ትምህርት 50
ይሖዋ ኢዮሳፍጥን ከጠላቶቹ አዳነው
የይሁዳ ንጉሥ የሆነው ኢዮሳፍጥ የባአልን መሠዊያዎችና ጣዖታት በሙሉ አስወገደ። ሕዝቡ የይሖዋን ሕግ እንዲያውቁ ይፈልግ ነበር። ስለዚህ የይሖዋን ሕግ በመላው ይሁዳ ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ መኳንንቱንና ሌዋውያኑን ላከ።
በአቅራቢያው የነበሩ አገሮች ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚረዳ ስላወቁ በይሁዳ ላይ ጥቃት መሰንዘር ይፈሩ ነበር። እንዲያውም ለንጉሥ ኢዮሳፍጥ ስጦታ ያመጡለት ነበር። በኋላ ግን ሞዓባውያን፣ አሞናውያንና በሴይር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከይሁዳ ጋር ለመዋጋት መጡ። ኢዮሳፍጥ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሁሉንም ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በኢየሩሳሌም ሰበሰበ። ከዚያም በእነሱ ፊት እንዲህ በማለት ጸለየ፦ ‘ይሖዋ፣ ያለአንተ እርዳታ ማሸነፍ አንችልም። እባክህ ምን ማድረግ እንዳለብን ንገረን።’
ይሖዋ እንዲህ በማለት ጸሎቱን መለሰለት፦ ‘አትፍሩ። እኔ እረዳችኋለሁ። ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ እንዴት እንደማድናችሁ ታያላችሁ።’ ታዲያ ይሖዋ ያዳናቸው እንዴት ነው?
በቀጣዩ ቀን ጠዋት፣ ኢዮሳፍጥ ዘማሪዎችን መረጠና ከሠራዊቱ ፊት ፊት እንዲሄዱ ነገራቸው። እነሱም ከኢየሩሳሌም ተነስተው ተቆአ በሚባል ቦታ እስከሚገኘው የጦር ሜዳ ድረስ ሄዱ።
ዘማሪዎቹ ከፍ ባለ ድምፅ ይሖዋን እያወደሱ ሳሉ ይሖዋ ለሕዝቡ ተዋጋላቸው። አሞናውያኑና ሞዓባውያኑ ግራ ተጋብተው እርስ በርስ እንዲዋጉ አደረገ፤ ከመካከላቸው አንድም ሰው አልተረፈም። የይሁዳን ሕዝብ፣ ወታደሮቹንና ካህናቱን ግን ከጠላቶቻቸው አዳናቸው። በይሁዳ ዙሪያ በሚገኙት አገሮች ያሉ ሰዎች በሙሉ ይሖዋ ያደረገውን ነገር ሲሰሙ አሁንም ሕዝቡን እንደሚጠብቅ ተገነዘቡ። አዎ፣ ይሖዋ ሕዝቡን በተለያዩ መንገዶች ያድናል። ደግሞም ሕዝቡን ለማዳን የሰዎች እርዳታ አያስፈልገውም።
“እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም። ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ።”—2 ዜና መዋዕል 20:17