በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ሕዝቡን መሰብሰብ ጀመረ፣ ለሥራም አስታጠቃቸው

ይሖዋ ሕዝቡን መሰብሰብ ጀመረ፣ ለሥራም አስታጠቃቸው

ይሖዋ ሕዝቡን መሰብሰብ ጀመረ፣ ለሥራም አስታጠቃቸው

ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ክህደቱ በመላው ምድር ሲሰራጭ ቆይቶአል። ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን የሚከተሉ ቢሆኑም በይበልጥ የሚያስተምሩት የሰዎችን ወጎችና ከአረማውያን የተገኙ ልማዶችን ሆነ። የክርስቶስን መመለስ ነቅቶ የመጠበቁ ጉዳይ በአብዛኛው ገሸሽ ተደረገ።—ከማቴዎስ 13: 24–30, 37–43 ጋር አወዳድር።

ኢየሱስ ግን እርሱ የሚመለስበትን ጊዜ ነቅቶ መጠበቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል! የኢየሱስን መመለስ ነቅቶ ይጠባበቅ የነበረ አንድ ቡድን በዩ ኤስ ኤ አሌጌኒ ፔንሲልቫኒያ ተገኘ። በ1870ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ቻርልስ ቴዝ ራስልና አንዳንድ ጓደኞቹ ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ክፍል ተጽእኖ ነፃ ሆነው ስለ ክርስቶስ መመለስ ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ጀመሩ። በሌሎች መሠረተ ትምህርቶች ላይም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መመርመር ጀመሩ። ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ የጀመረው በዚህ ዓይነት ነበር።—ማቴዎስ 24:42

ይህ ቡድን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን፤ ይሖዋ ብቻውን ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክና ፈጣሪ መሆኑን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ የመጀመሪያ ፍጥረትና አንድያ ልጅ መሆኑን፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ራሱን የቻለ ሕያው አካል ሳይሆን ከአምላክ የሚወጣ በዓይን የማይታይ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን ሊገነዘብ ቻለ። ይህ ቡድን ነፍስ ዘላለማዊት ሳትሆን ሟች እንደሆነች፣ የሙታን ተስፋ ትንሣኤ እንደሆነና ንስሐ ለማይገቡ ክፉ ሰዎች የሚሰጠው ቅጣት ዘላለማዊ ሥቃይ ሳይሆን ፍፁም ጥፋት መሆኑን ተረዳ።

ኢየሱስ ለሰው ዘር ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ መስጠቱ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሆኑ ታወቀ። በመጀመሪያ ከአንደኛው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ባለው ጊዜ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑ 144,000 ሰዎች ከምድር ይዋጃሉ። ከዚያም በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት በዚህች መንግሥት ሥር በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸው በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከሙታን የሚነሡ ናቸው።

በተጨማሪም ራስልና ባልንጀሮቹ ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ በመንፈስ እንደሚገኝ ተረድተው ነበር። የአምላክ ሉዓላዊነት በምድር ላይ በሚገኝ በማንኛውም መንግሥት በኩል የማይገለጽባቸው የአሕዛብ ዘመናት የሚያልቁት በ1914 ነበር። ከዚያ በኋላ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መቋቋም ነበረባት። እነዚህ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች በዛሬው ጊዜ ከሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ጋር አንድ ዓይነት ናቸው።

ራስልና ባልደረቦቹ እነዚህን እውነቶች በንግግርም ሆነ በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት በስፋትና በርቀት አስታወቁ። ራስል በ1879 በሐምሌ ወር የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ን (ዛሬ መጠበቂያ ግንብ የሚባለውን) ማሳተም ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያካሂዱት የስብከት ሥራ ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት በሚሰጥ መዋጮ መካሄድ እንዳለበትና አባሎችን በመጠየቅ ገንዘብ እንዳይሰበሰብ ወሰነ። እንደዚሁም መልእክቱ ደመወዝ በማይከፈላቸውና በፈቃደኝነት በሚያገለግሉ አማኞች ጥረት መሠራጨት ነበረበት። ራስል ራሱም እስከዚያ ጊዜ ድረስ በንግድ ሥራው ያጠራቀመውን ጥሪት በሙሉ ለዚህ ሥራ አበርክቶአል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በወቅቱ የጥናት ክፍሎች ብለው ይጠሯቸው በነበሩ ጉባኤዎቻቸው ተሰባሰቡ። ንግግሮችን ለመስማት፣ ቅዱስ ጽሑፉን ለማጥናትና የምሥክርነት ስብሰባዎችን ለማድረግ በሳምንት እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ ይሰበሰቡ ነበር። የእያንዳንዱን የጥናት ክፍል መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠሩ ሽማግሌዎች በየጊዜው ራሳቸው መርጠው ይሾሙ ነበር።

በ1884 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ትራክት ማኅበር አትራፊ ያልሆነ ማኅበር ሆኖ በፔንሲልቫኒያ በሕግ ተቋቋመ። የማኅበሩ ፕሬዘዳንት በየዓመቱ እንዲመረጥ ተወሰነ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩ ሥራ በማንም ግለሰብ በሕይወት መኖር ወይም አለመኖር ላይ ሳይመካ ዘወትር እንዲቀጥል የሚያስችል ሕጋዊ መሣሪያ አስገኘ። ሲ ቲ ራስል ፕሬዘዳንት ሆኖ ተመረጠ። የሱም ጽሕፈት ቤት እንደ ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ ማገልገል ጀመረ።

ሥራውን ወደ ሌሎች አገሮች ለማስፋፋት ትልቅ ጥረት ተደረገ። በ1880ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ወደ ካናዳና ወደ እንግሊዝ አገር ደረሰ። ራስል በ1891 እውነትን ለማስፋፋት ምን ማድረግ እንደሚቻል ለመገምገም አውሮፓንና መካከለኛውን ምሥራቅ ተዘዋውሮ ጐበኘ። በ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በብሪታኒያ፣ በጀርመንና በአውስትራልያ ተቋቋሙ።

የስብከቱን ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት እንዲቻል የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት በ1909 ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ተዛወረ። በኒው ዮርክ ሕግ መሠረት የተቋቋመውንና አሁን የኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በመባል የሚታወቀውን ተባባሪ ማኅበር ማቋቋም አስፈላጊ ሆነ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ሥራ በብሪታኒያ የጋራ ብልጽግና አገሮች በሙሉ ለማዳረስ በ1914 ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር በለንደን ኢንግላንድ ተቋቋመ። በአሁኑ ጊዜ 70 የሚሆኑ በሕግ የተቋቋሙ ማኅበሮች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ዓላማዎች በምድር በሙሉ በማስፈጸም ላይ ናቸው። ሁሉም ማኅበሮች ለበጐ አድራጎት የተቋቋሙና በፈቃደኛነት በሚሰጡ መዋጮዎችና በፈቃደኛ ሠራተኞች የሚደገፉ ናቸው።

ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1916 አረፈና በምትኩ ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ሆነ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዓመታት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በከባድ ሁኔታ የስደት ፈተና ደረሰባቸው። በአሜሪካ በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት በኃላፊነት ቦታዎች ያገለግሉ የነበሩ ስምንት ወንድሞች በግፍ ሲታሰሩ ስደቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሥራ በአደገኛ ሁኔታ ላይ የወደቀ መሰለ። ይሁን እንጂ እነዚህ ወንድሞች በ1919 ከማንኛውም ዓይነት ወንጀል ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦላቸው ከእሥራት ወጡ። የስብከቱም ሥራ በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋት ጀመረ።

አንድነት ያገኘው የቅቡዓን ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አካል በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት አማካኝነት ከድርጅቱ ጋር ለሚተባበሩ ግለሰቦች በሙሉ መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ ማቅረቡን ቀጠለ። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ኢየሱስ የጠቀሰው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆነ ሁሉ በዘመናችንም በመንግሥቱ ሥራ ላይ የተሰማሩት ራሳቸውን የወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የቅቡዓን ቡድንም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆኖአል። ኢየሱስ ጉባኤውን ሊቆጣጠር በመጣ ጊዜ ይህ ክፍል ለቤተሰቡ ምግብ ሲያቀርብ አግኝቶታል። ከዚያም በኋላ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ሾመው።—ማቴዎስ 24: 45–47፤ ሉቃስ 12:42

በክርስቶስ ኢየሱስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ እንደተቋቋመች ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በግልጽ ታየ። ስለዚህ ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የተናገራቸው ቃላት አሁን ሙሉ ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ይህን የመንግሥት መልእክት የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሕዝቦች ለማዳረስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ወሰደ።—ማቴዎስ 24:14

ስለዚህ ማኅበሩ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ባለማቋረጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማውጣት እንዲችል ሕይወታቸውን ለአምላክ የወሰኑ ፈቃደኛ ሠራተኞችን በመጠቀም የራሱን የኅትመት ሥራ ለማካሄድ ወሰነ። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩ ሥራ ዘወትር እንዲካፈሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። በሬዲዮ አማካኝነት የሚተላለፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችም ወደ በርካታ አገሮች ተሠራጭተዋል።

ከ1918 በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የስብከታቸው ዓላማ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በሰማይ እንዲነግሱ የሚመረጡትን መሰብሰብና ዓለምን ስለ መጪው የአምላክ ፍርድ ማስጠንቀቅ ብቻ እንደሆነ አድርገው ተረድተው ነበር። የአሁኑ ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት ተርፈው በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ስለመሰብሰብ ምንም ያህል አልታሰበበትም ነበር። ከ1918 በኋላ ግን “አሁን በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞትን ፈጽሞ ላያዩ ይችላሉ!” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ንግግር በሰፊው ይሰማ ጀመር።

በማቴዎስ 25:31–46 ላይ ኢየሱስ ስለ በጐችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ በተደረገው ምርምር ከአርማጌዶን በፊት የሰማያዊቱ መንግሥት ወራሾች ያልሆኑ ጽድቅ ወዳድ ሰዎች የአምላክን ሞገስ አግኝተው ከአርማጌዶን እንደሚተርፉ በ1923 ታወቀ። በ1935 የተደረገው ተጨማሪ ጥናት እነዚህ በግ መሰል ሰዎች በራእይ 7:9–17 ላይ ከተገለጹት ቁጥራቸው ያልተወሰነ እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር አንድ መሆናቸውን አሳየ። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ከሁሉም ብሔራት ተሰብስበው ታላቁን መከራ በሕይወት ካለፉ በኋላ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። ይህ ዕውቀት ለስብከቱ ሥራ ተጨማሪ ግፊት ሰጥቶአል።—ዮሐንስ 10:16

በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጠሪያ ተቀበሉ። ከዚያ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የሺህ ዓመት መባቻ ሰዎች እና የመጠበቂያ ግንብ ሰዎች ተብለው ይጠሩ ነበር። እንዲያውም ራስላውያንና ራዘርፎርዳውያን የሚል ቅጽል ስም ይሰጣቸው ነበር። ከእነዚህ ስሞች አንዳቸውም ቢሆኑ ማንነታቸውን በትክክል የሚገልጹ አልነበሩም። በአንደኛው መቶ ዘመን በመለኮታዊ ፈቃድ ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተሰጠው ክርስቲያን የሚለው መጠሪያ አሁንም የሚሠራ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ የሐሰት ትምህርቶችን የሚከተሉ ብዙ ቡድኖች የሚጠቀሙበት ስም ሆኖአል። የዘመናችንን እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በሚልዮን ከሚቆጠሩት አስመሳይ ክርስቲያኖች የሚለይ ስም አስፈለገ።

በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በተደረገው ምርምር ይሖዋ የእሥራኤልን ሕዝብ ምሥክሮቼ ብሎ እንደጠራቸው ሁሉ ስሙንና ዓላማውን ለማሳወቅ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑት በሥርዓቱ ፍጻሜ የሚኖሩትም ሕዝቦቹ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ቢጠሩ ተገቢ እንደሚሆን ግልጽ ሆነ። ይህ ስም የይሖዋ እውነተኛ ክርስቲያን አምላኪዎች በዘመናችን ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለዩ አድርጎ አሳውቋቸዋል።—መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 43:10–12

በ1942 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ወቅት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ሞተና ናታን ኤች ኖር ፕሬዘዳንት ሆነ። ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በፊት የስብከቱ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ የሚፈቅድ መጠነኛ ሰላምና ነፃነት የሚኖርበት ጊዜ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንደሚኖር ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መረዳት ተችሎ ነበር። በውጭ አገር በሚሲዮናዊነት ሥራ የሚሰማሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ለማሠልጠን የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በየካቲት ወር 1943 ተቋቋመ። በዚያው ዓመት ቆየት ብሎ ልዩ የአገልግሎት ማሠልጠኛ ፕሮግራም በይሖዋ ምሥክሮች ሳምንታዊ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ተጨመረ።

በ1950 ማኅበሩ ከጥንቶቹ በኩረ ጽሑፎች የተተረጎመና በዘመናዊ እንግሊዝኛ የተዘጋጀ የቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በክፍል በክፍል ማውጣት ጀመረ። ይህ በትክክለኛ አተረጓጎምና በቀላል ቋንቋ ተዘጋጅቶና በማኅበሩ ማተሚያ ቤቶች ታትሞ በዝቅተኛ ዋጋ የተሠራጨው መጽሐፍ ቅዱስ ለስብከቱ ሥራ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቶአል። እስከ አሁን ድረስ ከ70 ሚልዮን በላይ ቅጂዎች በ12 ቋንቋዎች ታትመዋል።

በ1991 መጨረሻ ላይ ከአራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከ210 በላይ በሆኑ አገሮችና ደሴቶች በስብከቱ ሥራ ተካፍለዋል። በ1991 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ከ66,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ 10,650,158 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ይህም ከዚያ በፊት ከተደረጉት ስብሰባዎች ሁሉ በተሰብሳቢዎች እጅግ የላቀ ቁጥር ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎቱ በትጋት መካፈላቸው፣ በመካከላቸው ዓለም አቀፍ አንድነት መኖሩ፣ የይሖዋን ስም ለመደገፍና ለማስከበር እንዲሁም መንግሥቱን ለመስበክ የሚያሳዩት ቅንዓት፣ ንጹሕ የሥነ ምግባር ደረጃ ያላቸው መሆኑ፣ መላው መጽሐፍ ቅዱስ የማይታበል የአምላክ ቃል መሆኑን መቀበላቸውና ከአጉል እምነቶችና ከመናፍስትነት ሥራዎች ነፃ መሆናቸው አምላክ በእርግጥ እየተጠቀመባቸው መሆኑን ያረጋግጣል።

እውነተኛው አምልኮ እንደገና በመቋቋሙ እርስዎ እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ክፍሎች ይገ ልጻሉ።

● የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት የሚለዩት በየትኞቹ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ነው?

● የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እስከ 1918 ድረስ ምን ድርጅታዊ ዕድገት አይተው ነበር?

በማቴዎስ 24:45–47 ላይ የተጠቀሰው “ታማኝና ልባም ባሪያ” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የቅቡዓን ቡድን ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

● ለስብከቱ ሥራ መስፋፋት ታላቅ ግፊት የሰጠው የትኛው ስለ አምላክ ዓላማ የተገኘው ዕውቀት ነው?

● የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው መጠሪያ ለምን ዓላማ ያገለግላል?

● አምላክ በእርግጥ በይሖዋ ምሥክሮች በመጠቀም ላይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምን ማስረጃዎች አሉ?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሲ ቲ ራስል በ1879

የሐምሌ 1879 እትም

በመጀመሪያዎቹ አካባቢ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን በፒትስበርግ፣ ፔንሲልቫንያ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዋናው መሥሪያ ቤት፣ 1889–1909፣ ፒትስበርግ፣ ፔንሲልቫንያ

ዋናው መሥሪያ ቤት፣ 1909–1918፣ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ

የዋናው መሥሪያ ቤት መኖሪያ ሕንፃ፣ 1909–1926፣ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዓለም አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት፣ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ

ከላይ በስተግራ:-ቢሮዎች

ከላይ በስተቀኝ:-መኖሪያ ሕንፃዎች

ከታች በስተግራ:-የፋብሪካ ሕንፃ

ከታች በስተቀኝ:-ጽሑፍ መላኪያ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሬዲዮ ስርጭት በጄ ኤፍ ራዘርፎርድ

በፈቃደኛ ሠራተኞች የሚንቀሳቀሰው የመጀመሪያው የማኅበሩ ሮተሪ ማተሚያ

አሁን በ12 ቋንቋዎች የታተመው የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም