በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንግሥት

መንግሥት

ፍቺ:- የአምላክ መንግሥት ይሖዋ የፍጥረታቱ ሁሉ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን የሚገልጽባት ወይም ይህን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ለመግለጽ የሚጠቀምባት መሣሪያ ናት። በተለይ ይህ ቃል የአምላክ ሉዓላዊነት መግለጫ የሆነውን በልጁ በኩል የሚመራ ንጉሣዊ አገዛዝ ለማመልከት ተሠርቶበታል። “መንግሥት” የሚለው ቃል ንጉሥ ሆኖ የተቀባን ሰው አገዛዝ ወይም በዚያ ሰማያዊ አስተዳደር ሥር የሚገዛውን ምድራዊ ግዛት ሊገልጽ ይችላል።

የአምላክ መንግሥት እውን የሆነች መስተዳድር ናትን?

ወይስ በሰዎች ልብ ውስጥ የሚኖር ሁኔታ?

ሉቃስ 17:21:- “እንኋት በዚህ፣ ወይም:- እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት።” (በቁጥር 20 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ይናገር የነበረው ግብዞች በማለት ላወገዛቸው ፈሪሳውያን ስለነበር መንግሥቲቱ በእነርሱ ልብ ውስጥ አለች ማለቱ ሊሆን እንደማይችል ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህም በመሆኑ ዘ ኤምፋቲክ ዳያግሎት እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “የአምላክ ንጉሥ በመካከላችሁ ነው።”)

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት መስተዳድር እንደሆነች ይናገራልን?

ኢሳ. 9:6, 7:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም [“መንግሥት” ሪስ፣ ኪጄ፣ አት፣ ዱዌይ፤ “አገዛዝ” ጀባ፣ ኒኢ፤ “መስፍናዊ አገዛዝ” አዓት] በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ [“መስፍን” አዓት ] ተብሎ ይጠራል። . . . በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም።”

የመንግሥቱ ገዥዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው?

ራእይ 15:3:- “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ [“የዘላለም” አዓት ] ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው።”

ዳን. 7:13, 14:- “የሰው ልጅ የሚመስል [ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ማርቆስ 14:61, 62⁠ን ተመልከት] ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም [ወደ ይሖዋ] ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም [ለኢየሱስ ክርስቶስ] ተሰጠው።”

ራእይ 5:9, 10:- “[አንተ ኢየሱስ ክርስቶስ] ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፣ በምድርም ላይ ይነግሣሉ።” (እነዚህ ‘ከምድር ተዋጅተው’ ከበጉ ጋር በሰማያዊት የጽዮን ተራራ የሚገዙት ሰዎች ቁጥራቸው 144,000 እንደሆነ በ⁠ራእይ 14:1–3 ላይ ተገልጿል።)

ይህች መንግሥት በሰብዓዊ መስተዳድሮች ላይ ምን ታስከትላለች?

ዳን. 2:44:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”

መዝ. 2:8, 9:- “ለምነኝ፣ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፣ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ትቀጠቅጣቸዋለህ።”

የአምላክ መንግሥት ወደፊት ምን ታከናውናለች?

የይሖዋን ስም እንዲቀደስና ሉዓላዊነቱ እንዲከበር ታደርጋለች

ማቴ. 6:9, 10:- “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ።” (እዚህ ላይ የአምላክ ስም መቀደስ ከመንግሥቱ መምጣት ጋር በጣም የተሳሰረ መሆኑ ተገልጿል።)

ሕዝ. 38:23:- “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” (የአምላክ ስም ከደረሰበት ነቀፋ ሁሉ ይነጻል። ስሙ የሚገባውን ቅድስናና አክብሮት ያገኛል። በሕይወት የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ሉዓላዊነት በፈቃደኝነት የሚደግፉና ፈቃዱን ለማድረግ ደስ የሚላቸው ብቻ ይሆናሉ። የመላው ጽንፈ ዓለም ሰላምና ደህንነት የተመካው በዚህ በይሖዋ ስም መቀደስ ላይ ነው።)

እስከ አሁን እንዲኖር የተፈቀደለት የሰይጣን ዓለም አገዛዝ እንዲያከትም ታደርጋለች

ራእይ 20:2, 3:- “[በሰማይ የሚኖረው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ] የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።” (በዚህ መንገድ ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ማድረግ ከባድ እንዲሆንባቸው ካደረገው ከሰይጣን ተጽእኖ ይገላገላሉ። እጅግ ሲበዛ ኢ–ሰብዓዊ ለሆኑት ድርጊቶች መንስኤ የሆነው የሰይጣን ተጽዕኖና የብዙ ሰዎችን ሕይወት ፍርሃት ላይ የጣለው የአጋንንት ተፅዕኖ ይወገዳል።)

ፍጥረታት ሁሉ በአንዱ እውነተኛ አምላክ አምልኮ እንዲጠቃለሉ ታደርጋለች

ራእይ 5:13፤ 15:3, 4:- “በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ:- በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው [ለይሖዋ አምላክ]፣ ለበጉም [ለኢየሱስ ክርስቶስ] ይሁን ሲሉ ሰማሁ።” “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ [“ሁሉን ማድረግ የምትችል ይሖዋ አምላክ” አዓት] ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ [“የዘላለም” አዓት] ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ [“ይሖዋ” አዓት] ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፣ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ።”

የሰው ልጅ እንደገና ከአምላክ ጋር ስምም እንዲሆን ታደርጋለች

ሮሜ 8:19–21:- “የፍጥረት [የሰው ልጅ] ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ [ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመኖር ሰማያዊ ትንሣኤ ያገኙት የገዥነት ሥራቸውን መጀመራቸውን የሚያሳየውን ማስረጃ] ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ [የሰው ልጅ በአጠቃላይ] ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።”

የሰውን ልጅ ከማንኛውም የጦርነት ሥጋት ነፃ ታወጣለች

መዝ. 46:8, 9:- “የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።”

ኢሳ. 2:4:- “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”

ምግባረ ብልሹ ገዥዎችንና ጭቆናን ከመላው ምድር ታስወግዳለች

መዝ. 110:5:- “እግዚአብሔር በቀኝህ ነገሥታትን በቁጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል።”

መዝ. 72:12–14:- “[የይሖዋ መሲሐዊ ንጉሥ] ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው [“ደማቸው” አዓት ] በፊቱ ክቡር ነው።”

ለመላው የሰው ልጅ የተትረፈረፈ ምግብ ታቀርባለች

መዝ. 72:16 አዓት:- “በምድር ላይ ብዙ እህል ይኖራል፤ በተራሮችም ጫፍ ይትረፈረፋል።”

ኢሳ. 25:6:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ [የአምላክ መንግሥት መቀመጫ በሆነችውና ለምድራዊ ተገዥዎች የሚሆን ዝግጅት በሚደረግበት በሰማያዊት የጽዮን ተራራ] ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።”

ሁሉንም ዓይነት ሕመምንና የአካል ጉድለትን ታስወግዳለች

ሉቃስ 7:22፤ 9:11:- “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፣ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ፣ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ፣ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል።” “[ኢየሱስ ክርስቶስ] ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፣ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።” (ስለዚህ ኢየሱስ በሰማይ በሚነግሥበት ጊዜ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግ አሳይቷል።)

እያንዳንዱ ሰው ተስማሚ ቤት እንዲያገኝ ታደርጋለች

ኢሳ. 65:21, 22:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም።”

ሁሉም ሰው አርኪ ሥራ እንዲያገኝ ታደርጋለች

ኢሳ. 65:23:- “እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ብሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።”

ማንም ሰው አካሉ ወይም ንብረቱ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይደርስበት ዋስትና ትሰጣለች

ሚክ. 4:4:- “የሠራዊት ጌታ፣ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሯልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ ዛፍ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”

መዝ. 37:10, 11:- “ገና ጥቂት፣ [“ከጥቂት ጊዜ በኋላ” አዓት ] ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”

ጽድቅና ፍትሕ ታሰፍናለች

2 ጴጥ. 3:13:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”

ኢሳ. 11:3–5:- “[መሲሐዊው ንጉሥ] ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤ ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ . . . የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፣ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።”

የሰው ልጆችን በተፈጥሮ ኃይሎች ምክንያት ሊመጣ ከሚችል ከማንኛውም አደጋ ትጠብቃለች

ማር. 4:37–41:- “ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። . . . [ኢየሱስም] ነቅቶ ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም:- ዝም በል፣ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅም ፀጥታም ሆነ። . . . እጅግም ፈሩና:- እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።” (በዚህ መንገድ ክርስቶስ በሰማይ በሚነግሥበት ጊዜ በእነዚህ የተፈጥሮ ኃይሎች ላይ የሚኖረውን ሥልጣን አሳይቷል።)

ሙታንን ታስነሣለች

ዮሐ. 5:28, 29:- “[“በመታሰቢያ” አዓት ] መቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን [የንጉሡን የክርስቶስን ድምፅ] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . በዚህ አታድንቁ።”

ራእይ 20:12:- “ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፣ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው [ከትንሣኤ በኋላ እንደሠሯቸው ሥራዎች፤ ከ⁠ሮሜ 6:7 ጋር አወዳድር] መጠን ተከፈሉ።”

በተወረሰው የአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣውን ሞት ታስወ ግዳለች

ኢሳ. 25:8:- “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”

ራእይ 21:4:- “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”

ሰዎች እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱበት ዓለም እንዲፈጠር ታደርጋለች

ዮሐ. 13:35:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ [በዚህም ምክንያት በሰማያዊው መንግሥት የኢየሱስ ተባባሪዎች ወይም የመንግሥቲቱ ምድራዊ ተገዥዎች] እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”

እንስሳትና ሰዎች እርስ በርሳቸው ተስማምተው በሰላም እንዲኖሩ ታደርጋለች

ኢሳ. 11:6–9:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፣ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም።” (እንዲሁም ኢሳይያስ 65:25)

ሆሴዕ 2:18 የ1980 ትርጉም:- “በዚያን ጊዜ ሕዝቦቼን እንዳይተናኮሉ ከአራዊትና ከወፎች ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ . . . በሰላምና በጸጥታ እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ።”

ምድርን ገነት ታደርጋለች

ሉቃስ 23:43 አዓት:- “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።”

መዝ. 98:7–9:- “ባሕርና ሞላዋ፣ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ። ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፤ ተራሮችም ደስ ይበላቸው፣ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና። ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል።”

ከ⁠ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15⁠ና ከ⁠ኢሳይያስ 55:11 ጋር አወዳድር።

የአምላክ መንግሥት መግዛት የምትጀምርበት ጊዜ መቼ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነበርን?

ቆላ. 1:1, 2, 13 የ1980 ትርጉም:- “በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችንም ከጢሞቴዎስ፣ . . . [የሰማያዊ መንግሥት ወራሾች ለነበሩት] ቅዱሳን . . . ለሆኑ . . . እርሱ [አምላክ] ከጨለማ ኀይል አድኖ [የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የነበሩትን ቅዱሳንን ማለት ነው] ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል።” (ስለዚህ ክርስቶስ ይህ ከመጻፉ በፊት በአንደኛው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ላይ መግዛት ጀምሮ ነበር፤ በምድር ላይ የሚገዛው መንግሥት የሚቋቋመው ግን ገና ወደፊት ነበረ።)

1 ቆሮ. 4:8:- “አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር።” (እነዚህ ክርስቲያኖች የተሳሳተ አመለካከት በመያዛቸው ሐዋርያው ጳውሎስ እነርሱን መውቀሱ እንደነበር ግልጽ ነው።)

ራእይ 12:10, 12:- “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (እዚህ ላይ የአምላክ መንግሥት መቋቋም ሰይጣን ከሰማይ ከመጣሉ ጋር ተያይዟል። በ⁠ኢዮብ መጽሐፍ ምዕራፍ 1, 2 ላይ እንደተገለጸው ይህ እርምጃ በኤደን ውስጥ ዓመፅ በተፈጸመ ጊዜ ገና አልተወሰደም ነበር። የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው በ96 እዘአ ሲሆን የሚናገረውም በወቅቱ ወደፊት ስለሚሆኑት ሁኔታዎች መሆኑን ራእይ 1:1 ይገልጻል።)

የአምላክ መንግሥት መግዛት እንድትጀምር በመጀመሪያ ዓለም ወደ ክርስትና መለወጥ ይኖርበታልን?

መዝ. 110:1, 2:- “እግዚአብሔር ጌታዬን [ኢየሱስ ክርስቶስን]:- ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ።” (ስለዚህ በቁጥጥር ሥር የሚያደርጋቸው ጠላቶች ይኖሩታል። ሁሉም እሺ ብለው አይገዙለትም።)

ማቴ. 25:31–46:- “የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ . . . እነዚያም [ለቅቡዓን ወንድሞቹ ፍቅር ያላሳዩት] ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ክርስቶስ በዙፋኑ ላይ ከመቀመጡ በፊት የሰው ልጆች በሙሉ ወደ ክርስትና እንደማይለወጡ ግልጽ ነው። ሁሉም ሰዎች የጽድቅ አቋም ይዘው አይገኙም።)

መንግሥቲቱ መቼ መግዛት እንደምትጀምር መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማልን?

በገጽ 94–97 ላይ “የዘመናት ስሌት” በሚለው ሥርና በገጽ 234–238 ላይ “የመጨረሻ ቀኖች” በሚለው ሥር ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘በእኔ ዕድሜ አትመጣም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ግን አንድ የሆነ ዘመን ላይ መምጣትዋ አይቀርም። አይደለም እንዴ? . . . ይህች መንግሥት በራሱ የትውልድ ዘመን እንደምትመጣ ሊያውቅ የሚችል ሰው ይኖራልን? የኢየሱስ ሐዋርያት ይህ ትውልድ የትኛው እንደሚሆን ለማወቅ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው መልስ በዛሬው ዘመን የምንኖረውን እኛን ሊያሳስበን የሚገባ ነው። (ማቴ. 24:3–14፤ ሉቃስ 21:29–32)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ይህ የተለመደ አባባል ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ የአምላክ መንግሥት በሰማያት ሆና በመግዛት ላይ እንደምትገኝ በጥብቅ ያምናሉ። በአምላክ የጽድቅ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለመኖር መፈለግ አለመፈለጋችንን ማሳየት የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ዛሬ ወደ እርስዎ የመጣሁትም ለዚህ ነው። እዚህ ማቴዎስ 25:31–33 ላይ የተገለጸውን ልብ ብለው ቢከታተሉ ደስ ይለኛል።’