ትምህርት 79
ኢየሱስ ብዙ ተአምራት ፈጽሟል
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ነው። ሆኖም ተአምር መፈጸም እንዲችል ይሖዋ ለኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ ሰጥቶታል፤ ይህን ያደረገው ኢየሱስ ንጉሥ በሚሆንበት ወቅት ምን ነገሮችን እንደሚያከናውን ማሳየት እንዲችል ነው። ኢየሱስ ማንኛውንም በሽታ መፈወስ ይችል ነበር። በሄደበት ቦታ ሁሉ፣ የታመሙ ሰዎች ከበሽታቸው እንዲያድናቸው ወደ እሱ ይመጡ ነበር፤ እሱም ሁሉንም ፈውሷቸዋል። ዓይናቸው የታወረ ማየት ችለዋል፤ መስማት የተሳናቸው መስማት ችለዋል፤ ሽባ የነበሩ መራመድ ችለዋል፤ እንዲሁም አጋንንት ይቆጣጠሯቸው የነበሩ ሰዎች ነፃ ወጥተዋል። የልብሱን ጫፍ እንኳ የነኩ ሰዎች ተፈውሰዋል። ኢየሱስ በሄደበት ቦታ ሁሉ ሰዎች ይከተሉት ነበር። ብቻውን መሆን በሚፈልግበት ጊዜም እንኳ ሰዎች እሱን ፈልገው ሲመጡ ይቀበላቸው ነበር።
በአንድ ወቅት ሰዎች አንድን ሽባ የሆነ ሰው ተሸክመው ኢየሱስ ወዳለበት ቤት መጡ። ሆኖም ቤቱ ውስጥ በጣም ብዙ ሰው ስለነበረ ወደ ውስጥ መግባት አልቻሉም። ስለዚህ ጣሪያውን ከፍተው ሰውየውን ወደ ታች አወረዱት። ከዚያም ኢየሱስ ሰውየውን ‘ተነስና ወደ ቤትህ ሂድ’ አለው። ሰውየው መሄድ ሲጀምር ሰዎቹ በጣም ተገረሙ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ወደ አንድ መንደር እየገባ ሳለ የሥጋ ደዌ ያለባቸው አሥር ሰዎች በርቀት ቆመው ‘ኢየሱስ፣ እባክህ እርዳን!’ እያሉ ጮኹ። በዚያ ዘመን የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች ወደ ሌሎች ሰዎች መጠጋት አይፈቀድላቸውም ነበር። የይሖዋ ሕግ የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች ከዳኑ በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲሄዱ ስለሚያዝ ኢየሱስ ሰዎቹን ወደ ቤተ መቅደስ እንዲሄዱ
ነገራቸው። ወደዚያ እየሄዱ ሳሉ ከበሽታቸው ዳኑ። ከመካከላቸው አንዱ ከበሽታው እንደዳነ ሲያይ ኢየሱስን ለማመስገንና አምላክን ለማወደስ ተመለሰ። ከአሥሩ ሰዎች መካከል ኢየሱስን ያመሰገነው ይህ ሰው ብቻ ነበር።ለ12 ዓመት ያህል ታማ የነበረች አንዲት ሴት ከበሽታዋ ለመዳን ትጓጓ ነበር። በሕዝቡ መካከል ከኋላ መጥታ የኢየሱስን ልብስ ጫፍ ነካች። ወዲያውኑም ከበሽታዋ ተፈወሰች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ሴትየዋ ይህን ስትሰማ በጣም ፈራች፤ ሆኖም ወደ ኢየሱስ መጥታ እውነቱን ነገረችው። ኢየሱስም ‘ልጄ ሆይ፣ በሰላም ሂጂ’ በማለት አጽናናት።
ኢያኢሮስ የተባለ አንድ የምኩራብ አለቃ ኢየሱስን እንዲህ ብሎ ለመነው፦ ‘እባክህ ወደ ቤቴ ና! ትንሿ ልጄ በጣም ታማለች።’ ሆኖም ኢየሱስ ወደ ኢያኢሮስ ቤት ከመድረሱ በፊት ልጅቷ ሞተች። ኢየሱስ ወደ ቤት እንደደረሰ ብዙ ሰዎች ቤተሰቡን ለማጽናናት እንደመጡ አየ። ኢየሱስም ‘አታልቅሱ፤ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም’ አላቸው። ከዚያም የልጅቷን እጅ ይዞ ‘አንቺ ልጅ፣ ተነሺ!’ አላት። እሷም ወዲያውኑ ተነስታ ተቀመጠች፤ ኢየሱስም ወላጆቿን ‘የምትበላው ነገር ስጧት’ አላቸው። በዚህ ጊዜ ወላጆቿ ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል አስብ!
“አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ቀባው፤ ደግሞም ኃይል ሰጠው፤ ኢየሱስም አምላክ ከእሱ ጋር ስለነበር መልካም ነገር እያደረገና በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የወደቁትን እየፈወሰ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ።”—የሐዋርያት ሥራ 10:38