የሰው ልጅ ሲገለጥ
ምዕራፍ 93
የሰው ልጅ ሲገለጥ
ኢየሱስ ገና በስተ ሰሜን እያለ (በሰማርያ አለዚያም በገሊላ ሳለ ማለት ነው)፣ ፈሪሳውያን ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት ጠየቁት። የአምላክ መንግሥት በታላቅ ድምቀትና ሥነ ሥርዓት ይመጣል የሚል እምነት ነበራቸው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው:- “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ሰዎች በሚጠባበቁት ዐይነት አይደለም፤ እንዲሁም ‘እነሆ እዚህ ናት ወይም እዚያ ናት’ የምትባል አይደለችም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ስለሆነች ነው።”—የ1980 ትርጉም
“በመካከላችሁ” በማለት ኢየሱስ የተናገረው ቃል አንዳንድ ጊዜ “በውስጣችሁ” ተብሎ ተተርጉሟል። ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት በአምላክ አገልጋዮች ልብ ውስጥ እየገዛች ነው ማለቱ እንደሆነ አድርገው ተረድተውታል። ሆኖም የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ እያነጋገራቸው በነበሩት በእነዚህ የማያምኑ ፈሪሳውያን ልብ ውስጥ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ የተሾመው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ እዚያው አብሯቸው ስለነበረ የአምላክ መንግሥት በመካከላቸው ነበር።
ኢየሱስ ፈሪሳውያኑ ከሄዱ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፣ የመንግሥቱን መምጣት በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ ነገር ነገራቸው። በተለይ ወደፊት በመንግሥቱ ሥልጣን የሚገኝበትን ሁኔታ በአእምሮው በመያዝ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው:- “እነርሱም:- እነሆ በዚህ፣ ወይም:- እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ [እነዚህን ሐሰተኛ መሲሖች] አትከተሉአቸውም። መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲሁ ይሆናል።” ኢየሱስ መብረቅ ብልጭ ሲል በብዙ ቦታ እንደሚታይ ሁሉ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚያሳየው ማስረጃም ሊያዩት ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ግልጽ ሆኖ እንደሚታይ ማመልከቱ ነበር።
ከዚያም ኢየሱስ ወደፊት በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ የሰዎች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ሁኔታውን በጥንት ዘመን ከተፈጸሙ ክንውኖች ጋር አነጻጽሯል። እንዲህ ሲል ገለጸ:- “በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፣ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። . . . እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል።”
ኢየሱስ በኖኅና በሎጥ ዘመን የነበሩት ሰዎች የጠፉት እንደ መብላት፣ መጠጣት፣ መግዛት፣ መሸጥ፣ መትከልና ቤት መሥራት ያሉትን የተለመዱ እንቅስቃሴዎች በማከናወናቸው ነው ማለቱ አይደለም። እንዲያውም ኖኅና ሎጥ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው እነዚህን ነገሮች አድርገዋል። ሆኖም ሌሎቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ያከናውኑ የነበረው ለአምላክ ፈቃድ ምንም ዓይነት ትኩረት ሳይሰጡ ነበር፤ የጠፉትም በዚህ ምክንያት ነው። ክርስቶስ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ በሚመጣው ታላቅ መከራ ወቅት በሚገለጥበት ጊዜም ሰዎች የሚጠፉት በዚሁ ምክንያት ነው።
ኢየሱስ ወደፊት በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን ለሚያሳየው ማስረጃ አፋጣኝ ምላሽ የመስጠትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ በመግለጽ እንዲህ ሲል አክሎ ተናገረ:- “በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፣ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስቡአት።”
ክርስቶስ በሥልጣኑ መገኘቱን የሚያመለክተው ማስረጃ በሚታይበት ጊዜ ሰዎች ለቁሳዊ ንብረቶቻቸው ያላቸው ፍቅር ፈጣን እርምጃ ከመውሰድ እንዲያግዳቸው መፍቀድ የለባቸውም። የሎጥ ሚስት ከሰዶም ወጥታ እየሄደች በነበረችበት ጊዜ ወደ ኋላ ዞራ የተመለከተችው ትታቸው የመጣቻቸው ነገሮች አጓጉተዋት ሳይሆን አይቀርም። ስትዞር የጨው አምድ ሆና ቀረች።
ኢየሱስ ወደፊት በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ስለሚኖረው ሁኔታ የሚሰጠውን መግለጫ በመቀጠል ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው:- “በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች።”
እዚህ ላይ መወሰድ የሚለው አባባል ኖኅና ቤተሰቡ ወደ መርከብ ከገቡበትና መላእክት ሎጥና ቤተሰቡ ከሰዶም እንዲወጡ ካደረጉበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። መዳንን የሚያመለክት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሳይወሰዱ መቅረት መጥፋትን ያመለክታል።
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ነው?” ብለው ጠየቁት።
ኢየሱስ “ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች [“ንስሮች፣” NW] ይሰበሰባሉ” ሲል መለሰላቸው። እንዲድኑ ‘የተወሰዱት’ ሰዎች ልክ ከርቀት እንደሚመለከቱት ንስሮች ወደ ‘ሥጋው’ ይሰበሰባሉ። ሥጋው በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ በማይታይ ሁኔታ የሚገኘውን እውነተኛውን ክርስቶስና ይሖዋ የሚያዘጋጀውን መንፈሣዊ ግብዣ ያመለክታል። ሉቃስ 17:20-37፤ ዘፍጥረት 19:26
▪ መንግሥቱ በፈሪሳውያን መካከል የነበረው እንዴት ነው?
▪ የክርስቶስ መገኘት ከመብረቅ ጋር የተመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
▪ ክርስቶስ በሚገኝበት ወቅት ሰዎች በፈጸሟቸው ድርጊቶች ሳቢያ የሚጠፉት ለምንድን ነው?
▪ መወሰድና መቅረት የሚሉት ቃላት ምን ያመለክታሉ?