የአምላክ አገልጋዮች ንጹሕ መሆን አለባቸው
ትምህርት 9
የአምላክ አገልጋዮች ንጹሕ መሆን አለባቸው
በሁሉም መንገድ ንጹሕ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው? (1)
በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን ምን ማለት ነው? (2) በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆንስ? (3) በአእምሮስ? (4) በአካልስ? (5)
ልናስወግዳቸው የሚገቡ ንጹሕ ያልሆኑ አነጋገሮች የትኞቹ ናቸው? (6)
1. ይሖዋ አምላክ ንጹሕና ቅዱስ ነው። አምላኪዎቹም በመንፈሳዊ፣ በሥነ ምግባር፣ በአእምሮና በአካል ንጹሕ ሆነው እንዲኖሩ ይፈልጋል። (1 ጴጥሮስ 1:16) በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆኖ መኖር ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። የምንኖረው በቆሸሸ ዓለም ውስጥ ነው። በተጨማሪም ስህተት እንድንሠራ ከሚገፋፋን ከራሳችን ዝንባሌ ጋር እንታገላለን። ቢሆንም መታከትና ጥረታችንን ማቋረጥ የለብንም።
2. መንፈሳዊ ንጽሕና:- ይሖዋን ለማገልገል ከፈለግን የትኛውንም የሐሰት ሃይማኖት ትምህርት ወይም ድርጊት የሙጥኝ ብለን ለመያዝ አንችልም። ከሐሰት ሃይማኖት መውጣትና የሐሰት ሃይማኖትን በማንኛውም መንገድ ከመደገፍ መራቅ ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 6:14-18፤ ራእይ 18:4) ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውነት ካወቅን በኋላ ሐሰት በሚያስተምሩ ሰዎች ተታልለን እንዳንወሰድ መጠንቀቅ አለብን።—2 ዮሐንስ 10, 11
3. የሥነ ምግባር ንጽሕና:- ይሖዋ አምላኪዎቹ በማንኛውም ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጠባይ እንዲያሳዩ ይፈልጋል። 1 ጴጥሮስ 2:12) የምናደርገውን ነገር ሁሉ፣ ሰው ሳያየን በምሥጢር የምናደርገውን ነገር እንኳን ሳይቀር ይመለከታል። (ዕብራውያን 4:13) ወሲባዊ ብልግናና ሌሎቹን በዚህ ዓለም የተለመዱ ርኩስ ድርጊቶች ከመፈጸም መራቅ ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
(4. የአእምሮ ንጽሕና:- አእምሮአችንን ንጹሕ በሆኑ ሐሳቦች ከሞላን ጠባያችንም ንጹሕ ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 4:8) ንጹሕ ያልሆኑ ነገሮችን ካሰላሰልን ግን ክፉ የሆኑ ድርጊቶች እንፈጽማለን። (ማቴዎስ 15:18-20) አእምሮአችንን ሊያሳድፍ ከሚችል ማንኛውም ዓይነት መዝናኛ መራቅ ይኖርብናል። የአምላክን ቃል በማጥናት አእምሮአችንን ንጹሕ በሆኑ ሐሳቦች ለመሙላት እንችላለን።
5. አካላዊ ንጽሕና:- ክርስቲያኖች አምላክን የሚወክሉ በመሆናቸው ገላቸውንና ልብሳቸውን በንጽሕና መያዝ አለባቸው። መጸዳጃ ቤት ከገባን በኋላ፣ እንዲሁም ምግብ ከመብላታችን ወይም ከመንካታችን በፊት እጃችንን መታጠብ ይኖርብናል። ተስማሚ የሆነ ቆሻሻ ማስወገጃ ከሌላችሁ የመጸዳጃ ቤት ቆሻሻዎችን መቅበር ያስፈልጋል። (ዘዳግም 23:12, 13) አካላዊ ንጽሕና መጠበቅ ለጥሩ ጤንነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የአንድ ክርስቲያን ቤት ውጪውም ሆነ ውስጡ ንጹሕ መሆን ይኖርበታል። በአካባቢው ኅብረተሰብ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ የሚታይ መሆን ይገባዋል።
6. ንጹሕ ንግግር:- የአምላክ አገልጋዮች ሁልጊዜ እውነቱን መናገር አለባቸው። ውሸታሞች ወደ አምላክ መንግሥት አይገቡም። (ኤፌሶን 4:25፤ ራእይ 21:8) ክርስቲያኖች ጸያፍ የሆኑ ቃላት አይጠቀሙም። የብልግና ቀልዶች ወይም ወሬዎች አይናገሩም ወይም አያዳምጡም። በንጹሕ ንግግራቸው ምክንያት በሥራ ቦታቸው፣ በትምህርት ቤታቸውና በመኖሪያ አካባቢያቸው ልዩ ሆነው ይታያሉ።—ኤፌሶን 4:29, 31፤ 5:3
[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ አገልጋዮች በሁሉም ረገድ ንጹሕ መሆን አለባቸው