በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀመረች

የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀመረች

ምዕራፍ 16

የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀመረች

1. (ሀ) የእምነት ሰዎች ለረጅም ጊዜ ምንን ሲጠባበቁ ቆይተዋል? (ለ) የአምላክ መንግሥት “ከተማ” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው?

በአምላክ መንግሥት ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች መንግሥቲቱ መግዛት የምትጀምርበትን ጊዜ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ታማኙ አብርሃም “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበር” ይላል። (ዕብራውያን 11:10) ያች “ከተማ” የአምላክ መንግሥት ናት። ታዲያ እዚህ ላይ “ከተማ” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በጥንት ጊዜ አንድ ንጉሥ በአንዲት ከተማ ላይ መግዛቱ የተለመደ ስለነበር ነው። ስለዚህም ሰዎች ብዙውን ጊዜ አንድን ከተማ እንደ አንድ መንግሥት አድርገው ይመለከቱ ነበር።

2. (ሀ) ለመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት መንግሥቲቱ እርግጠኛ ነገር እንደነበረች የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ስለ እርሷስ ምን ለማወቅ ፈልገው ነበር?

2 የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች የአምላክን መንግሥት እንደ ተጨባጭ እውነት አድርገው ይመለከቷት ነበር። ይህም ስለ አገዛዟ ለማወቅ በነበራቸው ጉጉት ታይቷል። (ማቴዎስ 20:20-23) በአእምሮአቸው የነበረው ጥያቄ:- ‘ክርስቶስና ደቀመዛሙርቱ መግዛት የሚጀምሩት መቼ ይሆናል?’ የሚል ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለደቀመዛሙርቱ በተገለጠበት ጊዜ “ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። (ሥራ 1:6) ታዲያ እንደ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ አንተስ ክርስቶስ በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበትን ጊዜ ለማወቅ ትጓጓለህን?

ክርስቲያኖች የሚጸልዩላት መንግሥት

3, 4. (ሀ) አምላክ ምን ጊዜም ንጉሥ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ታዲያ ኢየሱስ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት ትምጣ ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለምንድን ነው?

3 ክርስቶስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተማራቸው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይሁን እንጂ አንድ ሰው:- ‘ይሖዋ አምላክ ሁልጊዜ ንጉሥ ሆኖ ሲገዛ ቆይቶ የለምን? ከሆነስ መንግሥቲቱ እንድትመጣ ለምን እንጸልያለን?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል።

4 እውነት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “የዘላለም ንጉሥ” ብሎ ይጠራዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:17 አዓት) እንዲሁም “[ይሖዋ (አዓት)] ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፣ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች” ይላል። (መዝሙር 103:19) ስለዚህ ይሖዋ ምን ጊዜም የፍጥረቶቹ ሁሉ የበላይ ገዥ ሆኖ ቆይቷል። (ኤርምያስ 10:10) ይሁን እንጂ በኤደን ገነት ውስጥ በአገዛዙ ላይ በተነሣው ዓመፅ ምክንያት አምላክ አንድ ልዩ የሆነ መንግሥት ለማቋቋም ዝግጅት አደረገ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከጊዜ በኋላ መጥቶ ተከታዮቹ እንዲጸልዩላት ያስተማራቸው መንግሥት ይህች ናት። የመንግሥቲቱ ዓላማ ሰይጣን ዲያብሎስና ሌሎች ከአምላክ አገዛዝ በወጡበት ጊዜ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማስወገድ ነው።

5. መንግሥቲቱ የአምላክ መንግሥት ከሆነች የክርስቶስ መንግሥትና የ144, 000ዎቹ መንግሥት ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው?

5 ይህ አዲስ ንጉሣዊ መንግሥት የመግዛት ሥልጣኑንና መብቱን የሚቀበለው ከታላቁ ንጉሥ ከይሖዋ አምላክ ነው። ይህ የእርሱ መንግሥት ነው። መጽሐፍ ቅዱስም በተደጋጋሚ “የአምላክ መንግሥት” ብሎ ይጠራዋል። (ሉቃስ 9:2, 11, 60, 62፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 15:50) ሆኖም ይሖዋ ልጁን የዚህ መንግሥት ዋና ገዥ አድርጎ ስለሾመው የክርስቶስ መንግሥት ተብሎም ተጠርቷል። (2 ጴጥሮስ 1:11) ቀደም ብለን በአንድ ምዕራፍ ላይ እንዳጠናነው ከሰው ዘር መካከል የተመረጡ 144, 000 ሰዎች በዚህች መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ይገዛሉ። (ራዕይ 14:1-4፤ 20:6) በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “የእነርሱ መንግሥት” እንደሆነም ጭምር ይናገራል። — ዳንኤል 7:27 አዓት

6. አንዳንድ ሰዎች የአምላክ መንግሥት መቼ መግዛት ጀምራለች ይላሉ?

6 አንዳንድ ሰዎች መንግሥቲቱ መግዛት የጀመረችው ኢየሱስ ወደ ሰማይ በተመለሰበት ዓመት ነው ይላሉ። ክርስቶስ መግዛት የጀመረው በ33 እዘአ በተከበረው የአይሁዳውያን የጴንጠቆስጤ በዓል ዕለት በተከታዮቹ ላይ መንፈስ ቅዱስ ባፈሰሰ ጊዜ ነው ይላሉ። (ሥራ 2:1-4) ይሁን እንጂ ይሖዋ በሰይጣን ዓመፅ የተነሡትን ችግሮች ሁሉ ለማጥፋት ያቋቋመው መንግሥት በዚያን ጊዜ መግዛት አልጀመረም። ‘ወንዱ ልጅ’ ማለትም ክርስቶስ ገዥ የሆነለት የአምላክ መንግሥት በዚያን ጊዜ እንደተወለደና መግዛት እንደጀመረ የሚያሳይ ምንም ነገር የለም። (ራዕይ 12:1-10) ነገር ግን በ33 እዘአ ኢየሱስ በሆነ መንገድ መንግሥት ነበረውን?

7. ክርስቶስ ከ33 እዘአ ጀምሮ በእነማን ላይ ሲገዛ ቆይቷል?

7 አዎን፤ ኢየሱስ ወደፊት በሰማይ አብረውት በሚሆኑት ማለትም በተከታዮቹ ጉባኤ ላይ በዚያን ጊዜ መግዛት ጀምሮ ነበር። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ እነርሱ በምድር ላይ ባሉበት ጊዜ “ወደ ፍቅሩ የአምላክ ልጅ መንግሥት” እንደተወሰዱ አድርጎ ይናገራል። (ቆላስይስ 1:13) ይሁን እንጂ ይህ ሰማያዊ ተስፋ ባላቸው ክርስቲያኖች ላይ የሚገዛ መንግሥት ወይም አገዛዝ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ይምጣ ብለው እንዲጸልዩለት ያስተማራቸው ንጉሣዊ መንግሥት አይደለም። ይህ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ በሚነግሡት በ144, 000ዎቹ ላይ ብቻ የሚገዛ መንግሥት ነው። ባለፉት ክፍለ ዘመናት የዚህ መንግሥት ተገዢዎች እነርሱ ብቻ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ይህ አገዛዝ ወይም ‘የአምላክ የፍቅሩ ልጅ መንግሥት’ ሰማያዊ ተስፋ ካላቸው ከእነዚህ ተገዥዎች ውስጥ የመጨረሻው አባል ሲሞትና በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ሲተባበር ያበቃል። ከዚያ በኋላ የክርስቶስ ተገዥዎች አይሆኑም። ከረጅም ጊዜ በፊት ተስፋ በተሰጠበት የአምላክ ንጉሣዊ አገዛዝ ውስጥ ከእርሱ ጋር ነገሥታት ይሆናሉ።

በጠላቶቹ መካከል መግዛት ጀመረ

8. (ሀ) ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ መግዛት ከመጀመሩ በፊት የሚቆይበት ጊዜ እንዳለ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ለክርስቶስ ምን አለው?

8 ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ ወዲያው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት አልጀመረም። ከዚያ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ “እርሱ ግን (ኢየሱስ ክርስቶስ) ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፣ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደፊት ይጠብቃል ” ብሎ እንደገለጸው በመጠበቅ የሚያሳልፈው ጊዜ ነበረው። (ዕብራውያን 10:12, 13) ክርስቶስ መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ “[ሂድ (አዓት)] በጠላቶችህ መካከል ግዛ” ወይም ድል አድርግ ብሎ ነገረው። — መዝሙር 110:1, 2, 5, 6

9. (ሀ) የአምላክን መንግሥት የሚፈልገው ሁሉም ሰው ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት መግዛት ስትጀምር አሕዛብ ምን ያደርጋሉ ተብሎ ነበር?

9 ለአምላክ መንግሥት ጠላት የሚሆን አንድም ሰው መገኘቱ እንግዳ ነገር ይመስላልን? ይሁን እንጂ ተገዢዎቹን ትክክል የሆነውን ማድረግ አለባችሁ በሚል መንግሥት ስር ለመኖር የሚፈልገው ሁሉም ሰው አይደለም። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋና ልጁ የዓለምን አገዛዝ እንዴት እንደሚይዙ ከተናገረ በኋላ “አሕዛብም ተቆጡ” ይላል። (ራዕይ 11:15, 17, 18) ብሔራት የአምላክን መንግሥት በደስታ አይቀበሉም ፤ ምክንያቱም ሰይጣን አስቶ የመንግሥቱ ተቃዋሚ ያደርጋቸዋል።

10, 11. (ሀ) የአምላክ መንግሥት መግዛት ስትጀምር በሰማይ ምን ሆነ? (ለ) በምድርስ ላይ ምን ሆነ? (ሐ) ስለዚህ የትኛውን ትልቅ ነጥብ ለማስታወስ እንፈልጋለን?

10 የአምላክ መንግሥት አገዛዙን ሲጀምር ሰይጣንና መላእክቱ ገና በሰማይ ነበሩ። መንግሥታዊ አገዛዙን ስለሚቃወሙ ወዲያውኑ ጦርነት ተጀመረ። በዚህም ምክንያት ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ተባረሩ። በዚህ ጊዜ በሰማይ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ አለ:- “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ።” አዎን የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀመረ! ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ስለተባረሩም በዚያ ደስታ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ” ይላል። — ራዕይ 12:7-12

11 ይህ ለምድር ጭምር የደስታ ጊዜ ነውን? አይደለም! ከዚያ ይልቅ በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የችግር ጊዜ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ራዕይ 12:12) ስለዚህም ልናስታውሰው የሚገባን አንድ ትልቅ ነጥብ የሚከተለው ነው:- የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀመረ ማለት በምድር ላይ ወዲያውኑ ሰላምና ደኅንነት ሆናል ማለት አይደለም። እውነተኛ ሰላም የሚመጣው የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ ስትቆጣጠር ነው። ይህም የሚሆነው ያ “ጥቂት ዘመን” አብቅቶ ሰይጣንና አጋንንቱ በማንም ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ሲባል ከአካባቢው እንዲጠፉ ሲደረግ ነው።

12. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት መግዛት የምትጀምርበትን ጊዜ ይነግረናል ብለን ለመጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

12 ይሁን እንጂ ሰይጣን ከሰማይ የሚባረርበትና በዚያ ሳቢያ ‘ለጥቂት ዘመን’ በምድር ላይ መከራ የሚሆንበት ጊዜ መቼ ነው? የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረችው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ መልስ ይሰጣልን? መልስ ይሰጣል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ልጅ መሢሕ ለመሆን ሰብዓዊ ፍጡር ሆኖ ወደ ምድር መቼ እንደሚመጣ ከረጅም ዘመን በፊት አስታውቆ ስለነበር ነው። እንዲያውም መሢሕ የሚሆንበትን ዓመት ለይቶ አመልክቷል። ከዚያ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን መሢሑ ወይም ክርስቶስ መንግሥታዊ ግዛቱን ለመጀመር የሚመጣበትንስ ጊዜ ተናግሯልን? ይህ የሚሆንበትን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ብለን በእርግጥ ልንጠብቅ እንችላለን!

13. መሢሑ በምድር ላይ የሚገለጥበትን ዓመት መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው?

13 ይሁን እንጂ አንድ ሰው:- ‘መጽሐፍ ቅዱስ መሢሑ በምድር ላይ የሚገለጥበትን ዓመት አስቀድሞ የተናገረበት ቦታ የት ላይ ይገኛል?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዝ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባኤና (ሳምንታትና) ስድሳ ሁለት ሱባኤ (ሳምንታት) ይሆናል” ወይም በጠቅላላው 69 ሳምንታት ይሆናል። (ዳንኤል 9:25) ሆኖም እነዚህ ቃል በቃል 483 ቀኖችን ወይም ከአንድ ዓመት ትንሽ የሚበልጡትን 69 ሳምንታት ብቻ የሚያመለክቱ አይደሉም። እነርሱ 69 የዓመታት ሳምንታት ወይም 483 ዓመታት ናቸው። (ከዘኁልቁ 14:34 ጋር አወዳድር) የኢየሩሳሌምን ግንቦች እንደገና ለመሥራት ትእዛዝ የወጣው በ455 ከዘአበ ነበር። * (ነህምያ 2:1-8) ስለዚህ እነዚህ 69 የዓመታት ሳምንታት የተፈጸሙት ከ483 ዓመታት በኋላ በ29 እዘአ ነበር። ኢየሱስ ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ የሄደውም በዚሁ ዓመት ላይ ነበር! በዚያ ወቅት ላይ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባና መሢሕ ወይም ክርስቶስ ሆነ። — ሉቃስ 3:1, 2, 21-23

የአምላክ መንግሥት መግዛት የምትጀምርበት ጊዜ

14. በዳንኤል ምዕራፍ አራት ላይ የተገለጸው “ዛፍ” ለምን ነገር የቆመ ነው?

14 ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን መግዛት የሚጀምርበትን ዓመት የሚተነብየው የት ላይ ነው? ይህም ቢሆን የሚገኘው በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ነው። (ዳንኤል 4:10-37) በዚህም ላይ የባቢሎን ንጉሥ የነበረውን ናቡከደነፆርን የሚያመለክት ቁመቱ እስከ ሰማይ የሚደርስ አንድ ትልቅ ዛፍ ተጠቅሷል። በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር የሁሉም የሰብዓዊ ገዥዎች የበላይ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሥ ናቡከደነፆር ከእርሱ በላይ የሆነ አንድ ገዥ እየገዛ እንዳለ ለማወቅ ተገዷል። ይህም ‘የሁሉ የበላይ’ ወይም ‘የሰማያት ንጉሥ’ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። (ዳንኤል 4:34, 37) ስለዚህ ከዚህ በበለጠ መንገድ ይህ እስከ ሰማይ የሚደርስ ዛፍ በተለይ ከምድራችን ጋር ባለው ግንኙነት ከሁሉም በላይ የሆነውን የአምላክን የበላይ ገዥነት ያመለክታል። የይሖዋ አገዛዝ ለተወሰኑ ጊዜያት በእስራኤል ሕዝብ ላይ አቋቁሞት በነበረው መንግሥት አማካኝነት ተገልጾ ነበር። በዚህም ምክንያት በእስራኤላውያን ላይ ይገዙ የነበሩት ከይሁዳ ነገድ የሆኑ ነገሥታት “በይሖዋ ዙፋን ላይ ተቀምጠዋል” እየተባለ ይነገርላቸው ነበር። — 1 ዜና 29:23 አዓት

15. “ዛፉ” ሲቆረጥ በላዩ ላይ ለምን ማሰሪያ ተደረገበት?

15 በዳንኤል ምዕራፍ አራት ላይ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ቁመቱ እስከ ሰማይ የደረሰው ዛፍ ተቆረጠ። ይሁን እንጂ ጉቶው ቀርቶ በብረትና በናስ ማሠሪያ ታሠረ። እንደዚህ መደረጉ ማሰሪያው ተፈትቶ ጉቶው እንደገና ማቆጥቆጥ እንዲጀምር አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ጉቶውን እንዳያድግ ይከለክለዋል። ታዲያ የአምላክ አገዛዝ የተቆረጠው እንዴትና መቼ ነበር?

16. (ሀ) የአምላክ አገዛዝ የተቆረጠው እንዴትና መቼ ነበር? (ለ) ‘በይሖዋ ዙፋን’ ላይ ለመቀመጥ የመጨረሻ ለሆነው የይሁዳ ንጉሥ ምን ተብሎ ተነገረው?

16 ይሖዋ ያቋቋመው የይሁዳ መንግሥት ከጊዜ በኋላ ስለተበላሸ አምላክ ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲቆርጠው ወይም እንዲያጠፋው ፈቀደለት። ይህም የሆነው በ607 ከዘአበ ነበር። በዚያን ጊዜ በይሖዋ ዙፋን ላይ ለመቀመጥ የመጨረሻ ለሆነው የይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ “ዘውዱን አውልቅ . . . ሕጋዊ መብት ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህ የማንም አይሆንም፤ ለእርሱም እሰጠዋለሁ።” ተብሎ ተነገረው። — ሕዝቅኤል 21:25-27 አዓት

17. በ607 ከዘአበ የትኛው ጊዜ ጀመረ?

17 በዚህም መንገድ በዚህ “ዛፍ” ተመስሎ የነበረው የአምላክ አገዛዝ በ607 ከዘአበ ተቆረጠ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በምድር ላይ የአምላክን አገዛዝ የሚወክል ምንም መንግሥት አልነበረም። ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ወይም “የአሕዛብም ዘመን” በማለት በኋላ የጠቀሰው ጊዜ በ607 ከዘአበ ጀመረ። (ሉቃስ 21:24) በእነዚህ “የተወሰኑ ዘመናት” ውስጥ አምላክ አገዛዙን በምድር ላይ የሚወክል መንግሥት አልነበረውም።

18. “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ሲያበቁ ምን መሆን ነበረበት?

18 በእነዚህ “የተወሰኑ የአሕዛብ ዘመናት” ፍጻሜ ላይ ምን ነገር መሆን ነበረበት? ይሖዋ “ሕጋዊ መብት ያለው” ለተባለው የመግዛት ሥልጣን ይሰጠዋል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” የሚያበቁበትን ጊዜ ለማወቅ ከቻልን ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ እናውቃለን።

19. በምድር ላይ የአምላክ አገዛዝ ተቋርጦ የሚቆየው ለምን ያህል “ዘመናት” ነበር?

19 በዳንኤል ምዕራፍ አራት መሠረት እነዚህ “የተወሰኑ ዘመናት” “ሰባት ዘመናት” ናቸው። የዳንኤል መጽሐፍ ‘በዛፍ’ የተመሰለው የአምላክ አገዛዝ በምድር ላይ የማይኖርባቸው “ሰባት ዘመናት” እንደሚኖሩ ያሳያል። (ዳንኤል 4:16, 23) የእነዚህ “ሰባት ዘመናት” ርዝመት ምን ያህል ነው?

20. (ሀ) አንድ “ዘመን” ምን ያህል ርዝመት አለው? (ለ) ‘ሰባቱ ዘመናትስ’ ምን ያህል ርዝመት አላቸው? (ሐ) አንድን ቀን እንደ አንድ ዓመት አድርገን የምንቆጥረው ለምንድን ነው?

20 በራእይ ምዕራፍ 12 ቁጥር 6 እና 14 ላይ 1, 260 ቀኖች ‘ከአንድ ዘመን ከዘመናትና (ይኸውም 2 ዘመናት)፣ ከዘመናት እኩሌታ’ ጋር እኩል እንደሆኑ እንመለከታለን። ይህም በጠቅላላው 31/2 ዘመናት ይሆናል። ስለዚህም “አንድ ዘመን” 360 ቀን ይሆናል ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ‘ሰባቱ ዘመናት’ 7 ጊዜ 360 ወይም 2, 520 ቀናት ይሆናሉ። አሁን ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ደንብ መሠረት አንዱን ቀን እንደ አንድ ዓመት አድርገን ብንወስድ ‘ሰባቱ ዘመናት’ 2, 520 ዓመታት ይሆናሉ። — ዘኁልቁ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6

21. (ሀ) “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” የጀመሩትና ያበቁት መቼ ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት መቼ መግዛት ጀመረች? (ሐ) አሁንም ቢሆን የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ መጸለዩ ለምን ተገቢ ነው?

21 “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ607 ከዘአበ እንደጀመሩ ቀደም ብለን ተምረናል። ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 2, 520 ዓመታት ብንቆጥር ወደ 1914 እዘአ እንደርሳለን። “የተወሰኑት ዘመናት” ያበቁት በዚሁ ዓመት ነው። አሁንም ገና በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በ1914 የተፈጸሙትን ነገሮች ያስታውሳሉ። በዚያ ዓመት የተነሣው አንደኛው የዓለም ጦርነት እስከ ዘመናችን ድረስ የቀጠለ አስከፊ የችግር ጊዜ ከፈተ። ይህም ሲባል ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ ማለት ነው። መንግሥቲቱ መግዛት ስለጀመረች ‘እንድትመጣና’ የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከምድር ገጽ ላይ ጠራርጋ እንድታጠፋ መጸለያችን ምንኛ ወቅታዊ ነው! — ማቴዎስ 6:10፤ ዳንኤል 2:44

22. አንዳንዶች ምን ብለው ይጠይቁ ይሆናል?

22 ሆኖም አንድ ሰው ‘ታዲያ ክርስቶስ ከተመለሰና በአባቱ መንግሥት ውስጥ መግዛት ከጀመረ ለምን አናየውም?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ይህ ትእዛዝ የተሰጠው በ455 ከዘአበ ስለመሆኑ ታሪካዊ ማረጋገጫ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በታተመው Aid to Bible Understanding (መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባን የሚረዳን መጽሐፍ ) በሚባለው መጽሐፍ ላይ “Artaxerxes” (“አርጤክስስ”) ከሚለው አርእስት ስር ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 140, 141 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

በ607 ከዘአበ የይሁዳው የአምላክ መንግሥት ወደቀ

በ1914 እዘአ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ

607 ከዘአበ—1914 እዘአ

ጥቅምት 607 ከዘአበ—ጥቅምት 1 ከዘአበ = 606 ዓመታት

ጥቅምት 1 ከዘአበ—ጥቅምት 1914 እዘአ = 1,914 ዓመታት

ሰባት የአሕዛብ ዘመናት = 2,520 ዓመታት

[በገጽ 134 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?”

[በገጽ 139 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የተገለጸው ረጅም ዛፍ መለኰታዊ አገዛዝን ለማመልከት የቆመ ነው። የይሁዳ መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ የዚህ አገዛዝ መግለጫ ሆኖ አገልግሏል።

[በገጽ 140, 141 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሁዳ መንግሥት እንዲጠፋ በተደረገ ጊዜ ዛፉ ተቆርጦ ወደቀ