በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 5

አስማትን፣ መተትንና ጥንቆላን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

አስማትን፣ መተትንና ጥንቆላን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

1. አስማት፣ መተትና ጥንቆላ ምን ያህል ተስፋፍቷል?

አፍሪካን ትራዲሽናል ሪሊጅን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ጠንቋዮች አሉ ወይም የሉም የሚለው ጉዳይ በአፍሪካ ውስጥ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አፍሪካውያን ጥንቆላን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል።” የተማሩም ሆኑ ያልተማሩ ሰዎች በአስማት፣ በመተትና በጥንቆላ ያምናሉ። አንዳንድ የእስልምና እና የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ሳይቀሩ በእነዚህ ድርጊቶች ይካፈላሉ።

2. ብዙ አፍሪካውያን አስማታዊ ኃይል የሚገኘው ከየት ነው ብለው ያምናሉ?

2 ብዙ አፍሪካውያን አንድ ዓይነት ምትሃታዊ ወይም መንፈሳዊ ኃይል እንዳለ ያምናሉ። ይህን ኃይል የሚቆጣጠረው አምላክ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም መናፍስትና የሞቱ አያት፣ ቅድመ አያቶች ይህን ኃይል እንደሚጠቀሙበት ያስባሉ። ይህን ኃይል ማግኘትና ለበጎም ሆነ ለመጥፎ ዓላማ መጠቀም የሚችሉ ሰዎችም እንዳሉ ያምናሉ።

3. መተት ምንድን ነው? ብዙዎች መተት በሰዎች ላይ ምን ያስከትላል ብለው ያምናሉ?

3 መተት አንድን ሰው ለመጉዳት ታስቦ የሚፈጸም አስማታዊ ድርጊት ነው። እንዲህ ዓይነቱን አስማት የሚፈጽሙ ሰዎች የሌሊት ወፎችን፣ አእዋፍን፣ ዝንቦችንና አንዳንድ እንስሳትን ተጠቅመው ሰዎችን የመጉዳት ኃይል እንዳላቸው ይታመናል። ብዙ ሰዎች፣ መተት ሕመም፣ መካንነት፣ ጠብ አልፎ ተርፎም ሞት እንደሚያስከትል ያምናሉ።

4. ብዙዎች፣ ጠንቋዮች ምን እንደሚያደርጉ ያምናሉ? ጠንቋይ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ምን ፈጽመው እንደነበረ ተናግረዋል?

4 ከመተት ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ሌላው ተግባር ደግሞ ጥንቆላ ነው። በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ጠንቋዮች ማታ ማታ ከአካላቸው ተለይተው በመሄድ ከሌሎች ጠንቋዮች ጋር እንደሚገናኙ ወይም ሰለባዎቻቸው ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ይነገራል። ጠንቋዮቹ ከተኙበት አልጋ ላይ ስለማይነሱ ሰዎች እነዚህ አፈ ታሪኮች እንደተፈጸሙ እንዲያምኑ ምክንያት የሚሆናቸው ከዚያ በፊት ጠንቋይ የነበሩ ሰዎች የተናገሩትን መስማታቸው ነው። ለምሳሌ በአፍሪካ የሚታተም አንድ መጽሔት፣ ጠንቋይ የነበሩ ሰዎች (አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች ናቸው) እንደሚከተለው እንዳሉ ጠቅሷል፦ “የመኪና አደጋ እንዲደርስባቸው በማድረግ 150 ሰዎችን ገድያለሁ።” “አምስት ሕጻናትን ደማቸውን መጥጬ ገድያለሁ።” “ትተውኝ ስለሄዱ ሦስት የወንድ ጓደኞቼን ገድያቸዋለሁ።”

5. አንዳንዶች ምን ዓይነት አስማት እንዳለም ያምናሉ? ይህ ዓይነቱ አስማት የሚደረገውስ እንዴት ነው?

5 አንዳንዶች ከክፉ ነገር ጥበቃ የሚያስገኝ የአስማት ዓይነት እንዳለም ያምናሉ። እንዲህ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች ድግምት የተደረገበት ቀለበት ወይም አምባር ያደርጋሉ። ከክፉ ነገር እንደሚከላከል የሚታሰብ መድኃኒት ይጠጣሉ ወይም ሰውነታቸውን ይቀባሉ። ከአደጋ ይከላከሉልናል ብለው የሚያስቧቸውን ዕቃዎች መሬት ውስጥ ይቀብራሉ ወይም ቤታቸው ውስጥ ደብቀው ያስቀምጣሉ። የቁርዓን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተጻፈበት ክታብ ከአደጋ እንደሚጠብቃቸው ያምናሉ።

ሐሰትና ማታለያ

6. ሰይጣንና አጋንንቱ ምን ማድረግ ይችላሉ? ስላላቸው ኃይልስ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

6 ሰይጣንና አጋንንቱ የሰው ልጆች አደገኛ ጠላት መሆናቸው ምንም አያጠያይቅም። በሰዎች አእምሮና ሕይወት ላይ ተጽእኖ የማሳደር ኃይል አላቸው፤ ሌላው ቀርቶ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በማደር እነሱን መቆጣጠር ይችላሉ። (ማቴዎስ 12:43-45) አጋንንት ያላቸውን ኃይል አቅልለን ባንመለከትም ከልክ በላይ አጋንነን ማየት ግን የለብንም።

7. ሰይጣን ምን ብለን እንድናምን ይፈልጋል? ይህንን በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

7 ሰይጣን የተዋጣለት አታላይ ነው። ሰዎች ያለውን ኃይል አጋንነው እንዲመለከቱ በማድረግ ያታልላል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ በአንድ የአፍሪካ አገር በተደረገ ጦርነት ላይ ወታደሮቹ ጠላቶቻቸውን ለማሸበር በድምፅ ማጉያ መሣሪያ ተጠቅመው ነበር። ወታደሮቹ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት፣ የመድፍና የጠመንጃ ተኩስ ድምፅ አሰሙ። ይህን ያደረጉት ጠላቶቻቸው ብዙ ከባድ መሣሪያዎች ባሉት ሠራዊት እየተጠቁ እንዳሉ ሆኖ እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው። ሰይጣንም ሰዎች፣ ገደብ የለሽ ኃይል እንዳለው አድርገው እንዲያስቡ ይፈልጋል። ዓላማው ሰዎች በፍርሃት እንዲሸበሩና የይሖዋን ሳይሆን የእሱን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ማድረግ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ሰይጣን፣ ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀምባቸውን ሦስት ውሸቶች እንመለከታለን።

8. ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች መካከል አንዱ ምንድን ነው?

8 ሰይጣን የሚያስፋፋው አንደኛው ውሸት የሚከተለው ነው፦ ‘ክፉ ነገር በአጋጣሚ ሊደርስ አይችልም፤ ለተፈጠረው ክፉ ነገር ተጠያቂ የሚሆን ሰው ከሌለ ድርጊቱ የተፈጸመው በምትሃታዊ ኃይል አማካኝነት ነው።’ ለምሳሌ፣ አንድ ትንሽ ልጅ በወባ በሽታ ሞተ እንበል። የልጁ እናት ወባ የሚተላለፈው በወባ ትንኝ አማካኝነት እንደሆነ ታውቅ ይሆናል። ሆኖም ልጇ የሞተው አንድ ሰው በአስማታዊ ኃይል ተጠቅሞ የወባ ትንኟን ስለላከ እንደሆነ አድርጋ ልታስብ ትችላለች።

አንዳንድ ጊዜ በሰዎች ላይ አደጋ የሚደርሰው በአጋጣሚ ነው

9. መጥፎ ነገሮች ሁሉ እንዲከሰቱ የሚያደርገው ሰይጣን እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 እርግጥ ነው፣ ሰይጣን አንዳንድ ችግሮች እንዲከሰቱ የማድረግ ኃይል አለው፤ ሆኖም ሁሉንም ችግሮች የሚያመጣው እሱ ነው ብሎ ማመን ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም፤ ጥበበኞች ሁልጊዜ ምግብ አያገኙም፤ አስተዋዮች ሁልጊዜ ሀብት አያገኙም፤ እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።” (መክብብ 9:11) አንድ ሯጭ ከሌሎች የበለጠ ፈጣን ቢሆንም በውድድሩ ላያሸንፍ ይችላል። በአንዳንድ “ያልተጠበቁ ክስተቶች” የተነሳ ይሸነፍ ይሆናል። ተደናቅፎ ሊወድቅ፣ ሊታመም ወይም ወለም ሊለው ይችላል። ማንም ሰው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል። ችግሩ እንዲፈጠር ያደረገው የግድ ሰይጣን ወይም አንድ ምትሃታዊ ኃይል ነው ማለት አይደለም፤ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በአጋጣሚ ሊከሰቱ ይችላሉ።

10. ስለ ጠንቋዮች ምን ተብሎ ይነገራል? ይህ ውሸት መሆኑንስ እንዴት እናውቃለን?

10 ሰይጣን የሚያስፋፋው ሁለተኛው ውሸት የሚከተለው ነው፦ ‘ጠንቋዮች ማታ ማታ ከአካላቸው ተለይተው በመሄድ ከሌሎች ጠንቋዮች ጋር ይገናኛሉ ወይም ሰለባዎቻቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።’ እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ጠንቋዮች ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ከአካላቸው ተለይቶ የሚሄደው ነገር ምንድን ነው?’ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሰው ራሱ ነፍስ ነው፤ ስለሆነም ከአንድ ሰው ተለይቶ የሚሄድ ምንም ነገር የለም። መንፈስም ቢሆን አንድን ሰው እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው የሕይወት ኃይል ነው፤ ይህ ኃይል ደግሞ ከሰውነታችን ተለይቶ ምንም ማድረግ አይችልም።

ጠንቋዮች ከአካላቸው ተለይተው ሊሄዱ አይችሉም

11. ጠንቋዮች ከአካላቸው ተለይተው ሊሄዱ አይችሉም የምንለው ለምንድን ነው? አንተስ ይህን በተመለከተ ምን ትላለህ?

11 ነፍስም ሆነ መንፈስ ከአንድ ሰው አካል ተለይተው በመሄድ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። በመሆኑም ጠንቋዮች ከአካላቸው ተለይተው አይሄዱም። ስለሆነም አድርገናል ብለው የሚናገሩትም ሆነ እናደርጋለን ብለው የሚያስቡት ነገር ውሸት ነው።

12. ሰይጣን፣ ሰዎች ያላደረጉትን ነገር እንዳደረጉ ሆኖ እንዲሰማቸው የሚያደርገው እንዴት ነው?

12 ታዲያ ጠንቋይ የነበሩ ሰዎች እንዳደረጓቸው ስለሚናገሯቸው ነገሮችስ ምን ሊባል ይችላል? ሰይጣን፣ ሰዎች ያላደረጉትን ነገር እንዳደረጉ ሆኖ እንዲሰማቸው የማድረግ ችሎታ አለው። ሰይጣን ሰዎች አንድን ነገር ያዩ፣ የሰሙና ያደረጉ እንዲመስላቸው ለማድረግ በራእይ አማካኝነት ሊጠቀም ይችላል። በዚህ መንገድ ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅና መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንደሆነ ለማሳመን ይሞክራል።

13. (ሀ) ጥሩ የአስማት ዓይነት አለ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስማት ምን ይላል?

13 ሦስተኛው ውሸት ደግሞ የሚከተለው ነው፦ ‘ከመጥፎ የአስማት ዓይነት ጥበቃ የሚያስገኝ ጥሩ የአስማት ዓይነት አለ።’ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን የአስማት ዓይነት ጥሩ፣ ሌላውን ደግሞ መጥፎ እያለ አይፈርጅም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም ዓይነት አስማታዊ ድርጊት ያወግዛል። ይሖዋ አስማትንና አስማታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን አስመልክቶ እስራኤላውያንን ምን ብሏቸው እንደነበር እስቲ እንመልከት፦

  • “አስማት አትሥሩ።”—ዘሌዋውያን 19:26

  • “መናፍስት ጠሪ ወይም ጠንቋይ የሆነ ወንድ ወይም የሆነች ሴት ካሉ ይገደሉ።”—ዘሌዋውያን 20:27

  • “አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ።”—ዘዳግም 18:10-14

14. ይሖዋ አስማታዊ ድርጊቶችን የሚከለክል ሕግ የሰጠው ለምንድን ነው?

14 አምላክ፣ ሕዝቦቹ ከማንኛውም አስማታዊ ድርጊት እንዲርቁ እንደሚፈልግ እነዚህ ሕጎች በግልጽ ያሳያሉ። ይሖዋ እነዚህን ሕጎች ለሕዝቡ የሰጠው ስለሚወዳቸው እንዲሁም በፍርሃትና በአጉል እምነት ተተብትበው እንዲያዙ ስለማይፈልግ ነው። አጋንንት እንዲጨቁኗቸው አልፈለገም።

15. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ከሰይጣን የላቀ ኃይል እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንት ሊያደርጉ ስለሚችሏቸውና ስለማይችሏቸው ነገሮች በዝርዝር ባይገልጽም ይሖዋ አምላክ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ የላቀ ኃይል እንዳለው ይጠቁማል። ይሖዋ ሰይጣንን ከሰማይ አባርሮታል። (ራእይ 12:9) በተጨማሪም ሰይጣን ኢዮብን ለመፈተን የአምላክን ፈቃድ እንደጠየቀ እንዲሁም ኢዮብን እንዳይገድለው አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ እንዳከበረ ልብ በል።—ኢዮብ 2:4-6

16. ጥበቃ ለማግኘት በማን መታመን ይኖርብናል?

16 ምሳሌ 18:10 “የይሖዋ ስም ጽኑ ግንብ ነው። ጻድቅ ወደዚያ በመሮጥ ጥበቃ ያገኛል” ይላል። ስለሆነም ይሖዋ ጥበቃ እንዲያደርግልን ልንጠይቀው ይገባል። የአምላክ አገልጋዮች ሰይጣንና አጋንንቱ ጉዳት እንዳያደርሱባቸው በማሰብ ክታብ አያስሩም ወይም መድኃኒት አይጠቀሙም፤ እንዲሁም የጠንቋዮችን ድግምት አይፈሩም። የአምላክ አገልጋዮች የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክል እንደሆነ ያምናሉ፦ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።”—2 ዜና መዋዕል 16:9

17. ያዕቆብ 4:7 ምን ዋስትና ይሰጠናል? ሆኖም ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

17 አንተም ይሖዋን የምታገለግል ከሆነ እንዲህ ያለ ትምክህት ይኖርሃል። ያዕቆብ 4:7 “ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” በማለት ይናገራል። ራስህን ለእውነተኛው አምላክ በማስገዛት እሱን የምታገለግል ከሆነ ይሖዋ እንደሚጠብቅህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።