በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር መቀራረብ
ትምህርት 7
በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር መቀራረብ
አዘውትሮ መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (1)
መጸለይ የሚገባን ለማንና እንዴት ነው? (2, 3)
ልንጸልይባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? (4)
መጸለይ የሚገባህ መቼ ነው? (5, 6)
አምላክ ሁሉንም ጸሎቶች ይሰማልን? (7)
1. ጸሎት ማለት አምላክን በትህትና ማነጋገር ነው። አዘውትረህ ወደ አምላክ መጸለይ ይገባሃል። አዘውትረህ ከጸለይህ አምላክ ልክ እንደምትወደው ጓደኛህ ቅርብህ እንደሆነ ይሰማሃል። ይሖዋ በጣም ታላቅና ለኃይሉም ዳርቻ የሌለው ቢሆንም ጸሎታችንን ይሰማል! አዘውትረህ ወደ አምላክ ትጸልያለህን?—መዝሙር 65:2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17
2. ጸሎት የአምልኮታችን ክፍል ነው። ስለዚህ መጸለይ የሚገባን ወደ ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የጸለየው ወደ አባቱ ብቻ ነበር፤ ወደ ሌላ ወደ ማቴዎስ 4:10፤ 6:9) ይሁን እንጂ ጸሎታችን በሙሉ መቅረብ የሚኖርበት በኢየሱስ ስም ነው። ይህም የኢየሱስን ሥልጣንና ደረጃ እንደምናከብር፣ እንዲሁም በቤዛዊ መሥዋዕቱ እምነት እንዳለን ያሳያል።—ዮሐንስ 14:6፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
ማንም አልጸለየም። እኛም እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል። (3. በምንጸልይበት ጊዜ ልባችን ውስጥ ያለውን ለአምላክ መናገር ይኖርብናል። ከጸሎት መጽሐፍ እያነበብን ወይም በቃል ያጠናነውን እየደገምን መጸለይ የለብንም። (ማቴዎስ 6:7, 8) አክብሮት በሚያሳይ ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ፣ በማንኛውም ጊዜና በማንኛውም ቦታ መጸለይ እንችላለን። አምላክ ድምፅ ሳናሰማ በልባችን የጸለይነውን እንኳን መስማት ይችላል። (1 ሳሙኤል 1:12, 13) የግል ጸሎታችንን ለማቅረብ ከሰዎች ገለል ያለ ፀጥታ የሰፈነበት ቦታ ብናገኝ ጥሩ ነው።—ማርቆስ 1:35
4. ስለ ምን ጉዳዮች መጸለይ እንችላለን? ከአምላክ ጋር ያለህን ወዳጅነት ስለሚነካ ማንኛውም ጉዳይ መጸለይ ትችላለህ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ስለ ይሖዋ ስምና ዓላማ መጸለይ እንደሚገባን የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ያመለክታል። በተጨማሪም የሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች እንዲሟሉልን፣ ኃጢአቶቻችን እንዲሠረዩልንና ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠን መጸለይ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:9-13) ጸሎቶቻችን በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረቱ መሆን የለባቸውም። መጸለይ የሚገባን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ስለሚስማሙ ነገሮች ብቻ መሆን ይኖርበታል።—1 ዮሐንስ 5:14
5. አምላክን ለማመስገን ወይም ለማወደስ ልብህ በሚገፋፋህ ማንኛውም ጊዜ ልትጸልይ ትችላለህ። (1 ዜና መዋዕል 29:10-13) ችግር ሲያጋጥምህና እምነትህ ሲፈተን መጸለይ ይገባሃል። (መዝሙር 55:22፤ 120:1) ምግብ ከመብላትህ በፊትም ብትጸልይ ተገቢ ይሆናል። (ማቴዎስ 14:19) ይሖዋ ‘ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ’ እንድንጸልይ ይጋብዘናል።—ኤፌሶን 6:18 አዓት
6. በተለይ ከባድ ኃጢአት ከሠራን መጸለይ ያስፈልገናል። እንዲህ ባለው ጊዜ ይሖዋ ምሕረትና ይቅርታ እንዲያደርግልን አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል። ኃጢአታችንን ለአምላክ ብንናዘዝና ያንን ኃጢአት ደግመን ላለመሥራት የተቻለንን ሁሉ ብናደርግ አምላክ እኛን “ይቅር ለማለት ዝግጁ” ነው።—መዝሙር 86:5 አዓት፤ ምሳሌ 28:13
7. ይሖዋ የሚሰማው የጻድቅ ሰዎችን ጸሎት ብቻ ነው። ጸሎቶችህ በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እንዲያገኙ ከፈለግህ የአምላክን ሕግጋት ጠብቀህ ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። (ምሳሌ 15:29፤ 28:9) በምትጸልይበት ጊዜ ትሁት መሆን ይገባሃል። (ሉቃስ 18:9-14) በተጨማሪም ከምትጸልይለት ነገር ጋር የሚስማማ ጥረት ማድረግ ያስፈልግሃል። እንዲህ ስታደርግ በእርግጥ እምነት እንዳለህና የምትጸልየውን ነገር ከልብ እንደምትፈልግ ታሳያለህ። ይሖዋ ለጸሎትህ ምላሽ የሚሰጠው እንዲህ ስታደርግ ብቻ ነው።—ዕብራውያን 11:6