በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው አምላክ ማን ነው?

እውነተኛው አምላክ ማን ነው?

ትምህርት 2

እውነተኛው አምላክ ማን ነው?

እውነተኛው አምላክ ማን ነው? ስሙስ? (1, 2)

ምን ዓይነት አካል አለው? (3)

ዋና ዋና ባሕርያቱ ምንድን ናቸው? (4)

እርሱን ስናመልክ በምስሎችና ሥዕሎች መጠቀም ይገባናልን? (5)

ስለ አምላክ ልንማር የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች ምንድን ናቸው? (6)

1. ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ያመልካሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን ይነግረናል። በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው እርሱ ነው። ሕይወት ያገኘነው ከእርሱ ስለሆነ ማምለክ የሚገባን እርሱን ብቻ ነው።—1 ቆሮንቶስ 8:5, 6፤ ራእይ 4:11

2. አምላክ የተለያዩ የማዕረግ ስሞች ቢኖሩትም መጠሪያ ስሙ ግን አንድ ብቻ ነው። ስሙ ይሖዋ ነው። የአምላክ ስም ከብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች እንዲወጣ ተደርጎ ጌታ እና አምላክ በሚሉት የማዕረግ ስሞች ተተክቷል። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ጊዜ ግን ይሖዋ የሚለው ስም በመጽሐፉ ውስጥ ወደ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኝ ነበር!—ዘጸአት 6:31879 ትርጉም፤ መዝሙር 83:18 አዓት

3. ይሖዋ አካል አለው። የእርሱ አካል ግን እኛ ካለን አካል የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ይላል። (ዮሐንስ 4:24) መንፈስ እኛ ካለን ሕይወት እጅግ የላቀ የሕይወት ዓይነት ነው። አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም። ይሖዋ የሚኖረው በሰማይ ቢሆንም ሁሉንም ነገሮች ማየት ይችላል። (መዝሙር 11:4, 5፤ ዮሐንስ 1:18) መንፈስ ቅዱስስ ምንድን ነው? እንደ አምላክ የራሱ ሕልውና ያለው የተለየ አካል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።—መዝሙር 104:30

4. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ባሕርያት ይገልጽልናል። ዋና ዋና ባሕርያቱ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል እንደሆኑ ያስረዳል። (ዘዳግም 32:4፤ ኢዮብ 12:13፤ ኢሳይያስ 40:26፤ 1 ዮሐንስ 4:8) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ መሐሪ፣ ደግ፣ ይቅር ባይ፣ ለጋስና ታጋሽ እንደሆነ ይነግረናል። እኛም ታዛዥ እንደሆኑ ልጆች እርሱን ለመምሰል መጣር ይገባናል።—ኤፌሶን 5:1, 2

5. በአምልኮታችን ለምስሎች፣ ለሥዕሎችና ለምልክቶች መስገድ ወይም መጸለይ ይገባናልን? በፍጹም አይገባንም! (ዘጸአት 20:4, 5) ይሖዋ እርሱን ብቻ ማምለክ እንዳለብን ተናግሯል። ክብሩን ለማንም ወይም ለምንም ነገር አያካፍልም። ምስሎች እኛን ለመርዳት የሚያስችል ኃይል የላቸውም።—መዝሙር 115:4-8፤ ኢሳይያስ 42:8

6. አምላክን ይበልጥ ለማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ የፈጠራቸውን ነገሮች በመመልከትና እነዚህ ፍጥረታት ስለሚነግሩን ነገሮች በጥልቀት በማሰብ ነው። የአምላክ ፍጥረታት እርሱ ታላቅ ኃይልና ጥበብ እንዳለው ይነግሩናል። በፈጠራቸው ነገሮች በሙሉ የእርሱን ፍቅር መግለጫዎች ማየት እንችላለን። (መዝሙር 19:1-6፤ ሮሜ 1:20) ስለ አምላክ ልንማር የምንችልበት ሌላው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሱ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ይነግረናል። በተጨማሪም ዓላማዎቹ ምን እንደሆኑና ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግብን ይነግረናል።—አሞጽ 3:7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከፍጥረትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ እንማራለን