በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚታየው የአምላክ ድርጅት

የሚታየው የአምላክ ድርጅት

ምዕራፍ 23

የሚታየው የአምላክ ድርጅት

1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለማይታየው የአምላክ ድርጅት ምን ይላል?

አምላክ የሚታይ ድርጅት እንዳለው እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት በዐይን የማይታይ ድርጅት ያለው መሆኑ ነው። ይሖዋ በሰማይ ፈቃዱን የሚፈጽሙ ኪሩቤሎች፣ ሱራፌሎችና ሌሎች ብዙ መላእክት ፈጥሯል። (ዘፍጥረት 3:24፤ ኢሳይያስ 6:2, 3፤ መዝሙር 103:20) የእነዚህ ሁሉ መላእክት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:16፤ ይሁዳ 9፤ ራእይ 12:7) መላእክት ‘በዙፋናት፣ በጌትነት፣ በአለቅነት ወይም በሥልጣናት’ እንደተደራጁ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ቆላስይስ 1:16፤ ኤፌሶን 1:21) ሁሉም ይሖዋ በሚሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት ያገለግላሉ። እንደ አንድ ሆነው በመተባበር እርሱ የሰጣቸውን ሥራ ያከናውናሉ። — ዳንኤል 7:9, 10፤ ኢዮብ 1:6፤ 2:1

2. አምላክ ግዑዙን አጽናፈ ዓለማችን የፈጠረበት መንገድ ለድርጅት አስፈላጊነት ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጥ የሚያሳየው እንዴት ነው?

2 ከዚህም በተጨማሪ የሚታዩትን የአምላክ ግዑዛን ፍጥረቶች በመመልከት እርሱ ለድርጅት አስፈላጊነት ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ ለመረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በብዙ ሺህ ቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያሰባሰቡ የከዋክብት ረጨት ወይም ጋላክሲ ተብለው የሚጠሩ ትልልቅ ክምችቶች አሉ። እነዚህ የከዋክብት ረጨቶች በኅዋው ውስጥ በሥርዓት ይጓዛሉ፤ በእነዚህ የከዋክብት ረጨቶች ውስጥ ያሉት ነጠላ ከዋክብትና ፕላኔቶችም እንደዚያው ናቸው። ለምሳሌ ያህል ፕላኔቷ ምድራችን ለእኛ ቅርብ በሆነችው ኮከብ ማለትም በፀሐይ ዙሪያ የምታደርገውን ጉዞ በየዓመቱ በትክክል በ365 ቀን ከ5 ሰዓት ከ48 ደቂቃና ከ45.51 ሴኮንዶች ውስጥ ትጨርሳለች። አዎን፤ ግዑዙ አጽናፈ ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ ነው!

3. በማይታዩት የአምላክ ፍጥረታትና በግዑዙ ጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለው ጥሩ አደረጃጀት ምን ያስተምረናል?

3 በማይታዩት የአምላክ ፍጥረቶችና በግዑዙ አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለው ይህ አስደናቂ ድርጅት የሚያስተምረን ነገር አለን? አዎን፤ ይሖዋ የድርጅት አምላክ እንደሆነ ያስተምረናል። እንግዲያው እንደዚህ ያለው አምላክ እርሱን በእውነት የሚወዱትን በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ያለ መመሪያና ያለ ድርጅት እንደማይተዋቸው የተረጋገጠ ነው።

የሚታየው የአምላክ ድርጅት—በድሮ ጊዜና አሁን

4, 5. በአብርሃምና በእስራኤል ሕዝብ ዘመን አምላክ ሕዝቡን በተደራጀ መልክ ይመራ እንደነበረ እንዴት እናውቃለን?

4 ይሖዋ አገልጋዮቹን ምን ጊዜም በተደራጀ መልክ እንደመራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ለምሳሌ እንደ አብርሃም ያሉት የእምነት ሰዎች ቤተሰቦቻቸውንና አገልጋዮቻቸውን በማሰባሰብ ይሖዋን በኅብረት አምልከዋል። ይሖዋ አብርሃምን በማነጋገር ፈቃዱን አሳውቆታል። (ዘፍጥረት 12:1) አምላክ የነገረውንም ለሌሎች እንዲያስተላልፍ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቶት ነበር:- “ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ የሚመጡ ቤተሰቦቹን [የይሖዋን (አዓት)] መንገድ ጠብቁ ብሎ እንዲያዛቸው [ከአብርሃም] ጋር ተዋውቄአለሁ።” (ዘፍጥረት 18:19 አዓት) ሰዎች በቡድን መልክ ተደራጅተው ይሖዋን በትክክል እንዲያመልኩት የተደረገ ሥርዓታማ ዝግጅት እዚህ ላይ ማየት እንችላለን።

5 በኋላም እስራኤላውያን እየበዙ ሄደው በሚልዮን የሚቆጠሩ በሆኑበት ጊዜ ይሖዋ እያንዳንዱን ሰው ከተደራጀው ዝግጅት ተነጥሎ በራሱ መንገድ እንዲያመልክ አልተወውም። ከዚህ ይልቅ እስራኤላውያን ይሖዋን የሚያመልክ የተደራጀ ሕዝብ ሆነው ተቋቁመው ነበር። የእስራኤል ሕዝብ “የይሖዋ ጉባኤ” ተብሎ ይጠራ ነበር። (ዘኁልቁ 20:4፤ 1 ዜና 28:8) በዚያን ጊዜ ብትኖርና እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ ብትሆን ኖሮ የዚህ የአምላኪዎች ጉባኤ ክፍል እንጂ ከዚያ የተለየህ መሆን አትችልም ነበር። — መዝሙር 147:19, 20

6. (ሀ) አምላክ ሞገሱን በክርስቶስ ተከታዮች ላይ እንዳደረገ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ለአምልኮ የተደራጁ እንደነበሩ ምን ማስረጃ አለ?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁኔታው እንዴት ነበር? የይሖዋ ሞገስ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ላይ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን አፈሰሰላቸው። በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ሕዝብ ይልቅ በዚህ የክርስቲያን ድርጅት እየተጠቀመ እንዳለ ለማሳየትም ለአንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች በሽተኞችን እንዲፈውሱ፣ ሙታንን እንዲያስነሡና ሌሎች ተአምራቶችን እንዲያደርጉ ኃይል ሰጥቷቸዋል። ግሪክኛ ክርስቲያን ጽሑፎችን ስታነብ ክርስቲያኖች ለአምልኮ የተደራጁ እንደነበሩ ልብ ሳትለው ለማለፍ አትችልም። እንዲያውም ለዚሁ ዓላማ ሲባል አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ታዘዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብትኖርና እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ ብትሆን ኖሮ የክርስቲያናዊ ድርጅቱ ክፍል መሆን ነበረብህ።

7. በየትኛውም ጊዜ ቢሆን ይሖዋ ከአንድ በበለጠ ድርጅት እንዳልተጠቀመ እንዴት እናውቃለን?

7 ይሖዋ በየትኛውም ወቅት ላይ ከአንድ በሚበልጡ ድርጅቶች ተጠቅሞ ያውቃልን? በኖኅ ዘመን የአምላክን ጥበቃ በማግኘት ከጥፋት ውኃው የዳኑት ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከብ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ብቻ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 3:20) በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የክርስቲያን ድርጅቶች አልነበሩም። አምላክ ግንኙነት ያደርግ የነበረው ከአንድ ድርጅት ጋር ብቻ ነው። “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” እንጂ ከዚያ በላይ አልነበረም። (ኤፌሶን 4:5) በተመሳሳይም በዘመናችን ለአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ መመሪያ የሚሰጥ አንድ ምንጭ ብቻ እንደሚኖር ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ተናግሯል።

8. በዘመናችን አንድ የሚታይ የአምላክ ድርጅት ብቻ እንደሚኖር ኢየሱስ ያሳየው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ስለመገኘቱ በተናገረበት ጊዜ እንዲህ አለ:- “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ [ደስተኛ (አዓት)] ነው፤ እውነት እላችኋለሁ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴዎስ 24:45-47) ክርስቶስ በ1914 በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ሲመለስ መንፈሳዊ “ምግብ” ወይም ትምህርት የሚያቀርብ ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ቡድን አግኝቷልን? አዎን፣ ከ144, 000 “ወንድሞቹ” መካከል በምድር ላይ ያሉት ቀሪዎች የተሰባሰቡበትን “ባሪያ” አግኝቷል። (ራእይ 12:10፤ 14:1, 3) ከ1914 ወዲህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነርሱ ያዘጋጁትን “ምግብ” አግኝተዋል፤ ከእነርሱም ጋር የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታይ ሆነዋል። የአምላክን አገልጋዮች ያሰባሰበው የዚህ ድርጅት አባሎች የይሖዋ ምስክሮች በመባል ይታወቃሉ።

9. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋ ምስክሮች በሚለው ስም የሚጠሩት ለምንድን ነው? (ለ) ለአምልኮት የሚሰበሰቡበትን ቦታ የመንግሥት አዳራሽ ብለው የሚጠሩት ለምንድን ነው?

9 የይሖዋ ምስክሮች በሚያደርጓቸው ነገሮች ሁሉ መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክና ወደ ቃሉ ይመለከታሉ። የይሖዋ ምስክሮች የሚለው ስማቸው ራሱ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ የእነርሱም ዋና ሥራ ስለ ይሖዋ አምላክ ስምና ስለ መንግሥቱ መመስከር መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 17:6፤ ራእይ 1:5) በተጨማሪም ለአምልኮት የሚሰበሰቡበትን ቦታ የመንግሥት አዳራሽ ብለው ይጠሩታል፤ ምክንያቱም የጠቅላላው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት በመሢሑ ወይም በክርስቶስ የሚመራው መንግሥት ስለሆነ ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና የአምላክን ሞገስ ማግኘቱ ግልጽ በመሆኑ የይሖዋ ምስክሮች በዚያን ጊዜ የነበረውን የአደረጃጀት ምሳሌ ይከተላሉ። እስቲ አሁን የመጀመሪያውን የክርስትና ድርጅት በአጭሩ እንመልከትና በአሁኑ ጊዜ ካለው ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ጋር ያሉትን ተመሳሳይ ሁኔታዎች እናስተውል።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአደረጃጀት መልክ

10. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ድርጅት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በተገኙበት ስፍራ ሁሉ በቡድን በቡድን ሆነው ለአምልኮት ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ጉባኤዎች ተገናኝቶ ለመተናነጽና ለማጥናት ሲሉ ዘወትር ይሰበሰቡ ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) ዋነኛ ሥራቸውም ክርስቶስ እንዳደረገው ስለ አምላክ መንግሥት መስበክና ማስተማር ነበር። (ማቴዎስ 4:17፤ 28:19, 20) አንድ የጉባኤው አባል ወደ መጥፎ አኗኗር ዘወር ካለ ከጉባኤው ያስወግዱት ነበር። — 1 ቆሮንቶስ 5:9-13፤ 2 ዮሐንስ 10, 11

11, 12. (ሀ) የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ጉባኤዎች መመሪያንና ውሳኔን በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሐዋርያትና “ሽማግሌዎች” ያገኙ እንደነበረ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? (ለ) “ቲኦክራቲካዊ” አመራር ሲባል ምን ማለት ነው? (ሐ) ጉባኤዎች እንደዚህ ያለውን አመራር መቀበላቸው ምን ውጤት አስገኘ?

11 እነዚያ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤዎች እያንዳንዳቸው ከሌላው ተነጥለው ራሳቸውን ችለው የሚኖሩና በነገሮች ላይ የራሳቸውን ውሳኔ የሚሰጡ ነበሩን? አልነበሩም፤ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ የክርስቲያን እምነት የተባበሩ እንደነበሩ ያሳያል። ሁሉም ጉባኤዎች መመሪያና ውሳኔ የሚያገኙት ከአንድ ምንጭ ነበር። ስለዚህ በግዝረት ጉዳይ ላይ ክርክር በተነሣ ጊዜ ጉባኤዎች ወይም ግለሰቦች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ራሳቸው አልወሰኑም። በዚህ ፋንታ ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ስለ ክርክሩ “ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ።” እነዚህ የበሰሉ ሰዎች በአምላክ ቃልና ‘በመንፈስ ቅዱስ’ እየተረዱ ውሳኔ ካደረጉ በኋላ ይህንን ለጉባኤዎች እንዲያሳውቁ ታማኝ ሰዎችን ላኩ። — ሥራ 15:2, 27-29

12 ጉባኤዎቹ ይህንን ቲኦክራቲካዊ ወይም ከአምላክ የተሰጠ መመሪያና ውሳኔ መቀበላቸው ምን ውጤት አስገኘ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኞቹ “በከተማዎች ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቆረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጧቸው። [ጉባኤዎችም በእምነት] ይበረቱ ነበር፣ በቁጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።” (ሥራ 16:4, 5) አዎን፤ ሁሉም ጉባኤዎች በኢየሩሳሌም የነበረው የሽማግሌዎች አካል ካስተላለፈው ውሳኔ ጋር ተባበሩ፤ ስለዚህም በእምነት የበለጠ እየጠነከሩ ሄዱ።

በዛሬው ጊዜ ያለው አምላካዊ አመራር

13. (ሀ) የሚታየው የአምላክ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ አመራርን የሚያገኘው በምድር ላይ ከሚገኝ ከየትኛው ቦታና በየትኛው የሰዎች ቡድን በኩል ነው? (ለ) የአስተዳደር አካሉ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ ጋር ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

13 በዛሬው ጊዜም የሚታየው የአምላክ ድርጅት አምላካዊ አመራርና ውሳኔ ያገኛል። በብሩክሊን፣ ኒውዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ዓለም አቀፉን የአምላክ ሕዝቦች የሥራ እንቅስቃሴ ለማካሄድ አስፈላጊ አመራር የሚሰጥ ከተለያዩ የምድር ክፍሎች የተውጣጡ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አባል የሆኑበት አንድ የአስተዳደር አካል አለ። ይህ የአስተዳደር አካል ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ አባሎች የተውጣጣ ነው። ለዚህ ታማኝ ‘ባሪያ’ እንደ ተወካይ ወይም ቃል አቀባይ ሆኖ ይሠራል።

14. የአምላክ ሕዝቦች የአስተዳደር አካል በምን ላይ ተደግፎ ውሳኔዎች ያደርጋል?

14 በአስተዳደር አካሉ ውስጥ ያሉት ወንዶች በኢየሩሳሌም እንደነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በአምላክ አገልግሎት የብዙ ዓመት ልምድ አላቸው። ይሁን እንጂ በሰብዓዊ ጥበብ ላይ የተመረኰዘ ውሳኔ አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ በአምላካዊ አገዛዝ ስር ያሉ እንደመሆናቸው መጠን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ያደርግ የነበረውን የጥንቱን የኢየሩሳሌም የአስተዳደር አካል ምሳሌ ይከተላሉ። — ሥራ 15:13-17, 28, 29

ዓለም አቀፉን ድርጅት መምራት

15. በማቴዎስ 24:14 ያሉት የኢየሱስ ቃላት በፍጻሜው ዘመን አምላክ በምድር ላይ ሰፊ ድርጅት እንደሚኖረው የሚያሳዩት ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ክርስቶስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሎ በተናገረ ጊዜ በፍጻሜው ዘመን የአምላክ ድርጅት የቱን ያህል ስፋት እንደሚኖረው ሐሳብ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14) በብዙ ሺህ ሚልዮን ለሚቆጠሩት የምድር ሕዝቦች ስለተቋቀመው የአምላክ መንግሥት ለመንገር ምን ያህል ትልቅ ሥራ መከናወን እንደሚያስፈልገው ገምት። መመሪያና ውሳኔ ለማግኘት ወደ አስተዳደር አካሉ የሚመለከተው ዘመናዊው የክርስቲያን ድርጅት ይህንን ታላቅ ሥራ ለመሥራት የተሟላ ትጥቅ አለውን?

16. (ሀ) የይሖዋ ምስክሮች ብዙ ትልልቅ የማተሚያ ፋብሪካዎችን ያቋቋሙት ለምንድን ነው? (ለ) በእነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚመረተው ምንድን ነው?

16 የይሖዋ ምስክሮች በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት በመላው ምድር ላይ ከ200 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ ይሰብካሉ። ከ4, 000, 000 (በ1990) በላይ የሆኑት የመንግሥት ሰባኪዎች ይህንን ሥራ እንዲያከናውኑ ለማገዝ በብዙ አገሮች ታላላቅ የማተሚያ ፋብሪካዎች ተቋቁመዋል። በእነዚህም ፋብሪካዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በብዛት ይዘጋጃሉ። በእያንዳንዱ የሥራ ቀን ላይ በአማካይ ከሁለት ሚልዮን በላይ የሆኑ የመጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶች ታትመው ከእነዚህ ፋብሪካዎች ወደ ልዩ ልዩ ስፍራ ይላካሉ።

17. (ሀ) ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ የሚዘጋጀው ለምንድን ነው? (ለ) ምን እንድታደርግ ተጋብዘሃል?

17 ይህ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ የሚዘጋጀው ሰዎች የይሖዋ አምላክን ታላላቅ ዓላማዎች በበለጠ እያወቁ እንዲሄዱ ለመርዳት ነው። እንዲያውም “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉት ቃላት መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ርዕስ ክፍል ናቸው። ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጽሔት በማሰራጨቱና በውስጡ ያሉትን እውነቶች ለሌሎች በማስረዳቱ ሥራ እንድትሳተፍ ተጋብዘሃል። ለምሳሌ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ ከተባለው ከዚህ መጽሐፍ የተማርከውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ልታካፍለው የምትችል ሰው ይኖራልን?

18. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያለው የአምላክ ድርጅት ምን ዓይነት ድርጅት ነው? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ ብዙ ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

18 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም የአምላክ ድርጅት ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና የተጠመቁ የመንግሥት ሰባኪዎችን ያቀፈ ድርጅት ነው። ድርጅቱም አባሎቹ ሁሉ በዚህ የስብከት እንቅስቃሴ እንዲካፈሉ ለመርዳት የተቋቋመ ነው። እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ማበረታቻና መንፈሳዊ ማጠናከሪያ ያስፈልጋቸዋል፤ ምክንያቱም ሰይጣንና እርሱ በቁጥጥሩ ሥር ሊያደርጋቸው የቻላቸው ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ይቃወማሉ። ኢየሱስ ይህንን መንግሥት በመስበኩ እንደነዚህ ያሉት ተቃዋሚዎች አስገድለውታል። ተከታዮቹም ጭምር እንደሚሰደዱ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቅቋል። — ዮሐንስ 15:19, 20፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12

19. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች ለመርዳትና ለማጠናከር እነማን ተሹመዋል? (ለ) ጉባኤው ሊያበላሹት ከሚችሉ መጥፎ ግፊቶች ጥበቃ የሚደረግለት እንዴት ነው?

19 ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም እያንዳንዱን ጉባኤ ለመርዳትና ለማጠናከር ሽማግሌዎች ይሾማሉ። እነርሱም ጭምር የተለያዩ ችግሮችን እንድትቋቋም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እያሳዩ ሊረዱህ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ እነዚህ ሽማግሌዎች “የአምላክን መንጋ” ከጥቃት ይከላከሉለታል። ስለዚህ አንድ የጉባኤው አባል ወደ መጥፎ የሕይወት መንገድ ቢመለስና ለመለወጥ እምቢ ቢል እንደዚህ ያለው ሰው ከጉባኤው እንዲወጣ ወይም እንዲወገድ ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ ጉባኤው ጤናማና በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆኖ ይቀጥላል። — ቲቶ 1:5፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3፤ ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 1 ቆሮንቶስ 5:13

20. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም ከነበረው የአስተዳደር አካል ይላኩ የነበሩት እነማን ናቸው? ለምንስ ዓላማ? (ለ) በዛሬውስ ጊዜ የአስተዳደር አካል እነማንን ይልካል?

20 በኢየሩሳሌም የነበረው የአስተዳደር አካል ለአምላክ ሕዝቦች መመሪያዎችን እንዲያደርሱና ማጽናኛዎችን እንዲሰጡ እንደ ጳውሎስና ሲላስ ያሉትን ልዩ ተወካዮች ይልክ እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ያለው የአስተዳደር አካልም በተመሳሳይ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ልክ እንደዚያው ያደርጋል። (ሥራ 15:24-27, 30-32) በዓመት ሁለት ጊዜ ያህል የክልል የበላይ ተመልካች ተብሎ የሚጠራ ጥሩ የሥራ ልምድ ያለው አገልጋይ በክልሉ ውስጥ ባለው በእያንዳንዱ ጉባኤ አንድ ሳምንት እንዲያሳልፍ ይላካል።

21. የክልል የበላይ ተመልካቹ የአምላክን ሕዝብ ጉባኤዎች የሚረዳው እንዴት ነው?

21 በመላው ዓለም ላይ ከ63, 000 በላይ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች አሉ። እነዚህም በብዙ ክልሎች የተከፋፈሉ ሲሆን እያንዳንዱ ክልል 20 ጉባኤዎች ያህል ያቅፋል። የክልል የበላይ ተመልካቹ በክልሉ ውስጥ ያሉትን ጉባኤዎች ሲጎበኝ በስብከትና በማስተማር ሥራቸው አብሯቸው በመሄድ የመንግሥቱን ምስክሮች ይገነባቸዋል። በዚህ መንገድ እነርሱን ከማነቃቃቱም በተጨማሪ አገልግሎታቸውን ለማሻሻል የሚረዳ ሐሳብ ይሰጣቸዋል። — ሥራ 20:20, 21

22. (ሀ) የአምላክን ሕዝቦች ለማጠናከር በዓመት ሁለት ጊዜ ምን ተጨማሪ ዝግጅት ተደርጓል? (ለ) ምን ግብዣ ቀርቦልሃል?

22 ብዙውን ጊዜ በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ያሉ ጉባኤዎች በዓመት አንድ ጊዜ ወደሚደረገው የልዩ ስብሰባ ቀንና በዓመት አንድ ጊዜ ወደሚደረገው የሁለት ቀን የክልል ስብሰባ በመምጣት ተጨማሪ ማበረታቻና ማጠናከሪያ ያገኛሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በአንድ ቦታ ከሁለት ወይም ከሦስት መቶ እስከ 2, 000 የሚሆኑ ወይም ከዚህ የሚበልጡ ሰዎች ይገኛሉ። በሚቀጥለው ጊዜ በአካባቢህ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ተጋብዘሃል። ስብሰባውን በመንፈሳዊ የሚያነቃቃና በግል የሚጠቅም ሆኖ እንደምታገኘው እርግጠኞች ነን።

23. (ሀ) በዓመት አንድ ጊዜ ምን ሌሎች ስብሰባዎች ይደረጋሉ? (ለ) ከእነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች ውስጥ በአንደኛው ላይ ምን ያህል ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር?

23 ከዚህም በተጨማሪ የወረዳ ስብሰባ ተብሎ የሚጠራ በትልቅነቱ ከሌሎቹ በጣም የሚበልጥ ስብሰባ በዓመት አንድ ጊዜ ይደረጋል። እንደነዚህ ባሉት ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘቱ የቱን ያህል አስደሳች እንደሆነና በመንፈሳዊ እንዴት እንደሚያንጽህ ራስህ እንድታይ በስብሰባው ለመገኘት ለምን ከልብ ጥረት አታደርግም? በአንዳንድ ዓመታት ላይ በወረዳ ስብሰባዎች ፋንታ ታላላቅ የሆኑ ብሔራዊ ወይም ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። እስከ ዛሬ ድረስ በአንድ ቦታ ከተደረጉት ስብሰባዎች ውስጥ ትልቁ በ1958 በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ ለስምንት ቀናት የተደረገው ስብሰባ ነው። በዚያን ጊዜ “የአምላክ መንግሥት ትገዛለች—የዓለም ፍጻሜ ቀርቧልን?” የሚለውን የሕዝብ ንግግር ለመስማት 253, 922 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ይህንን ያህል ብዙ የሆነ ሕዝብ ሊይዝ የሚችል ቦታ አልተገኘም። ስለዚህም ለትልልቅ ስብሰባዎች በዋና ዋናዎቹ ከተሞች ብዙ ሕዝብ በሚይዙ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ለመጠቀም ዝግጅቶች ተደርገዋል።

በየጉባኤው የሚደረጉ ስብሰባዎች

24. የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎች ምን አምስት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ያደርጋሉ?

24 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል በሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ላይ አንድ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥበት ፕሮግራም አውጥቷል። እያንዳንዱ ጉባኤ በሳምንት አምስት ስብሰባዎች አሉት። እነዚህም አምላካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት፣ የአገልግሎት ስብሰባ፣ የሕዝብ ስብሰባ፣ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ናቸው። እነዚህን ስብሰባዎች ላታውቃቸው ስለምትችል ቀጥለን በአጭሩ እንገልጻቸዋለን።

25, 26. አምላካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ ለምን ዓላማ ያገለግላሉ?

25 አምላካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በሚናገሩበት ጊዜ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በትምህርት ቤቱ የተመዘገቡት ተማሪዎች በየጊዜው ለመላው ተሰብሳቢ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አጫጭር ንግግሮችን ያቀርባሉ። ከዚያም ልምድ ያለው አንድ ሽማግሌ ለማሻሻል የሚረዱ ሐሳቦችን ይሰጣቸዋል።

26 ብዙውን ጊዜ በዚያው ምሽት ላይ የአገልግሎት ስብሰባም ይደረጋል። የዚህ ስብሰባ አስተዋጽዖ በአስተዳደር አካሉ በሚዘጋጀው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ገጾች ባሉትና ወርሃዊ በሆነው የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ታትሞ ይወጣል። በዚህ ስብሰባ ላይ የመንግሥቱን መልእክት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሌሎች እንዴት ለመንገር እንደምንችል የሚያሳዩ ተግባራዊ ሐሳቦችና ትዕይንቶች ይቀርባሉ። ክርስቶስ ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ተከታዮቹን ያበረታታ ነበር፤ እንዲሁም አገልግሎታቸውን እንዴት ለማከናወን እንደሚችሉ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል። — ዮሐንስ 21:15-17፤ ማቴዎስ 10:5-14

27, 28. የሕዝብ ስብሰባ፣ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ምን ዓይነት ስብሰባዎች ናቸው?

27 የሕዝብ ስብሰባና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ብዙውን ጊዜ የሚደረጉት እሁድ ዕለት ነው። በቂ ችሎታ ባለው አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር በሚሰጥበት በዚህ የሕዝብ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ፍላጎት ያላቸው አዲስ ሰዎችን ለመጋበዝ ልዩ ጥረት ይደረጋል። የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በቅርብ የወጣ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በያዘው በአንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕስ ላይ በጥያቄና መልስ የሚደረግ ውይይት ነው።

28 ከላይ ለተዘረዘሩት ስብሰባዎች ጉባኤው በሙሉ በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ይሰበሰብ ይሆናል። ከዚህ ያነሰ ቁጥር ያላቸው ቡድኖች ደግሞ ለሳምንታዊው የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ይሰበሰባሉ። አሁን እንደምታነበው መጽሐፍ ያሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ መጻሕፍት ለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ያገለግላሉ። ይህም አንድ ሰዓት ያህል የሚቆይ ነው።

29. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ምን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ? (ለ) ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል የሚችሉት እነማን ናቸው?

29 ከእነዚህ የዘወትር ስብሰባዎች በተጨማሪ የይሖዋ ምስክሮች በየዓመቱ ለኢየሱስ ሞት መታሰቢያ አንድ ልዩ ስብሰባ ያደርጋሉ። ኢየሱስ ይህ የሞቱ መታሰቢያ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲደረግ መመሪያ በሰጠበት ጊዜ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።” (ሉቃስ 22:19, 20) ቀላል በሆነ ሥነ ሥርዓት በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ኢየሱስ ለሰው ዘር መሥዋዕት አድርጎ ለሚሰጠው ሕይወቱ ምሳሌ በሚሆኑ ወይን ጠጅና ባልቦካ ቂጣ ተጠቅሟል። ስለዚህ በዚህ ዓመታዊ በዓል ላይ ከ144, 000 ቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮች ውስጥ ገና በምድር ላይ ያሉት ቀሪዎች ከቂጣውና ከወይኑ በመካፈል ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ያሳያሉ።

30. (ሀ) በመታሰቢያው በዓል ላይ እነማን ጭምር መገኘታቸው ትክክል ነው? ተስፋቸውስ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች እንዴት ብሎ ገልጿቸዋል?

30 በምድር ዙሪያ በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ በሚደረገው በዚህ መታሰቢያ በዓል የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች የሁኔታው ተመልካቾች በመሆናቸው ይደሰታሉ። እንዲሁም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለመውጣት እንዲችሉ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጉላቸውን ነገሮች የሚያስታውሳቸው ንግግር ይቀርባል። ሆኖም ሰማያዊ ሕይወት በመጠበቅ ፋንታ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ለመኖር ባላቸው ተስፋ ይደሰታሉ። ‘የሙሽራው ሚዜ ነኝ’ ብሎ እንደተናገረው እንደ አጥማቂው ዮሐንስ ናቸው እንጂ 144, 000 አባላት ያሏት የክርስቶስ ሙሽራ ክፍል አይደሉም። (ዮሐንስ 3:29) እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ የተናገረላቸው “ሌሎች በጎች” ክፍል ናቸው። ‘የታናሹ መንጋ’ አባሎች አይደሉም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደተናገረው ከ“ታናሹ መንጋ” አባሎች ጋር በኅብረት ያገለግላሉ። ስለዚህ ሁሉም “አንድ መንጋ ይሆናሉ።” — ዮሐንስ 10:16፤ ሉቃስ 12:32

አምላክን ከድርጅቱ ጋር ሆኖ ማገልገል

31. ከሐሰት ሃይማኖት ሳይወጡ የይሖዋ ድርጅት ክፍል ለመሆን የሚሞክሩትን አምላክ እንደማይቀበላቸው ምን ማረጋገጫ አለ?

31 እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ዛሬም ይሖዋ አምላክ የሚታይ ድርጅት ያለው መሆኑ እንዴት ግልጽ ነው! በአሁኑ ጊዜ አምላክ ድርጅቱን በአዲሱ የጽድቅ ሥርዓቱ ውስጥ ለሚኖረው ሕይወት ሰዎችን ለማሠልጠን እየተጠቀመበት ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ ድርጅት ክፍል ሆነን እያለን የሐሰት ሃይማኖት አባል መሆን አንችልም። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?” ስለዚህ አምላክ “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ” ብሎ አዟል። — 2 ቆሮንቶስ 6:14-17

32. (ሀ) ‘ከመካከላቸው ወጥተናል’ ለማለት እንድንችል ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ከሚታየው አምላካዊ ድርጅት ጋር ሆነን ለማገልገል ስንል አስፈላጊውን እርምጃ ብንወስድ ምን በረከት እናገኛለን?

32 “ከመካከላቸው ውጡ” ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ አምላክ አሁን ከሚጠቀምበት ድርጅት ውጭ የሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት ክፍል ሆነን ብንቀጥል ወይም ለእርሱ ድጋፍ ብንሰጥ ይህንን ትእዛዝ አላከበርንም ማለት ነው። ስለዚህ ገና አሁንም የእንደዚህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል የሆንን ካለን ከዚያ መውጣታችንን እንድናስታውቃቸው ያስፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ የሐሰት ሃይማኖትን ከሚከተሉት መካከል ከወጣንና በሚታየው የአምላክ ድርጅት ውስጥ ሆነን እርሱን ለማገልገል እርምጃ ከወሰድን አምላክ “በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ” ብሎ ከተናገረላቸው መካከል እንሆናለን። — 2 ቆሮንቶስ 6:16

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 192 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥፋት ውኃው ጊዜ አምላክ ከአንድ በላይ ድርጅት ነበረውን?

[በገጽ 196 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሥራ አመራር የሚሰጥባቸው ቢሮዎች

የጠቅላላውን ዓለም ሥራ የሚያካሄደው የይሖዋ ምስክሮች ዋና መሥሪያ ቤት

የኮምፒተር ክፍል

የሮታሪ ማተሚያ

የመጻሕፍት ጥረዛ

የመጻሕፍት መላኪያ

ብሩክሊን ያሉት ማተሚያዎች

[በገጽ 197 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከብዙዎቹ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሌሎች ማተሚያ ቤቶች መካከል ጥቂቶቹ

ደቡብ አፍሪካ

ዎልኪል፣ ኒውዮርክ

ካናዳ

ብራዚል

እንግሊዝ አገር

[በገጽ 198 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በኒውዮርክ በተደረገ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 253, 922 ተሰብሳቢዎች ጥቂቶቹ

ፖሎ ግራውንድስ

ያንኪ ስታዲየም

[በገጽ 201 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ምስክሮች ስብሰባዎች ላይ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣል