሁሉም ነገሮች ፍጻሜያቸውን ያገኙበት የገሃዱ ዓለም ትክክለኛ ነጸብራቅ ናቸው።”—ዚ አርኪኦሎጂካል ኢንሳይክለፒዲያ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ
[በገጽ 50 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአርኪኦሎጂ አቅም እስከ ምን ድረስ ነው?
“አርኪኦሎጂ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው ወይም ውሸት ነው ብሎ ቁርጥ ባለ መንገድ ማረጋገጥ አይችልም። ይሁንና የማይናቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለትን የገሃዱን ዓለም በተወሰነ ደረጃ ምን ይመስል እንደነበር መልሶ ያሳየናል። አንድ ቤት የተገነባበትን ነገር ወይም ‘ኮረብቶቹ’ ምን ይመስሉ እንደነበር ማወቃችን ስለ ጥቅሱ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ታሪካዊ ዘገባው ምሉዕ እንዲሆን ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል የሞዓባውያኑ ጽላት በ2 ነገሥት 3:4 ላይ የተገለጸውን ታሪክ ከሌላኛው ወገን ሆነን እንድናየው ያስችለናል። . . . በሦስተኛ ደረጃ የጥንቷ እስራኤል አጎራባቾች ሕይወትና አመለካከት ምን እንደሚመስል ይገልጽልናል። ይህም ራሱ ትኩረት የሚስብና የጥንቷ እስራኤል አመለካከት የዳበረበትን የሐሳብ ባሕር ለመረዳት የሚያስችል ብርሃን ይፈነጥቅልናል።”—ኢብላ—ኤ ሪቬሌሽን ኢን አርኪኦሎጂ
[በገጽ 41 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚልተን የተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶችን ተከትሎ እንጂ በአንድ ዓይነት ስልት ብቻ አልጻፈም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎቹ ሥራው የተለያዩ ጸሐፊዎች የሥራ ውጤት ነው ብለው ያምናሉን?
[በገጽ 45 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የናቦኒደስ የታሪክ ሰነድ” ናቦኒደስ ንግሥናውን ለበኩር ልጁ እንደሰጠ ይገልጻል
[በገጽ 46 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሞዓባውያኑ ጽላት ንጉሥ ሞሳህ የሞዓብንና የእስራኤልን ግጭት አስመልክቶ የተናገረውን ቃል አስፍሯል
[በገጽ 47 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የባቢሎን ኦፊሴላዊ መዛግብት መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሩሳሌምን አወዳደቅ በተመለከተ ያሰፈረውን ዘገባ ይደግፋሉ