ትምህርት 2
አምላክ ማን ነው?
1. አምላክን ማምለክ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
እውነተኛው አምላክ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው። እሱ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም። (መዝሙር 90:2) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምሥራች የመጣው ከእሱ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ሕይወት የሰጠን አምላክ ስለሆነ ማምለክ የሚኖርብን እሱን ብቻ ነው።—ራእይ 4:11ን አንብብ።
2. ፈጣሪያችን ምን ዓይነት አምላክ ነው?
አምላክ መንፈሳዊ አካል በመሆኑ ማንም ሰው አይቶት አያውቅም፤ መንፈሳዊ አካል ነው ሲባል በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት እጅግ የላቀ ነው ማለት ነው። (ዮሐንስ 1:18፤ 4:24) ያም ቢሆን የአምላክን ባሕርያት ከሠራቸው ነገሮች በግልጽ መመልከት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ዓይነታቸው ብዙ የሆነው ፍራፍሬዎችና አበቦች አምላክ ምን ያህል አፍቃሪና ጥበበኛ እንደሆነ ያሳዩናል። የጽንፈ ዓለም ስፋት ደግሞ የአምላክ ኃይል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።—ሮም 1:20ን አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ደግሞ ስለ አምላክ ባሕርያት ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ምን እንደሚወድና ምን እንደሚጠላ እንዲሁም ሰዎችን እንዴት እንደሚይዝና የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ምን እርምጃ እንደሚወስድ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።—መዝሙር 103:7-10ን አንብብ።
3. አምላክ ስም አለው?
ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:9) አምላክ ብዙ የማዕረግ ስሞች ቢኖሩትም የግል ስሙ ግን አንድ ብቻ ነው። የዚህ ስም አነባበብ ከቋንቋ ቋንቋ ይለያያል። ለምሳሌ በአማርኛ “ይሖዋ” ወይም “ያህዌ” ተብሎ ይጠራል።—መዝሙር 83:18ን አንብብ።
የአምላክ ስም ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንዲወጣ ተደርጎ ጌታ ወይም አምላክ በሚሉት የማዕረግ ስሞች ተተክቷል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ሲጻፍ የአምላክን ስም 7,000 ጊዜ ያህል ይዞ ነበር። ኢየሱስ፣ ሰዎችን ስለ አምላክ በማስተማር የአምላክ ስም እንዲታወቅ አድርጓል።—ዮሐንስ 17:26ን አንብብ።
አምላክ ስም አለው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት
4. ይሖዋ ስለ እኛ ያስባል?
በአሁኑ ጊዜ ሥቃይና መከራ መብዛቱ አምላክ ስለ እኛ እንደማያስብ የሚያሳይ ነው? አንዳንድ ሰዎች አምላክ ሥቃይ እንዲደርስብን የሚያደርገው እኛን ለመፈተን እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይሁንና ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው።—ያዕቆብ 1:13ን አንብብ።
አምላክ፣ ነፃ ምርጫ የማድረግ መብት በመስጠት የሰው ልጆችን አክብሯቸዋል። ታዲያ አምላክን ለማገልገል የመምረጥ ነፃነት በማግኘታችን አመስጋኝ ልንሆን አይገባም? (ኢያሱ 24:15) ይሁንና ብዙዎች በሌሎች ላይ መጥፎ ነገር ለማድረግ ስለመረጡ መከራና ሥቃይ በዝቷል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ግፍ ሲመለከት ልቡ ያዝናል።—ዘፍጥረት 6:5, 6ን አንብብ።
ይሖዋ ስለ እኛ የሚያስብ አምላክ ነው። ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ ይፈልጋል። በቅርቡ ይሖዋ መከራንም ሆነ ለመከራ መንስኤ የሚሆኑትን ሁሉ ጠራርጎ ያጠፋቸዋል። እስከዚያው ድረስ ግን መከራና ሥቃይ እንዲደርስብን የፈቀደበት በቂ ምክንያት አለው። አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ትምህርት 8 ላይ እንመለከታለን።—2 ጴጥሮስ 2:9ን እና 3:7, 13ን አንብብ።
5. ወደ አምላክ ይበልጥ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ በጸሎት ከእሱ ጋር በመነጋገር ወደ እሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። ከእያንዳንዳችን ጋር መቀራረብ ይፈልጋል። (መዝሙር 65:2፤ 145:18) ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። አንዳንድ ጊዜ ብንሳሳትም እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት ያደንቃል። በመሆኑም ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንችላለን።—መዝሙር 103:12-14ን እና ያዕቆብ 4:8ን አንብብ።
ሕይወት የሰጠን ይሖዋ በመሆኑ ከማንም በላይ እሱን ልንወደው ይገባል። (ማርቆስ 12:30) ስለ እሱ የበለጠ በማወቅና እንድታደርግ የሚፈልግብህን ነገር በመፈጸም ለእሱ ያለህን ፍቅር ማሳየት ትችላለህ፤ ይህን ማድረግህ ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል።—1 ጢሞቴዎስ 2:4ን እና 1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።