በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እግዚአብሔርን እሱ በሚፈልገው መንገድ አምልከው

እግዚአብሔርን እሱ በሚፈልገው መንገድ አምልከው

እግዚአብሔርን እሱ በሚፈልገው መንገድ አምልከው

ኢየሱስ ሲጸልይ:– “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንክ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ይህ እውቀት ምን ዓይነት እውቀት ነው? “የአምላክ ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ወደ ትክክለኛው የእውነት እውቀት እንዲደርሱ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 2:4 አዓት ) ዘ አምፕሊፋይድ ባይብል ይህን የኋለኛውን ሐረግ ሲተረጉም “[መለኮታዊውን] እውነት በቀጥታና በትክክል እንዲያውቁ” ብሏል።

ስለዚህ እግዚአብሔር ከመለኰታዊ እውነት ጋር በመስማማት እሱንና ዓላማውን በትክክል እንድናውቅ ይፈልጋል። የዚህ እውነት ምንጭ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር የሚናገረውን በትክክል ሲማሩ ሮሜ 10:2, 3 ላይ:- “በእውነት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁ” እንደተባለላቸው ሰዎች መሆናቸው ይቀራል። ኢየሱስ “እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ” ካላቸው ሳምራውያን የተለዩ ይሆናሉ።—ዮሐንስ 4:22

ስለዚህ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን ራሳችንን አምላክ ስለ ራሱ ምን ይናገራል? ሊመለክ የሚፈልገውስ እንዴት ነው? ዓላማዎቹ ምንድን ናቸው? እኛስ በዚህ ዓላማው ውስጥ ቦታ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ትክክለኛው የእውነት እውቀት ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ እንድናገኝ ያስችለናል። ይህን ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን ደግሞ አምላክን እርሱ በሚፈልገው መንገድ እንድናመልከው ያስችለናል።

እግዚአብሔርን ማዋረድ

አምላክ “ያከበሩኝን አከብራለሁ” ይላል። (1 ሳሙኤል 2:30) ማንንም ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከል እርሱን ማክበር ነውን? ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደሚለው ማርያምን “የእግዚአብሔር እናት” ወይም “በፈጣሪና በፍጡራን መካከል መካከለኛ የሆነች አማላጅ” ብሎ መጥራት አምላክን ማክበር ነውን? እንደነዚህ ያሉት አስተሳሰቦች ሁሉን ለሚችለው አምላክ እንደ ስድብ የሚቆጠሩ ናቸው። ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር የሚተካከል ማንም የለም። ኢየሱስ እግዚአብሔር ስላልነበረ እግዚአብሔር ሥጋዊ እናት የለችውም። እግዚአብሔር “በሰዎችና በእግዚአብሔር ዘንድ መካከለኛ” እንዲሆን የሾመው ኢየሱስን ብቻ ስለሆነ “የጭንቅ አማላጅ” የምትባል የለችም።—1 ጢሞቴዎስ 2:5፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ሰዎች ስለ ትክክለኛው የአምላክ ደረጃ ያላቸውን ግንዛቤ እንዳዘበራረቀባቸውና እንደበረዘባቸው አያጠራጥርም። ሰዎች የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ የሆነውን ይሖዋ አምላክን በትክክል እንዳያውቁና እርሱ በሚፈልገው መንገድ እንዳያመልኩት አድርጓቸዋል። የሃይማኖት ትምህርት ምሁር የሆኑት ሃንስ ኩንግ እንዳሉት “አምላክ አንድና ብቸኛ መሆኑን የሚበርዝና ዋጋ የሚያሳጣ ሐሳብ መጨመር ለምን አስፈላጊ ሆነ?” የሥላሴ ትምህርት አምላክ አንድና ብቸኛ መሆኑን ዋጋ ቢስ አድርጓል።

በሥላሴ የሚያምኑ ሁሉ ‘እግዚአብሔርን በትክክል አላወቁትም።’ (ሮሜ 1:28 አዓት ) በተጨማሪም ይህ ጥቅስ “እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” ይላል። ከ29 እስከ 31 ባሉት ቁጥሮች ላይ ከእነዚህ ‘የማይገቡ ሥራዎች’ መካከል ‘ነፍሰ ገዳይነት፣ ጥል፣ አታላይነት፣ ውል አፍራሽነት፣ የተፈጥሮ ፍቅር ማጣት፣ ምህረት የለሽነት’ ተመዝግበው ይገኛሉ። የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የሚቀበሉ ሃይማኖቶች በሙሉ እነዚህን ነገሮች ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

ለምሳሌ የሥላሴ አማኞች በሥላሴ የማያምኑ ሰዎችን አሳድደዋል፣ ገድለዋል። በዚህ ብቻም አላቆሙም። የሥላሴ አማኞችንም በጦርነት ጊዜያት ገድለዋል። ካቶሊኮች ካቶሊኮችን፣ ኦርቶዶክሶች ኦርቶዶክሶችን፣ ፕሮቴስታንቶች ፕሮቴስታንቶችን ሁሉም በሚያመልኩት ሥላሴያዊ አምላክ ስም ከመግደላቸው የበለጠ ምን ‘የማይገባ’ ነገር ሊኖር ይችላል?

ኢየሱስ ግን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) የአምላክ ቃል ይህን ሲያብራራ እንደሚከተለው ይላል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፣ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውን የማይወዱ ሁሉ “ከክፉው [ከሰይጣን] እንደነበረ ወንድሙንም እንደገደለ እንደ ቃየል” እንደሆኑ ይናገራል።—1 ዮሐንስ 3:10–12

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መሠረተ ትምህርቶችን ስለ አምላክ ማስተማር ሕጎቹን የሚጻረሩ ድርጊቶችን ወደ መፈጸም መርቷል። በእርግጥም በመላው የሕዝበ ክርስትና ዓለም ውስጥ የተፈጸመው ነገር የዴንማርኩ ሃይማኖታዊ ምሁር ዞረን ኪርከጋርድ እንደገለጹት ነው። “ሕዝበ ክርስትና ሳታውቀው ፈጽማ ከክርስትና ርቃለች።”

የሕዝበ ክርስትና መንፈሳዊ ሁኔታ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጻፈው ጋር ይስማማል:- “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጐ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለሆኑ በሥራቸው ይክዱታል።”—ቲቶ 1:16

በቅርቡ አምላክ ይህንን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ የሥላሴ አማኝ የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ላደረገቻቸው ነገሮች በሙሉ ለፍርድ ትቀርባለች። አምላክን በማዋረድ ለፈጸመቻቸው ድርጊቶችና ላስተማረቻቸው መሠረተ ትምህርቶች የቅጣት ፍርዷን ትቀበላለች። — ማቴዎስ 24:14, 34፤ 25:31–34, 41, 46፤ ራእይ 17:1–6, 16፤ 18:1–8, 20, 24፤ 19:17–21

የሥላሴን ትምህርት አትቀበል

የአምላክን እውነት በሚመለከት ልዝብ አቋም መያዝ አይቻልም። ስለዚህ አምላክን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለክ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አለመቀበልን ይጨምራል። የሥላሴ ትምህርት ነቢያት፣ ኢየሱስ፣ ሐዋርያትና የጥንት ክርስቲያኖች ካመኑትና ካስተማሩት ጋር የሚጋጭ ነው። በዚህም ምክንያት “አምላክ እኔ ብቻ እንደሆንሁና እኔንም የሚመስል ሌላ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ” ሲል ይመክረናል።—ኢሳይያስ 46:9 የ1980 ትርጉም

አምላክን እርስ በርሱ በሚጋጭና ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ለመግለጽ መሞከር የአምላክን ዓላማ አያራምድም። እንዲያውም ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ያላቸው ግንዛቤ ይበልጥ በተዘበራረቀ መጠን የአምላክ ጠላትና ‘የዚህ ዓለም አምላክ’ የሆነውን የሰይጣን ዲያብሎስን ዓላማ በይበልጥ ያራምዳል። ‘የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ ለማሳወር’ ሲል ይህን የመሰለውን የሐሰት መሠረተ ትምህርት የሚያስፋፋው ሰይጣን ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) በተጨማሪም የሥላሴ መሠረተ ትምህርት የቀሳውስትን ፍላጎት የሚያራምድ ነው። ምክንያቱም ይህን መሠረተ ትምህርት ለመረዳት የሚችሉት ቀሳውስት ብቻ እንደሆኑ ስለሚያስመስል ተከታዮቻቸው ከእጃቸው እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል።—ዮሐንስ 8:44ን ተመልከት።

ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ከፍተኛ እፎይታ ያስገኛል። ከአምላክ ቃል ጋር ከሚጋጩ ትምህርቶችና ወደ ክህደት ካዘነበሉ ድርጅቶች ነፃ ያወጣናል። ኢየሱስ እንዳለው “እውነትን ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:32

ሁሉን የሚችለውን አምላክ ከሁሉ የበላይ በማድረግና እርሱ በሚፈልገው መንገድ በማምለክ ብናከብረው በቅርቡ በከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ላይ ከሚመጣው ፍርድ ለመዳን እንችላለን። ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት በተስፋ ልንጠባበቅ እንችላለን። “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:17 (የ1980 ትርጉም)

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ የብዙ መቶ ዓመታት ዕድሜ ያለው በፈረንሳይ አገር የሚገኝ ቅርጽ ሥላሴዎች “ለድንግል” ማርያም ሥርዓተ ንግሥና ሲፈጽሙ ያሳያል። የሥላሴ እምነት ማርያም “ወላዲተ አምላክ” ተብላ የቅድስና ደረጃ እንዲሰጣት አድርጓል