ምዕራፍ 17
ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
“እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ . . . ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ [ኑሩ]።”—ይሁዳ 20, 21
1, 2. ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ሁላችንም ጤነኞችና ጠንካሮች መሆን እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። በመሆኑም ጥሩ ምግብ ለመመገብ፣ አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲሁም ሰውነታችንን ለመንከባከብ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። እርግጥ ነው፣ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ጥረት ይጠይቃል፤ ያም ቢሆን ውጤቱ ስለሚያስደስተን ጥረት ማድረጋችንን አናቋርጥም። በሌላ በኩል ደግሞ የአካላዊ ጤንነታችንን ያህል ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ አለ።
2 ስለ ይሖዋ ለማወቅ በምናደርገው ጥረት ጥሩ ጅምር ኖሮን ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ከእሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ይበልጥ እያጠናከርን መሄድ ያስፈልገናል። ይሁዳ “ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ [ኑሩ]” በማለት ክርስቲያኖችን የመከረ ሲሆን ይህን ማድረግ የሚችሉበትን መንገድም አብራርቷል፤ “እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ” ብሏል። (ይሁዳ 20, 21) ታዲያ ጠንካራ እምነት መገንባት የምንችለው እንዴት ነው?
ምንጊዜም እምነታችሁን ገንቡ
3-5. (ሀ) ሰይጣን ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች ምን እንዲሰማህ ይፈልጋል? (ለ) ስለ ይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን አመለካከት አለህ?
3 የይሖዋ መመሪያዎች እጅግ ጠቃሚ እንደሆኑ ከልብህ ማመንህ አስፈላጊ ነው። ሰይጣን፣ የአምላክ መሥፈርቶች በጣም ጥብቅ እንደሆኑ እንዲሁም ትክክል ወይም ስህተት የሆኑትን ነገሮች ራስህ ብትወስን ይበልጥ ደስተኛ እንደምትሆን ሊያሳምንህ ይፈልጋል። ሰይጣን፣ የሰው ልጆች እንዲህ ያለ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ጥረት ማድረግ የጀመረው ከኤደን ገነት አንስቶ ነው። (ዘፍጥረት 3:1-6) ዛሬም ቢሆን ይህን ጥረቱን አፋፍሞ ቀጥሏል።
4 ሆኖም ሰይጣን የሚናገረው ነገር ትክክል ነው? የይሖዋ መሥፈርቶች በጣም ጥብቅ ናቸው? በፍጹም። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ የሚያምር መናፈሻ ውስጥ እየተንሸራሸርክ ነው እንበል። መናፈሻው ውስጥ በረጅም አጥር የተከለለ አንድ ቦታ እንዳለ አስተዋልክ። አጥሩ፣ መናፈሻው ውስጥ ወደፈለግከው ቦታ እንዳትሄድ እንደሚገድብህ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ብለህ እያሰብክ ሳለ በአጥር ከተከለለው ቦታ ውስጥ አንድ አንበሳ ሲያገሳ ሰማህ። በዚህ ጊዜ ስለ አጥሩ ያለህ አመለካከት እንደሚቀየር ጥርጥር የለውም። አጥሩ በመሠራቱ ደስተኛ መሆንህ አይቀርም፤ ምክንያቱም የአንበሳው ራት ከመሆን ይጠብቅሃል! ዲያብሎስ ከአንበሳው፣ የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ደግሞ ከዚህ አጥር ጋር ይመሳሰላሉ። የአምላክ ቃል “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” በማለት ያስጠነቅቀናል።—1 ጴጥሮስ 5:8
5 ይሖዋ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ይፈልጋል። በሰይጣን እንድንታለል አይፈልግም። ጥበቃ የሚሆኑልን እንዲያውም ደስተኞች እንድንሆን የሚረዱን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሰጠን ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 6:11) ያዕቆብ “ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው . . . በሚያደርገውም ነገር ደስተኛ ይሆናል” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 1:25
6. የይሖዋ መመሪያዎች ጠቃሚ መሆናቸውን እንድንተማመን ምን ሊረዳን ይችላል?
6 የይሖዋን መመሪያዎች ስንከተል የተሻለ ሕይወት ይኖረናል፤ ከአምላክ ጋር ያለን ወዳጅነትም ይበልጥ ይጠናከራል። ለምሳሌ፣ ወደ እሱ አዘውትረን እንድንጸልይ ያቀረበልንን ግብዣ ስንቀበል እንጠቀማለን። (ማቴዎስ 6:5-8፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) ለአምልኮ አንድ ላይ እንድንሰበሰብ፣ እርስ በርስ እንድንበረታታ እንዲሁም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ ይሖዋ የሰጠንን መመሪያ ስንታዘዝም ደስተኞች እንሆናለን። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ገላትያ 6:2፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እነዚህን ነገሮች ማድረጋችን እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን እንደረዳን ስንመለከት ደግሞ የይሖዋ መመሪያዎች ጠቃሚ እንደሆኑ ይበልጥ እንተማመናለን።
7, 8. ወደፊት ሊያጋጥሙን የሚችሉ ፈተናዎችን እያሰብን እንዳንጨነቅ ምን ይረዳናል?
7 ወደፊት ከባድ የእምነት ፈተናዎች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ በማሰብ እንጨነቅ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ አስታውስ፦ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ። ትእዛዛቴን ብትሰማ ምንኛ መልካም ነው! እንዲህ ብታደርግ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ ይሆናል።”—ኢሳይያስ 48:17, 18
8 ይሖዋን የምንታዘዝ ከሆነ ሰላማችን መቼም ቢሆን እንደማይደርቅ ወንዝ፣ ጽድቃችን ደግሞ ምንጊዜም ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንደሚመጣ የባሕር ሞገድ ይሆናል። በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ለአምላክ ታማኝ መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—መዝሙር 55:22
‘ወደ ጉልምስና ለመድረስ ተጣጣሩ’
9, 10. ጎልማሳ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
9 ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት እያጠናከርክ ስትሄድ “ወደ ጉልምስና ለመድረስ” መጣጣር ትጀምራለህ። (ዕብራውያን 6:1) ይሁንና ጎልማሳ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
10 ዕድሜያችን ስለጨመረ ብቻ ጎልማሳ ክርስቲያኖች እንሆናለን ማለት አይደለም። ጎልማሳ ክርስቲያን ለመሆን ይሖዋን የቅርብ ወዳጃችን ማድረግና የእሱ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ያስፈልገናል። (ዮሐንስ 4:23) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።” (ሮም 8:5) ጎልማሳ የሆነ ክርስቲያን፣ ደስታን በማሳደድ ወይም ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት አይመራም። ከዚህ ይልቅ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ይሖዋን ለማገልገል ሲሆን ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ለማድረግም ይጥራል። (ምሳሌ 27:11፤ ያዕቆብ 1:2, 3ን አንብብ።) በሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፎ መጥፎ ነገር አይፈጽምም። ጎልማሳ የሆነ ክርስቲያን ትክክለኛው ጎዳና የቱ እንደሆነ ያውቃል፤ በዚህ ጎዳና ለመመላለስም ቆርጧል።
11, 12. (ሀ) ጳውሎስ ‘የማስተዋል ችሎታን’ በተመለከተ ምን ብሏል? (ለ) ጉልምስና ላይ መድረስ የተዋጣለት ስፖርተኛ ከመሆን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
11 ጉልምስና ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጠንካራ ምግብ . . . ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ላሠለጠኑ ጎልማሳ ሰዎች ነው።” (ዕብራውያን 5:14) “ላሠለጠኑ” የሚለው ቃል አንድ ስፖርተኛ የሚያደርገውን ልምምድ ወይም ሥልጠና እንድናስብ ያደርገናል።
12 ጥሩ ችሎታ ያለው አንድ ስፖርተኛ ስንመለከት ግለሰቡ እንዲህ ያለ ብቃት ሊኖረው የቻለው ጊዜ ወስዶ ልምምድ ስላደረገ መሆኑን አንጠራጠርም። ግለሰቡ ስፖርተኛ ሆኖ እንዳልተወለደ ግልጽ ነው። አንድ ሕፃን ሲወለድ እጆቹንና እግሮቹን እንኳ እንዴት መጠቀም እንዳለበት አያውቅም። ውሎ አድሮ ግን በእጆቹ ዕቃ መያዝ እንዲሁም በእግሩ መሄድ ይጀምራል። ሥልጠና ካገኘ ደግሞ የተዋጣለት ስፖርተኛ መሆን ይችላል። በተመሳሳይ እኛም ጎልማሳ ክርስቲያኖች ለመሆን ጊዜ ወስደን ራሳችንን ማሠልጠን አለብን።
13. የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ምን ይረዳናል?
13 የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተምረናል። የይሖዋን መሥፈርቶች እንድንወድና ከፍ አድርገን እንድንመለከት የሚረዱን ሐሳቦችም አግኝተናል። በመሆኑም በሕይወታችን ውስጥ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ራሳችንን የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንጠይቃለን፦ ‘ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚያያዙት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል የምችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ምን ዓይነት ውሳኔ እንዳደርግ ይፈልጋል?’—ምሳሌ 3:5, 6ን እና ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።
14. እምነታችንን ለመገንባት ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
14 በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት መገንባት መቼም ቢሆን የሚያበቃ ነገር አይደለም። የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ሰውነታችን ጠንካራ እንዲሆን እንደሚረዳን ሁሉ ስለ ይሖዋ መማራችንም ጠንካራ እምነት ለማዳበር ያስችለናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስንጀምር ስለ ይሖዋና ስለ መመሪያዎቹ መሠረታዊ የሆነ እውቀት አግኝተናል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ጥልቀት ያላቸውን ነገሮች መረዳት ያስፈልገናል። ጳውሎስ ‘ጠንካራ ምግብ ጎልማሳ ለሆኑ ሰዎች ነው’ ብሎ ሲናገር ይህን ማጉላቱ ነው። የተማርናቸውን ነገሮች በተግባር ስናውል ጥበብ እያዳበርን እንሄዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ናት” ይላል።—ምሳሌ 4:5-7፤ 1 ጴጥሮስ 2:2
15. ለይሖዋ እንዲሁም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልባዊ ፍቅር ማዳበራችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
15 ጠንካራና ጤናማ የሆነ ሰውም እንኳ ጤንነቱ በዚሁ እንዲቀጥል ለሰውነቱ ሁልጊዜ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም ጎልማሳ የሆነ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለው ወዳጅነት ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ተግቶ መሥራት እንዳለበት ያውቃል። ጳውሎስ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) ጠንካራ እምነት ያለን መሆኑ ብቻ ግን በቂ አይደለም። ለይሖዋ እንዲሁም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅርም እያደገ መሄድ ይኖርበታል። ጳውሎስ “እውቀትን ሁሉ ባውቅ እንዲሁም ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 13:1-3
በተስፋችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ
16. ሰይጣን ምን እንዲሰማን ይፈልጋል?
16 የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን፣ ይሖዋን ፈጽሞ ማስደሰት እንደማንችል ሊያሳምነን ይሞክራል። ተስፋ እንድንቆርጥ እንዲሁም የሚያጋጥሙን ችግሮች ምንም መፍትሔ እንደሌላቸው እንድናስብ ይፈልጋል። በተጨማሪም ሰይጣን በእምነት ባልንጀሮቻችን እንድንተማመንና ደስተኞች እንድንሆን አይፈልግም። (ኤፌሶን 2:2) ሰይጣን፣ አሉታዊ አስተሳሰብ እንደሚጎዳንና ከአምላክ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዳይኖረን እንቅፋት እንደሚሆን ያውቃል። ይሁንና አሉታዊ አስተሳሰብን ለማሸነፍ የሚረዳን ነገር አለ። ይህም ይሖዋ የሰጠን ተስፋ ነው።
17. ተስፋ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
17 መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ተሰሎንቄ 5:8 ላይ ተስፋችንን ከራስ ቁር ጋር አመሳስሎታል፤ በውጊያ ላይ ያለ ወታደር ጭንቅላቱ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ሲል የራስ ቁር ያደርጋል። ‘የመዳን ተስፋችንም’ እንደ ራስ ቁር እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ይሖዋ የሰጠን ተስፋ፣ አእምሯችንን የሚጠብቅልን ከመሆኑም ሌላ አሉታዊ አስተሳሰብን ለማሸነፍ ይረዳናል።
18, 19. ኢየሱስ በተስፋው ላይ ትኩረት ማድረጉ ብርታት የሰጠው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ የነበረው ተስፋ ብርታት ሰጥቶታል። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አጋጥመውት ነበር። የቅርብ ወዳጁ ለጠላቶቹ አሳልፎ ሰጠው። ሌላው ወዳጁ ደግሞ ጨርሶ እንደማያውቀው በመናገር ካደው። አንዳንድ ወዳጆቹ ጥለውት ሸሹ። የገዛ አገሩ ሰዎች በእሱ ላይ በመነሳት ተሠቃይቶ እንዲገደል ጥያቄ አቀረቡ። ታዲያ ኢየሱስ እነዚህን ስሜት የሚጎዱ ነገሮች እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።”—ዕብራውያን 12:2
19 ኢየሱስ ታማኝነቱን መጠበቁ ለአባቱ ክብር እንደሚያመጣና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ያውቅ ነበር። ይህ ተስፋ የላቀ ደስታ አስገኝቶለታል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሰማይ ተመልሶ ከአባቱ ጋር እንደሚኖር ያውቅ ነበር። ይህ ተስፋም እንዲጸና ረድቶታል። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም በተስፋችን ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። ተስፋ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ለመጽናት ይረዳናል።
20. አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳሃል?
20 ይሖዋ እምነትህንና የምታሳየውን ጽናት ይመለከታል። (ኢሳይያስ 30:18፤ ሚልክያስ 3:10ን አንብብ።) ደግሞም “የልብህን መሻት” እንደሚሰጥህ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:4) እንግዲያው በተስፋህ ላይ ትኩረት አድርግ። ሰይጣን ተስፋ እንድትቆርጥና ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች መቼም ቢሆን እንደማይፈጸሙ እንድታስብ ይፈልጋል። ይሁንና አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲቆጣጠርህ ልትፈቅድ አይገባም! ተስፋህ እየደበዘዘ እንዳለ ከተሰማህ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ። በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር አስታውስ፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”
21, 22. (ሀ) ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
21 ወደፊት ስለሚጠብቀን አስደሳች ሕይወት አዘውትረህ አሰላስል። ሕይወት ያለው ሁሉ ይሖዋን የሚያመልክበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። (ራእይ 7:9, 14) በአዲሱ ዓለም ውስጥ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው። ሕይወት ልንገምተው ከምንችለው በላይ አስደሳች ይሆናል! ሰይጣንና አጋንንቱ ተጠራርገው ይጠፋሉ፤ ክፋትም ጨርሶ ይወገዳል። ሕመምም ሆነ ሞት አይኖርም። በየዕለቱ ጠዋት ኃይልህ ታድሶና ደስተኛ ሆነህ ከእንቅልፍ ትነቃለህ። ሁሉም ሰው ምድርን ገነት ለማድረግ ተባብሮ ይሠራል። በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ በቂ ምግብ የሚያገኙ ሲሆን ያለስጋት የሚኖሩበት ቤት ይኖራቸዋል። ጨካኝ ወይም ዓመፀኛ ሰዎች አይኖሩም፤ ከዚህ ይልቅ ምድር ለሌሎች ከልባቸው በሚያስቡ ሰዎች ትሞላለች። ውሎ አድሮም በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በሙሉ “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት” ይችላሉ።—ሮም 8:21
22 ይሖዋ የቅርብ ወዳጅህ እንድታደርገው ይፈልጋል። እንግዲያው በየዕለቱ ይሖዋን ለመታዘዝና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ሁላችንም ለዘላለም ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር ምኞታችን ነው!—ይሁዳ 21