ስፖርትና መዝናኛ
ምዕራፍ 16
ስፖርትና መዝናኛ
1, 2. (ሀ) አንተ የምትደሰተው በተለይ በምን ዓይነት ስፖርቶችና መዝናኛዎች ነው? (ለ) ይሖዋ በሕይወት እንድንደሰት እንደሚፈልግ የሚያሳዩ የእጁ ሥራዎች የሆኑ ምን ነገሮች አሉ? (መዝሙር 104:14–24)
በመላው ዓለም ልዩ ልዩ ስፖርቶችና የመዝናኛ ዓይነቶች ትኵረትን የሚስቡ ሆነዋል። በእነርሱ ለመደሰት ሲባልም በየዓመቱ በቢልዮን የሚቆጠር ብር ይወጣል። አንተስ ለስፖርት ፍላጎት ካላቸው ሰዎች አንዱ ነህን? ለምሳሌ የመረብ ወይም የእግር ኳስ መጫወት ትወዳለህን? ዋና፣ ቴኒስ መጫወት ወይም በሌሎች ስፖርቶች መሳተፍ ትወዳለህን? ወይስ ሲኒማ ቤት በመሄድ ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመመልከት ትደሰታለህን?
2 አንዳንድ ሰዎች እንደነዚህ ያሉት መደሰቻዎች ስሕተት ናቸው ይሉ ይሆናል። አንተስ ምን ይመስልሃል? እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ነገሮች ይከለክላል ይላሉ። ይሁን እንጂ እውነቱን ለመናገር እንዲህ የሚሉት ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ደራሲው ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ የተሳሳተ ነገር እየተናገሩ ነው። የአምላክ ቃል በሚያዝናኑ እንቅስቃሴዎች ተካፍለው ስለተደሰቱ ወጣቶች በመልካም ይናገራል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ስለተባረኩት የአምላክ ሕዝቦች ሲገልጽ “የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ” ይላል። በተጨማሪም “ለመዝፈንም ጊዜ አለው” ይላል። (ዘካርያስ 8:5፤ መክብብ 3:4) በግልጽ እንደሚታየው ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች እንድንደሰት አምላክ ዓላማው ነበር። ከአምላክ የመንፈስ ፍሬዎች አንዱ “ደስታ” ነው። (ገላትያ 5:22) ጤናማ በሆኑ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች መደሰታችን ተገቢና ተፈጥሮአዊ ነው።
ደስታን የሚጨምር መመሪያ
3–8. (ሀ) በ1 ጢሞቴዎስ 4:7, 8 ላይ ስለ መዝናኛ ምን ሚዛናዊ ምክር ተሰጥቷል? (ለ) “የሰውነት ማሠልጠኛ” ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ አንድ ሰው ስፖርትን ሥራዬ ብሎ የሚከታተል ከሆነ ምን ሊደርስ ይችላል? (ሐ) አንድ ግለሰብ በትምህርት ቤት ቡድኖች ውስጥ ገብቶ የሚጫወት ከሆነ ምን ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ? ምን ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበት ጥበብ ባለበት መንገድ ለመወሰን ምን ሊረዳው ይገባል?
3 እንደነዚህ ካሉት እንቅስቃሴዎች ደስታን እንድናገኝ ለመርዳት አምላክ በፍቅሩ ተነሳስቶ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። ለምሳሌ ከመጠን በላይ በመብላት ጤናችን እንዳይቃወስ የአምላክ ቃል “ለሥጋም ከሚሳሱ (ከሆዳሞች) ጋር አትቀመጥ” በማለት ይመክረናል። (ምሳሌ 23:20) በተመሳሳይም የመዝናኛ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የሚከተለውን ጥበብ ያለበት ምክር ይሰጠናል:- “ለአምላከ ያደሩ መሆንን ዓላማህ በማድረግ ራስህን አሠልጥን። የሰውነት ማሠልጠኛ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ ለአም ላክ ያደሩ መሆን ግን ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁሉ ነገር ይጠቅማል።” — 1 ጢሞቴዎስ 4:7, 8 አዓት
4 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰውነት ማሠልጠኛ” ይኸውም ከስፖርት የምናገኘው ዓይነት ልምምድ የራሱ ቦታ እንዳለው ይገልጻል። ስፖርት ጥሩ ነው። የአካል ቅልጥፍና እንዲኖረን፣ ሰውነታችን እንደልብ እንዲታዘዝልን ለማድረግ፣ የጡንቻን ብርታትና ጥንካሬ እንድናዳብር ሊረዳን ይችላል። በተለይ በጥናት ብዙ ጊዜ የምናሳልፍ ከሆነ አእምሮአችንንም ሊያድስልን ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰውነት ማሠልጠኛ ለጥቂት ይጠቅማል” በማለት ማስጠንቀቁንም ልብ በል። እንደዚህ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችላ ብለህ ሙሉ በሙሉ በስፖርት ብትዋጥ ምን ሊደርስብህ ይችላል?
5 መጀመሪያ ነገር ስፖርቱን አስደሳች መዝናኛ በማድረግ ፋንታ ‘የገንዘብ ማግኛ ሥራ’ ስለሚያደርገው ደስታውን ያጠፋዋል። የስፖርት ሳይኮሎጂስት የሆኑት ብሩስ ኦግልቢ ለውድድር ጨዋታዎች ከልክ ያለፈ ቦታ መስጠት የሚያስከትለውን ውጤት ሲያመለክቱ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ጊዜ በ10 ከፍተኛ የቤዝ ቦል ክበቦች ውስጥ ጀማሪ ለሆኑ ቅጥረኛ ተጫዋቾች ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። ከእነርሱም ውስጥ 87 በመቶ የሚሆኑት ድሮ ከአዝናኙ ጨዋታ ያገኙት የነበረውን ደስታ ስላጡ በትንንሽ የቤዝ ቦል ክበቦች ገብተው ባይጫወቱ ይሻላቸው እንደነበር በጸጸት ገልጸውልኛል።”
6 በተጨማሪም እንደ አሜሪካ ፉት ቦል ያሉ አንዳንድ ስፖርቶች በተለይ ሰውነትህ በእድገት ለውጥ ላይ ከሆነ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። 12, 000, 000 የሚያህሉ አሜሪካውያን ልጆች በአንዳንድ ስፖርቶች በመሳተፋቸው ምክንያት አሥራ ስምንት ዓመት ዕድሜ ከመሙላታቸው በፊት አንድ ዓይነት የማይጠገን የአካል ጕዳት እንደሚደርስባቸው ሳይንስ ዳይጀስት ዘግቧል። ስመ ጥር ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሆኑት አንዱ ሁለት ወንዶች ልጆቹ በሕፃናት የእግር ኳስ ክበብ ውስጥ ገብተው እንዳይጫወቱ ከልክሏል። “ወላጆች ወጣቱ ልጅ ሊደርስበት የሚችለውን አደጋ ቆም ብለው አያስቡትም። ጥርሶቹ ረግፈው ወደ ቤቱ ሊመ
ለስ ይችላል” ብሏል። አንዳንዶቹን የስፖርት ዓይነቶች በጣም አደገኛ የሚያደርጋቸው ከመጠን ያለፈ የውድድር መንፈስ ይኸውም ብዙውን ጊዜ የሚበረታታው የተከፈለው ተከፍሎ ማሸነፍ አለብህ የሚለው አስተሳሰብ ነው።7 ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ነገር በተደራጁ ስፖርቶች ውስጥ ገብቶ መጫወት ለመጥፎ ጓደኝነት ሊያጋልጥ መቻሉ ነው። ባጠቃላይ ሲታይ በልብስ መለወጫ ክፍል ውስጥ የሚደረጉ ጭውውቶች በፆታ ብልግና የተሞሉ መሆናቸው የታወቀ ነው። ከዚህም በላይ አንድ ቡድን ከሌላ ትምህርት ቤት ጋር ለመጋጠም በሚሄድበት ጊዜ አንድ ወጣት ረዘም ላለ ጊዜ ለአምላክ ታማኝ ስለመሆን ደንታ ከሌላቸው ሰዎች ጋር አብሮ ሊሆን ይችላል። ይህ ሊታሰብበት የሚገባው ነገር ነው ምክንያቱም የአምላክ ቃል “ለአምላክ ያደሩ መሆንን ዓላማህ በማድረግ ራስህን አሠልጥን” በማለት አጥብቆ ስለሚናገር ነው። ታዲያ የምትከተላቸውን የስነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓችና ከፈጣሪህ ጋር ያለህን ዝምድና በቀላሉ ሊያበላሽ በሚችል ነገር መጠላለፉ እንዴት ተገቢ ሊሆን ይችላል?
8 ስለዚህ ስፖርቶች ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እስኪጋርዱብህ ድረስ ሕይወትህን ካልተቆጣጠሩት ወይም ለጐጂ ሁኔታዎች ካላጋለጡህ በሚዛናዊነት ሲያዙ ምንም ጉዳት እንደሌላቸው እንደ ሌሎቹ ነገሮች ናቸው። ቅልጥፍና የሚጠይቅ ስፖርታዊ ጨዋታ መጫወትና ሰውነት እንደልብ ሲታዘዝና ጥሩ ችሎታ ሲያሳይ እንዴት ደስ ያሰኛል! ለረጅም ጊዜ የሚታወስ ደስታና እርካታ ሊሰጥ ይችላል። እንደዚህ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ከሚያበቁ ችሎታዎች ጋር የፈጠረንን ፈጣሪ እንድታደንቀው ሊረዳህ ይችላል።
ሲኒማና ቴሌቪዥን
9–14. (ሀ) አንድ ሰው ሲኒማ ወይም ቴሌቪዥን ለማየት በሚመርጥበት ጊዜ ከምን ዓይነት ነገሮች መጠንቀቅ ያስፈልገዋል? (ለ) አንድ ሰው በስነ ምግባር ብልሹ የሆኑ ነገሮችን እንደ መደሰቻ አድርጐ ቢመለከታቸው ይህ እንዴት ሊነካው ይችላል? ለምንስ? እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ስሕተት መሆናቸውን ብናውቅም እንኳ እነርሱን መመልከቱ ሊያስከትልብን የሚችለውን ውጤት አቅልለን መመልከት የማይገባን ለምንድን ነው?
9 የምንመርጠው በሲኒማና በቴሌቪዥን የሚቀርብ መዝናኛ
ዓይነትም ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊነካብን ይችላል። አንዳንድ የሲኒማና የቴሌቪዥን ትርዒቶች አስደሳች መዝናኛዎች ናቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለፈጣሪ የእጅ ሥራ ያለንን አድናቆት ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙ ትርዒቶች ምንዝርን፣ ዝሙትን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ዓመፅንና የሕዝብን መጨፍጨፍ የሚያሳዩ ታሪኮችን የሚያጎሉ መሆናቸውን እንዳስተዋልህ አያጠራጥርም። እነዚህ ትርዒቶች እንደ መዝናኛ ተደርገው ይታዩ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድን ሰው እንዴት ሊነኩት ይችላሉ?10 እስቲ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ:- ‘ዛሬ ያለሁት ዓይነት ሰው ለመሆን የቻልኩት እንዴት ነው? በአካባቢዬና በቀሰምኩት ትምህርት አማካኝነት ይኸውም በተለይም በዓይኖቼና በጆሮዎቼ አማካኝነት ወደ አእምሮዬ በገቡት ነገሮች አማካኝነት አይደለምን?’ አዎን፤ በአብዛኛው አንተነትህን ያስገኘው አእምሮህን የመገብከው ነገር ነው። ለአንድ ነገር ይበልጥ በተጋለጥክ መጠን የዚያኑ ያህል ያ ነገር በግለሰባዊ ባሕርይህ ውስጥ ተቀርጾ የአንተው ክፍል መሆኑ የማይቀር ነው።
11 ከቆሻሻ ጋር የተቀላቀለ ምግብ ለመብላት እንደማትመርጥና እንደማታስበው የተረጋገጠ ነው። አይደለም እንዴ? ታዲያ አእምሮን የሚያቆሽሽ ነገር ሁልጊዜ ብትሰማና ብታይ ምን ይሆናል? ያየኸው ነገር የአስተሳሰብህ ክፍል መሆኑ አይቀርም። ተንቀሳቃሽ ፊልም በምትመለከትበት ጊዜ በፊልሙ ላይ ከሚታዩት ዓይነት ሰዎች ጋር እንደዋልህ ያህል የሚቆጠር ነው። ፊልሞች ደግሞ አንተም ከገጸ ባሕርያቱ ጋር በስሜት ተካፋይ እንድትሆን ለማድረግ ሆነ ተብለው የተዘጋጁና በአብዛኛውም ለአጥፊው ወገን ማለትም ለሴሰኛው፣ ለግብረ ሰዶም ፈጻሚው፣ ለነፍሰ ገዳዩም ሳይቀር የኀዘኔታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ናቸው። ታዲያ አንተ በዚህ ዓይነት መንገድ ከሴትና ከወንድ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች፣ ከሴሰኞች፣ ከአመንዝሮችና ከወንጀለኞች ጋር በጥልቅ ለመተሳሰር ትፈልጋለህን?
12 ይህም ሆኖ በፊልሙ ላይ አንድ ዓይነት የጾታ ብልግና ወይም የዓመፅ ድርጊት ስትመለከት “እኔስ እንደዚህ ያለውን ድርጊት አልፈጽመውም!” ብለህ ታስብ ይሆናል። እውነት ነው፤
አሁን ከጎረቤትህ እንድትሰርቅ፣ ለጓደኞችህ ውሸት እንድትናገር ወይም ዝሙት እንድትፈጽም አንድ ሰው ሐሳብ ቢያቀርብልህ ይቀፍህ ይሆናል። ነገር ግን ጠማማ አስተሳሰባቸውን እያዳመጥህ ከሌቦች፣ ከሴሰኞችና ከግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ጋር ጓደኛ ሆነህ ረዘም ላለ ጊዜ ብትቆይስ? ከጊዜ በኋላ የእነርሱ ደጋፊ ልትሆን ትችላለህ። ለመጀመሪያ ጊዜ ቀፋፊ ይመስል የነበረው ነገር ከጊዜ በኋላ ግን እንደዚያ ሆኖ ላይታይህ ይችላል። እስቲ የሚከተለውን ነገር አስብበት:- አብዛኞቹ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች እንደዚህ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ስለ ግብረሰዶም በማሰብና እንደዚህ ካሉት ሰዎች ጋር አብረው ብዙ ጊዜ ስላሳለፉ ነው።13 በፆታ ብልግና እንደማትካፈል ይሰማህ ይሆናል። ነገር ግን ከተቃራኒ ጾታ ጋር ሲኒማ ቤት ብትገባና በተደጋጋሚ የመተቃቀፍ የመተሻሸትና የብልግና ድርጊት ብትመለከት ምን ይሆናል? እንዲህ ዓይነቱን ፊልም ካየህ በኋላ በተለይም አቋምን የሚያዳክሙ የአልኮል መጠጦች ከተጨመሩበት ምን የምታደርግ ይመስልሃል? መልሱን ታውቀዋለህ። በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ፊልሞች “መጥፎ ነገር ልንሠራ ነው፤ ሕግን ሁሉ፣ የአምላክ
ንም ሕግ እንኳ ሳይቀር እናፈርሳለን!” እያሉ እንደሚጮኹ ያህል ነው። በአንተ ላይ እንዲሠራ የምትፈልገው ግፊት ይህን የመሰለ ነውን?14 በመጥፎ ተጽዕኖዎች ልበላሽ አልችልም ብለህ በሐቀኝነት ልታስብ ትችላለህን? በአንድ ወቅት ጨዋና ጠንካራ ሠራተኞች የነበሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ አውሮፓውያን በናዚ ፕሮፓጋንዳ “አእምሮአቸው ታጥቦ” በሰው ዘር ላይ አሠቃቂ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ወይም ወንጀሎቹ እንዲፈጸሙ መደገፋቸውን አስታውስ። ስለዚህ በተንቀሳቃሽ ፊልሞች አማካኝነት ስለ ጾታና ስለ ወንጀል የሚነዛው ምግባረ ብልሹ ፕሮፓጋንዳ በአንተ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ውጤት አቅልለህ አትመልከት።
የመዝናኛ ፍላጐታችንን ማሟላት
15–19. የመዝናኛ ፍላጐታችንን ልናረካባቸው የምንችል አንዳንድ ጤናማ እንቅስቃሴዎች ምንድን ናቸው?
15 ፈጣሪያችን መዝናኛ እንደሚያስፈልገን አድርጎ ሠርቶናል። ይሁን እንጂ መዝናኛው በቆሻሻ ምግባር ወይም በዓመፅ ወይም የእርሱን ሕጎች በመጣስ ላይ እንዲያተኩር ፈጽሞ ዓላማው አልነበረም። እውነት ነው፣ እነዚህን ነገሮች የሚያሳዩ የሲኒማና የቴሌቪዥን ትርዒቶችን መተው ካለብህ ብዙ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ማስቀረት እንደሚኖርብህ ትገነዘብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ልትደሰትባቸው የምትችል ብዙ ጤናማ የመዝናኛ ዓይነቶች አሉ።
16 ያም ሆነ ይህ መዝናኛው ወይም መደሰቻው ካለቀ በኋላ መንፈስህ ካልታደሰ ወይም ከረበሸህና ካበሳጨህ ጥቅሙ እምኑ ላይ ነው? አንድ ሰው አንድ ነገር እንድትበላ ቢያቀርብልህና ስታየውና ስትቀምሰው ጥሩ ሆኖ በኋላ ግን ቢያምህ ድጋሚ ልትበላው ትመለሳለህን? እንግዲያውስ ትርፍ ጊዜህን በመዝናኛና በመደሰቻ እንዴት እንደምታሳልፈው ስታስብ መራጭ ሁን። በተገኘው መዝናኛ ሁሉ በመርካት ‘ጊዜህን አትግደል።’ ከዚህ ይልቅ በትርፍ ጊዜህ እውነተኛ ደስታንና እርካታን የሚያመጣና መለስ ብለህ ስታስበው በደስታ ልታስታውሰው የምትችለው ነገር በመሥራት በመጠቀም ተደሰትበት።
17 ከቤት ወጣ ብለህ ልትጫወታቸው የምትችል የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች አሉ። ብዙ ሰዎች በጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ ማድረግን፣ የእጅ ኳስ በመጫወት ወይም በመሳሰሉት መዝናኛዎች የብዙ ሰዓት ደስታ ያገኛሉ። አንዳንድ ወጣቶች የጠረጴዛ ቴኒስ መጫወቻ ወይም የመሳሰሉትን መጫወቻዎች በቤታቸው በማዘጋጀት ጓደኞቻቸው መጥተው እንዲጫወቱ ይጋብዛሉ። ወላጆችህን ከጠየቅሃቸው ይህን እንድታደርግ ይፈቅዱልህ ይሆናል።
18 ሊያዝናኑና ወዲያውም እውቀት ሊሰጡ የሚችሉ ሙዚየሞችን ወይም ሌሎች ተደናቂ ቦታዎችን ለመጐብኘትም ትችላለህ። የዶሮ እርባታ ጣቢያ፣ የከብት ርቢ ጣቢያ፣ የሐራጅ ሽያጭ የሚካሄድበትን ቦታ ወይም ማተሚያ ቤት ጐብኝተህ ታውቃለህን? የምትኖረው በከተማ ከሆነ በከተማ ውስጥ ስላሉ ታሪካዊ ቦታዎች መረጃ የሚሰጡህ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይኖሩ ይሆናል። በአቅራቢያህ ያሉ ጐብኚዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኞች የሆኑ የኢንዱስትሪ ተቋሞችን ይነግሩህ ይሆናል። በተጨማሪም በተለይ ቤተሰቦች አንድ ላይ ከሄዱ እንደ ሐይቆች፣ ተራሮችና የባሕር ዳርቻዎች ያሉ ውብ ቦታዎችም አስደሳች መዝናኛዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
19 እርግጥ ደስታ ለማግኘት እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች ማሳደድ በሕይወታችን ውስጥ ዋናው ግብ እንዳይሆንና በዚህ ምክንያት መዝናኛዎቹ ሊሰጡን የሚችሉትን ጥቅሞች ሳናገኝ እንዳንቀር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሁንና ፈጣሪያችን እንደነዚህ ባሉት የተለያዩ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች ለመካፈልና በእነርሱ ለመደሰት ከሚያስችል ችሎታ ጋር ስለ ፈጠረን እንዴት ልናመሰግነው ይገባናል! እነዚህ ነገሮች ሕይወትን በእርግጥም የበለጠ ትርጉም ያለው ያደርጉታል።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትመለከተው ነገር አንተን ይነካልን?