ምዕራፍ 21
ኢየሱስ ‘ከአምላክ የመጣውን ጥበብ’ ገልጧል
1-3. ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት የአገሩ ሰዎች ላስተማረው ትምህርት ምን ምላሽ ሰጡ? ያልተገነዘቡትስ ነገር ምን ነበር?
አድማጮቹ በትምህርቱ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ ፈዘው ያዳምጡታል። ወጣቱ ኢየሱስ በምኩራብ ውስጥ ቆሞ እያስተማረ ነው። ኢየሱስ እዚያው ከተማ ውስጥ ያደገና በአናጺነት ሲሠራ የቆየ በመሆኑ ለአድማጮቹ እንግዳ ሰው አልነበረም። እንዲያውም አንዳንዶቹ እሱ ባነጻቸው ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ወይም እሱ በሠራው ሞፈርና ቀንበር የሚገለገሉ ሊሆኑ ይችላሉ። a ይሁንና አናጺ የነበረው ይህ ሰው ፊታቸው ቆሞ ሲያስተምር ምን ተሰምቷቸው ይሆን?
2 ሲያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ “ይህ ሰው ይህን ጥበብ . . . ከየት አገኘ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ “ይህ አናጺው የማርያም ልጅ . . . አይደለም?” ሲሉም አክለው ተናግረዋል። (ማቴዎስ 13:54-58፤ ማርቆስ 6:1-3) የሚያሳዝነው፣ ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት የአገሩ ሰዎች ‘ይህ ሰው የምናውቀው ተራ አናጺ አይደል እንዴ?’ በማለት ናቁት። በጥበቡ ቢገረሙም አልተቀበሉትም። ይህ ጥበብ ከራሱ የመነጨ እንዳልሆነ አልተገነዘቡም ነበር።
3 እውነት ግን ኢየሱስ ይህን ጥበብ ያገኘው ከየት ነው? “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ለእኛ ከአምላክ የመጣ ጥበብ . . . ሆኖልናል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 1:30) የይሖዋ ጥበብ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት ተገልጧል። በመሆኑም ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ መናገር ችሏል። (ዮሐንስ 10:30) ኢየሱስ ‘ከአምላክ የመጣውን ጥበብ’ የገለጠባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመርምር።
ያስተማረው ትምህርት
4. (ሀ) የኢየሱስ መልእክት ዋነኛ ጭብጥ ምን ነበር? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ምክር ምንጊዜም ተግባራዊና አድማጮቹን የሚጠቅም የሆነው ለምንድን ነው?
4 በመጀመሪያ ኢየሱስ ምን እንዳስተማረ እንመርምር። የመልእክቱ ዋና ጭብጥ ‘የአምላክ መንግሥት ምሥራች’ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ይህ መንግሥት የይሖዋን ስም በማስቀደስ፣ ጻድቅ ገዢ መሆኑን በማረጋገጥና ለሰው ዘር ዘላቂ በረከት በማስገኘት ረገድ ትልቅ ሚና ስለሚጫወት የመልእክቱ ዋነኛ ጭብጥ መሆኑ ተገቢ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ለዕለታዊ ሕይወት የሚጠቅሙ ምክሮችን ያዘለ ነው። በትንቢት በተነገረለት መሠረት “ድንቅ መካሪ” መሆኑን አስመሥክሯል። (ኢሳይያስ 9:6) ደግሞስ ምክሩ ድንቅ መሆኑ ምን ያስገርማል? ስለ አምላክ ቃልና ፈቃድ ጥልቅ እውቀት ያለው ከመሆኑም በላይ የሰዎችን ተፈጥሮ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ከዚህም በተጨማሪ ለሰዎች ከፍተኛ ፍቅር አለው። በመሆኑም ምክሩ ምንጊዜም ተግባራዊና አድማጮቹን የሚጠቅም ነው። ኢየሱስ ያስተማረው “የዘላለም ሕይወት ቃል” ነው። አዎን፣ ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ መዳን ያስገኛል።—ዮሐንስ 6:68
5. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ከጠቀሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
5 የተራራው ስብከት፣ ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ወደር የለሽ ጥበብ የተንጸባረቀበት መሆኑን የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ከማቴዎስ 5:3 እስከ 7:27 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ስብከት ከ20 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ሊቀርብ ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ የተራራ ስብከት ውስጥ የሚገኘው ምክር፣ ጊዜ የማይሽረው በመሆኑ በዚያን ጊዜ ጠቃሚ የነበረውን ያህል ዛሬም ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር (5:23-26, 38-42፤ 7:1-5, 12)፣ በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆን (5:27-32) እንዲሁም ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት (6:19-24፤ 7:24-27) እንዴት እንደሚቻል የሚገልጹ ሐሳቦችን ጨምሮ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ጠቅሷል። ሆኖም ኢየሱስ ጥበብ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ በመናገር ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ማስረጃ በማቅረብ አሳማኝ በሆነ መንገድ አብራርቶላቸዋል።
6-8. (ሀ) ኢየሱስ ጭንቀትን ማስወገድ እንደሚገባ ለማስገንዘብ ምን አሳማኝ ምክንያቶችን ጠቅሷል? (ለ) የኢየሱስ ምክር አምላካዊ ጥበብ ያዘለ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
6 ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ ስለ ቁሳዊ ነገሮች መጨነቅን አስመልክቶ የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር እንመልከት። ኢየሱስ “ስለ ሕይወታችሁ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ” ሲል ምክር ሰጥቷል። (ቁጥር 25) ምግብና ልብስ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ስለሆኑ እነዚህን ነገሮች ስለማግኘት ማሰብ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች “አትጨነቁ” ብሎናል። b ለምን?
7 ኢየሱስ ይህን ጉዳይ አሳማኝ በሆነ መንገድ እንዴት እንዳስረዳ ተመልከት። ሕይወታችንንና አካላችንን የሰጠን ይሖዋ ሕይወታችንን ለማቆየት የሚያስችል ምግብና ሰውነታችንን ለመሸፈን የሚያስችል ልብስ መስጠት ይሳነዋል? (ቁጥር 25) አምላክ ወፎችን የሚመግብና አበቦችን ውበት የሚያለብስ ከሆነ ለሚያመልኩት ሰዎችማ ይበልጥ አያስብም? (ቁጥር 26, 28-30) በእርግጥም ከልክ በላይ መጨነቅ ዋጋ የለውም። ምንም ያህል ብንጨነቅ በዕድሜያችን ርዝማኔ ላይ ቅንጣት ታክል መጨመር አንችልም። c (ቁጥር 27) ታዲያ እንዲህ ያለውን ጭንቀት እንዴት ማስወገድ ይቻላል? ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ምንጊዜም ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ እንድንሰጥ መክሮናል። ይህን የሚያደርጉ ሰዎች በየዕለቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሰማያዊ አባታቸው ‘እንደሚሰጣቸው’ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (ቁጥር 33) በመጨረሻም ኢየሱስ ከዛሬ አልፈን ነገ ስለሚሆነው ነገር እያሰብን መጨነቅ እንደማይገባ በመግለጽ በጣም ጠቃሚ የሆነ ምክር ሰጥቷል። (ቁጥር 34) ደግሞስ ገና ይሁን አይሁን ለማናውቀው ነገር ከልክ በላይ የምንጨነቅበት ምን ምክንያት አለ? እንዲህ ያለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ሥራ ላይ ማዋላችን አስጨናቂ በሆኑ ነገሮች በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ውጥረት ይቀንስልናል።
8 በእርግጥም ኢየሱስ የሰጠው ምክር ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት ጠቃሚ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው። ይህ ሁኔታ የኢየሱስ ምክር አምላካዊ ጥበብ ያዘለ እንደሆነ አያሳይም? ሰዎች የሚሰጡት በጣም የተሻለ ነው የሚባለው ምክር እንኳ ጊዜ ሊያልፍበትና በሌላ ሊተካ ይችላል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ትምህርቶች ፈጽሞ ጊዜ የማይሽራቸው ናቸው። ይህ ድንቅ መካሪ ያስተማረው “የአምላክን ቃል” በመሆኑ በዚህ ልንገረም አይገባም።—ዮሐንስ 3:34
ያስተማረበት መንገድ
9. ኢየሱስን እንዲይዙ የተላኩት ወታደሮች ስለ ኢየሱስ ትምህርት ምን አሉ? ይህስ የተጋነነ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
9 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ የአምላክን ጥበብ እንዴት እንደሚያንጸባርቅ እንመልከት። በአንድ ወቅት ኢየሱስን እንዲይዙ ተልከው የነበሩ ወታደሮች ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፤ ለምን? “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” ብለዋል። (ዮሐንስ 7:45, 46) ይህ ምንም ማጋነን አይደለም። “ከላይ” ማለትም ከሰማይ የመጣው ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የላቀ እውቀትና ተሞክሮ አለው። (ዮሐንስ 8:23) ማንም ሰው እንደ እሱ ሊያስተምር አይችልም። ይህ ጥበበኛ አስተማሪ ከተጠቀመባቸው የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል እስቲ ሁለቱን ብቻ እንመልከት።
“ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ”
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበት መንገድ አስደናቂ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ምን ዓይነት ታሪኮችን ይጠቀም ነበር? ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ታሪኮች ውጤታማ እንደሆኑ የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?
10 ምሳሌዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ ለሕዝቡ . . . በምሳሌ ተናገረ። እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር” ሲል ይገልጻል። (ማቴዎስ 13:34) በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያጋጥሙ ነገሮችን እየጠቀሰ ጥልቅ የሆኑ እውነቶችን በማስተማር ረገድ ያለው ወደር የለሽ ችሎታ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ዘር የሚዘሩ ገበሬዎችን፣ ሊጥ የሚያቦኩ ሴቶችን፣ በገበያ ቦታ የሚጫወቱ ልጆችን፣ መረባቸውን የሚጥሉ ዓሣ አጥማጆችንና የጠፋባቸውን በግ የሚፈልጉ እረኞችን ምሳሌ አድርጎ ጠቅሷል፤ እነዚህ ነገሮች ለኢየሱስ አድማጮች እንግዳ አልነበሩም። አንድን አስፈላጊ እውነት በየዕለቱ ከሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ጋር አዛምዶ መግለጽ ትምህርቱ በአድማጮች አእምሮና ልብ ውስጥ በቀላሉ እንዲቀረጽ እንዲሁም እንዳይረሱት ለማድረግ ይረዳል።—ማቴዎስ 11:16-19፤ 13:3-8, 33, 47-50፤ 18:12-14
11 ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ጥሩ ሥነ ምግባርን ወይም መንፈሳዊ እውነትን ለማስተማር ምሳሌዎችን ወይም አጫጭር ታሪኮችን ይጠቀም ነበር። አጫጭር ታሪኮችን መረዳትም ሆነ ማስታወስ ቀላል በመሆኑ ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ታሪኮች ትምህርቱ በአድማጮቹ አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኢየሱስ በተጠቀመባቸው በብዙዎቹ ታሪኮች ላይ አባቱን ሊረሱ በማይችሉ ሕያው ምሳሌዎች ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጠፍቶ ስለነበረው ልጅ የሚናገረውን ታሪክ ሲያነብ ነጥቡ የማይገባው ማን አለ? የእውነትን መንገድ ትቶ የነበረ ሰው ከልብ ንስሐ ሲገባና ሲመለስ ይሖዋ እንደሚያዝንለትና በርኅራኄ እንደሚቀበለው ሕያው በሆነ መንገድ የሚያስተምር ታሪክ ነው።—ሉቃስ 15:11-32
12. (ሀ) ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ ጥያቄዎችን ለምን ዓላማ ይጠቀም ነበር? (ለ) ኢየሱስ ሥልጣኑን በተመለከተ ጥያቄ ያነሱትን የሃይማኖት መሪዎች አፍ ያስያዘው እንዴት ነው?
12 ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም። ኢየሱስ አድማጮቹ በራሳቸው አንድ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ፣ የልባቸውን ዝንባሌ እንዲመረምሩ ወይም አንድ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ጥያቄዎችን ይጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 12:24-30፤ 17:24-27፤ 22:41-46) የሃይማኖት መሪዎቹ ማን ሥልጣን እንደሰጠው ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ “ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን ያገኘው ከአምላክ ነው ወይስ ከሰው?” በማለት ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለሰላቸው። የሃይማኖት መሪዎቹ በጥያቄው በመደናገጥ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ?” ሆኖም “ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።” ስለዚህም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። (ማርቆስ 11:27-33፤ ማቴዎስ 21:23-27) ኢየሱስ ይህን ቀላል ጥያቄ በመጠቀም አፋቸውን ያስያዛቸው ከመሆኑም በላይ የልባቸው ተንኮል እንዲጋለጥ አድርጓል።
13-15. ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረው ታሪክ የኢየሱስን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ በሚጠቅሳቸው ምሳሌዎች መካከል አንዳንድ የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን በማንሳት ሁለቱን የማስተማሪያ ዘዴዎች አጣምሮ የተጠቀመባቸው ጊዜያት አሉ። አንድ አይሁዳዊ ሕግ አዋቂ ‘የዘላለም ሕይወት እንዳገኝ ምን ላድርግ?’ ብሎ በጠየቀው ጊዜ አምላክንና ባልንጀራውን እንዲወድ የሚያዙትን በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙ ትእዛዛት አስታወሰው። ሰውየው ግን ጻድቅ መሆኑን ማሳየት ስለፈለገ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አንድ ታሪክ ነገረው። አንድ አይሁዳዊ ሰው ብቻውን እየተጓዘ ሳለ ዘራፊዎች ደብድበው በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ። ሁለት አይሁዳውያን በዚያ አለፉ፤ መጀመሪያ ያለፈው ካህን ሲሆን ቀጣዩ ደግሞ ሌዋዊ ነው። ሁለቱም ሰውየውን እንዳላዩ ሆነው አልፈውት ሄዱ። በኋላም አንድ ሳምራዊ በዚያ በኩል መጣ። ሲያየው በጣም ስላዘነለት ቁስሎቹን በመጠራረግ ካሰረለት በኋላ ወደ እንግዶች ማደሪያ በመውሰድ በዚያ እንዲያርፍና እንዲያገግም አደረገ። ኢየሱስ ታሪኩን ሲደመድም “ታዲያ ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” ሲል ሕግ አዋቂውን ጠየቀው። ሰውየውም “ምሕረት በማሳየት የረዳው ነው” በማለት መለሰለት።—ሉቃስ 10:25-37
14 ይህ ታሪክ የኢየሱስን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው? በኢየሱስ ዘመን አይሁዳውያን እንደ “ባልንጀራ” የሚቆጥሩት የእነሱን ወግ የሚከተሉትን አይሁዳውያን ብቻ ነበር፤ ሳምራውያንንማ ጨርሶ እንደ ባልንጀራ አይመለከቷቸውም ነበር። (ዮሐንስ 4:9) ኢየሱስ፣ የተደበደበው ሰው ሳምራዊ፣ የረዳው ደግሞ አይሁዳዊ እንደሆነ አድርጎ ታሪኩን ቢያቀርብ ኖሮ አይሁዳዊው ሕግ አዋቂ ለሳምራውያን የነበረውን መጥፎ አመለካከት እንዲለውጥ ለማድረግ ይረዳው ነበር? ኢየሱስ፣ ሳምራዊው አይሁዳዊውን እንደረዳው አድርጎ ታሪኩን ያቀረበው ሆን ብሎ ነው። ኢየሱስ በታሪኩ መደምደሚያ ላይ ያቀረበውን ጥያቄም ልብ በል። ጥያቄው የሕግ አዋቂው የትኩረት አቅጣጫ እንዲቀየር የሚያደርግ ነበር። ሕግ አዋቂው ‘ባልንጀራዬ ማን ነው?’ ብሎ ሲጠይቅ ትኩረት ያደረገው የእሱ ባልንጀራ የሚሆነው ሰው እንዲያሟላ በሚጠበቅበት ነገር ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ያተኮረው መልካም በተደረገለት ማለትም በተደበደበው ሰው ላይ ሳይሆን መልካም ባደረገው ማለትም በሳምራዊው ሰው ላይ ነው። እውነተኛ ባልንጀራ የትኛውንም ዘር ሳይለይ በራሱ ተነሳስቶ ለሌሎች ፍቅር ያሳያል። ኢየሱስ ይህን ነጥብ ለማስገንዘብ ከዚህ የተሻለ ሌላ የማስተማሪያ ዘዴ ሊጠቀም አይችልም።
15 ታዲያ ሰዎች “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [ቢደነቁና]” ወደ እሱ ለመቅረብ ቢነሳሱ ያስደንቃል? (ማቴዎስ 7:28, 29) እንዲያውም በአንድ ወቅት “ብዙ ሰዎች” የሚበሉት እንኳ ሳይኖራቸው ከእሱ ጋር ሦስት ቀን ቆይተዋል!—ማርቆስ 8:1, 2
አኗኗሩ
16. ኢየሱስ በመለኮታዊ ጥበብ እንደሚመራ በተግባር ‘ያሳየው’ እንዴት ነው?
16 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ በአኗኗሩ የይሖዋን ጥበብ እንዴት እንዳንጸባረቀ እንመርምር። ጥበብ በተግባር የሚገለጽ ከመሆኑም ሌላ የተፈለገውን ውጤት ያስገኛል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል ጥበበኛ . . . ማን ነው?” ሲል ከጠየቀ በኋላ “[ይህን] በመልካም ምግባሩ ያሳይ” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ያዕቆብ 3:13) የኢየሱስ አኗኗር በመለኮታዊ ጥበብ እንደሚመራ ‘የሚያሳይ’ ነበር። በአኗኗሩም ሆነ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት፣ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንደነበረው ያሳየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
17. ኢየሱስ አኗኗሩ ፍጹም ሚዛናዊ እንደነበረ የሚጠቁሙት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
17 ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የሌላቸው ሰዎች በአብዛኛው ወደ አንድ ጽንፍ የመሄድ ዝንባሌ እንደሚታይባቸው አስተውለሃል? አዎን፣ ሚዛናዊ መሆን ጥበብ ይጠይቃል። ኢየሱስ በመለኮታዊ ጥበብ ስለሚመራ ፍጹም ሚዛናዊ ነበር። በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ነገሮች ነበር። ምሥራቹን በማወጁ ሥራ ተጠምዶ ነበር። “የመጣሁት ለዚሁ ነው” ሲል ተናግሯል። (ማርቆስ 1:38) ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጥ እንዳልነበር የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ብዙም ቁሳዊ ንብረት አልነበረውም። (ማቴዎስ 8:20) ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል ባሕታዊ ነበር ማለት አይደለም። ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደሆነው እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ደስተኛ የነበረ ሲሆን ሌሎችም እንዲደሰቱ ያደርግ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ 6:15) በሙዚቃ፣ በዘፈንና በጭፈራ በሚደምቀው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኘ ጊዜ የሠርጉን የደስታ መንፈስ የሚያጠፋ ነገር አላደረገም። እንዲያውም የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦታል፤ እንደሚታወቀው ደግሞ የወይን ጠጅ “የሰውን ልብ ደስ [ያሰኛል]።” (መዝሙር 104:15፤ ዮሐንስ 2:1-11) ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት በሰዎች ቤት የተጋበዘ ሲሆን እነዚህንም አጋጣሚዎች ለማስተማር ተጠቅሞባቸዋል።—ሉቃስ 10:38-42፤ 14:1-6
18. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ሌሎችን የሚይዝበት መንገድም ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው የሚያሳይ ነበር። የሰዎችን አፈጣጠር ማወቁ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ረድቶታል። ፍጹም እንዳልሆኑ በሚገባ ያውቅ የነበረ ቢሆንም ያሏቸውን መልካም ባሕርያትም ተገንዝቧል። ይሖዋ ወደ ራሱ የሳባቸው እነዚህ ሰዎች ለውጥ አድርገው ምን ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስተውሏል። (ዮሐንስ 6:44) አንዳንድ ድክመቶች ቢኖሩባቸውም እምነት ጥሎባቸዋል። ለደቀ መዛሙርቱ ከባድ ኃላፊነት መስጠቱ እምነት እንደጣለባቸው የሚያሳይ ነው። ምሥራቹን የመስበክ ተልእኮ የሰጣቸው ሲሆን ይህን ተልእኮ እንደሚወጡም እርግጠኛ ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የሰጣቸውን ሥራ በታማኝነት እንዳከናወኑ ይመሠክራል። (የሐዋርያት ሥራ 2:41, 42፤ 4:33፤ 5:27-32) በእርግጥም ኢየሱስ በእነሱ ላይ እምነት መጣሉ ትክክል ነበር።
19. ኢየሱስ ‘ገርና በልቡ ትሑት’ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
19 በምዕራፍ 20 ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ትሕትናና ገርነት ከጥበብ ጋር የሚዛመዱ ባሕርያት እንደሆኑ ይገልጻል። በዚህ ረገድ ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ኢየሱስስ? ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየው ትሕትና ልብ የሚነካ ነው። ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን ከእነሱ ይበልጥ ነበር። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱን አልናቃቸውም። የበታች እንደሆኑ ወይም ብቃት እንደሌላቸው ሆኖ እንዲሰማቸውም አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ያለባቸውን የአቅም ገደብ ግምት ውስጥ ያስገባ የነበረ ሲሆን ድክመቶቻቸውንም በትዕግሥት ያልፍ ነበር። (ማርቆስ 14:34-38፤ ዮሐንስ 16:12) ሕፃናት እንኳ ሳይፈሩ ወይም ሳይሸማቀቁ ይቀርቡት የነበረ መሆኑ አስደናቂ አይደለም? በነፃነት ሊቀርቡት የቻሉት ‘ገርና በልቡ ትሑት’ መሆኑን ስለተገነዘቡ ነው።—ማቴዎስ 11:29፤ ማርቆስ 10:13-16
20. ኢየሱስ ልጇ በጋኔን የተያዘች ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት ካቀረበችለት ልመና ጋር በተያያዘ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
20 ኢየሱስ የይሖዋን የትሕትና ባሕርይ ያንጸባረቀበት ሌላም ወሳኝ መንገድ አለ። ምሕረት ለማሳየት በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ምክንያታዊና እሺ ባይ መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ አንዲት ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት፣ ጋኔን የያዛትን ልጇን እንዲፈውስላት የጠየቀችውን ጊዜ አስታውስ። ኢየሱስ ልጇን እንደማይፈውስላት በሦስት የተለያዩ መንገዶች ጠቁሟት ነበር፦ በመጀመሪያ ምንም መልስ ሳይሰጣት ቀረ፤ ቀጥሎ ደግሞ የተላከው ለአይሁድ እንጂ ለአሕዛብ አለመሆኑን በቀጥታ ነገራት፤ በመጨረሻም ይህንኑ ነጥብ የሚያስገነዝብ ምሳሌ በደግነት ነገራት። ሆኖም ሴትየዋ ውትወታዋን በመቀጠል ከፍተኛ እምነት እንዳላት አሳየች። ኢየሱስ ይህን ለየት ያለ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ምን ምላሽ ሰጠ? ሐሳቡን በመለወጥ፣ አላደርግም ብሎ የነበረውን ነገር አደረገ። የሴትየዋን ልጅ ፈወሰላት። (ማቴዎስ 15:21-28) ይህ እጅግ የሚያስደንቅ ትሕትና አይደለም? ትሕትና ደግሞ የእውነተኛ ጥበብ ዋና መሠረት ነው።
21. የኢየሱስን ባሕርይ፣ ያስተማረውን ትምህርትና ያደረጋቸውን ነገሮች ለመኮረጅ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
21 በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ የሆነው ሰው ያስተማረው ትምህርትና ያደረገው ነገር በወንጌሎች ውስጥ ሰፍሮ የሚገኝ በመሆኑ እጅግ አመስጋኞች ነን! ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን እናስታውስ። የኢየሱስን ባሕርይ፣ ያስተማረውን ትምህርትና ያደረጋቸውን ነገሮች በመኮረጅ የአምላክን ጥበብ ማዳበር እንችላለን። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የአምላክን ጥበብ እንዴት በሕይወታችን ማሳየት እንደምንችል እንመለከታለን።
a በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አናጺዎች ቤቶችን ይገነቡ እንዲሁም የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችንና የእርሻ መገልገያ መሣሪያዎችን ይሠሩ ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ሰማዕቱ ጀስቲን “ኢየሱስ ሞፈርና ቀንበር በመሥራት የሚታወቅ አናጺ ነበር” ሲል ጽፏል።
b “መጨነቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ሰው ሐሳቡ መከፋፈሉን ወይም ትኩረቱ መሰረቁን ያመለክታል። በመሆኑም ቃሉ በማቴዎስ 6:25 ላይ የተሠራበት ሐሳብን የሚከፋፍልንና ደስታን የሚያሳጣን ጭንቀትና ፍርሃት ለማመልከት ነው።
c እንዲያውም ከልክ ያለፈ ጭንቀትና ውጥረት ለልብ በሽታና ለሌሎች በርካታ በሽታዎች በማጋለጥ ዕድሜን ሊያሳጥር እንደሚችል አንዳንድ ሳይንሳዊ ጥናቶች ይጠቁማሉ።