ሴቶች
ፍቺ:- ለአካለ መጠን የደረሱ እንስት ሰብዓዊ ፍጡሮች። በዕብራይስጥ ቋንቋ ሴት የሚለው ቃል ኢሽሻህ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጐም “እንስት ሰው” ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን ያንኳስሳቸዋልን? ወይም ዝቅተኛ ፍጡር እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋልን?
ዘፍ. 2:18 አዓት:- “ይሖዋ አምላክ እንዲህ አለ:- ‘ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም አይደለም። ስለዚህ የጐደለውን የምታሟላና ረዳት የምትሆነውን እፈጥርለታለሁ።’” (እዚህ ላይ አምላክ ወንዱ ከሴቲቱ የተሻለ ሰው እንደሆነ አልገለጸም። ከዚያ ይልቅ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ሴት የወንድን ባሕርያት የሚያሟሉ ባሕርያት እንደሚኖሯት አምላክ አመልክቷል። ማሟያ ማለት አንድ ላይ ሲሆኑ አንድ አካል ከሚፈጥሩ ሁለት ነገሮች አንዱ ነው። ሴቶች በቡድን መልክ በአንዳንድ ባሕርያትና ችሎታዎች የላቁ ሲሆኑ፣ ወንዶችም እንዲሁ በሌሎች ነገሮች የላቁ ናቸው። ከ1 ቆሮንቶስ 11:11, 12 ጋር አወዳድር።)
ዘፍ. 3:16:- “[አምላክም ለሴቲቱ] አለ:- . . . ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።” (ይህ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ የተገለጸው ነገር ወንዶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሳይሆን ራስ ወዳድነት ወደፊት የሰው ሕይወት ክፍል መሆኑ ስለማይቀር ወንዶች ወደፊት ምን እንደሚያደርጉ ይሖዋ አስቀድሞ ስላወቀ ያንን መናገሩ ነበር። ከዚህ የሰዎች የራስ ወዳድነት አገዛዝ የተነሣ የተስፋፉትን ደስ የማያሰኙ ሁኔታዎች ከዚህ በኋላ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ገልጸዋቸዋል። ሆኖም እንዲህ የመሰለውን ጠባይ አምላክ እንደተቀበለው መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ወይም ሌሎች ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ ነው አይልም።)
የራስነትን ቦታ ለወንዶች መስጠት ሴቶችን ዝቅ ያደርጋቸዋልን?
አንድ ሰው በሌላው ራስነት ሥር መሆኑ ዝቅ ተደረገ ማለት አይደለም። የራስነት ቦታ መኖር ነገሮችን ሥርዓት ባለው ዝግጅት ለማከናወን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይሖዋ “የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮ. 14:33) ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሖዋ አምላክ ራስነት ሥር ነው። በዚህ ቦታውም ታላቅ እርካታ ያገኛል።—ዮሐ. 5:19, 20፤ 8:29፤ 1 ቆሮ. 15:27, 28
አንጻራዊ የሆነ የራስነት ቦታ በተለይ በቤተሰብ ውስጥና በክርስቲያን ጉባኤ ለወንድ ተሰጥቷል። ወንድ በሴት ላይ ፍጹም ሥልጣን እንዲኖረው አልተደረገም፤ ወንድ ስለ ራስነቱ ቦታ አጠቃቀም ራሱ ለሆነው ክርስቶስና ለአምላክ መልስ መስጠት አለባት። (1 ቆሮ. 11:3) በተጨማሪ ወንዶች “እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን [እንዲወዱ]” እና ለሚስቶቻቸው ‘ክብር እንዲሰጡአቸው’ ታዝዘዋል። (ኤፌ. 5:28፤ 1 ጴጥ. 3:7) አምላክ ለተጋቡት ሰዎች በሰጠው ዝግጅት ውስጥ በሩካቤ ሥጋ የመርካቱ ችሎታ ለባል ብቻ ሳይሆን ለሚስትም ተሰጥቷል። (1 ቆሮ. 7:3, 4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው ባለሞያ የሆነች ሴት የተሰጣት ቦታ በቤተሰቧና በአካባቢዋ ያላትን ዋጋ አጉልቶ ያሳያል። ይህም የባልዋን የራስነት ቦታ ሳትዘነጋ በግሏ ተነሣሥታ ለመሥራት የሚያስችላት ሰፊ መስክ ይሰጣታል። (ምሳሌ 31:10–31) ልጆች አባታቸውን ብቻ ሳይሆን እናታቸውንም ጭምር እንዲያከብሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያዝዛቸዋል። (ኤፌ. 6:1–3) መጽሐፍ ቅዱስ መበለቶችን በችግራቸው ለመርዳቱ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። (ያዕ. 1:27) ስለዚህ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ሴቶች ሳይሰጉ ተማምነው ሊኖሩ ይችላሉ፤ በግለሰብ ደረጃ ለራሳቸው እውነተኛ አድናቆትና በሥራቸው ግላዊ እርካታ ሊያገኙ ይችላሉ።
ይሖዋ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረቶቹ የሚገኙበትን የራሱን ድርጅት እንደ አንዲት ሴት፣ እንደ ራሱ ሚስት፣ እንደ ልጆቹ እናት አድርጎ መግለጹ ሴት ራእይ 12:1፤ ገላ. 4:26) እንዲሁም በመንፈስ የተቀባችው የኢየሱስ ክርስቶስ ጉባኤ የእርሱ ሙሽራ እንደሆነች ተነግሮናል። (ራእይ 19:7፤ 21:2, 9) በመንፈሳዊ አመለካከት በወንድና በሴት መካከል ምንም ልዩነት የለም። ከክርስቶስ ጋር ሰማያዊ መንግሥት እንዲካፈሉ ከተጠሩት መካከል ወንዶችም ሴቶችም ይገኛሉ።—ገላ. 3:26–28
በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያላትን ቦታ ያሳያል። (ሴቶች የጉባኤ አገልጋዮች መሆን ይገባቸዋልን?
የጉባኤ የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶች መሆናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። የኢየሱስ ክርስቶስ 12ቱ ሐዋርያት ሁሉም ወንዶች ነበሩ፣ በኋላም የክርስቲያን ጉባኤዎች የበላይ ተመልካቾችና አገልጋዮች ነበሩ። (ማቴ. 10:1–4፤ 1 ጢሞ. 3:2, 12) ሴቶች በጉባኤ ስብሰባዎች “በሁሉ ነገር እየተገዙ በጸጥታ እንዲማሩ” ተመክረዋል፣ በጉባኤ ወንዶችን የሚፈታተኑ ጥያቄዎች አያነሡም። ሴቶች የሚናገሩት ነገር ታዛዥነት እንደጎደላቸው የሚያሳይ ከሆነ እንዲህ በመሰሉ ስብሰባዎች ላይ ‘አይናገሩም’። (1 ጢሞ. 2:11, 12፤ 1 ቆሮ. 14:33, 34) ስለዚህ ሴቶች ምንም እንኳ በጉባኤ ሥራዎች ጠቃሚ አሰተዋጽኦ ቢያበረክቱም ብቁ ወንዶች እያሉ ጉባኤውን እንዲመሩ ወይም ጉባኤውን በማስተማር ቀዳሚ እንዲሆኑ አልተደረገም።
ሆኖም ሴቶች ከጉባኤ ስብሰባዎች ውጪ ሰባኪዎች፣ አዋጅ ነጋሪዎች፣ የምሥራቹ አገልጋዮች መሆን ይችላሉን? በ33 እዘአ በዋለው በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በወንዶችና በሴቶች ላይ ፈሰሰ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢዩኤል 2:28, 29ን ጠቅሶ ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ሥራ 2:17, 18) ዛሬም በተመሳሳይ ሴቶች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ እየሰበኩና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየመሩ በክርስቲያን አገልግሎት በሚገባ ይካፈላሉ።—በተጨማሪ መዝሙር 68:11ን በአዓት እና ፊልጵስዩስ 4:2, 3ን ተመልከት።
ክርስቲያን ሴቶች በአንዳንድ ወቅቶች ራሳቸውን የሚሸፍኑት ለምንድን ነው?
1 ቆሮ. 11:3–10:- “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር [ነው።] . . . ራስዋን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን [ባልዋን] ታዋርዳለች፤ . . . ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና። ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና። ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል።” (አንዲት ክርስቲያን ሴት ተገቢ በሆኑ ወቅቶች ራሷን መሸፈኗ በአምላክ ለተቋቋመው የራስነት ዝግጅት ክብር እንደምትሰጥ አንድ ማስረጃ ነው። ክርስቶስ ቲኦክራሲያዊ የራስነት ሥልጣንን ያከብራል፤ ወንድና ሴት እንደዚሁ እንዲያደርጉ ግዴታ አለባቸው። የመጀመሪያው ሰው አዳም ከሴት የተወለደ ሳይሆን በአምላክ የተፈጠረ ነበር። አምላክ ሔዋንን ሲፈጥር ከአዳም አንድ የጎን አጥንት ወስዶ እንደመሠረት ተጠቅሞበታል፣ አምላክም ሴቲቱ ለአዳም ረዳቱ እንደምትሆን ገልጿል። ስለዚህ መጀመሪያ ለተፈጠረው ሰው የራስነት ቦታ ተሰጥቶታል። ወንድ ‘በሚጸልይበት ወይም ትንቢት በሚናገርበት’ ጊዜ ራሱን አይሸፍንም ምክንያቱም ራስነትን በተመለከተ ወንድ ‘የአምላክ ምሳሌ’ ነው፤ ማለትም የራሱን ቤተሰብ በተመለከቱ ጉዳዮች ሌላ ምድራዊ ራስ የለውም። ይሁን እንጂ ሴት ራሷን ሳትሸፍን ‘መጸለይ ወይም ትንቢት መናገር’ አምላክ ለወንድ ለሰጠው ቦታ ክብር አለመስጠት እንደሆነ ያሳያል፣ እርሱንም ያሳፍረዋል። የይሖዋ ሚስት መሰል ሰማያዊት ድርጅት አባሎች የሆኑት መላእክት እንኳ ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች የሚያደርጉትን ‘የራስነት ምልክት’ ይመለከቱታል፣ እነሱ ራሳቸው ለይሖዋ እንደሚገዙ ያስታውሳቸዋል።)
አንዲት ሴት ራሷን መሸፈን የሚያስፈልጋት መቼ ነው?
አንዲት ሴት ራሷን መሸፈን ያለባት በ1 ቆሮንቶስ 11:5 ላይ እንደተገለጸው ‘በምትጸልይበትና ትንቢት በምትናገርበት ጊዜ’ ነው። በግልዋ ስትጸልይ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከሌሎች ጋር ስትወያይ ራሷን መሸፈን ያስፈልጋታል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ባልዋ የሚያከናውናቸውን ወይም ሌላ ወንድ የሚያደርጋቸውን አምልኮ ነክ ጉዳዮች ስታከናውን የወንድን የራስነት ቦታ እንደምታከብር በውጪ ምልክት እንዲሆን ራሷን መሸፈን አለባት። ራሷና ሌሎችን በመወከል የምትጸልይ ከሆነ ወይም መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ፣ ባልዋ በሚገኝበት ስታስተምር ባልዋ የእርሷ ዓይነት እምነት ባይኖረውም እንኳ ራሷን መሸፈን አለባት። ነገር ግን ልጆችዋን የማስተማር መለኮታዊ ሥልጣን ስለተሰጣት ባልዋ በማይኖርበት ጊዜ ራሳቸውን ካልወሰኑ ትናንሽ ልጆች ጋር ስትጸልይ ወይም ስታስጠና ራሷን መከናነብ አያስፈልጋትም። ከዚህ ለየት ባለ ሁኔታ ራሱን የወሰነ የጉባኤ አባል የሆነ ወንድ በተገኘበት ወይም ጐብኚ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አብሯት በሚያገለግልበት ጊዜ አስቀድሞ ቀጠሮ የተያዘለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ራሷን መከናነብ አለባት፤ ጸሎት ግን እርሱ ማቅረብ አለበት።
ሴቶች ኮስሜቲክስ ቢጠቀሙ ወይም ጌጣጌጥ ቢያደርጉ ተገቢ ነውን?
1 ጴጥ. 3:3, 4:- “ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።” (ይህ ማለት ሴቶች ጌጣጌጥ ማድረግ የለባቸውም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ሴቶች ልብስ መልበስ የለባቸውም ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ይህም እንደዚያ ማለት ነው። ሆኖም ግን እዚህ ላይ የፀጉር አበጣጠራቸውንና የልብስ አለባበሳቸውን በተመለከተ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ይዘው በቅድሚያ ለመንፈሳዊ ጌጥ ትኩረት እንዲሰጡ ተመክረዋል።)
1 ጢሞ. 2:9, 10 አዓት:- “ሴቶች በሚገባ ልብስ ከልከኝነትና ከጤናማ አስተሳሰብ ጋር ራሳቸውን እንዲሸልሙ እወዳለሁ፤ ነገር ግን በፀጉር አሠራር ዘዴና በወርቅ ወይም በእንቁ ወይም በዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ ሳይሆን እግዚአብሔርን እናከብራለን ለሚሉ ሴቶች በሚስማማ መንገድ ይኸውም በመልካም ሥራዎች ይሁን።” (በአምላክ ዘንድ በእርግጥ ዋጋ ያለው ምንድን ነው? የአንድ ሰው የውጪ ገጽታ ወይስ የአንድ ሰው ልብ ሁኔታ? አንዲት ሴት የፆታ ብልግና እየፈጸመች ብትኖር ግን ኮስሜቲክስ ባትጠቀምና ጌጣ ጌጥ ባታደርግ አምላክ ደስ ይሰኛልን? ወይስ ቅባትና ጌጣ ጌጥ በልክ የሚያደርጉትንና ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸውን፣ በቅድሚያ ራሳቸውን በአምላካዊ ጠባዮችና ክርስቲያናዊ ጠባይ የሚሸልሙትን ሴቶች ይቀበላል? ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና። . . . ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።”—1 ሳሙ. 16:7)
ምሳሌ 31:30:- “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።”