ምዕራፍ 30
“በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”
1-3. ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋ የተወልንን ምሳሌ መኮረጃችን ምን ውጤት ያስገኛል?
“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት የሚከተለውን እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ፦ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር መልሶ ይክሳል። ፍቅርን መቀበል ደስታ የሚያስገኝ ቢሆንም ፍቅርን ለሌሎች መስጠት ወይም ማሳየት የሚያስገኘው ደስታ ግን እጅግ የላቀ ነው።
2 ይህን እውነታ በሰማይ ካለው አባታችን ይበልጥ የሚያውቅ የለም። በዚህ ክፍል ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ከሁሉ የላቀ የፍቅር ተምሳሌት ነው። ከይሖዋ በላቀ ደረጃ ፍቅርን ያሳየ ማንም የለም፤ ይህን ባሕርይ ለረጅም ዘመን በማንጸባረቅ ረገድም ቢሆን ተወዳዳሪ አይገኝለትም። ታዲያ ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ሊያስደንቀን ይገባል?—1 ጢሞቴዎስ 1:11
3 አፍቃሪ የሆነው አምላካችን በተለይ ፍቅርን በማሳየት ረገድ እሱን ለመምሰል እንድንጥር ይፈልጋል። ኤፌሶን 5:1, 2 “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤ . . . በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” ይላል። ፍቅርን በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ ከኮረጅን፣ በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ መቅመስ እንችላለን። በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ’ የሚሰጠንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ በማድረጋችን ይሖዋን እናስደስተዋለን፤ ይህ ደግሞ ትልቅ እርካታ ያስገኝልናል። (ሮም 13:8) ይሁን እንጂ ‘በፍቅር መመላለሳችንን መቀጠላችን’ አስፈላጊ የሆነባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።
ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት
4, 5. ለእምነት ባልንጀሮቻችን የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ፍቅር ለእውነተኛ ክርስትና መሠረታዊ የሆነ ባሕርይ ነው። ፍቅር ከሌለን ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አንችልም። ከሁሉ የከፋው ደግሞ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት የሚያሳጣን መሆኑ ነው። የአምላክ ቃል እነዚህን እውነታዎች እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚያሳይ ተመልከት።
5 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34, 35) “እኔ እንደወደድኳችሁ” ማለቱን ልብ በል፤ አዎን፣ ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት ፍቅር እንድናሳይ ታዝዘናል። በምዕራፍ 29 ላይ ኢየሱስ የሌሎችን ጥቅምና ፍላጎት በማስቀደም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ የላቀ ምሳሌ እንደተወልን ተመልክተናል። እኛም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት ይጠበቅብናል፤ ደግሞም ፍቅራችን ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች እንኳ ሳይቀር በግልጽ መታየት ይኖርበታል። በእርግጥም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀው ይህ የወንድማማች ፍቅር የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን የሚያሳውቅ መለያ ምልክት ነው።
6, 7. (ሀ) የይሖዋ ቃል ለፍቅር የላቀ ግምት እንደሚሰጥ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የተናገረው ስለ የትኛው ፍቅር ነው?
6 ፍቅር የሚጎድለን ቢሆንስ? ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር . . . ከሌለኝ በኃይል እንደሚጮኽ ደወል ወይም ሲምባል ሆኛለሁ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:1) የሚጮኽ ደወልም ሆነ ሲምባል የሚያወጡት ድምፅ የሚረብሽ ነው። እንዴት ተስማሚ ምሳሌ ነው! ፍቅር የሌለው ሰው፣ የሚረብሽና ጆሮ የሚያደነቁር ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ሊሰሙት እንደማይፈልጉት ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ ነው። እንዲህ ያለ ሰው ከሌሎች ጋር እንዴት ጥሩ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል? በተጨማሪም ጳውሎስ “ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:2) እስቲ አስበው፣ አንድ ሰው የቱንም ያህል ትልቅ ነገር ማከናወን ቢችል ፍቅር ግን ከሌለው “ጥቅሙ ምንድን ነው?” (ሕያው ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) የይሖዋ ቃል ለፍቅር ምን ያህል የላቀ ግምት እንደሚሰጥ ከዚህ መረዳት አይቻልም?
7 ይሁንና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የሚገኙትን ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት እንመርምር። በዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ የሚገልጸው አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ወይም እኛ ለአምላክ ያለንን ፍቅር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ የተናገረው አንዳችን ለሌላው ልናሳየው ስለሚገባው ፍቅር ነው። ፍቅር የሚያደርጋቸውንና የማያደርጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝሯል።
ፍቅር የሚያደርገው ነገር
8. ታጋሽ መሆናችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
8 “ፍቅር ታጋሽ . . . ነው።” ስለዚህ ፍቅር ለማሳየት ሌሎችን በትዕግሥት መቻል አለብን ማለት ነው። (ቆላስይስ 3:13) እንዲህ ዓይነት ትዕግሥት ማሳየት እንደሚያስፈልገን ጥያቄ የለውም። እኛም ሆንን አብረውን የሚያገለግሉት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም አንዳችን ሌላውን የምናበሳጭበት ጊዜ እንደሚኖር የታወቀ ነው። ታጋሾችና ቻዮች መሆናችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የሚፈጠሩ ቀላል ቅሬታዎችን እንዲሁ ማለፍ እንድንችል ይረዳናል፤ ይህም የጉባኤው ሰላም እንዳይደፈርስ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
9. ለሌሎች ደግነት ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
9 “ፍቅር . . . ደግ ነው።” ደግነት ሌሎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን በማድረግና አሳቢነት የሚንጸባረቅባቸውን ቃላት በመናገር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ፍቅር፣ ደግነት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች እንድንፈልግ ያነሳሳናል፤ በተለይ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች። ለምሳሌ ብቸኝነት የሚሰማቸውና ጠያቂ የሚያስፈልጋቸው አረጋዊ ወንድም ሊኖሩ ይችላሉ። ብቻዋን ሆና ልጆቿን የምታሳድግ ወይም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላት እህት እገዛ ወይም ማበረታቻ ያስፈልጋት ይሆናል። ወይም ደግሞ የሚያጽናናው ወዳጅ የሚፈልግ የታመመ ወይም ችግር ላይ የወደቀ ወንድም ሊኖር ይችላል። (ምሳሌ 12:25፤ 17:17) እነዚህ ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት ደግነት ለማሳየት የምንጥር ከሆነ የፍቅራችን እውነተኝነት በግልጽ ይታያል።—2 ቆሮንቶስ 8:8
10. ሐቁን መቀበል አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ፍቅር ከእውነት ጎን እንድንቆምና እውነትን እንድንናገር የሚረዳን እንዴት ነው?
10 “ፍቅር . . . ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ፍቅር . . . ከእውነት ጎን በደስታ ይቆማል” ይላል። ፍቅር እውነት ለሆነው ነገር እንድንቆምና ‘እርስ በርሳችን እውነትን እንድንነጋገር’ ይገፋፋናል። (ዘካርያስ 8:16) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የምንወደው ሰው ከባድ ኃጢአት ሠራ እንበል፤ ለይሖዋ እንዲሁም ስህተቱን ለሠራው ሰው ያለን ፍቅር ኃጢአቱን ለመሸፋፈን፣ ለማቃለል ይባስ ብሎም ስለ ጉዳዩ ለመዋሸት ከመሞከር ይልቅ አምላክ ያወጣው መሥፈርት የሚጠይቀውን ነገር እንድናደርግ ኃይል ይሰጠናል። እርግጥ ነው፣ እውነታውን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ሆኖም ለዚህ ወዳጃችን ከልብ የምናስብ ከሆነ የአምላክን ፍቅራዊ ተግሣጽ እንዲያገኝና እንዲስተካከል እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ምሳሌ 3:11, 12) በተጨማሪም በፍቅር የምንመራ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18
11. ፍቅር ‘ሁሉን ችሎ የሚያልፍ’ በመሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚሠሯቸውን ስህተቶች በተመለከተ ምን ማድረግ አይኖርብንም?
11 “ፍቅር . . . ሁሉን ችሎ ያልፋል።” ይህ አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ፍቅር ሁሉን ይሸፍናል” ማለት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) አንደኛ ጴጥሮስ 4:8 “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” በማለት ይገልጻል። አዎን፣ በፍቅር የሚመራ አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልንጀሮቹን ድክመትና ገመና ሁሉ አይገልጥም። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችን የሚሠሯቸው ስህተቶች ቀላል ናቸው፤ በመሆኑም በፍቅር ልንሸፍንላቸው ይገባል።—ምሳሌ 10:12፤ 17:9
12. ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልሞና ላይ እምነት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ ከጳውሎስ ምን ልንማር እንችላለን?
12 “ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል።” የሞፋት ትርጉም ፍቅር “ምንጊዜም ጥሩ ጥሩውን ማመን ይቀናዋል” ይላል። የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር በጥርጣሬ ዓይን አንመለከትም። ፍቅር ስለ ወንድሞቻችን ‘ጥሩ ጥሩውን እንድናምን’ እና እንዳንጠረጥራቸው ይረዳናል። a ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው ፊልሞና፣ ትቶት ሄዶ የነበረውንና ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን የሆነውን አገልጋዩን አናሲሞስን በቀና መንፈስ እንዲቀበለው ለማበረታታት ነው። ጳውሎስ ፊልሞናን ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ በፍቅር ተማጽኖታል። ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ ያለውን መተማመን ሲገልጽ “ይህን የምጽፍልህ በዚህ እንደምትስማማ በመተማመንና ከምጠይቅህም በላይ እንደምታደርግ በማወቅ ነው” ብሏል። (ቁጥር 21) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እምነት እንደምንጥልባቸው እንድንነግራቸው ይገፋፋናል፤ ይህ ደግሞ መልካም ባሕርያቸው እንዲወጣ ያደርጋል።
13. ለወንድሞቻችን መልካም እንደምንመኝ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13 “ፍቅር . . . ሁሉን ተስፋ ያደርጋል።” ፍቅር ሁሉን ማመን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ተስፋ ያደርጋል። ወንድሞቻችንን ስለምንወዳቸው መልካም የሆነውን ነገር እንመኝላቸዋለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም “ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል” የሚሰጠውን ፍቅራዊ እርዳታ ተቀብሎ ይስተካከላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። (ገላትያ 6:1) እምነታቸው የተዳከመባቸው ወንድሞቻችንም ቢሆኑ ዳግመኛ በመንፈሳዊ እንደሚበረቱ ተስፋ እናደርጋለን። እምነታቸው እንዲጠነክር ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ ጥረት በማድረግ በትዕግሥት እንይዛቸዋለን። (ሮም 15:1፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) አንድ የምንወደው ሰው ከእውነት መንገድ ቢወጣ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ልጅ አንድ ቀን ልብ እንደሚገዛና ወደ ይሖዋ እንደሚመለስ ተስፋ እናደርጋለን።—ሉቃስ 15:17, 18
14. በጉባኤ ውስጥ ጽናታችንን የሚፈታተን ሁኔታ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ፍቅር ሊረዳን የሚችለውስ እንዴት ነው?
14 “ፍቅር . . . ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።” ጽናት፣ የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ወይም ችግር ሲያጋጥመን ተስፋ ቆርጠን ወደኋላ እንዳንል ይረዳናል። ጽናታችንን የሚፈታተን ነገር የሚመጣው ከጉባኤ ውጭ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎችም ፈተና ሊሆኑብን ይችላሉ። ወንድሞቻችን ፍጹማን ባለመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኙን ይሆናል። አሳቢነት የጎደለው አነጋገር ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ወይም አንድ የጉባኤ ጉዳይ እኛ ባሰብነው መንገድ እልባት አላገኘ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በጉባኤ ውስጥ የተከበረ አንድ ወንድም የሚያደርገው ነገር ሊያበሳጨንና ‘እንዴት አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያደርጋል?’ በሚል ስሜት ቅሬታ ሊያድርብን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ራሳችንን ከጉባኤው በማግለል ይሖዋን ማገልገላችንን እናቆማለን? ፍቅር ካለን እንዲህ እንደማናደርግ የታወቀ ነው! አዎን፣ ፍቅር ካለን አንድ ወንድም ያለበት ድክመት እሱም ሆነ መላው ጉባኤ ያለውን መልካም ጎን ማየት እንዲሳነን ሊያደርገን አይችልም። ፍቅር፣ ፍጽምና የጎደለው አንድ ሰው የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ነገር ምንም ይሁን ምን ለአምላክ ታማኝ እንድንሆንና ከጉባኤው ጎን እንድንቆም ይረዳናል።—መዝሙር 119:165
ፍቅር የማያደርገው ነገር
15. ተገቢ ያልሆነን ቅናት ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው? ፍቅር ይህን ጎጂ ስሜት እንድናስወግድ የሚረዳንስ እንዴት ነው?
15 “ፍቅር አይቀናም።” ተገቢ ያልሆነ ቅናት በሌሎች ንብረት፣ መብት ወይም ችሎታ እንድንመቀኝ ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ቅናት ከራስ ወዳድነት የመነጨ ጎጂ ስሜት ሲሆን ይህን ስሜት ማስወገድ ካልተቻለ የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርስ ይችላል። የቅናት መንፈስ እንዳያድርብን ምን ሊረዳን ይችላል? (ያዕቆብ 4:5) በአጭር አነጋገር ፍቅር ነው። ይህ ውድ ባሕርይ ሌሎች ከእኛ የተሻለ ነገር ቢያገኙ ወይም ቢኖራቸው ከመቅናት ይልቅ አብረናቸው እንድንደሰት ያደርገናል። (ሮም 12:15) በተጨማሪም ፍቅር አንድ ሰው ባለው ልዩ ችሎታ ወይም ባከናወነው ላቅ ያለ ነገር ቢመሰገን ቅር እንዳንሰኝ ይረዳናል።
16. ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወድ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት እያከናወንን ስላለው ነገር ጉራ ከመንዛት የምንታቀበው ለምንድን ነው?
16 “ፍቅር . . . ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም።” ፍቅር ስለ ችሎታችን ወይም ስላከናወንነው ነገር ጉራ ከመንዛት እንድንቆጠብ ያደርገናል። ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ በአገልግሎት ስላገኘነው ስኬት ወይም በጉባኤ ውስጥ ስላገኘናቸው መብቶች ነጋ ጠባ እናወራለን? እንዲህ ያለው ጉራ የሌሎችን ቅስም ሊሰብርና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱ ሊያደርግ ይችላል። ፍቅር፣ አምላክ በሰጠን የአገልግሎት መብት ስላከናወንናቸው ነገሮች ጉራ ከመንዛት እንድንታቀብ ያደርገናል። (1 ቆሮንቶስ 3:5-9) ጳውሎስ እንዳለው ፍቅር “አይታበይም” ወይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚለው “ራሱን ከልክ በላይ ከፍ አድርጎ አይመለከትም።” ፍቅር ስለ ራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዳያድርብን ይረዳናል።—ሮም 12:3
17. ፍቅር ለሌሎች እንዴት ያለ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል? ምን ዓይነት ምግባር ከማሳየትስ እንድንቆጠብ ያደርገናል?
17 “ፍቅር . . . ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም።” ጨዋነት የጎደለው ምግባር ያለው ሰው ከሥርዓት ውጭ የሆነ ወይም ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ያደርጋል። እንዲህ ያለው ምግባር ለሌሎች ስሜት ደንታ ቢስ መሆንን የሚያሳይ ስለሆነ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው። በአንጻሩ ግን ፍቅር ሥርዓታማ እንድንሆንና ለሌሎች አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። ፍቅር ጨዋ እንድንሆን፣ አምላካዊ ምግባር እንዲኖረንና ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት እንድናሳይ ያደርገናል። በመሆኑም ፍቅር “አሳፋሪ ምግባር” ማለትም ክርስቲያን ወንድሞቻችንን የሚያሸማቅቅ ወይም ቅር የሚያሰኝ ጠባይ ከማሳየት እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ኤፌሶን 5:3, 4
18. አፍቃሪ የሆነ ሰው ሁሉ ነገር እኔ ባልኩት መንገድ ካልሆነ ብሎ ድርቅ የማይለው ለምንድን ነው?
18 “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን አገላለጽ “ፍቅር እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ አይልም” ሲል ተርጉሞታል። አፍቃሪ የሆነ ሰው ሁልጊዜ የእሱ ሐሳብ ብቻ ትክክል የሆነ ይመስል ሁሉም ነገር በእኔ መንገድ ካልተከናወነ አይልም። ከእሱ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በማግባባትና በማሳመን የእሱን አመለካከት እንዲደግፉ ለመጫን አይሞክርም። እንዲህ ያለው ግትርነት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከኩራት የመነጨ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “ኩራት ጥፋትን . . . ይቀድማል” ይላል። (ምሳሌ 16:18) ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ አመለካከታቸውን የምናከብር ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእኛን አመለካከት ለመለወጥ ፈቃደኞች እንሆናለን። ይህም ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” ሲል የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል።—1 ቆሮንቶስ 10:24
19. ፍቅር ካለን ሌሎች ሲያስቀይሙን ምን እናደርጋለን?
19 “ፍቅር . . . በቀላሉ አይበሳጭም። . . . የበደል መዝገብ የለውም።” ፍቅር ሌሎች በሚናገሩትም ሆነ በሚያደርጉት ነገር ቶሎ አይበሳጭም። እርግጥ ነው፣ ሌሎች ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲፈጽሙብን እንደምናዝን የታወቀ ነው። ሆኖም እንድንቆጣ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ቢኖረንም እንኳ ፍቅር ካለን ቁጣችን ቶሎ ይበርዳል። (ኤፌሶን 4:26, 27) ቅር ያሰኘንን አነጋገር ወይም ድርጊት በመዝገብ ጽፈን የመያዝ ያህል ሁልጊዜ በውስጣችን ይዘን አንኖርም። ከዚህ ይልቅ ፍቅር ካለን አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል እንገፋፋለን። በምዕራፍ 26 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እስካለ ድረስ ይቅር ይላል። አንዴ ይቅር ካለ ደግሞ የሠራነውን በደል ዳግመኛ አያስበውም፤ ወይም ያንኑ ጥፋት መልሶ መላልሶ እየጠቀሰ አይወነጅለንም። ይሖዋ የበደል መዝገብ የማይዝ አምላክ በመሆኑ አመስጋኞች መሆን አይገባንም?
20. አንድ የእምነት ባልንጀራችን በኃጢአት ወጥመድ ቢወድቅና መጥፎ ነገር ቢደርስበት ምን ሊሰማን አይገባም?
20 “ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ፍቅር . . . ሌሎች ሰዎች በኃጢአት ሲወድቁ በማየት አይፈነድቅም” ይላል። የሞፋት ትርጉም ደግሞ “ፍቅር ሌሎች ሲሳሳቱ አይደሰትም” ይላል። ፍቅር በዓመፅ የማይደሰት በመሆኑ ማንኛውንም የሥነ ምግባር ብልግና አቅልለን አንመለከትም። አንድ የእምነት ባልንጀራችን በኃጢአት ወጥመድ ቢወድቅና መጥፎ ነገር ቢደርስበት ምን ይሰማናል? ፍቅር ካለን ‘ጎሽ፣ ዋጋውን አገኘ!’ ብለን አንደሰትም። (ምሳሌ 17:5) ከዚህ ይልቅ ኃጢአት የሠራ አንድ ወንድም አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ከደረሰበት መንፈሳዊ ውድቀት ሲያገግም ስንመለከት ደስ ይለናል።
‘ከሁሉ የላቀው መንገድ’
21-23. (ሀ) ጳውሎስ “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ለ) በዚህ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
21 “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።” ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ለጥንት ክርስቲያኖች ስለተሰጡት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ነው። እነዚህ ስጦታዎች አምላክ፣ በወቅቱ በተቋቋመው አዲስ ጉባኤ እየተጠቀመ መሆኑን የሚያመለክቱ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች መፈወስ፣ መተንበይ ወይም በልሳን መናገር ይችሉ ነበር ማለት አይደለም። ሆኖም አንድ ክርስቲያን እነዚህ ስጦታዎች ኖሩት አልኖሩት የሚያመጣው ለውጥ አልነበረም፤ ምክንያቱም እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎች ለሁልጊዜው የሚቀጥሉ አልነበሩም። ይሁንና ማንኛውም ክርስቲያን ሊያዳብረው የሚችል ለዘላለም የሚቀጥል አንድ ነገር አለ። ይህ ነገር ከየትኛውም ተአምራዊ ስጦታ የላቀና ለዘላለም የሚጸና ነው። እንዲያውም ጳውሎስ ‘ከሁሉ የላቀው መንገድ’ ሲል ጠርቶታል። (1 ቆሮንቶስ 12:31) ይህ ‘ከሁሉ የላቀ መንገድ’ ምንድን ነው? የፍቅር መንገድ ነው።
22 በእርግጥም ጳውሎስ የገለጸው ክርስቲያናዊ ፍቅር “ለዘላለም ይኖራል”፤ በሌላ አነጋገር የሚያከትምበት ጊዜ አይኖርም። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀው የወንድማማች ፍቅር እስከዛሬም ድረስ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መለያ ምልክት ነው። በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ይህ ፍቅር እየታየ አይደለም? ይሖዋ ታማኝ ለሆኑት አገልጋዮቹ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጥ ቃል የገባ በመሆኑ ይህ ፍቅር ዘላለማዊ ነው። (መዝሙር 37:9-11, 29) እንግዲያው ‘በፍቅር መመላለሳችንን ለመቀጠል’ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ ማጣጣም እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ አፍቃሪ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በመምሰል ለዘላለም ፍቅርን እያንጸባረቅን መኖር እንችላለን።
የይሖዋ ሕዝቦች መለያ ምልክት እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር ነው
23 ስለ ፍቅር የሚያብራራው ክፍል መደምደሚያ በሆነው በዚህ ምዕራፍ ላይ አንዳችን ለሌላው ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። ይሁንና ከይሖዋ ፍቅር ብሎም ኃይል፣ ፍትሕና ጥበብ በእጅጉ የምንጠቀም ከመሆኑ አንጻር ‘ይሖዋን ከልብ እንደምወደው ላሳየው የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ይህ ጥያቄ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።