የቀድሞ አባቶችን ማምለክ
ፍቺ:- የቀድሞ አባቶች በማይታይ ዓለም ውስጥ በሕይወት ይኖራሉ፤ ስለሆነም ሕያዋን የሆኑትን ሰዎች ሊረዷቸው ወይም ሊጐዷቸው ይችላሉ፤ ስለዚህ እነርሱን ለማስደሰት (በአንድ ዓይነት ሥርዓት ወይም በሌላ መንገድ) አክብሮት ወይም አምልኮ መስጠት ይገባል የሚል እምነት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።
የሞቱት የቀድሞ አባቶች በሕይወት ያሉት የሚሠሩትን ሊያውቁና እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይችላሉን?
መክ. 9:5:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም።”
ኢዮብ 14:10, 21:- “ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፤ እርሱስ ወዴት አለ? ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም።”
መዝ. 49:10, 17–19:- “ብልሃተኞች እንዲሞቱ፣ ሰነፎችና ደንቆሮች በአንድነት እንዲጠፉ፣ ገንዘባቸውንም ለሌሎች እንዲተዉ አይቶአል። በሞተ ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፣ ክብሩም ከእርሱ በኋላ አይወርድምና። . . . ሆኖም ወደ አባቶቹ ትውልድ ይወርዳል፤ ለዘላለም ብርሃንን አያይም።”
በመሠዊያ ወይም በመቃብር ላይ የተቀመጠ ምግብ ምንም ሳይነካው እዚያው የተቀመጠበት ይቆይ የለምን? ይህስ ሙታን ከምግቡ ምንም ሊጠቀሙ እንደማይችሉ አያሳይምን?
በተጨማሪም “መናፍስትነት” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።
የሞቱት የቀድሞ አባቶች ጉዳት ያደርሱብናል ብለን የምንፈራበት ምክንያት ይኖራልን?
መክ. 9:5, 6:- “ሙታን . . . ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፣ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።”
ሰው ሥጋው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትኖር መንፈሳዊ አካል አለችውን?
ሕዝ. 18:4:- “እነሆ፣ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (በተጨማሪም ቁጥር 20ን ተመልከት።)
መዝ. 146:3, 4 አዓት:- “በአለቆችና በሰው ልጆች አትተማመኑ፣ መንፈሱ ይወጣል፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።”
ሳይንቲስቶችና የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች የሰው አካል ከሞተ በኋላ ሕያው ሆና የምትኖር አካል ስለመኖሯ ምንም ማረጋገጫ አላገኙም።
በተጨማሪ በገጽ 99–101 ላይ “ሞት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።
ልጆችህና የልጅ ልጆችህ በሕይወት ሳለህ አክብሮትና ፍቅር እንዲያሳዩህ ትመርጣለህ ወይስ ከሞትክ በኋላ በመቃብርህ ላይ አንዳንድ ሥርዓቶችን እንዲፈጽሙልህ?
ኤፌ. 6:2, 3:- “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።” (በመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች የሠለጠኑ ልጆች ወላጆቻቸው በሕይወት ሳሉ አክብሮት እያሳዩ የወላጆቻቸውን ልብ ደስ ያሰኛሉ።)
ምሳሌ 23:22:- “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።”
1 ጢሞ. 5:4:- “ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።”
መናፍስት ጠሪዎች ከሞቱት ሰዎች መልእክት ተቀብለናል ብለው ቢናገሩም መልእክቱን ያገኙት ከየት ነው?
ኢሳ. 8:19:- “እነርሱም:- የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፣ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?” (በእርግጥ በሞት ከተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ጋር የሚያገናኘን ድርጊት ቢሆን ኖሮ አምላክ እንዲህ ከመሰለው አድራጎት እንድንርቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጥ ነበርን?)
ሥራ 16:16:- “ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፣ የምዋርተኝነት መንፈስ [ጋኔን አዓት] የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።”
በተጨማሪ በገጽ 383, 384 ላይ “መናፍስትነት” በሚለው ሥር ተመልከት።
ማምለክ ያለብን ማንን ነው?
ሉቃስ 4:8:- “ኢየሱስም መልሶ:- ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው።”
ዮሐ. 4:23, 24:- “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”
የቤተሰብ አባሎች በሙሉ፣ የሞቱትም ጭምር፣ ዳግመኛ ለመገናኘት ስለ መቻላቸው ምን የወደፊት ተስፋ አለ?
ዮሐ. 5:28, 29:- “[“በመታሰቢያ መቃብር” አዓት] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”