ምዕራፍ 44
ጓደኞቻችን አምላክን የሚወዱ መሆን ይኖርባቸዋል
ጓደኞቻችን የሚባሉት ከእኛ ጋር ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ናቸው፤ አብዛኛውን ጊዜ ከእነሱ ጋር ማውራት ደስ ይለናል። ይሁን እንጂ ጥሩ ዓይነት ጓደኞች ሊኖሩን ይገባል። ከሁሉ የተሻለ ጓደኛ ወይም ወዳጅ ሊሆነን የሚችለው ማን ይመስልሃል?— አዎ፣ ይሖዋ አምላክ ነው።
በእርግጥ ከአምላክ ጋር ወዳጆች መሆን እንችላለን?— መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን የኖረው አብርሃም “የይሖዋ ወዳጅ” እንደነበረ ይናገራል። (ያዕቆብ 2:23) አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ የነበረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ አብርሃም አምላክን እንደታዘዘ ይገልጻል። አብርሃም በጣም ከባድ ትእዛዝ በተሰጠው ጊዜም እንኳን ሳይቀር ታዟል። ስለዚህ እኛም የይሖዋ ወዳጆች ለመሆን ከፈለግን አብርሃም እንዳደረገውና ታላቁ አስተማሪም ሁልጊዜ ያደርግ እንደነበረው አምላክን የሚያስደስት ነገር ማድረግ አለብን።—ዘፍጥረት 22:1-14፤ ዮሐንስ 8:28, 29፤ ዕብራውያን 11:8, 17-19
ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እያዘዝኳችሁ ያለውን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:14) ኢየሱስ ለሰዎች የተናገረው ከይሖዋ የተማረውን ነው፤ በመሆኑም ኢየሱስ ይህን ሲናገር ወዳጆቹ አድርጎ የሚመርጠው አምላክ ያዘዛቸውን የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሆነ መግለጹ ነበር። አዎ፣ የኢየሱስ ወዳጆች ወይም ጓደኞች በሙሉ አምላክን የሚወዱ ናቸው።
የታላቁ አስተማሪ የቅርብ ጓደኞች ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ በዚህ መጽሐፍ ገጽ 75 ላይ በሥዕል የምታያቸው ሐዋርያቱ ናቸው። የኢየሱስ ሐዋርያት ከእሱ ጋር ይጓዙ የነበረ ከመሆኑም በላይ በስብከቱ ሥራ ይረዱት ነበር። ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ነበር። አብረው ይበሉ ነበር። አብረው ሆነው ስለ አምላክ ያወሩ ነበር። ሌሎች ነገሮችንም አብረው ይሠሩ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሌሎች ብዙ ጓደኞች ነበሩት። እነሱ ጋር ያርፍ የነበረ ሲሆን አብሯቸው ጥሩ ጊዜ ያሳልፍ ነበር።
ዮሐንስ 11:1, 5, 11) ኢየሱስ ይህን ቤተሰብ የወደደውና ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተው የነበረው ይሖዋን ይወዱና ያገለግሉ ስለነበረ ነው።
ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ቢታንያ በምትባል አነስተኛ ከተማ ውስጥ አንድ ቤተሰብ ይኖር የነበረ ሲሆን ኢየሱስ ከዚህ ቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይወድ ነበር። የዚህ ቤተሰብ አባላት እነማን እንደሆኑ ታስታውሳለህ?— ማርያም፣ ማርታና ወንድማቸው አልዓዛር ናቸው። ኢየሱስ፣ አልዓዛርን ወዳጄ ብሎ ጠርቶታል። (ይህ ማለት ግን ኢየሱስ አምላክን ለማያገለግሉ ሰዎች ደግ አልነበረም ማለት አይደለም። ለእነሱም ቢሆን ደግ ነበር። እንዲያውም ቤታቸው ድረስ ሄዶ ከእነሱ ጋር በልቷል። በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ ሰዎች ኢየሱስን “የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ” ብለውት ነበር። (ማቴዎስ 11:19) ኢየሱስ ወደነዚህ ሰዎች ቤት የሄደው አኗኗራቸውን ስለወደደው አይደለም። ቤታቸው ድረስ ይሄድ የነበረው ስለ ይሖዋ ሊነግራቸው ፈልጎ ነው። መጥፎ ድርጊት መፈጸማቸውን ትተው አምላክን እንዲያገለግሉ ሊረዳቸው ይጥር ነበር።
አንድ ቀን በኢያሪኮ ከተማ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ተፈጽሟል። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በኢያሪኮ ከተማ በኩል እያለፈ ነበር። በዚያም ብዙ ሕዝብ የነበረ ሲሆን በሕዝቡ መካከል ዘኬዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። ዘኬዎስ ኢየሱስን ማየት ፈልጎ ነበር። ነገር ግን ዘኬዎስ ቁመቱ አጭር ስለነበርና በቦታው ብዙ ሰዎች ስለነበሩ
ኢየሱስን ማየት አልቻለም። ስለዚህ ኢየሱስን በመንገድ ሲያልፍ በደንብ ለማየት ሮጦ ወደፊት በመሄድ ዛፍ ላይ ወጣ።ኢየሱስ ዛፉ አጠገብ ሲደርስ ቀና ብሎ ተመለከተና ‘ዛሬ ወደ ቤትህ ስለምመጣ ቶሎ ውረድ’ አለው። ዘኬዎስ ግን ብዙ መጥፎ ነገሮች የሠራ ሀብታም ሰው ነበር። ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቤት መሄድ የፈለገው ለምንድን ነው?—
ኢየሱስ ወደ ቤቱ የሄደው የዘኬዎስን አኗኗር ስለወደደው አይደለም። እዚያ የሄደው ለዘኬዎስ ስለ አምላክ ሊነግረው ነው። ኢየሱስ ይህ ሰው እሱን ለማየት ምን ያህል ጥረት እንዳደረገ ተመልክቷል። ስለዚህ ዘኬዎስ የሚነገረውን ሊሰማ እንደሚችል አውቆ ነበር። ሰዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው አምላክ የሚናገረውን ነገር ለዚህ ሰው ለመንገር ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።
ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘ?— ዘኬዎስ ኢየሱስ ያስተማረውን ነገር ወደደው። ሰዎችን ሲያታልል በመቆየቱ በጣም ከማዘኑም በላይ አግባብ ባልሆነ መንገድ የወሰደውን ገንዘብ ለመመለስ ቃል ገባ። ይህን ካደረገ በኋላ የኢየሱስ ተከታይ ይሆናል። ኢየሱስና ዘኬዎስ ወዳጆች ሊሆኑ የሚችሉት ይህ ከሆነ ብቻ ነበር።—ሉቃስ 19:1-10
የታላቁን አስተማሪ ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ወዳጆቻችን ያልሆኑ ሰዎች ቤት እንሄዳለን ማለት ነው?— አዎ። ነገር ግን ወደ ቤታቸው የምንሄደው
አኗኗራቸውን ስለምንወድ አይደለም። በተጨማሪም ከእነሱ ጋር ሆነን መጥፎ ነገር አንሠራም። ወደ ቤታቸው የምንሄደው ስለ አምላክ ለመንገር ነው።የቅርብ ጓደኞቻችን ከምንላቸው ሰዎች ጋር ግን አብረናቸው ጊዜ የምናሳልፍ ሲሆን ከእነሱ ጋር መሆን ያስደስተናል። ጥሩ ዓይነት ጓደኞች እንዲሆኑልን ከተፈለገ አምላክ የሚወዳቸው ዓይነት ሰዎች መሆን አለባቸው። አንዳንዶች ይሖዋ ማን እንደሆነ እንኳን አያውቁ ይሆናል። ነገር ግን ስለ እሱ ለመማር ከፈለጉ ልንረዳቸው እንችላለን። ከዚያ በኋላ እነሱም ልክ እንደ እኛ ይሖዋን የሚወዱ ሲሆኑ የቅርብ ጓደኞቻችን ሊሆኑ ይችላሉ።
አንድ ሰው ጥሩ ጓደኛ ሊሆን ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ የሚቻልበት ሌላም መንገድ አለ። ይህም የሚያደርገውን ነገር በመመልከት ነው። በሌሎች ሰዎች ላይ መጥፎ ነገር እያደረገ በሠራው ነገር ይሥቃል? ይህ ተገቢ ይመስልሃል?— ሁልጊዜ በገዛ እጁ ችግር ውስጥ ይገባል? እንዲህ ከመሰለ ሰው ጋር ገጥመን ችግር ውስጥ መግባት አንፈልግም፣ አይደል? ይህ ሰው መጥፎ ነገር ሲሠራ ባይያዝም እንኳ አምላክ ግን ያየዋል፣ አይደል?— እንዲህ ዓይነት ነገር የሚያደርጉ ሰዎች ለእኛ ጥሩ ጓደኞች ሊሆኑን የሚችሉ ይመስልሃል?—
መጽሐፍ ቅዱስህን ግለጥና ጓደኞች አድርገን የምንመርጣቸው ሰዎች በሕይወታችን ላይ ምን ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ እንመልከት። ጥቅሱ የሚገኘው በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 33 ላይ ነው። ጥቅሱን አገኘኸው?— እንዲህ ይላል:- “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።” ይህ ማለት ከመጥፎ ሰዎች ጋር የምንውል ከሆነ እኛም መጥፎ ልንሆን እንችላለን ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ ጓደኞች ጥሩ ልማድ እንድናዳብር እንደሚረዱን የተረጋገጠ ነው።
በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማበላሸት አንፈልግም፣ አይደል?— ስለዚህ ጓደኝነት መመሥረት ያለብን አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ብቻ ነው።
ጥሩ ዓይነት ጓደኞች መምረጥ አስፈላጊ እንደሆነ መዝሙር 119:115፤ ምሳሌ 13:20፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22 እና 1 ዮሐንስ 2:15 ላይ ተገልጿል።