ምዕራፍ 1
የአምላክ ፍቅር ለዘላለም ይኖራል
“አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም።”—1 ዮሐንስ 5:3
1, 2. ይሖዋ አምላክን የምትወደው ለምንድን ነው?
አምላክን ትወደዋለህ? አምላክን ከልብህ ስለምትወደው ራስህን ለእሱ ወስነህ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አምላክን እንደ ቅርብ ወዳጅህ አድርገህ ትመለከተው ይሆናል። እርግጥ ነው፣ አንተ ይሖዋን ከመውደድህ በፊት እሱ ወዶሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን” ይላል።—1 ዮሐንስ 4:19
2 ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየባቸውን መንገዶች እስቲ ለማሰብ ሞክር። መኖሪያ እንድትሆነን ይህችን ውብ ምድር ሰጥቶናል፤ እንዲሁም ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉንን ነገሮች በሙሉ አሟልቶልናል። (ማቴዎስ 5:43-48፤ ራእይ 4:11) ከዚህም በላይ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንድንችል አጋጣሚውን ከፍቶልናል፤ ይህን ያደረገው ስለ እሱ መማር የምንችልበት መንገድ በማዘጋጀት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይሖዋ የሚነግረንን ለማዳመጥ ያስችለናል። ስንጸልይ ደግሞ ይሖዋ እኛን ያዳምጠናል። (መዝሙር 65:2) አምላክ፣ ኃያል በሆነው ቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ ይመራናል እንዲሁም ያጠነክረናል። (ሉቃስ 11:13) እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ሲል ውድ ልጁን እንኳ ወደ ምድር ልኮታል።—ዮሐንስ 3:16ን እና ሮም 5:8ን አንብብ።
3. ከይሖዋ ጋር ምንጊዜም ጥሩ ወዳጅነት እንዲኖረን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 እስቲ ስለ አንድ የቅርብ ወዳጅህ ለማሰብ ሞክር፤ ከዚህ ወዳጅህ ጋር ክፉውንም ደጉንም አብራችሁ አሳልፋችሁ ይሆናል። ያም ቢሆን በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ የታወቀ ነው። ከይሖዋ ጋር ባለን ወዳጅነት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ እሱ ከማንም በላይ የቀረበ ወዳጃችን ሊሆን ይችላል። ደግሞም ከይሖዋ ጋር ለዘላለም የሚዘልቅ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ [ኑሩ]” የሚል ምክር ይሰጠናል። (ይሁዳ 21) ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል።—1 ዮሐንስ 5:3
“አምላክን መውደድ” ሲባል ምን ማለት ነው?
4, 5. ይሖዋን መውደድ የጀመርከው እንዴት ነው?
4 ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክን መውደድ” በማለት ሲጽፍ እያንዳንዳችን ለአምላክ ስላለን ጥልቅ የፍቅር ስሜት እየገለጸ ነበር። አንተስ ይሖዋን መውደድ የጀመርክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ?
5 ይሖዋ፣ ወደፊት በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንድትኖር የማድረግ ዓላማ እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ ስትማር ምን እንደተሰማህ ለማስታወስ ሞክር። ይህን ዓላማውን እውን ለማድረግ ሲል ስላከናወናቸው ነገሮች ተማርክ፤ በተጨማሪም ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ታላቅ ስጦታ እንደሰጠን አወቅክ። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 8:29፤ ሮም 5:12, 18) ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወድህ በመገንዘብህ ልብህ ስለተነካ አንተም እሱን መውደድ ጀመርክ።—1 ዮሐንስ 4:9, 10ን አንብብ።
6. አንድን ሰው መውደድ ምን ማድረግን ይጨምራል? ለአምላክ ያለህ ፍቅር ምን እንድታደርግ አነሳስቶሃል?
6 ሆኖም ለአምላክ ያለህ ፍቅር የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ለአንድ ሰው ፍቅር ካለን ግለሰቡን “እወድሃለሁ” በማለት ብቻ አንወሰንም። ለግለሰቡ ያለን ፍቅር እሱን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ያነሳሳናል። በተመሳሳይም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እሱን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር አነሳስቶሃል። ፍቅርህ እያደገ ሲሄድ ደግሞ ራስህን ለእሱ በመወሰን ተጠመቅክ። እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰድህ ይሖዋን ለዘላለም ለማገልገል ቃል መግባትህን ያሳያል። (ሮም 14:7, 8ን አንብብ።) ታዲያ የገባኸውን ቃል ጠብቀህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
“ትእዛዛቱን መጠበቅ”
7. ይሖዋን የምንወደው ከሆነ ምን እናደርጋለን? ከአምላክ ትእዛዛት መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
7 ይሖዋን ስለምንወደው ‘ትእዛዛቱን እንጠብቃለን።’ ይሖዋ ሕይወታችንን በምን መንገድ እንድንመራ እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ለምሳሌ መስከር፣ መስረቅ፣ መዋሸት እንዲሁም የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት እንደሆነ ይሖዋ ገልጾልናል፤ በተጨማሪም ልናመልክ የሚገባው እሱን ብቻ እንደሆነ ነግሮናል።—1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:18፤ 10:14፤ ኤፌሶን 4:28፤ ቆላስይስ 3:9
8, 9. ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ያልተሰጠበት ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
8 ይሁን እንጂ ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን በግልጽ የተቀመጡ ትእዛዛቱን በማክበር ብቻ መወሰን የለብንም። ይሖዋ ከእያንዳንዱ የሕይወታችን ክፍል ጋር የተያያዙ ዝርዝር ሕጎችን አልሰጠንም። ስለዚህ አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተቀመጡ ሕጎችን ላናገኝ እንችላለን። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳናል? (ኤፌሶን 5:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እናገኛለን፤ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚባሉት የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ የሚያስችሉ እውነታዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንማራለን። የእሱን አስተሳሰብ ይኸውም የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች እንረዳለን።—መዝሙር 97:10ን አንብብ፤ ምሳሌ 6:16-19፤ ተጨማሪ ሐሳብ 1ን ተመልከት።
9 ለምሳሌ ያህል፣ በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት ምን ዓይነት ነገሮችን እንደምንመለከት መወሰን የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ምን መመልከት እንዳለብንና እንደሌለብን በቀጥታ አይነግረንም። ሆኖም እሱ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ትክክለኛውን ውሳኔ ለማድረግ ይረዱናል። በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ መዝናኛዎች በዓመፅ ድርጊቶችና በፆታ ብልግና የተሞሉ ናቸው። ይሖዋ “ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው [እንደሚጠላ]” እንዲሁም “ሴሰኞችን” ማለትም የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎችን ‘እንደሚፈርድባቸው’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 11:5፤ ዕብራውያን 13:4) እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን እንዴት ነው? ይሖዋ የሚጠላቸውን ወይም ትክክል እንዳልሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸውን ነገሮች ማወቃችን ከእነዚህ ነገሮች እንድንርቅ ያነሳሳናል።
10, 11. ይሖዋን የምንታዘዘው ለምንድን ነው?
10 ይሖዋን የምንታዘዘው ለምንድን ነው? አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ቅጣት ወይም መጥፎ ውሳኔ ማድረግ የሚያመጣውን ችግር ስለምንፈራ ብቻ አይደለም። (ገላትያ 6:7) ይሖዋን የምንታዘዘው ስለምንወደው ነው። ልጆች አባታቸውን ማስደሰት እንደሚፈልጉ ሁሉ እኛም በሰማይ ያለውን አባታችንን ማስደሰት እንፈልጋለን። ደግሞስ ይሖዋ እንደተደሰተብን ከማወቅ የሚበልጥ ምን ነገር አለ?—መዝሙር 5:12፤ ምሳሌ 12:2፤ ተጨማሪ ሐሳብ 2ን ተመልከት።
11 ይሖዋን የምንታዘዘው መመሪያዎቹ ቀላል በሚሆኑልን ወይም ከመታዘዝ ውጭ ሌላ ምርጫ በማይኖረን ጊዜ ብቻ አይደለም። እንዲሁም የምንታዘዘው አንዳንዶቹን ሕጎችና መሥፈርቶች መርጠን አይደለም። (ዘዳግም 12:32) ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ሕጎች በሙሉ እንታዘዛለን፤ “ትእዛዛትህ ደስ ያሰኙኛል፤ አዎ፣ እወዳቸዋለሁ” በማለት እንደተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት አመለካከት አለን። (መዝሙር 119:47፤ ሮም 6:17) ይሖዋ ያዘዘውን ነገር ሁሉ በማድረግ ለአምላክ ያለውን ፍቅር እንዳሳየው እንደ ኖኅ መሆን እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:22) ይሖዋ ስለ አንተም ተመሳሳይ ነገር ቢናገር ደስ አይልህም?
12. ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ መመሪያዎቹን ስንታዘዝ ምን ይሰማዋል? ‘ልቡ ደስ ይሰኛል።’ (ምሳሌ 11:20፤ 27:11) እስቲ አስበው! የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ በመታዘዝ ልቡን ደስ ማሰኘት እንችላለን። ያም ሆኖ ይሖዋ እንድንታዘዘው አያስገድደንም። ከዚህ ይልቅ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በሌላ አባባል፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለማድረግ የመምረጥ ነፃነት አለን። ይሖዋ ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ጥሩ ውሳኔዎች እንድናደርግ ይፈልጋል፤ ይህን ማድረጋችን ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ያስችለናል።—ዘዳግም 30:15, 16, 19, 20፤ ተጨማሪ ሐሳብ 3ን ተመልከት።
‘ትእዛዛቱ ከባድ አይደሉም’
13, 14. የአምላክ ትእዛዛት በጣም ከባድ እንዳልሆኑ እንዴት እናውቃለን? በምሳሌ አስረዳ።
13 የይሖዋ ትእዛዛት በጣም ከባድ እንደሆኑ ወይም ነፃነታችንን እንደሚገድቡብን ቢሰማንስ? መጽሐፍ ቅዱስ “ትእዛዛቱ . . . ከባድ አይደሉም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:3) እዚህ ጥቅስ ላይ “ከባድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ በሌሎች ጥቅሶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ ደንቦችን እንዲሁም ሌሎችን የሚጨቁኑ ወይም የሚበድሉ ሰዎችን ለመግለጽ ተሠርቶበታል። (ማቴዎስ 23:4፤ የሐዋርያት ) ኒው ኢንግሊሽ ትራንስሌሽን የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ትእዛዛቱ ሸክም አይሆኑብንም” ይላል። የይሖዋ ትእዛዛት “ሸክም” አይደሉም፤ አምላክን መታዘዝም አስቸጋሪ አይደለም። ይሖዋ ምክንያታዊ ያልሆነ ነገር ፈጽሞ አይጠብቅብንም። ሥራ 20:29, 30
14 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ ወዳጅህ ቤት ሲቀይር ዕቃ በማጓጓዝ እንድታግዘው ጠየቀህ እንበል። አንዳንዶቹ ዕቃዎች ቀላል ስለሆኑ አንድ ሰው ብቻውን ሊሸከማቸው ይችላል፤ ሌሎቹን ዕቃዎች ለመሸከም ግን የግድ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ። ወዳጅህ በጣም ከባድ የሆነ ዕቃ ብቻህን እንድትሸከም ይጠይቅሃል? በፍጹም! ለምን? ምክንያቱም ወዳጅህ እንድትጎዳ አይፈልግም። በተመሳሳይም ይሖዋ በጣም ከባድ የሆነ ነገር እንድናደርግ በጭራሽ አይጠይቀንም። (ዘዳግም 30:11-14) ይሖዋ ማንነታችንን በሚገባ ይረዳል። “እሱ እንዴት እንደተሠራን [ያውቃል]፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል።”—መዝሙር 103:14
15. ይሖዋ መመሪያዎቹን የሰጠን ለእኛው ጥቅም መሆኑን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
15 እስራኤላውያን የይሖዋን ትእዛዛት ቢጠብቁ ‘ምንጊዜም መልካም እንደሚሆንላቸው’ እንዲሁም ‘በሕይወት እንደሚኖሩ’ ሙሴ ነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 5:28-33፤ 6:24) ከእኛ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ የሚያዘንን ማንኛውንም ነገር መፈጸማችን የተሻለ ሕይወት ለመምራት ያስችለናል። (ኢሳይያስ 48:17ን አንብብ።) አባታችን ይሖዋ ለእኛ የሚጠቅመን ምን እንደሆነ ያውቃል። (ሮም 11:33) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይህም ሲባል ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው ማለት ነው።
16. ፍጹም አለመሆናችንና የምንኖርበት ክፉ ዓለም ተጽዕኖ ቢያደርጉብንም ይሖዋን መታዘዝ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?
16 እርግጥ ነው፣ ይሖዋን መታዘዝ ሁልጊዜ ቀላል ይሆንልናል ማለት አይደለም። የምንኖረው በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ባለ ክፉ ዓለም ውስጥ ነው። ዲያብሎስ ሰዎች መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ ለመገፋፋት ይሞክራል። (1 ዮሐንስ 5:19) በተጨማሪም አምላክን ለመታዘዝ ከራሳችን አስተሳሰብና ስሜት ጋር መታገል ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ፍጹማን ባለመሆናችን ትክክል ያልሆነውን ማድረግ ይቀናናል። (ሮም 7:21-25) ይሁንና ለይሖዋ ያለን ፍቅር ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ብርታት ይሰጠናል። ይሖዋም እሱን ለመታዘዝ የምናደርገውን ጥረት ሲመለከት፣ ኃያል የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ይረዳናል። (1 ሳሙኤል 15:22, 23፤ የሐዋርያት ሥራ 5:32) መንፈስ ቅዱስ ይሖዋን መታዘዝ ቀላል እንዲሆንልን የሚያደርጉ ባሕርያትን ለማዳበር ያስችለናል።—ገላትያ 5:22, 23
17, 18. (ሀ) በዚህ መጽሐፍ ላይ ምን እንማራለን? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
17 ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ መጽሐፍ ላይ እንማራለን። በይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንደምንችልም እንመለከታለን። ይሖዋ እንድንታዘዘው መቼም ቢሆን እንደማያስገድደን መዘንጋት የለብንም። እሱን ለመታዘዝ ከመረጥን በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንመራለን፤ ወደፊትም አስደሳች ሕይወት ይኖረናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ አምላክን መታዘዛችን እሱን ምን ያህል እንደምንወደው የምናሳይበት አጋጣሚ ይሰጠናል።—ተጨማሪ ሐሳብ 4ን ተመልከት።
18 ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንድንችል ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ሕሊና ሰጥቶናል። ሕሊናችንን ካሠለጠንነው የአምላክን ‘ትእዛዛት ለመጠበቅ’ ይረዳናል። ለመሆኑ ሕሊና ምንድን ነው? ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለውስ እንዴት ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህን እንመለከታለን።