ክፍል 9
እውነተኛው ሃይማኖት ለዘላለም ይጠቅምሃል!
1. ‘ወደ አምላክ መቅረባችን’ ምን ያስገኝልናል?
ይሖዋ እሱን የሚያገለግሉ ሰዎችን ይወዳቸዋል። ይሖዋን የምታመልከው ከሆን አሁንም ሆነ ወደፊት ይባርክሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል።—ያዕቆብ 4:8
2. ወደ አምላክ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ በጸሎታችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል?
2 ወደ አምላክ ለመቅረብ ቃሉን ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል ይኖርብሃል። ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ጸሎት የምታቀርብ ከሆነ ይሖዋ ጸሎትህን ሰምቶ መልስ ይሰጥሃል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል። የምንጠይቀውንም ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ የምንጠይቀውን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን።”—1 ዮሐንስ 5:14, 15
3-7. አምላካዊ ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ምን ጥቅሞችስ አሉት?
3 ከዚህም በላይ ወደ አምላክ ይበልጥ በቀረብክ መጠን በዕለት ተዕለት ሕይወትህ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ ታገኛለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን” ይላል።—ያዕቆብ 1:5
4 አምላክ የሚሰጥህ ጥበብ ጥቅም የሚያስገኝልህ እንዴት ነው? አንደኛ፣ ይሖዋ የማይደሰትባቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለይተህ ማወቅ ትችላለህ። በተጨማሪም እነዚህ ነገሮች ስህተት የሆኑት ለምን እንደሆነና ከእነዚህ ድርጊቶች መራቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ትገነዘባለህ። እንዲህ ያለው እውቀት በዛሬው ጊዜ በአብዛኞቹ ሰዎች ላይ ከሚደርሱት ችግሮች ይጠብቅሃል። ለምሳሌ የአምላክ ሕዝቦች፣ ንጹሕ ሥነ ምግባር እንዲከተሉ አምላክ የሰጣቸውን ምክር መታዘዛቸው ካልተፈለገ እርግዝና፣ ከአባለ ዘር በሽታዎች፣ ደስታ ከራቀው ትዳርና ከፍቺ ጠብቋቸዋል።
5 አምላክ የሚሰጠው ጥበብ ምን ሌላ ጥቅም ሊያስገኝልህ ይችላል? ሕይወትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድትጠቀምበት ያስችልሃል። እንደ ገንዘብ አያያዝ ባሉ አስፈላጊ ጉዳዮች ረገድ ጥሩ ውሳኔ እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። ጠቃሚ የሆኑ ግቦችን እንድታወጣ ብሎም ዘላቂ ጥቅም የሌላቸውን ግቦች ከመከታተል እንድትቆጠብ ይረዳሃል።
6 አምላክ የሚሰጠው ጥበብ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድም ጥቅም ያስገኝልሃል። ደስተኛ ቤተሰብ ይኖርሃል። ከሰዎች ጋር ዘላቂ የሆነ እውነተኛ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችልሃል፤ አምላክን የማያገለግሉ ሰዎችን ጨምሮ የሌሎችን አክብሮት ማትረፍ ትችላለህ።
7 ከዚህም በላይ አምላካዊ ጥበብ ካለህ ስለ ሕይወት ትክክለኛ አመለካከት ይኖርሃል። በሕይወትህ የሚያጋጥሙህን ችግሮችና አሳዛኝ ሁኔታዎች መቋቋም ትችላለህ። በተጨማሪም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሚዛናዊና ብሩህ አመለካከት ይኖርሃል። ብሩህ አመለካከት መያዝህ ደግሞ ለአእምሮህም ሆነ ለአካልህ ጤንነት አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ምሳሌ 14:30፤ ኢሳይያስ 48:17
8. አምላክን የምታገለግል ከሆነ ምን ነገሮች አያስፈሩህም?
8 እውነተኛውን አምላክ የምታገለግል ከሆነ የእሱ አገልጋይ ያልሆኑ ሰዎች ከሚሰማቸው ፍርሃት ነፃ ትሆናለህ። የሞቱ ሰዎች ከሕልውና ውጭ እንደሆኑ ስለምታውቅ ሙታንን አትፈራም። አምላክ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም ስለምትተማመን ዮሐንስ 8:32
ሞት አያስፈራህም። እንዲሁም አምላክ ከማንም የበለጠ ኃይል እንዳለው ስለምታውቅ አስማታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ወይም ጠንቋዮች ጉዳት ያደርሱብኛል ብለህ አትሰጋም።—ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ
9-11. በገነት ውስጥ የሚኖሩት እነማን ናቸው? የማይኖሩትስ?
9 ወደ አምላክ ከቀረብክ የወደፊቱ ጊዜ አያስፈራህም። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ስለምናያቸው ብዙ ችግሮች ተንብዮአል። ይሖዋ እነዚህ ችግሮች ጊዜያዊ እንደሆኑ ነግሮናል፤ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ምድርን ገነት ያደርጋታል።—ሉቃስ 21:10, 11, 31፤ 23:43
10 በገነት ውስጥ የሚኖሩት ወደ ይሖዋ የሚቀርቡና እሱን የሚያገለግሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም። የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:10, 11
11 የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ለመታዘዝ እምቢተኛ የሆኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አያገኙም። (2 ተሰሎንቄ 1:8, 9) ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። ልክ እንደ ሰይጣንና አጋንንቱ እነሱም ለዘላለም ሞተው ይቀራሉ። (ራእይ 20:10, 14) ስለ ይሖዋ የሚማሩና እሱን የሚያገለግሉ ሁሉ ግን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በደስታ ይኖራሉ።
አስደናቂ ተስፋ!
12. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይላል?
12 ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ሰዎች አስደናቂ በረከቶችን አዘጋጅቶላቸዋል! ምድር ገነት ስትሆን ስለሚኖረው ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እስቲ ተመልከት፦
-
ምግብ ይትረፈረፋል፦ “በምድር ላይ እህል [ወይም ምግብ] ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16
-
ምቹ መኖሪያ፦ “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ።”—ኢሳይያስ 65:21
-
አስደሳች ሥራ፦ “የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ። በከንቱ አይለፉም።”—ኢሳይያስ 65:22, 23
-
በሽታ አይኖርም፦ “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24
-
አካል ጉዳተኛ አይኖርም፦ “በዚያን ጊዜ የዓይነ ስውራን ዓይን ይገለጣል፤ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮም ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የዱዳም ምላስ በደስታ እልል ይላል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6
-
ሥቃይ፣ ሐዘንና ሞት አይኖርም፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4
-
ጦርነት አይኖርም፦ “[አምላክ] ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።”—መዝሙር 46:9
-
የዘላለም ሕይወት፦ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
13. ምድርን ገነት ማድረግ የሚችለው ማን ብቻ ነው? ለምንስ?
13 የሰው ልጆች እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማድረግ አይችሉም፤ ይሖዋ ግን ቃል የገባውን ማንኛውም ነገር ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል አለው። የፈለገውን ነገር ከማድረግ ማንም ሊያግደው አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ የተናገረው ቃል ሳይፈጸም አይቀርም” ይላል።—ሉቃስ 1:37
14. ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ የምትችለው እንዴት ነው?
14 ይሖዋ በምሥክሮቹ አማካኝነት በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች “በጠባቡ በር” እንዲገቡና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ ግብዣ እያቀረበ ነው። አንተም ይህን ግብዣ ከተቀበሉት ደስተኛ ሕዝቦች መካከል እንድትሆን ምኞታችን ነው። እውነተኛውን ሃይማኖት በመከተል ዘላለማዊ በረከት እንደምታገኝ ተስፋ እናደርጋለን።—ማቴዎስ 7:13, 14