ትምህርት 26
አሥራ ሁለቱ ሰላዮች
እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ተነስተው፣ በፋራን ምድረ በዳ በኩል በመጓዝ ቃዴስ ወደሚባል ቦታ ደረሱ። በዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ለእስራኤላውያን የምሰጣቸውን የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው መርጠህ 12 ሰዎችን ላክ።’ ሙሴም 12 ሰዎችን መረጠና እንዲህ አላቸው፦ ‘ወደ ከነአን ሄዳችሁ ምድሪቱ ጥሩ እህል የምታበቅል መሆን አለመሆኗን እዩ። ሰዎቹ ደካማ ወይም ጠንካራ መሆናቸውን እንዲሁም የሚኖሩት በድንኳን ይሁን በከተሞች አጣርታችሁ ኑ።’ ኢያሱና ካሌብን ጨምሮ 12ቱ ሰላዮች ወደ ከነአን ሄዱ።
ከ40 ቀን በኋላ ሰላዮቹ በለስ፣ ሮማንና ወይን ይዘው ተመለሱ። ሰላዮቹ ‘ምድሪቱ ለኑሮ ተስማሚ ነች፤ ሰዎቹ ግን በጣም ጠንካሮች ናቸው፤ ከተሞቹም ረጃጅም ግንብ አላቸው’ በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ካሌብ ‘ሰዎቹን እናሸንፋቸዋለን። አሁኑኑ እንሂድ!’ አለ። ካሌብ እንዲህ ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? እሱና ኢያሱ በይሖዋ ይተማመኑ ስለነበረ ነው። ሌሎቹ አሥር ሰላዮች ግን እንዲህ አሉ፦ ‘አይሆንም! እዚያ ያሉት ሰዎች በጣም ግዙፎች ናቸው! እኛ ከእነሱ ጋር ስንነጻጸር እንደ ፌንጣ ነን።’
እስራኤላውያን ይህን ሲሰሙ ተስፋ ቆረጡ። ማጉረምረምና እርስ በርሳቸው እንዲህ መባባል ጀመሩ፦ ‘ወደ ከነአን ሄደን እነዚያ ሰዎች ከሚገድሉን ሌላ መሪ መርጠን ወደ ግብፅ ብንመለስ አይሻለንም?’ በዚህ ጊዜ ኢያሱና ካሌብ ‘በይሖዋ
ላይ አታምፁ፤ አትፍሩ። ይሖዋ ይጠብቀናል’ አሏቸው። እስራኤላውያን ግን አልሰሟቸውም። እንዲያውም ኢያሱንና ካሌብን ለመግደል አሰቡ!ይሖዋ ይህን ሲያይ ምን አደረገ? ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ለእስራኤላውያን ብዙ ነገር አድርጌላቸዋለሁ፤ እነሱ ግን አሁንም አይታዘዙኝም። ስለዚህ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት ይቆያሉ፤ ከዚያም እዚያው ይሞታሉ። እሰጣቸዋለሁ ብዬ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር የሚገቡት ልጆቻቸው እንዲሁም ኢያሱና ካሌብ ብቻ ናቸው።’
“እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?”—ማቴዎስ 8:26