የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
ትምህርት 6
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
የአምላክ መንግሥት የሚገኘው የት ነው? (1)
የዚህ መንግሥት ንጉሥ ማን ነው? (2)
ከንጉሡ ጋር አብረው የሚገዙ ሌሎች ይኖራሉን? ካሉስ ስንት ናቸው? (3)
በመጨረሻው ቀን እንደምንኖር የሚያሳየው ምንድን ነው? (4)
የአምላክ መንግሥት ወደፊት ለሰው ልጆች ምን ያደርጋል? (5-7)
1. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ አስተምሮ ነበር። መንግሥት በአንድ ንጉሥ የበላይነት የሚተዳደር መስተዳድር ነው። የአምላክ መንግሥት ልዩ ዓይነት መስተዳድር ነው። የተቋቋመው በሰማይ ሲሆን ምድርን ያስተዳድራል። የአምላክንም ስም ይቀድሳል ወይም የስሙን ቅድስና ያረጋግጣል። የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ በምድርም ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:9, 10
2. ኢየሱስ የመንግሥቱ ንጉሥ እንደሚሆን አምላክ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 1:30-33) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደግ፣ ትክክለኛና ፍጹም ገዥ ለመሆን የሚችል መሆኑን አስመስክሯል። ወደ ሰማይ እንደተመለሰ ወዲያው የእግዚአብሔር መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ዙፋን ላይ አልተቀመጠም። (ዕብራውያን 10:12, 13) በ1914 ይሖዋ ለኢየሱስ ቃል ገብቶለት የነበረውን ሥልጣን ሰጠው። ከዚያ ወዲህ ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ ሆኖ በሰማይ በመግዛት ላይ ይገኛል።—ዳንኤል 7:13, 14
3. በተጨማሪም ይሖዋ ወደ ሰማይ የሚሄዱ የተወሰኑ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች መርጧል። እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት፣ ዳኞችና ካህናት ሆነው የሰው ልጆችን ያስተዳድራሉ። (ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 5:9, 10) ኢየሱስ እነዚህን የመንግሥቱ ተባባሪ ገዥዎች “ታናሽ መንጋ” ሲል ጠርቷል። ቁጥራቸው 144,000 ነው።—ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 14:1-3
4. ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ ወዲያውኑ ሰይጣንንና ክፉ መላእክቱን ከሰማይ ወደ ምድር አካባቢ ወርውሯል። ከ1914 ወዲህ የምድር ሁኔታ በጣም የተበላሸው በዚህ ምክንያት ነው። (ራእይ 12:9, 12) ጦርነት፣ ረሀብ፣ ቸነፈር፣ የሕገ ወጥነት መስፋፋት፣ እነዚህ ሁሉ ኢየሱስ በመግዛት ላይ እንዳለና ይህ ሥርዓት በመጨረሻ ቀን ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ከሚያመለክቱት ‘የምልክቱ’ ክፍሎች ጥቂቶቹ ናቸው።—ማቴዎስ 24:3, 7, 8, 12፤ ሉቃስ 21:10, 11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
5. ኢየሱስ በቅርቡ እረኛ በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ የሰው ልጆችን በመለየት ይፈርዳል። ‘በጎቹ’ የአምላክ ታማኝ ተገዥዎች መሆናቸውን ያስመሰከሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ‘ፍየሎቹ’ ደግሞ የአምላክን መንግሥት አንቀበልም ያሉ ሰዎች ናቸው። (ማቴዎስ 25:31-34, 46) ኢየሱስ በቅርቡ ፍየል መሰል ሰዎችን ጠራርጎ ያጠፋል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ከኢየሱስ “በጎች” መካከል ለመሆን ከፈለግህ የመንግሥቱን መልእክት ማዳመጥና የተማርካቸውን ነገሮች ሥራ ላይ ማዋል ይኖርብሃል።—ማቴዎስ 24:14
6. በአሁኑ ጊዜ ምድር በብዙ አገሮች ተከፋፍላለች። እያንዳንዱ አገር የራሱ መስተዳድር አለው። እነዚህ ብሔራት ብዙ ጊዜ እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር መንግሥት እነዚህን ሰብዓዊ መስተዳድሮች በሙሉ አስወግዶ ቦታቸውን ይወስዳል። በመላው ምድር ላይ ብቸኛው መስተዳድር የአምላክ መንግሥት ብቻ ይሆናል። (ዳንኤል 2:44) በዚያ ጊዜ ጦርነት፣ ወንጀልና ዓመፅ አይኖርም። ሰዎች ሁሉ በሰላምና በአንድነት አብረው ይኖራሉ።—ሚክያስ 4:3, 4
7. በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ፍጽምና ያገኛሉ። ምድር በሞላ ገነት ትሆናለች። ኢየሱስ በሺህ ዓመቱ ፍጻሜ ላይ አምላክ እንዲያከናውን ያዘዘውን ሁሉ አከናውኖ ይጨርሳል። ከዚያ በኋላ መንግሥቱን ለአባቱ ያስረክባል። (1 ቆሮንቶስ 15:24) የአምላክ መንግሥት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ለምን ለጓደኞችህና ለምትወዳቸው ሰዎች አትናገርም?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ አስተዳደር ጥላቻ ወይም አድልዎ አይኖርም