አምላክ የማይደሰትባቸው እምነቶችና ልማዶች
ትምህርት 11
አምላክ የማይደሰትባቸው እምነቶችና ልማዶች
ስህተት የሆኑ እምነቶችና ልማዶች የትኞቹ ናቸው? (1)
ክርስቲያኖች አምላክ ሥላሴ ነው ብለው ማመን ይገባቸዋልን? (2)
እውነተኛ ክርስቲያኖች ገናን፣ በዓለ ትንሣኤን ወይም የልደት ቀን የማያከብሩት ለምንድን ነው? (3, 4)
ሙታን ሕያዋንን ሊጎዱ ይችላሉን? (5)
ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነበርን? (6)
አምላክን ማስደሰት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (7)
1. ሁሉም ዓይነት እምነቶችና ልማዶች መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ አምላክ ከሐሰት ሃይማኖት የመጡትን ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የሚቃረኑትን እምነቶችና ልማዶች አይደግፍም።—ማቴዎስ 15:6
2. ሥላሴ:- ይሖዋ ሦስትም አንድም ማለትም ሥላሴ ነውን? አይደለም! “እውነተኛ አምላክ” ይሖዋ ማለትም አብ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 17:3፤ ማርቆስ 12:29) ኢየሱስ የይሖዋ የበኩር ልጅ ሲሆን የአምላክ ተገዥ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) አብ ከወልድ ይበልጣል። (ዮሐንስ 14:28) መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል እንጂ የራሱ ሕልውና ያለው አካል አይደለም።—ዘፍጥረት 1:2፤ ሥራ 2:18
3. ገና እና በዓለ ትንሣኤ:- ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 29 ቀን አይደለም። የተወለደው እረኞች መንጎቻቸውን በሌሊት ውጭ ሊያሰማሩ በሚችሉበት ወቅት፣ ጥቅምት 1 አካባቢ ነው። (ሉቃስ 2:8-12) ኢየሱስ ክርስቲያኖች ልደቱን እንዲያከብሩ አላዘዘም። ይልቁን ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ሞቱን እንዲያስቡ ወይም እንዲያስታውሱ ነበር። (ሉቃስ 22:19, 20) ገናና በዚህ በዓል ላይ የሚፈጸሙት ልማዶች የመጡት ከጥንት የሐሰት ሃይማኖቶች ነው። በአንዳንድ አገሮች እንደሚደረገው ለበዓሉ አከባበር ዕንቁላልና ጥንቸል መጠቀምን የመሳሰሉ በበዓለ ትንሣኤ ላይ የሚፈጸሙ ልማዶችም ቢሆኑ ከዚህ የተለዩ አይደሉም። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ገናንም ሆነ በዓለ ትንሣኤን አላከበሩም። በዘመናችን ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም አያከብሩም።
4. የልደት ቀን:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የምናገኛቸው የልደት በዓሎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነዚህም በዓሎች የተከበሩት ይሖዋን በማያመልኩ ሰዎች ነው። (ዘፍጥረት 40:20-22፤ ማርቆስ 6:21, 22, 24-27) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የልደት ቀኖቻቸውን አላከበሩም። የልደት ቀን የማክበር ልማድ የመጣው ከጥንት የሐሰት ሃይማኖቶች ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ቀን ስጦታ ይሰጣጣሉ፤ አብረውም ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ይደሰታሉ።
5. ሙታንን መፍራት:- ሙታን ምንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም፣ አንዳችም ነገር ሊሰማቸው አይችልም። እኛ ልንረዳቸው ወይም እነርሱ ሊጎዱን አይችሉም። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10) ነፍስ ከሞት በኋላ በሕይወት አትኖርም፣ ትሞታለች። (ሕዝቅኤል 18:4) ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ አጋንንት ተብለው የሚጠሩ ክፉ መላእክት የሙታን መናፍስት መስለው ይገለጣሉ። ሙታንን ከመፍራት ወይም እነርሱን ከማምለክ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም ዓይነት ልማድ ስህተት ነው።—ኢሳይያስ 8:19
6. መስቀል:- ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ አይደለም። ኢየሱስ የሞተው አንድ ወጥ በሆነ እንጨት ወይም ምሰሶ ላይ ነው። በብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች “መስቀል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ወጥ የሆነ እንጨት የሚያመለክት ቃል ነው። የመስቀል ምልክት የመጣው ከጥንት የሐሰት ሃይማኖቶች ነው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በመስቀል አይጠቀሙም ወይም አያመልኩም ነበር። ታዲያ መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም ትክክል ይመስልሃልን?—ዘዳግም 7:26፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14
7. እነዚህን ልማዶችና እምነቶች እርግፍ አድርጎ መተው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ዘመዶችና ወዳጆችህ እምነትህን እንዳትለውጥ ሊያሳምኑህ ይሞክሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ሰዎችን ማስደሰት ሳይሆን አምላክን ማስደሰት ነው።—ምሳሌ 29:25፤ ማቴዎስ 10:36, 37
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ሥላሴ አይደለም
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገና እና በዓለ ትንሣኤ ከጥንት የሐሰት ሃይማኖቶች የመጡ ልማዶች ናቸው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙታንን የምናመልክበት ወይም እነርሱን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም