በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፋት

ክፋት

ፍቺ:- በሥነ ምግባር ረገድ በጣም መጥፎ የሆነ ነገር ሁሉ ክፋት ይባላል። ብዙ ጊዜ ጐጂ፣ ክፉ፣ ወይም አጥፊ የሆነን ነገር ያመለክታል።

ክፋት ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?

ለክፋት መብዛት ተወቃሹ አምላክ አይደለም። አምላክ ሰውን ፍጹም አድርጎ ፈጥሮት ነበር። ሰዎች ግን የአምላክን ሕግጋት ችላ ለማለትና ጥሩና መጥፎ ስለሆኑ ነገሮች ራሳቸው ለመወሰን መረጡ። (ዘዳ. 32:4, 5፤ መክ. 7:29፤ ዘፍ. 3:5, 6) ይህን በማድረጋቸው ከሰዎች የበለጠ ኃይል ባላቸው ክፉ መናፍስት ተፅዕኖ ሥር ወደቁ።—ኤፌ. 6: 11, 12

1 ዮሐ. 5:19:- “ዓለምም በሞላው በክፉው [ተይዟል።]”

ራእይ 12:7–12:- “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ . . . ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። . . . ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ይህ በምድር ላይ የወረደው ከፍተኛ ወዮታ መንግሥቲቱ ከተወለደችበትና ሰይጣን ከሰማይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ ጨምሯል። ቁጥር 10⁠ን ተመልከት።)

2 ጢሞ. 3:1–5:- “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።” (ይህ ለብዙ መቶ ዓመታት የቆየው በእውነተኛ አምልኮ ላይ የተፈጸመ ክህደት ያስገኘው ፍሬ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ሊስፋፉ የቻሉት ሃይማኖተኞች ነን የሚሉ ሰዎች የአምላክ ቃል በግልጽ የሚናገረውን ችላ በማለታቸው የተነሣ ነው። እውነተኛ የሆነ ለአምላክ የማደር ባሕርይ በአኗኗር ላይ በጎ ተጽእኖ ለማሳደር ኃይል ያለው መሆኑን በሕይወታቸው አያሳዩም።)

  አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

 አንዳንድ ጊዜ ክፉዎች በሙሉ ከምድር ቢወገዱ የተሻለ የሚሆን ይመስለናል። ክፋት እንዳይኖር እንመኛለን። ይሁን እንጂ ክፋት ከጀመረበት ረዥም ዘመን ጋር ሲወዳደር እኛ ከክፋት ጋር አብረን የኖርንበት ዘመን በጣም አጭር ነው። ይሖዋ በዚህ ሁሉ ዘመን እንዴት ተሰምቶት ይሆን? ሰዎች በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ለደረሰባቸው በደልና መጥፎ ሁኔታ እርሱን ሲወቅሱና ሲረግሙ ኖረዋል። ለነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች ግን ምክንያቶቹ ሰይጣንና ክፉ ሰዎች ናቸው። ይሖዋ ክፉዎችን ለማጥፋት የሚያስችል ኃይል አለው። ይህን ለሚያክል ጊዜ ራሱን የገታው ጥሩ ምክንያት ቢኖረው እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። የይሖዋ አሠራር እኛ መደረግ ይኖርበታል ከምንለው የተለየ መሆኑ ሊያስደንቀን ይገባልን? የአምላክ ልምድና ተሞክሮ ከማንኛውም ሰው ተሞክሮ እጅግ የላቀ ነው። ስለ ሁኔታዎች ያለው አመለካከት ከማንኛውም ሰው እጅግ የሰፋ ነው።—ኢሳይያስ 55:8, 9⁠ን ከ⁠ሕዝቅኤል 33:17 ጋር አወዳድር።

አምላክ የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጡሮቹ የፈቀዱትን የማድረግ ነፃነት ባይሰጣቸው ኖሮ ክፋት ሊኖር አይችልም ነበር። አምላክ ግን ለእርሱ ባለን ፍቅር ተነሣሥተን የመታዘዝ ወይም ያለመታዘዝ ምርጫ እንድናደርግ አስችሎናል። (ዘዳ. 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15) ከዚህ በተለየ ሁኔታ ቢፈጠር ይሻል ነበር ብለን እናስባለንን? ወላጆች ከሆንን ይበልጥ የሚያስደስተን ልጆቻችን በፍቅር ተነሣሥተው ሲታዘዙን ነው ወይስ በግዳጅ ሲታዘዙን? አምላክ አዳም በግድ እንዲታዘዘው ማድረግ ይገባው ነበረን? አምላክን በግዴታ በምንታዘዝበት ዓለም ውስጥ ብንኖር ይበልጥ ደስተኞች እንሆን ነበርን? አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ ሕግጋት ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚፈልጉና የማይፈልጉ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ፈቅዷል። ራሱ በቆረጠው ጊዜ ክፉዎችን ማጥፋቱ አይቀርም።—2 ተሰ. 1:9, 10

አምላክ በጥበቡ አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል በቂ ጊዜ ፈቅዷል። (1) የይሖዋ አገዛዝ በጽድቅ ላይ የተመሠረተና ትክክለኛ የመሆኑ ጉዳይ በኤደን ውስጥ ጥያቄ ተነሥቶበታል። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:1–5) (2) በሰማይና በምድር የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ያላቸው የአቋም ፍጹምነት ጥያቄ ተነሥቶበታል። (ኢዮብ 1:6–11፤ 2:1–5፤ ሉቃስ 23:31) አምላክ ዓመፀኞቹን (ሰይጣንን፣ አዳምንና ሔዋንን) ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር፤ ነገር ግን ይህ እርምጃ ለተነሣው ጥያቄ መልስ መፍትሔ አይሆንም። አንድ ሰው ትክክለኛነቱን በጉልበት ሊያረጋግጥ አይችልም። የተነሡት ጥያቄዎች የሥነ ምግባር ጥያቄዎች ናቸው። አምላክ ረዘም ያለ ጊዜ የፈቀደው ለራሱ ለማረጋገጥ የፈለገው ነገር ኖሮ ሳይሆን የፈቀዱትን የማድረግ ነፃነት ያላቸው ፍጥረቶቹ ሁሉ በእርሱ አገዛዝ ላይ ማመፅ የሚያስከትለውን ውጤት ራሳቸው መመልከት እንዲችሉ ሲል ነው። በተጨማሪም በዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ ላይ ከየትኛው ወገን የሚሰለፉ መሆናቸውን እንዲያሳዩ አጋጣሚ ለመስጠት ፈልጎ ነው። እነዚህ ጉዳዮች እልባት ካገኙ በኋላ ማንም ፍጡር ዳግመኛ የጽንፈ ዓለሙን ሰላም እንዲያደፈርስ አይፈቀድለትም። የመላው ጽንፈ ዓለም የሥርዓት መስተካከል፣ ስምምነትና ደህንነት የተመካው በይሖዋ ስም መቀደስና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮች በሙሉ ለእርሱ ልባዊ የሆነ ክብር በመስጠታቸው ላይ ነው። (በተጨማሪ በገጽ 362, 363 ላይ “ሰይጣን ዲያብሎስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)

ምሳሌ:- አንድ ሰው በአካባቢው ኅብረሰተሰብ ፊት የቤተሰብ ራስነትህን ሥልጣን አለአግባብ እንደምትጠቀምበት፣ ልጆችህ ከአንተ ነፃ ሆነው የራሳቸውን ውሣኔ ቢያደርጉ እንደሚሻላቸው፣ የቤተሰብህ አባሎች የሚታዘዙህ በፍቅር ተነሣሥተው ሳይሆን ለምትሰጣቸው ቁሳዊ ጥቅሞች ብለው ብቻ እንደሆነ ቢናገር ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘት ከሁሉ የሚሻለው መንገድ ምን ይሆናል? የሐሰት ከሳሹን ተኩሶ መግደል የተነሣው ክስ ከአካባቢው ሰዎች አእምሮ እንዲፋቅ ያስችላልን? ከዚህ ይልቅ ልጆችህ ትክክለኛና አፍቃሪ የቤተሰብ ራስ መሆንህንና ልጆችህም አብረውህ የሚኖሩት ስለሚያፈቅሩህ እንደሆነ ራሳቸው እንዲመሰክሩልህ አጋጣሚ ብትሰጣቸው የተሻለ አይሆንምን? ከልጆችህ አንዳንዶቹ የከሰሰህን ሰው አምነው ከቤት ቢወጡና ሌላ ዓይነት የአኗኗር መንገድ ተከትለው ሕይወታቸውን ቢያበላሹ ቅን የሆኑ ተመልካቾች ልጆቹ የአንተን መመሪያ ቢከተሉ ኖሮ ይሻላቸው እንደነበር እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል።

አምላክ እስከ አሁን ክፋት እንዲኖር በመፍቀዱ በሆነ መንገድ ተጠቅመናልን?

2 ጴጥ. 3:9:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (ትዕግሥቱ እስከ እኛ ዘመን ድረስ ስለቆየ ንሥሐ ለመግባትና መልካምና ክፉ ስለሆኑ ነገሮች የየራሳችንን ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ለይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ለመታዘዝ የምንፈልግ መሆናችንን በተግባር ለማሳየት ችለናል።)

ሮሜ 9:14–24:- “እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም። . . . ነገር ግን እግዚአብሔር ቁጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ፣ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ፣ [ይህም ማለት ከዓላማው ጋር በመስማማት ለአንዳንዶች ምሕረት ለማሳየት ጊዜውን ይጠቀምበታል ማለት ነው] ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ [ማለትም የክፉ ሰዎችን መኖር ለተወሰነ ጊዜ ከታገሠ] እንዴት ነው? የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፣ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን።” (ስለዚህ አምላክ ከክርስቶስ ጋር ክብር የሚሰጣቸውን የሰማያዊ መንግሥት አባሎችን ለመምረጥ ጊዜ ለመፍቀድ ሲል የክፉዎችን ጥፋት አቆይቶታል። አምላክ ይህን በማድረጉ የሌሎች ፍትሕ ተጓድሏልን? አልተጓደለም፤ ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ሞገስ ለሚያገኙት ይህ ሁሉንም ሰዎች ለመባረክ ይሖዋ ያዘጋጀው ዝግጅት አንዱ ክፍል ነው። ከ⁠መዝሙር 37:10, 11 ጋር አወዳድር።)

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘አምላክ ይህን የመሰለ ክፋት የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ጥያቄዎ ጥሩ ነው። ብዙ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በዙሪያችን ባለው ክፋት መንፈሳቸው ታውኳል። (ዕን. 1:3, 13)’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘አምላክ ክፋት እንዲቀጥል የፈቀደው ግዴለሽ በመሆኑ አይደለም። ክፋትን የሚያስወግድበት ቀን እንደወሰነ ያረጋግጥልናል። (ዕን. 2:3)’ (2) ‘ሆኖም ያ ጊዜ ሲደርስ ከጥፋት ከሚተርፉት መካከል እንድንሆን በእኛ በኩል ምን ይፈለግብናል? (ዕን. 2:4 አዓት፤ ሶፎ. 2:3)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ይህንን ጥያቄ በማንሣትዎ ደስ ብሎኛል። ጥያቄው ብዙ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች የሚያሳስብ ነው። ለጥያቄዎ መልስ የሚሆኑ አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎች አሉኝ። (ከዚያም  በገጽ 428–430 ላይ ያሉትን አንዳንዶቹን መረጃዎች በአንድነት አንብቧቸው።)’

‘ይህን የሚያህሉ ዓመታት ካለፉ በኋላ አምላክ ሁኔታዎችን ለመለወጥ አንዳች ያደርጋል ብዬ አላምንም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘በአምላክ እንደሚያምኑ በመስማቴ ደስ ይለኛል። ብዙ ክፋት መኖሩና እኛ ከምንኖርበት ከረጅም ዘመን በፊት መጀመሩ በእርግጥ እውነት ነው። ሆኖም ግን ይህንን ጉዳይ አስበውበት ያውቃሉ . . . ? (አምላክ የታገሠበትን የጊዜ ርዝማኔ በተመለከተ  በገጽ 428 አንቀጽ 2 ላይ የቀረበውን ሐሳብ ተጠቀምበት።)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ቤት የመሥራት ችሎታ ያለው ሰው ለማጽዳት ደግሞ ይችላል ብዬ ብናገር ከእኔ ጋር እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ። . . . አምላክ መሬትን ስለፈጠረ እርሷን ለማጽዳት አስቸጋሪ ነገር አይሆንበትም። እስከ አሁን የቆየው ለምንድን ነው? ይህ መልስ በጣም የሚያረካ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እርስዎም ምን እንደሚያስቡ ይነግሩኛል። (ከዚያም  በገጽ 428–430 ላይ ያለውን ሐሳብ አንድ ላይ አንብቡት።)’