በሰንበት ቀን እሸት መቅጠፍ
ምዕራፍ 31
በሰንበት ቀን እሸት መቅጠፍ
ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ገሊላ ለመመለስ ከኢየሩሳሌም ተነሱ። ጊዜው የጸደይ ወቅት ስለነበረ በማሳዎቹ ላይ ያለው አዝመራ አሽቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ተርበው ነበር። ስለዚህ እሸቱን ቀጥፈው በሉ። ሆኖም ቀኑ ሰንበት ስለነበር ድርጊታቸው በቸልታ አልታለፈም።
ከጥቂት ጊዜ በፊት በኢየሩሳሌም የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች የሰንበትን ሕግ ጥሰሃል ብለው ኢየሱስን ሊገድሉት ፈልገው ነበር። አሁን ፈሪሳውያን ክስ አቀረቡ። “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ” ብለው ከሰሱ።
ፈሪሳውያን እሸት መቅጠፍና በእጅ አሽቶ መብላት ከማጨድና ከመውቃት ተለይቶ አይታይም ይሉ ነበር። ለሥራ የሚሰጡት የማያፈናፍን ፍቺ የሰንበትን ሕግ ሸክም አድርጎት ነበር፤ ሆኖም የሰንበት ሕግ የተቋቋመው የሚያስደስትና በመንፈሳዊ የሚገነባ ጊዜ እንዲሆን ታስቦ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ይሖዋ አምላክ የሰንበትን ሕግ ያወጣው ይህን በመሰለ ከልክ በላይ ጥብቅ በሆነ መንገድ እንዲሠራበት ብሎ እንዳልሆነ ለማስረዳት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች በመጥቀስ ሐሳባቸውን ተቃወመ።
ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ወደ ማደሪያው ድንኳን ገብተው የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደበሉ ኢየሱስ ገለጸ። ኅብስቱ ከይሖዋ ፊት ተነስቶ በሌላ ትኩስ ኅብስት ተተክቶ የነበረ ሲሆን በደንቡ መሠረት የሚበሉት ካህናቱ ነበሩ። ሆኖም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ኅብስቱን መብላታቸው አላስወቀሳቸውም።
ኢየሱስ ሌላ ምሳሌ በማቅረብ እንዲህ አለ:- “ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን?” አዎን፣ ካህናት በሰንበት ቀንም እንኳ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የእንስሳት መሥዋዕቶችን ለማዘጋጀት እንስሳትን ያርዱ ነበር፤ ሌሎች ሥራዎችንም ያከናውኑ ነበር! ኢየሱስ “ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” አላቸው።
ኢየሱስ በመቀጠል ፈሪሳውያንን እንዲህ ሲል ገሠጻቸው:- “ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር።” ከዚያም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና” ሲል ደመደመ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ ሰላማዊውን የሺህ ዓመት ንጉሣዊ አገዛዙን ማመልከቱ ነበር።
የሰው ዘር የኃይል አድራጎትና ጦርነት እጅግ በተስፋፋበትና አድካሚ በሆነው የሰይጣን ዲያብሎስ የባርነት አገዛዝ ላለፉት 6,000 ዓመታት ሲማቅቅ ኖሯል። በሌላ በኩል ግን የክርስቶስ ታላቁ የሰንበት አገዛዝ የሰው ልጅ አሁን ካለው መከራና ጭቆና የሚያርፍበት ጊዜ ይሆናል። ማቴዎስ 12:1-8፤ ዘሌዋውያን 24:5-9፤ 1 ሳሙኤል 21:1-6፤ ዘኍልቁ 28:9፤ ሆሴዕ 6:6
▪ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ምን ክስ ተሰንዝሮ ነበር? ኢየሱስ ለክሱ መልስ የሰጠው እንዴት ነው?
▪ ኢየሱስ ፈሪሳውያን ምን ጉድለት እንዳለባቸው ለይቶ አመልክቷል?
▪ ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ” የሆነው በምን መንገድ ነው?