ምዕራፍ 14
በሁሉም ነገር ሐቀኞች ሁኑ
“በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18
1, 2. ሐቀኞች ለመሆን ጥረት ስናደርግ ይሖዋ ምን ይሰማዋል?
አንድ ትንሽ ልጅ ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ ሲመለስ መንገድ ላይ የገንዘብ ቦርሳ ወድቆ አገኘ፤ በቦርሳው ውስጥ ብዙ ገንዘብ ነበረ። ልጁ ምን ያደርግ ይሆን? ገንዘቡን ሊወስደው ይችል የነበረ ቢሆንም ለባለቤቱ መለሰለት። የዚህ ልጅ እናት ልጇ ምን እንዳደረገ ስትሰማ በጣም እንደምትኮራበት ጥያቄ የለውም።
2 አብዛኞቹ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ሐቀኛ ሲሆኑ ደስ ይላቸዋል። በሰማይ ያለው አባታችን ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው፤ በመሆኑም ሐቀኞች ስንሆን ደስ ይለዋል። (መዝሙር 31:5) እኛም “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት [በመኖር]” እሱን ማስደሰት እንፈልጋለን። (ዕብራውያን 13:18) ይሁን እንጂ ሐቀኛ መሆን ተፈታታኝ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል እስቲ አራቱን እንመልከት። ከዚያም እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንመለከታለን።
ለራሳችን ሐቀኛ መሆን
3-5. (ሀ) ራሳችንን ልናታልል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ለራሳችን ሐቀኛ ለመሆን ምን ይረዳናል?
3 ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሐቀኛ ለመሆን፣ በቅድሚያ ለራሳችን ሐቀኛ መሆን ይኖርብናል። ሆኖም ይህን ማድረግ ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሎዶቅያ ጉባኤ የነበሩት ወንድሞች፣ አካሄዳቸው አምላክን የማያስደስት ቢሆንም አምላክን እያስደሰቱ እንደሆነ በማሰብ ራሳቸውን አታልለው ነበር። (ራእይ ) እኛም ትክክለኛ ማንነታችንን በተመለከተ ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። 3:17
4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው።” (ያዕቆብ 1:26) አንዳንዶች መልካም ነገሮችን እስካደረጉ ድረስ ተገቢ ያልሆነ ወይም አሽሙር የተቀላቀለበት ነገር ቢናገሩ አሊያም ቢዋሹ አምላክ እንደማያዝንባቸው ይሰማቸዋል፤ እንዲህ ብሎ ማሰብ ግን ራስን ማታለል ነው። ታዲያ ራሳችንን እንዳናታልል ምን ይረዳናል?
5 በመስታወት ራሳችንን ስንመለከት ውጫዊ ገጽታችንን ማየት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ደግሞ ውስጣዊ ማንነታችንን ማስተዋል እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎናችንን ለይተን ለማወቅ ይረዳናል። በአስተሳሰባችን፣ በድርጊታችን እንዲሁም በንግግራችን ላይ ምን ማስተካከያዎች ማድረግ እንዳለብን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን። (ያዕቆብ 1:23-25ን አንብብ።) ምንም ድክመት እንደሌለብን የምናስብ ከሆነ ግን አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ አንችልም። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:40፤ ሐጌ 1:5) እውነተኛ ማንነታችንን ለማወቅ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ጸሎት ነው። ይሖዋ ውስጣችንን እንዲመረምረው እንዲሁም ድክመታችንን ለማስተዋልና ለማስተካከል እንዲረዳን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። (መዝሙር 139:23, 24) “ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋልና፤ ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው” የሚለውን ጥቅስ እናስታውስ።—ምሳሌ 3:32
በቤተሰብ ውስጥ ሐቀኛ መሆን
6. ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ሐቀኛ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
6 በቤተሰብ ውስጥ ሐቀኝነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ሐቀኛ ከሆኑ ትዳራቸው ከስጋት ነፃ ይሆናል፤ እንዲሁም አንዳቸው በሌላው ይተማመናሉ። አንድ ሰው ለትዳሩ ሐቀኛ አለመሆኑ የሚታይባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ አንድ ባለትዳር፣ ሌላ ሴት ቢያሽኮረምም ወይም የብልግና ምስሎችን ቢመለከትና ጽሑፎችን ቢያነብ አሊያም ከሌላ ሴት ጋር በድብቅ የፍቅር ግንኙነት ቢመሠርት ሐቀኝነቱን እያጎደለ ነው። መዝሙራዊው “አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር አልቀራረብም፤ ማንነታቸውን ከሚደብቁም እርቃለሁ” ብሏል። (መዝሙር 26:4) በልብህም እንኳ ለትዳር ጓደኛህ ታማኝ ካልሆንክ ይህ ትዳርህን ሊያናጋው ይችላል።
7, 8. ወላጆች የሐቀኝነትን አስፈላጊነት ለልጆቻቸው ለማስተማር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?
7 ወላጆች ሐቀኝነት አስፈላጊ መሆኑን ለልጆቻቸውም ሊያስተምሯቸው ይገባል። ይህን ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችን መጠቀም ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሐቀኛ ያልነበሩ ሰዎች ታሪክ ተጠቅሷል፤ ከእነዚህ መካከል የራሱ ያልሆነውን ንብረት የሰረቀውን አካንን፣ ገንዘብ ለማግኘት ሲል የዋሸውን ግያዝን እንዲሁም ገንዘብ ይሰርቅ የነበረውንና በኋላም ኢየሱስን በ30 የብር ሳንቲሞች አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።—ኢያሱ 6:17-19፤ 7:11-25፤ 2 ነገሥት 5:14-16, 20-27፤ ማቴዎስ 26:14, 15፤ ዮሐንስ 12:6
8 መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኛ የሆኑ በርካታ ሰዎችን ታሪክም ይዟል፤ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑት ከእነዚህ ሰዎች መካከል ያዕቆብ፣ ዮፍታሔና ሴት ልጁ እንዲሁም ኢየሱስ ይገኙበታል። ያዕቆብ፣ ልጆቹ ያገኙትን ገንዘብ እንዲመልሱ አሳስቧቸዋል፤ ዮፍታሔና ሴት ልጁ ለአምላክ የገቡትን ቃል ጠብቀዋል፤ ኢየሱስም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንኳ እውነቱን ተናግሯል። (ዘፍጥረት 43:12፤ መሳፍንት 11:30-40፤ ዮሐንስ 18:3-11) እነዚህ ምሳሌዎች ልጆች የሐቀኝነትን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል።
9. ወላጆች ሐቀኞች መሆናቸው ልጆቻቸውን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
9 “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም? አንተ ‘አትስረቅ’ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?” ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ለወላጆች ትልቅ ትምህርት ይዟል። (ሮም 2:21) ወላጆች ለልጆቻቸው የሚነግሯቸውን ነገር እነሱ ራሳቸው የማያደርጉት ከሆነ ልጆች ይህን ያስተውላሉ። ልጆቻችንን ሐቀኛ መሆን እንዳለባቸው እያስተማርናቸው እኛ ራሳችን ሐቀኞች ካልሆንን ልጆቹ ግራ ይጋባሉ። ልጆች ወላጆቻቸው በጥቃቅን ነገሮችም እንኳ እንደሚዋሹ ከተመለከቱ እነሱም መዋሸታቸው አይቀርም። (ሉቃስ 16:10ን አንብብ።) በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች ወላጆቻቸው ሐቀኞች እንደሆኑ ከተመለከቱ እነሱም አድገው የራሳቸው ልጆች ሲኖሯቸው ሐቀኛ ወላጆች ይሆናሉ።—ምሳሌ 22:6፤ ኤፌሶን 6:4
በጉባኤ ውስጥ ሐቀኛ መሆን
10. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ስንጨዋወት ሐቀኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
10 ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነትም ሐቀኞች መሆን አለብን። ከሌሎች ጋር የምናደርገው ጭውውት ሳናስበው ወደ ሐሜት ይባስ ብሎም ስም ወደ ማጥፋት ሊቀየር ይችላል። አንድ ነገር እውነት መሆኑን ሳናጣራ ለሌሎች የምናወራው ከሆነ ውሸት እያዛመትን ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ‘ከንፈራችንን መግታታችን’ በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 10:19) ሐቀኛ እንሆናለን ሲባል የምናስበውን፣ የምናውቀውን ወይም የሰማነውን ነገር ሁሉ እናወራለን ማለት አይደለም። ልንናገር ያሰብነው ነገር እውነት ቢሆንም እንኳ ጉዳዩ አይመለከተን ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ ጉዳዩን ማውራት አላስፈላጊ ወይም ሌሎችን የሚጎዳ ሊሆን ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 4:11) አንዳንድ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ከተናገሩ በኋላ “እውነቱን ነው የተናገርኩት” የሚል ሰበብ ያቀርባሉ። እኛ ግን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ንግግራችን ምንጊዜም ለዛ ያለውና ደግነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን እንፈልጋለን።—ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።
11, 12. (ሀ) ኃጢአት የሠራ አንድ ግለሰብ ጉዳዩን ቢደብቅ የባሰ ስህተት የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ጓደኛችን ከባድ ስህተት እንደሠራ ብናውቅ ምን ብለን ማሰብ አይኖርብንም? ለምንስ? (ሐ) ለይሖዋ ድርጅት ሐቀኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ጉባኤውን እንዲንከባከቡ ለሽማግሌዎች ኃላፊነት ሰጥቷል። ሐቀኞች ስንሆን ሽማግሌዎች እኛን መርዳት ይቀላቸዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ ታመህ ሐኪም ጋ ብትሄድ አንዳንድ የሕመምህን ምልክቶች ከሐኪሙ ትደብቃለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሐኪሙ ተገቢውን ሕክምና ሊያደርግልህ አይችልም። በተመሳሳይም ከባድ ስህተት ከሠራን ስለ ጉዳዩ መዋሸት አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ወደ ሽማግሌዎች ሄደን ሐቁን ልንነግራቸው ይገባል። (መዝሙር 12:2፤ የሐዋርያት ሥራ ) እስቲ ሌላ ሁኔታ ደግሞ እንመልከት፦ አንድ ጓደኛህ ከባድ ስህተት እንደሠራ ብታውቅ ምን ታደርጋለህ? ( 5:1-11ዘሌዋውያን 5:1) ‘የጓደኛዬን ሚስጥር እንዴት አወጣለሁ?’ ትላለህ? ወይስ ጓደኛህ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማስተካከልና ለማጠናከር የሚያስፈልገውን እርዳታ ሽማግሌዎች እንደሚሰጡት በማስታወስ ጉዳዩን ትነግራቸዋለህ?—ዕብራውያን 13:17፤ ያዕቆብ 5:14, 15
12 የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት በምናደርግበት ጊዜም ለይሖዋ ድርጅት ሐቀኞች መሆን አለብን። በተጨማሪም በአቅኚነት ወይም በሌላ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ማመልከቻ ስንሞላ ሐቀኞች ልንሆን ይገባል።—ምሳሌ 6:16-19ን አንብብ።
13. ከእምነት ባልንጀራችን ጋር በሥራ የምንገናኝ ከሆነ በየትኞቹ መንገዶች ሐቀኞች ለመሆን መጣር ይኖርብናል?
13 ክርስቲያኖች ከሰብዓዊ ሥራ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ከአምልኳቸው ጋር ላለመቀላቀል መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ወይም በአገልግሎት ላይ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ እንቆጠባለን። በተጨማሪም ከሰብዓዊ ሥራ ጋር በተያያዘ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት መሞከር የለብንም። የይሖዋ ምሥክሮች ቀጥረህ የምታሠራ ከሆነ የተስማማችሁበትን ደሞዝ በጊዜው ልትከፍላቸው ይገባል፤ እንዲሁም በሕግ የተፈቀዱላቸውን ጥቅማ ጥቅሞች (ለምሳሌ የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን ወይም የዓመት ፈቃድ መስጠት) ልትከለክላቸው አይገባም። (1 ጢሞቴዎስ 5:18፤ ያዕቆብ 5:1-4) በሌላ በኩል ደግሞ አሠሪህ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ ከሌሎች ሠራተኞች የተለየ ነገር እንዲደረግልህ አትጠብቅ። (ኤፌሶን 6:5-8) በተስማማችሁት መሠረት ሰዓትህን አክብረህ የሚጠበቅብህን ሥራ ለመሥራት ጥረት አድርግ።—2 ተሰሎንቄ 3:10
14. ክርስቲያኖች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አብረው መሥራት ከመጀመራቸው በፊት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
14 ከአንድ ወንድም ወይም ከአንዲት እህት ጋር አብረን ለመሥራት ብናስብስ? ለምሳሌ በሽርክና አብረን መሥራት አሊያም ከእምነት ባልንጀራችን መበደር እንፈልግ ይሆናል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ በጣም ሊጠቅም የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አለ፤ ይኸውም ስምምነቱን በዝርዝር መጻፍ ነው! ነቢዩ ኤርምያስ መሬት ሲገዛ፣ የውል ሰነዱን በሁለት ቅጂዎች አዘጋጅቷል፤ ከዚያም አንደኛው ሰነድ ላይ ምሥክሮች ካስፈረመ በኋላ ሁለቱንም ሰነዶች ለወደፊት ማመሣከሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ አስቀምጧቸዋል። (ኤርምያስ 32:9-14፤ በተጨማሪም ዘፍጥረት 23:16-20ን ተመልከት።) አንዳንዶች ስምምነቱን በጽሑፍ ማስፈር ወንድማቸውን እንደማያምኑት የሚያሳይ ድርጊት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ስምምነቱን በጽሑፍ ማስፈር አለመግባባት፣ ቅር መሰኘትና ውዝግብ እንዳይኖር ያደርጋል። ክርስቲያኖች ከማንኛውም የንግድ ስምምነት የበለጠ የጉባኤውን ሰላም ሊያስቀድሙ እንደሚገባ ማስታወስ አለባቸው።—1 ቆሮንቶስ 6:1-8፤ ተጨማሪ ሐሳብ 30ን ተመልከት።
በንግዱ ዓለምና በሌሎች መስኮች ሐቀኛ መሆን
15. ይሖዋ ሐቀኝነት የጎደለው የንግድ እንቅስቃሴን በተመለከተ ምን ይሰማዋል?
15 የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ከሁሉም ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ሐቀኞች መሆን አለብን። ሐቀኛ መሆናችን በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። “አባይ ሚዛን በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 11:1፤ 20:10, 23) በጥንት ዘመን ሰዎች ሲገበያዩ ብዙውን ጊዜ ሚዛን ይጠቀሙ ነበር። ሆኖም አንዳንድ ነጋዴዎች የተዛባ ሚዛን በመጠቀም አሊያም ከተገቢው በላይ በማስከፈል ደንበኞቻቸውን ያጭበረብሩ ነበር። በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ከንግድ ጋር በተያያዘ ሐቀኝነትን ማጉደል በጣም የተለመደ ነው። ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት ጥንትም ሆነ ዛሬ ያው ነው፤ ማጭበርበርን ይጠላል።
16, 17. ከየትኞቹ የተለመዱ የማጭበርበር ድርጊቶች መራቅ አለብን?
16 ሁላችንም ሐቀኝነታችንን ለማጉደል የምንፈተንባቸው ሁኔታዎች ያጋጥሙናል፤ ለምሳሌ የሥራ ማመልከቻ ስናስገባ፣ መንግሥት ያዘጋጃቸውን ቅጾች ስንሞላ ወይም የትምህርት ፈተና ስንወስድ ሐቀኝነታችን ይፈተናል። ብዙዎች መዋሸት፣ መረጃዎችን አጋንኖ ማቅረብ አሊያም የሚያሳስት ምላሽ መስጠት ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል። ይህ መሆኑ አያስገርመንም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ጥሩ ነገር የማይወዱ” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
17 በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚሳካላቸው የሚመስልበት ጊዜ አለ። (መዝሙር 73:1-8) እንዲያውም አንድ ክርስቲያን ሐቀኛ በመሆኑ ምክንያት ሥራውን ሊያጣ ወይም ሊጭበረበር ይችላል፤ አሊያም ደግሞ የሥራ ባልደረቦቹ ያስቸግሩት ይሆናል። ይሁንና ሐቀኛ መሆን ፈጽሞ የማያስቆጭ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ሐቀኛ መሆን የሚያስገኛቸው በረከቶች
18. ጥሩ ስም ውድ ነገር ነው የምንለው ለምንድን ነው?
18 ‘ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት ሰው ነው’ የሚል ስም ማትረፍ በዛሬው ጊዜ በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ስም ለማትረፍ የሚያስችል አጋጣሚ አለን። (ሚክያስ 7:2) እርግጥ ነው፣ ሐቀኛ በመሆንህ ምክንያት አንዳንዶች ያሾፉብህ ይባስ ብሎም እንደ ሞኝ ይቆጥሩህ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ሐቀኛ በመሆንህ የሚያደንቁህ እንዲሁም እምነት የሚጥሉብህ ሰዎች ይኖራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚታወቁት ሐቀኞች በመሆናቸው ነው። አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኞች እንደሆኑ ስለሚያውቁ እነሱን መቅጠር ይመርጣሉ። አንዳንድ ሠራተኞች ሐቀኝነታቸውን በማጉደላቸው ምክንያት ከሥራቸው ሲባረሩ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ብዙውን ጊዜ በሥራቸው መቀጠል ችለዋል።
19. ሐቀኛ መሆን ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
19 በሁሉም ነገር ሐቀኛ መሆናችን ጥሩ ሕሊና እና ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን ያደርጋል። “ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እናምናለን” በማለት የጻፈውን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። (ዕብራውያን 13:18) ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ አፍቃሪ የሆነው አባትህ ይሖዋ በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ያስተውላል እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—መዝሙር 15:1, 2ን እና ምሳሌ 22:1ን አንብብ።