ምዕራፍ 25
‘ከአንጀት የሚራራልን አምላካችን’
1, 2. (ሀ) አንዲት እናት ልጇ ሲያለቅስ ምን ታደርጋለች? (ለ) እናት ለልጇ ካላት ርኅራኄ የሚበልጠው የማን ርኅራኄ ነው?
እኩለ ሌሊት ላይ ሕፃኑ ያለቅሳል። እናትየው ወዲያውኑ ከእንቅልፏ ነቃች። የልጇ ነገር ስለሚያሳስባት እንደ ድሮው እንቅልፍ ድብን አድርጎ አይወስዳትም። ሕፃኑ ምን ፈልጎ እንዳለቀሰ ለይታ ታውቃለች። ጡት ፈልጎ፣ መታቀፍ ፈልጎ ወይም ደግሞ የሽንት ጨርቅ እንዲቀየርለት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ሕፃኑ ያለቀሰበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የሚያስፈልገውን ታደርግለታለች። ልጇ እያለቀሰ አስችሏት ዝም ብላ አትተኛም።
2 አንዲት እናት የአብራኳ ክፋይ ለሆነው ልጇ እጅግ ጥልቅ የሆነ ርኅራኄ ስሜት እንዳላት የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላካችን ለሰው ልጆች ያለው ርኅራኄ ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። ይህን ግሩም ባሕርይ መመርመራችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል። እንግዲያው ርኅራኄ ምን እንደሆነና አምላካችን ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቀው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
ርኅራኄ ምንድን ነው?
3. “ምሕረት ማሳየት” ወይም “መራራት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ ምን ያመለክታል?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርኅራኄና በምሕረት መካከል የቅርብ ዝምድና አለ። ከአንጀት የመራራት ስሜትን የሚገልጹ በርከት ያሉ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ራኻም የተባለው የዕብራይስጥ ግስ ብዙውን ጊዜ “ምሕረት ማሳየት” ወይም “መራራት” ተብሎ ይተረጎማል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህ ግስ “የምንወዳቸውን ወይም የእኛን እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ችግር ወይም ሥቃይ ስንመለከት የሚሰማንን ጥልቅ የሆነ የርኅራኄ ስሜት” ያመለክታል። ይሖዋ ስሜቱን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ የዕብራይስጥ ቃል “ማህፀን” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ዝምድና ያለው ሲሆን “የእናት ርኅራኄ” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። a—ዘፀአት 33:19፤ ኤርምያስ 33:26
4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ርኅራኄ ለመግለጽ እናት ለልጇ ያላትን ስሜት እንደ ምሳሌ አድርጎ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ርኅራኄ ለመግለጽ እናት ለልጇ ያላትን ስሜት እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። በኢሳይያስ 49:15 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች? ከማህፀኗ ለወጣውስ ልጅ አትራራም [በዕብራይስጡ፣ ራኻም]? እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም።” ይህ ልብ የሚነካ አገላለጽ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ያህል እንደሚራራ ጎላ አድርጎ ያሳያል። እንዴት?
5 አንዲት እናት፣ ሕፃን ልጇን ማጥባት ወይም መንከባከብ ትረሳለች ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። አንድ ሕፃን ሌት ተቀን የእናቱን ፍቅርና እንክብካቤ ካላገኘ በራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል የታወቀ ነው። የሚያሳዝነው ግን “ተፈጥሯዊ ፍቅር” በጠፋበት “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ልጆቻቸውን ቸል የሚሉ አልፎ ተርፎም የሚጥሉ እናቶች እንዳሉ የሚገልጹ ዘገባዎችን መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3) ይሖዋ ግን “እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም” ሲል ተናግሯል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለው ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ምንጊዜም አይለወጥም። እናት ለልጇ ካላት ርኅራኄ እንኳ የላቀ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ ኢሳይያስ 49:15ን አስመልክተው ሲናገሩ “ይህ አገላለጽ የአምላክን ፍቅር በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተጠቀሱት እጅግ ልብ የሚነኩ መግለጫዎች አንዱ ምናልባትም ከሁሉ የላቀው ነው” ብለዋል።
6. ብዙ ሰዎች ርኅራኄን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው? ሆኖም ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?
6 ርኅራኄ የደካማነት ምልክት ነው? ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሴኔካ የተባለው በኢየሱስ ዘመን የኖረ ሮማዊ ፈላስፋና የታወቀ ምሁር “አዘኔታ የሚያሳይ ደካማ አእምሮ ያለው ነው” ሲል አስተምሯል። ሴኔካ ስሜት አልባ መሆንን የሚያበረታታው የኢስጦይኮች ፍልስፍና አራማጅ ነበር። ‘አስተዋይ ሰው ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን መርዳት ቢችልም እንዲህ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ ማሳየት የለበትም፤ ምክንያቱም ይህ አእምሮውን እረፍት ይነሳዋል’ ሲል ተናግሯል። እንዲህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት አመለካከት ሰዎች ለሌሎች ከልብ የመነጨ ርኅራኄ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው። ይሖዋ ግን እንዲህ ዓይነት አምላክ አይደለም! “ከአንጀት የሚራራና መሐሪ” አምላክ ስለመሆኑ በቃሉ ውስጥ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ያዕቆብ 5:11 የግርጌ ማስታወሻ) ደግሞም ቀጥለን እንደምንመለከተው ርኅራኄ ደካማነትን ሳይሆን ጥንካሬን የሚያሳይ አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ይህን ባሕርይ የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ ለአንድ ሕዝብ ያሳየው ርኅራኄ
7, 8. እስራኤላውያን በጥንቷ ግብፅ መከራ የደረሰባቸው እንዴት ነው? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠ?
7 ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ነገር ርኅራኄውን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ማብቂያ አካባቢ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ይኖሩ ነበር፤ በዚያ ከባድ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር። ግብፃውያን “የሸክላ ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና . . . ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን መራራ [አድርገውባቸው]” ነበር። (ዘፀአት 1:11, 14) እስራኤላውያን ሥቃዩ ሲበዛባቸው እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ታዲያ ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?
8 ይሖዋ በእጅጉ አዘነላቸው። እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “በግብፅ የሚኖረውን የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ አስገድደው በሚያሠሯቸው ሰዎች የተነሳ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ።” (ዘፀአት 3:7) ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ሲያይ ወይም ጩኸታቸውን ሲሰማ አንጀቱ አልቻለም። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 24 ላይ እንዳየነው ይሖዋ የሌላውን ችግር እንደ ራሱ የሚያይ አዛኝ አምላክ ነው። የሕዝቡን ሥቃይ እንደ ራሱ ሥቃይ አድርጎ መመልከቱ እንዲራራ አድርጎታል። ይሁንና የይሖዋ አዘኔታ በስሜት ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ እነሱን ለመርዳት እርምጃ ወስዷል። ኢሳይያስ 63:9 “በፍቅሩና በርኅራኄው ተቤዣቸው” ይላል። ይሖዋ እስራኤላውያንን “በብርቱ እጅ” ከግብፅ ነፃ አወጣቸው። (ዘዳግም 4:34) ከዚያም በተአምር እየመገበ ለም ወደሆነች ምድር አስገባቸው።
9, 10. (ሀ) ይሖዋ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላም በተደጋጋሚ ከጠላቶቻቸው ያድናቸው የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) በዮፍታሔ ዘመን ይሖዋ እስራኤላውያንን ነፃ ያወጣቸው ከእነማን ጭቆና ነው? ይህን እርምጃ እንዲወስድ የገፋፋውስ ምንድን ነው?
9 ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያሳየው ርኅራኄ በዚህ ብቻ አላበቃም። እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜያት በአምላክ ላይ በማመፃቸው ለችግር ይዳረጉ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ተጸጽተው ወደ እሱ በጮኹ ቁጥር ያድናቸው ነበር። ለምን? ‘ለሕዝቡ ስለራራ ነው።’—2 ዜና መዋዕል 36:15፤ መሳፍንት 2:11-16
10 እስቲ በዮፍታሔ ዘመን የተፈጸመውን ሁኔታ ተመልከት። እስራኤላውያን የሐሰት አማልክትን ወደማምለክ ዘወር ብለው ስለነበረ ይሖዋ ለ18 ዓመታት አሞናውያን እንዲጨቁኗቸው ፈቀደ። በመጨረሻ እስራኤላውያን ንስሐ ገቡ። መጽሐፍ ቅዱስ “እነሱም ከመካከላቸው ባዕዳን አማልክትን አስወግደው ይሖዋን አገለገሉ፤ በመሆኑም በእስራኤል ላይ እየደረሰ የነበረውን መከራ ሊታገሥ አልቻለም” በማለት ይገልጻል። (መሳፍንት 10:6-16) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ከልብ ንስሐ ከገቡ በኋላ ሲሠቃዩ ማየት አላስቻለውም። በመሆኑም የርኅራኄ አምላክ የሆነው ይሖዋ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ እንዲያወጣ ለዮፍታሔ ኃይል ሰጠው።—መሳፍንት 11:30-33
11. ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ካደረገው ነገር ስለ ርኅራኄ ምን እንማራለን?
11 ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ የያዘበት መንገድ ስለ ርኅራኄ ምን ያስተምረናል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ርኅራኄ የተቸገረን ሰው አይቶ እንዲሁ አዝኖ ከማለፍ የበለጠ ነገር እንደሚጠይቅ እንረዳለን። አንዲት እናት ልጇ ሲያለቅስ በርኅራኄ ተገፋፍታ የሚያስፈልገውን እንደምታደርግለት የሚገልጸውን ምሳሌ አስታውስ። በተመሳሳይም ይሖዋ የሕዝቦቹን ጩኸት እየሰማ ዝም አይልም። ከዚህ ይልቅ ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ ተገፋፍቶ ሕዝቦቹ እየደረሰባቸው ካለው ሥቃይ እፎይታ የሚያገኙበትን እርምጃ ይወስዳል። በተጨማሪም ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያደረገው ነገር ርኅራኄ የደካማነት ምልክት አለመሆኑን ያሳያል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማዳን ሲል ጠንከር ያለና ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ የገፋፋው ይህ ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ርኅራኄ የሚያሳየው በቡድን ደረጃ ብቻ ነው?
ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚያሳየው ርኅራኄ
12. ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች ያለውን ርኅራኄ የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች እንደሚራራ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ለድሆች ያሳየውን አሳቢነት እንመልከት። ይሖዋ፣ የትኛውም እስራኤላዊ አጋጣሚዎች በሚፈጥሩት ሁኔታ ሳቢያ ለድህነት ሊዳረግ እንደሚችል ያውቅ ነበር። እስራኤላውያን ለድሆች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? ይሖዋ የሚከተለውን ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፦ “በድሃው ወንድምህ ላይ ልብህ አይጨክንበት ወይም እጅህን አትጠፍበት። በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠው ልብህ ቅር እያለው መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ በሥራህ ሁሉና በምታከናውነው በማንኛውም ነገር የሚባርክህ በዚህ የተነሳ ነው።” (ዘዳግም 15:7, 10) በተጨማሪም እስራኤላውያን የእርሻቸውን ዳርና ዳር ሙልጭ አድርገው እንዳያጭዱ እንዲሁም ቃርሚያውን እንዳይለቅሙ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ማሳውን የሚቃርሙት ችግረኞች ናቸው። (ዘሌዋውያን 23:22፤ ሩት 2:2-7) ሕዝቡ በመካከላቸው ላሉት ድሆች የወጣውን ይህን አሳቢነት የተንጸባረቀበት ሕግ ከታዘዙ ችግረኛ የሆኑ ግለሰቦች ለልመና አይዳረጉም። ይህ የይሖዋን ርኅራኄ የሚያሳይ አይደለም?
13, 14. (ሀ) ዳዊት የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከልብ እንደሚያስብልን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ‘ልባቸው ለተሰበረና መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ ቅርብ መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
13 አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ዛሬም ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል። የሚደርስብንን መከራና ሥቃይ ሁሉ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማሉ። ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።” (መዝሙር 34:15, 18) እዚህ ላይ የተገለጹትን ሰዎች በተመለከተ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “እነዚህ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ልባቸው የተሰበረ ከመሆኑም በላይ የጥፋተኝነት ስሜት አንገታቸውን አስደፍቷቸዋል። ራሳቸውን አዋርደውና ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ፤ እንዲሁም ምንም እንደማይረቡና ከንቱ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።” እንዲህ ያሉ ሰዎች ይሖዋ ከእነሱ የራቀ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ይሆናል፤ በፊቱ ከቁብ የማይቆጠሩ በመሆናቸው ስለ እነሱ ሊያስብ እንደማይችል ሆኖ ይሰማቸዋል። ሐቁ ግን ይህ አይደለም። የዳዊት ቃላት ይሖዋ ‘ምንም እንደማይረቡ የሚሰማቸውን’ ሰዎች በፍጹም እንደማይተዋቸው ያረጋግጡልናል። ሩኅሩኅ የሆነው አምላካችን ከምንጊዜውም ይበልጥ የእሱ ድጋፍ የሚያስፈልገን በዚህ ወቅት እንደሆነ ያውቃል፤ ስለሆነም ቅርባችን ይሆናል።
14 እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ተመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ የምትገኝ አንዲት እናት የሁለት ዓመት ልጇ በመተንፈሻ አካል ላይ በሚከሰት ከባድ ሕመም እየተሠቃየ ስለነበረ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ይዛው ሄደች። ዶክተሮቹ ልጁን ከመረመሩት በኋላ እዚያው ሆስፒታል ማደር እንዳለበት ነገሯት። በዚህ ጊዜ እናቲቱ ምን አደረገች? በሆስፒታሉ መኝታ ክፍል ውስጥ ባለ አንድ ወንበር ላይ ልጇ አጠገብ ኩርምት ብላ አደረች! ልጇ ስለታመመ ከአጠገቡ መራቅ አልፈለገችም። አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ከዚህ የበለጠ እንደሚያደርግልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! ደግሞስ የተፈጠርነው በእሱ አምሳል አይደል? (ዘፍጥረት 1:26) በመዝሙር 34:18 ላይ የሚገኙት ልብ የሚነኩ ቃላት ‘ልባችን በሚሰበርበት’ ወይም ‘መንፈሳችን በሚደቆስበት’ ወቅት ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ‘ቅርባችን እንደሚሆን’ ይገልጹልናል። በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሚራራልን ከመሆኑም በላይ በሚያስፈልገን ሁሉ ይረዳናል።
15. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚረዳን እንዴት ነው?
15 ታዲያ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚረዳን እንዴት ነው? ችግሩን ያስወግድልናል ማለት ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ወደ እሱ የሚጮኹትን ሰዎች የሚረዳባቸው ብዙ ዝግጅቶች አሉት። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን የሚችል እጅግ ጠቃሚ ምክር ይዟል። በጉባኤ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በሚረዱበት ጊዜ የእሱን ርኅራኄ ለማንጸባረቅ የሚጥሩ በመንፈሳዊ የጎለመሱ የበላይ ተመልካቾችን አዘጋጅቷል። (ያዕቆብ 5:14, 15) “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደመሆኑ መጠን “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” ይሰጣል። (መዝሙር 65:2፤ ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ መንግሥት መጥቶ ችግሮችን ሁሉ እስኪያስወግድልን ድረስ ለመጽናት የሚያስችለንን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ለእነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች አመስጋኞች አይደለንም? እነዚህ የይሖዋ ርኅራኄ መግለጫዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።
16. ይሖዋ ርኅራኄውን ያሳየበት ከሁሉ የላቀ መንገድ ምንድን ነው? ይህስ በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው?
16 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ርኅራኄውን ከሁሉ በላቀ መንገድ ያሳየው ከማንም በላይ የሚወደውን ልጁን ለእኛ ቤዛ አድርጎ በመስጠት ነው። ይህ መሥዋዕት የይሖዋን ፍቅር የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ መዳን የምናገኝበትን በር ከፍቶልናል። ይሖዋ የቤዛውን ዝግጅት ያደረገው ለእያንዳንዳችን መሆኑን አስታውስ። የአጥማቂው ዮሐንስ አባት የሆነው ዘካርያስ ይህ ስጦታ ‘አምላካችን ከአንጀት እንደራራልን’ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ መናገሩ የተገባ ነው።—ሉቃስ 1:78
ይሖዋ ርኅራኄ ከማሳየት የሚቆጠብበት ጊዜ
17-19. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ርኅራኄ ገደብ እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ርኅራኄ እንዲሟጠጥ ያደረገው ምንድን ነው?
17 የይሖዋ ርኅራኄ ገደብ እንደሌለው አድርገን ልናስብ ይገባል? በፍጹም፤ ይሖዋ በእሱ ላይ ማመፃቸውን ለሚቀጥሉ ሰዎች ርኅራኄ እንደማያሳይ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዕብራውያን 10:28) እንዲህ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ የማያሳየው ለምን እንደሆነ ለመረዳት የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ መለስ ብለን እንመልከት።
18 ምንም እንኳ ይሖዋ እስራኤላውያንን በተደጋጋሚ ጊዜ ከጠላቶቻቸው ያዳናቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ ርኅራኄው ተሟጥጦ ነበር። እነዚህ አንገተ ደንዳና ሰዎች ጣዖት ያመልኩ የነበረ ከመሆኑም በላይ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ እስከ ማስገባት ደርሰዋል! (ሕዝቅኤል 5:11፤ 8:17, 18) በተጨማሪም እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነድና ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣ ቃሉን ይንቁና በነቢያቱ ላይ ያፌዙ ነበር።” (2 ዜና መዋዕል 36:16) እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ለእነሱ ርኅራኄ ሊያሳይ የሚችልበት ምክንያት እስኪያጣ ድረስ በዓመፅ ድርጊታቸው ገፉበት፤ በመሆኑም ይሖዋ በእነሱ ላይ የጽድቅ ቁጣ መቆጣቱ ተገቢ ነበር። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስከተለ?
19 ይሖዋ ለሕዝቡ ርኅራኄ ከማሳየት ለመታቀብ ተገድዷል። “ምንም ዓይነት ርኅራኄም ሆነ አዘኔታ አላሳይም፤ ምሕረትም አላደርግላቸውም፤ እነሱን ከማጥፋት ምንም ነገር አያግደኝም” ሲል ተናግሯል። (ኤርምያስ 13:14) በመሆኑም ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የጠፉ ሲሆን እስራኤላውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወስደዋል። ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የአምላክ ርኅራኄ እስኪሟጠጥ ድረስ እንዲህ ማመፃቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው!—ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:21
20, 21. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ርኅራኄው ሲሟጠጥ ምን እርምጃ ይወስዳል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የይሖዋ ርኅራኄ የሚንጸባረቅበትን የትኛውን ዝግጅት እንመረምራለን?
20 ዛሬስ ሁኔታው እንዴት ነው? ይሖዋ አልተለወጠም። ይሖዋ ለሰው ልጆች ካለው ርኅራኄ በመነሳት ምሥክሮቹ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመላው ምድር እንዲሰብኩ አዝዟል። (ማቴዎስ 24:14) አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ የመንግሥቱን መልእክት እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:14) ሆኖም ይህ የስብከት ሥራ ለዘላለም አይቀጥልም። ይሖዋ በመከራና በሥቃይ የተሞላው ይህ ክፉ ዓለም ለዘላለም እንዲቀጥል ቢፈቅድ በምንም ዓይነት የርኅራኄ መግለጫ ሊሆን አይችልም። ይሖዋ ርኅራኄው ሲሟጠጥ በዚህ ሥርዓት ላይ እርምጃ ይወስዳል። ይሁንና ይህንን እርምጃ እንዲወስድ የሚያነሳሳውም ርኅራኄ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ‘ለቅዱስ ስሙና’ ለታማኝ አገልጋዮቹ ስለሚያስብ ነው። (ሕዝቅኤል 36:20-23) ይሖዋ ክፋትን ጠራርጎ በማጥፋት ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያመጣል። ክፉዎችን አስመልክቶ ሲናገር “ዓይኔ አያዝንም፤ ደግሞም አልራራም። የተከተሉት መንገድ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ” ብሏል።—ሕዝቅኤል 9:10
21 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ይሖዋ ጥፋት ለሚጠብቃቸው ሰዎችም እንኳ ሳይቀር ርኅራኄ ያሳያል። ከልብ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኛ ሰዎች ከይሖዋ የምሕረት ዝግጅት መጠቀም ይችላሉ፤ ይህ የይሖዋ ይቅር ባይነት ርኅራኄው ከሚገለጽባቸው እጅግ የላቁ መንገዶች አንዱ ነው። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ምሕረት እንደሚያደርግ የሚያሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ግሩም ምሳሌያዊ አገላለጾችን እንመለከታለን።
a ይሁንና ራኻም የተባለው የዕብራይስጥ ግስ በመዝሙር 103:13 ላይ አባት ለልጆቹ የሚያሳየውን ምሕረት ወይም ርኅራኄ ለማመልከት ተሠርቶበታል።