ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ምክንያት
ምዕራፍ 24
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ምክንያት
ኢየሱስ በቅፍርናሆም ከአራቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ሆኖ ቀኑን ያሳለፈው በሥራ ተወጥሮ ነበር። ሥራውን ያበቃው የቅፍርናሆም ሰዎች ያመጡለትን የታመሙ ሰዎች በሙሉ በምሽት ከፈወሰ በኋላ ነበር። ብቻውን ሆኖ የሚያሳልፈው ምንም ጊዜ አላገኘም።
አሁን በሚቀጥለው ቀን ማለዳ ላይ ነው። ጨለማው ገና ሳይገፈፍ ኢየሱስ ብቻውን ወደ ውጪ ወጣ። በግል ለአባቱ መጸለይ ወደሚችልበት ጭር ያለ አካባቢ ሄደ። ሆኖም ጴጥሮስና ሌሎች የኢየሱስን አለመኖር ሲያዩ እሱን ፍለጋ ስለ ወጡ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ረዘም ያለ ጊዜ ሊያሳልፍ አልቻለም።
ኢየሱስን ሲያገኙት ጴጥሮስ “ሁሉ ይፈልጉሃል” አለው። የቅፍርናሆም ሰዎች ኢየሱስ እነሱ ጋር እንዲቆይ ፈልገው ነበር። ያደረገላቸውን ነገር ከልብ አድንቀዋል! ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ እንዲህ ዓይነት ተአምራዊ ፈውስ ለመፈጸም ነውን? ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን አለ?
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በሚለው መሠረት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና።” ሰዎቹ እነሱ ጋር እንዲቆይ ቢጎተጉቱትም “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” አላቸው።
አዎን፣ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ትልቁ ዓላማ የአባቱን ስም ቅድስና ስለሚያረጋግጠውና የሰዎችን ችግሮች ለዘለቄታው ስለሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ለመስበክ ነው። ይሁን እንጂ በአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያሳምን ማስረጃ ለማቅረብ ኢየሱስ ተአምራዊ ፈውስ ፈጽሟል። ሙሴም እንደዚሁ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የአምላክ አገልጋይ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ለማቅረብ ተአምራት ፈጽሟል።
አሁን ኢየሱስ በሌሎች ከተሞች ለመስበክ ቅፍርናሆምን ለቅቆ ሲሄድ አራቱ ደቀ መዛሙርት አብረውት ሄዱ። እነዚህ አራት ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ እንዲሁም ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ ናቸው። ከዚህ በፊት በነበረው ሳምንት ኢየሱስ ከእሱ ጋር እየተጓዙ የሚያገለግሉ የመጀመሪያዎቹ ተባባሪ ሠራተኞች እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቦላቸው እንደነበረ ታስታውሳለህ።
ኢየሱስ ከአራቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ በገሊላ ውስጥ ያደረገው የስብከት ጉዞ እጅግ የተሳካ ነበር! እንዲያውም ስላከናወናቸው ነገሮች የሚገልጸው ወሬ በሶርያ ሁሉ ተዳርሶ ነበር። ከገሊላ፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ተከተሏቸው። ማርቆስ 1:35-39፤ ሉቃስ 4:42, 43፤ ማቴዎስ 4:23-25፤ ዘጸአት 4:1-9, 30, 31
▪ ኢየሱስ በቅፍርናሆም ቀኑን ሙሉ በሥራ ተጠምዶ ካሳለፈ በኋላ በነጋታው ጠዋት ምን ሁኔታ ተፈጸመ?
▪ ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው ለምንድን ነው? የፈጸማቸው ተአምራትስ ለምን ዓላማ አገልግለዋል?
▪ ኢየሱስ በገሊላ እየተዘዋወረ ባከናወነው የስብከት ሥራ እነማን አብረውት ነበሩ? ኢየሱስ ያከናወናቸው ነገሮች ምን ምላሽ አግኝተዋል?