አራት ደቀ መዛሙርት ተጠሩ
ምዕራፍ 22
አራት ደቀ መዛሙርት ተጠሩ
ኢየሱስ ባደገባት በናዝሬት ከተማ የግድያ ሙከራ ከተደረገበት በኋላ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሄደ። ይህም አንድ ሌላ የኢሳይያስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። ይህ ትንቢት በባሕሩ አቅራቢያ የሚኖሩ የገሊላ ሰዎች ታላቅ ብርሃን እንደሚያዩ የሚናገረው ትንቢት ነው።
ኢየሱስ በዚህች ከተማ ውስጥ ብርሃን የማብራት ሥራውን በማከናወን ላይ ሳለ አራቱን ደቀ መዛሙርቱን አገኛቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ቀደም ሲል አብረውት ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ከኢየሱስ ጋር ወደ ይሁዳ ተመልሰው ሲመጡ ወደ ቀድሞው ዓሣ የማጥመድ ሥራቸው ተመልሰው ነበር። ኢየሱስ እሱ ከሄደ በኋላ አገልግሎቱን እንዲያከናውኑ ሊያሰለጥናቸው የሚችል ሁልጊዜ አብረውት የሚሆኑ ቋሚ ረዳቶች የሚያስፈልጉት በመሆኑ አሁን ፈልጎ ያገኛቸው ይመስላል።
ስለዚህ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ እየሄደ ሳለ ስምዖን ጴጥሮስና ጓደኞቹ መረባቸውን ሲያጥቡ አየና ወደ እነሱ ሄደ። የጴጥሮስ ጀልባ ላይ ወጣና ከመሬቱ ራቅ እንዲያደርጋት ጠየቀው። ትንሽ ራቅ እንዳሉ ኢየሱስ ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ በባሕሩ ዳርቻ የተሰበሰበውን ሕዝብ ማስተማር ጀመረ።
ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ” አለው።
ጴጥሮስም መልሶ “አቤቱ፣ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።
መረቦቹን ሲጥሉ መረቦቹ በጣም ብዙ ዓሦች ከመያዛቸው የተነሳ መቀደድ ጀመሩ። ወዲያውኑ በአቅራቢያቸው በነበረች አንዲት ጀልባ ላይ ያሉት ጓደኞቻቸው መጥተው እንዲረዷቸው ምልክት ሰጧቸው። ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም ጀልባዎች በብዙ ዓሦች ስለተሞሉ መስመጥ ጀመሩ። ጴጥሮስ ይህን ሲመለከት ኢየሱስ ፊት ወድቆ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ” አለው።
ኢየሱስም መልሶ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው።
ኢየሱስ የጴጥሮስን ወንድም እንድርያስንም ጠራው። “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። አብረዋቸው ዓሣ ያጠምዱ የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ይኸው ጥሪ ቀረበላቸው፤ እነሱም ያለ ምንም ማመንታት ጥሪውን ተቀበሉ። ስለዚህ እነዚህ አራት ሰዎች ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው የመጀመሪያዎቹ አራት የኢየሱስ ቋሚ ተከታዮች ሆኑ። ሉቃስ 5:1-11፤ ማቴዎስ 4:13-22፤ ማርቆስ 1:16-20፤ ኢሳይያስ 9:1, 2
▪ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲከተሉት የጠራቸው ለምንድን ነው? እነርሱስ እነማን ናቸው?
▪ ጴጥሮስ የትኛውን ተአምር ሲመለከት ፍርሃት አድሮበታል?
▪ የሱስ ደቀ መዛሙርቱን የጠራው ምን ዓይነት የማጥመድ ሥራ እንዲያከናውኑ ነው?