ሣጥን 10ሐ
ተመልሰን በእግራችን እንድንቆም የሚያስችል እርዳታ
በሕዝቅኤል 37:1-14 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው አስደናቂ ራእይ ላይ ስናሰላስል በግል ሕይወታችን ሊጠቅመን የሚችል ግሩም ትምህርት እናገኛለን። ይህ ትምህርት ምንድን ነው?
አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን ችግሮችና ፈተናዎች ምክንያት ፈጽሞ እንደደከምንና ኃይላችን እንደተሟጠጠ ሊሰማን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ስሜት በሚሰማን ጊዜ ሕዝቅኤል በተመለከተው አስደናቂ ራእይ ላይ ማሰላሰላችን ብርታት ሊሰጠን ይችላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በደረቁ አጥንቶች ላይ ሕይወት ለመዝራት የሚያስችል ኃይል ያለው አምላክ፣ በሰው አመለካከት ፈጽሞ የማይቻሉ መስለው የሚታዩትን ጨምሮ የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች በሙሉ ማሸነፍ የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን ከዚህ ራእይ እንማራለን።—መዝሙር 18:29ን አንብብ፤ ፊልጵ. 4:13
ሕዝቅኤል ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የኖረው ነቢዩ ሙሴ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ለመርዳት የሚያስችል ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም እንዳለው ተናግሮ ነበር። ሙሴ “አምላክ ከጥንት ጀምሮ መሸሸጊያ ነው፤ ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው” ሲል ጽፏል። (ዘዳ. 33:27) በእርግጥም አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እርዳታ ለማግኘት አምላክን የምንጠይቀው ከሆነ በክንዶቹ አንስቶ በእግራችን እንደሚያቆመን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሕዝ. 37:10