በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኝነት ዋጋ አለውን?

እውነተኝነት ዋጋ አለውን?

ምዕራፍ 22

እውነተኝነት ዋጋ አለውን?

1–4. በወጣቶች ዘንድ ምን የውሸተኝነት ጠባይ ታዝበሃል? ብዙ ወጣቶች እነዚህን ነገሮች ማድረጋቸው የማያስደንቀው ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 9:16)

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ሁልጊዜ እውነቱን መናገር የሚቻል አይመስላቸውም። ይህን አስተውለሃልን? ብዙ ነጋዴዎች ካላጭበረበሩ ፉክክሩን እንደማይችሉት ይናገራሉ። ከመጠን በላይ የሚያጋንኑ ወይም ያልሆነውን ሆነ የሚሉ ማስታወቂያዎች በየቀኑ ያጋጥሙናል። የፖለቲካ መሪዎች የሕዝቡን ደህንነት እንደሚጠብቁ ቢታሰብም ብዙ ሰዎች ግን እምነት እንደማይጣልባቸው አድርገው ይመለከቱአቸዋል።

2 ወጣቶችም በአዋቂዎች መካከል ብዙ ማጭበርበር ስለሚመለከቱ ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ ጠባይ ይይዛሉ። ብዙዎቹ በትምህርት ቤት ፈተና ጊዜ ይሰርቃሉ ወይም የውሸት ሰበብ በማቅረብ ከክፍል ይቀራሉ። ለጓደኞቻቸው ስለ ራሳቸው ወይም ስለ ሠሩት ሥራ ሐሰተኛ መግለጫ በመስጠት ጉራቸውን ይነዛሉ። እቤታቸውም ቢሆን ወላጆቻቸውን ያታልሉ ይሆናል። ስለሚያደርጓቸው ነገሮች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ከፊል እውነት ይናገራሉ፣ ስለ ራሳቸው ፈጽሞ ውሸት የሆነ አስተሳሰብ ለማሳደር በዘዴኛ አነጋገር ሐቁን ይሸፋፍናሉ። ወላጆቻቸው ወይም ሌሎች ሰዎች ስለ ፆታ ብልግና፣ ስለ አደንዛዥ መድኃኒቶች ወይም ስለ ተመሳሳይ ነገሮች ያላቸውን ስሜት ለማወቅ ፈልገው ሲጠይቋቸው የራሳቸውን አስተያየት ሳይሆን ጠያቂዎቹ ለመስማት ይፈልጋሉ ብለው ያሰቡትን ብቻ በመናገር እውነቱን በለሰለሰ አነጋገር ይሰውሩት ይሆናል። ገንዘብ ለማግኘት ወይም አንድ ነገር ለመሥራት እንዲፈቀድላቸው ሲሉ በወላጃቸው ላይ እውነተኛ ያልሆነ ፍቅር ወይም ቁልምጫ ያዥጎደጉዳሉ።

3 ነገር ግን ይህ በእርግጥ አዲስ ነገር ነውን? ሐቁ ግን ብዙ ወጣቶች ይህን ማድረግ የማያስወቅሳቸው እንደሆነ የሚሰማቸው መሆኑ ነው። ለምን? እውነት ነው፣ ወላጆቻቸው መዋሸት ስሕተት መሆኑን ያስተምሩአቸው ይሆናል። ሆኖም ወላጆቻቸው ከመጥፎ ሁኔታ ለመውጣት ብለው ወይም አንድ ዓይነት የሚከፈል ሒሳብ ሲመጣ ዕዳ ወይም ቀረጥ ላለመክፈል ሲሉ ያልሆነውን ሆነ ብለው ሲዋሹ ይመለከታሉ። እንዲያውም አንዳንድ ወላጆች የውሸት ሰበብ ለመስጠት በልጆቻቸው እንደሚጠቀሙ አስተውለሃልን?

4 እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በሞሉበት ሁኔታ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎቻችን በሁሉ ነገር እውነተኞች ለመሆን እንድንጥር ምን የሚያበረታታ ነገር አለ? መዋሸት፣ ማታለልና ስርቆት በጣም የተለመዱ በሆነበት ዓለም ውስጥ እውነት ለሆነው ነገር መጽናት ምን ያህል ተግባራዊና ጠቃሚ ሊሆንልህ ይችላል? እውነተኝነት በእርግጥ ማጭበርበር ከሚያስገኘው የበለጠ ጥቅም ሊያመጣልህ ይችላልን? ከሆነስ ምን ዓይነት ጥቅም?

ያጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ጥቅሞችን ማወዳደር

5–7. በማጭበርበር የሚገኝ ማናቸውም ጥቅም ጊዜያዊ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- የምፈልገው ምንድን ነው? ቅጽበታዊ ትርፍ፣ ላይ ላዩን ጠቃሚ የሚመስል ነገር? ወይስ ዘላቂ ጥቅም የሚሰጠውን? ነገሩን ካሰብክበት በውሸትና በማታለል የሚገኝ ማንኛውም የይምሰል ጥቅም ግፋ ቢል ላጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ አይደለምን? አዎን፤ ያምላክ ቃል “የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው። — ምሳሌ 12:19

6 አንድን ዓይነት ምርት ያልሆነውን አስመስሎ የሚያቀርብን ነጋዴ እንደ ምሳሌ አድርገህ ውሰድ። ሽያጭ ያገኝ ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግን አንዱ ሰው መታለሉን ሲደርስበት ነጋዴው አንድ ደንበኛ አጣ ማለት ነው። ወይም በትምህርት ቤት ፈተና ሰርቀሃል እንበል። ስትኮርጅ ካልተያዝህ ከፍተኛ ማርክ ታገኝ ይሆናል። ይሁን እንጂ ትምህርትህን ስትጨርስ የረባ እውቀት ከሌለህ ምናልባትም በደንብ ማንበብና ማስላት የማትችል ከሆንክ ዳር እስከ ዳር “A” ቢደረደርልህ ምን ይጠቅምሃል?

7 እንግዲያስ የሚያታልል ሰው ከሁሉ በላይ ያታለለው ራሱን መሆኑን በመጨረሻው ያገኘዋል። ሐቀኛንና አጭበርባሪን ሰው እስቲ አወዳድራቸው። አጭበርባሪው ግለሰብ የሚያጣቸውን አንዳንድ ነገሮች መርምርና አጭበርባሪነት ወደተሻለ ወይም ወደ ደስተኛ ሕይወት ለመድረስ ይረዳል ብሎ የሚያስብ ሰው በእርግጥ አርቆ የማያስብ ሰው ስለመሆኑ ሳትስማማ አትቀርም።

8–10. እውነተኝነት (ሀ) በሥራ ቦታ (ለ) በቤተሰብ ግንኙነት (ሐ) ከጓደኞች ጋር በተያያዘ መንገድ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

8 ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት እውነቱን የምትናገርና የማትዋሽ በመሆን የምትታወቅ ከሆነ የሌሎችን አክብሮትና እምነት ታተርፋለህ። የምታተርፋቸው ወዳጆች እውነተኞች መሆናቸው የማይቀር ነው ምክንያቱም አንተ እውነተኛ መሆንህን የተረዱና ይህንንም ጠባይ አድንቀው የመጡ ስለሆኑ ነው። ዘመናዊው የንግድ ዓለም ብዙውን ጊዜ አጭበርባሪ መሆኑ ቢታወቅም አሠሪዎች ወይም ሠራተኛ የሚቀጥሩ ሰዎች ባጠቃላይ ሲታይ ለታማኝ ሠራተኞች ከፍ ያለ ግምት ለመስጠት የሚያስችል በቂ የማመዛዘን ችሎታ እንዳላቸው እሙን ነው። እንግዲያስ በእውነተኝነት መታወቅ ሥራ በሚታጣበት ጊዜ ሥራ ሊያስገኝ ወይም ሌሎች ከሥራቸው ሲባረሩ በሥራው ላይ ለመቆየት ሊረዳ ይችላል።

9 በቤት ውስጥም እውነተኝነት በባልና በሚስት እንዲሁም በወላጆችና በልጆች መካከል ጥርጣሬን ወይም አለመተማመንን አጥፍቶ አስደሳች የሆነ የመዝናናት መንፈስ እንዲሠፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ልጆች በእውነተኝነታቸው የወላጆቻቸውን ሙሉ አመኔታ ሲያተርፉ አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ቀስ በቀስ የበለጠ ነፃነት ሊሰጧቸው ፈቃደኞች ይሆናሉ። እርግጥ ነው ስለ አንድ ስሕተት ወይም ጥፋት እውነቱን መናገር ተግሳጽን ሊያመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ እውነቱን በመናገርህ ተግሳጹ ቀላል ሊሆንልህ ይችላል። ከዚያ በኋላ ጥፋት እንዳልሠራህ ከልብ ስትናገር ቃልህ የበለጠ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል።

10 ይህንንም “ከቁንጥጫ ለማምለጥ” ወይም አንድ ጥቅም ለማግኘት ብሎ ውሸት ከሚቀናው ሰው ጋር እስቲ አነጻጽረው። እነዚህን መልካም ጥቅሞች ሁሉ የማጣት አደጋ ያጋጥመዋል። ምክንያቱም ውሸታም የሆነ ሰው ምኑን ከምን ጋር አምታቶ እንደሚያታልልህ ፈጽሞ ልታውቀው ስለማትችል ከእርሱ ጋር የሚደረግ ግንኙነት የመሪ ብልሽት ያለውን መኪና ከመንዳት ጋር ይመሳሰላል። ስለዚህ አንድን ሰው በመዋሸት ወይም በማታለል የምትፈጥረውን ጥርጣሬ ለመፋቅ ብዙ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ተገንዘበው። ያታለልከው ወላጅህን ወይም ጓደኛህን ከሆነ ቁስሉ ይድን ይሆናል፤ ነገር ግን መጥፎ ትዝታው እንደማይጠፋ ጠባሳ ሆኖ ሊቀር ይችላል። መዋሸትን ልማድ ካደረግኸው ሌሎች እንዲያምኑህና ቃልህን እንዲቀበሉ አጥብቀህ የምትፈልግበት ጊዜ ይመጣና እነርሱ ግን ፈጽሞ ሊያምኑህ ወይም እምነት ሊጥሉብህ አይችሉም። ታዲያ መዋሸት የሚያስገኘው ጊዜያዊ ጥቅም ይህ ሁሉ ዋጋ ሊከፈልለት ይገባልን?

11–13. (ሀ) የመዋሸት ልማድ ብዙውን ጊዜ የሚጀመረው እንዴት ነው? (ለ) መዋሸት ከጉብዝና ይልቅ ፈሪነት የሆነው ለምንድን ነው?

11 እንደ እውነቱ ከሆነ መዋሸት በምድረ በዳ በሚገኝ ሲረግጡት በሚከዳ አሸዋ ውስጥ ተይዞ ከዚያ ለመውጣት እንደ መንፈራገጥ የሚቆጠር ነው። ብዙውን ጊዜ እያንዳንዱ ውሸት እርሱን የሚደግፈው ሌላ ውሸት ይፈልጋል። ውሸታሙ ሰው ብዙም ሳይቆይ ራሱን በውሸት ዑደት ተተብትቦ ያገኘዋል። “እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ” የሚለውን ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥበባዊነት ለመመልከት አንችልምን? — ቆላስይስ 3:9

12 የሚዋሹ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚጀምሩት ከፊል እውነትና “ጥቂት ውሸት” ያለበትን ነገር በመናገር ሲሆን ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ወደባሰ ውሸት ይሻገራሉ። ስለዚህ ውሸት የሚጀመረው ልክ እንደ ቁማር ጨዋታ ነው። ቁማርተኛው በትንሽ ገንዘብ በመወራረድ ይጀምራል። አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርገው የተበላውን ገንዘብ ለማስመለስ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን ከፍ ወዳለ የገንዘብ ውርርድ ይገባል።

13 ለመጀመሪያ ጊዜ ፊትን ሳያጥፉ መዋሸት ጉብዝና መስሎ ሊታይ ይችላል። ሲዋሹ የሌላውን ዓይን ትኩር ብሎ ለማየት ራሳቸውን የሚያለማምዱ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። ታዲያ ይህ ጉብዝና አይደለምን? አይደለም፤ መዋሸት ጉብዝና ሳይሆን ፈሪነት ነው። እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር እንደሚባለው ጉብዝና የሚጠይቀው እውነቱን ተናግሮ የመጣውን ነገር መጋፈጥ ነው። ውሸት ጥንካሬን ማመልከቱ ቀርቶ ደካማ፣ በራሱ ሊቆም የማይችል፣ ሌሎች ውሸቶች ደግፈው እንዲያቆሙት የሚፈልግና ከእውነት ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት ፈጽሞ ፈቃደኛ ያልሆነ ነው። ታዲያ ዕድሜውን ሙሉ ያልሆነውን ሆኖ በመቅረብ ራሱን ሲደባብቅ፣ ሲሽሎከሎክና ሰበብ ሲፈጥር እንደሚኖር ሰው ለመሆን ለምን ትፈልጋለህ? አታላይ እንደሆነው፣ በግብዝነት ሁለት ዓይነት አኗኗር ለመኖር እንደሞከረውና በመጨረሻም ሳይሳካለት ቀርቶ ራሱን እንደገደለው እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ለመሆን ለምን ትፈልጋለህ? ሐቀኛ ለመሆን የምትበቃ ሰው ለምን አትሆንም? ራስህ ለራስህ አክብሮት ሊኖርህ የሚችለውና ጥሩ ሕሊና ይዘህ ለመኖር የሚያስችልህ ብቸኛው መንገድ ይኸው ነው።

ቃልህን መጠበቅ

14–16. ቃልህን መጠበቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ይህ የእውነተኝነት ጉዳይ ቃልህን መጠበቅህንም ይመለከታል። ወላጆችህ አንድ ነገር ሊያደርጉልህ ቃል ከገቡልህ በኋላ ሳይፈጽሙት ቢቀሩ በጣም ሳታዝን አትቀርም። አንተስ ለወላጆችህ የገባኸውን ቃል ባትጠብቅ የሚሰማህ የዚህኑ ያህል ነውን? በዚህ ረገድ እንዴት ነህ? አንድን ሰው በሥራ እንደምትረዳው ወይም አንድ ዓይነት አገልግሎት እንደምታቀርብለት ስትናገር ሁልጊዜ ቃልህን ለመጠበቅ ትጥራለህን? ከአንድ ሰው ጋር በተወሰነ ጊዜ ለመገናኘት ቀጠሮ ብታደርግ በዚያው ሰዓት በቦታው ትገኛለህን? ቃልህ ምን ያህል ክብደት አለው?

15 ቃልህን የመጠበቅ ልማድ ማሳደግ የምትጀምርበት ጥሩው ጊዜ ወጣትነት ነው። ቃልህን መጠበቅ ወይም አለመጠበቅ አሁን በውስጥህ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ። አእምሮህንና ልብህን የመቅረጽ ውጤትም አለው። ለረጅም ጊዜ አብሮ የሚኖሩ የግል ባሕርያትን የሚቀርጽ ስለ ነገሮች አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም አዝማሚያ ይገነባል።

16 አሁን እምነት የሚጣልብህ ከሆንክ የኋላ ኋላም እንዲሁ ልትሆን ትችላለህ። በግልባጩም እንዲሁ ነው። ለምሳሌ ዛሬ ቃልህን የማታከብር ከሆንክ የኋላ ኋላም አንድ ዓይነት ሥራ ወይም ምድብ ለመጀመር ትዋዋልና ወዲያው ለማፈግፈግ ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ሆኖም በሌሎች ሰዎች ዘንድ በአክብሮት አይታዩም።

17–19. (ሀ) ሰዎች ቃላቸውን የሚያፈርሱት ለምንድን ነው? (ለ) ቃልህን ለማፍረስ ከሚጋብዙ ሁኔታዎች ለመራቅ ምን ሊረዳህ ይችላል?

17 ሰዎች ቃላቸውን የሚያፈርሱት ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር ቃልን መጠበቅ በአንድ ሰው ላይ ገደብ ያደርግበታል፤ ግዴታ ውስጥ ያስገባዋል። ቀጠሮውን ወይም ቃል የገባውን ነገር የሚፈጽምበት ሰዓት ሲደርስ ማራኪ መስሎ የሚታይ ሌላ ነገር ሊቀርብለት ይችላል። በዚህን ጊዜ ሰውየው ቃሉን ማክበር እርሱ ካሰበው በላይ ከባድ ሥራ ሆኖ ያገኘው ይሆናል።

18 እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? ችግር የሚፈጥርብህ ወይም ኪሳራ የሚያስከትልብህ ቢሆንም በቃልህ ትጸናለህን? አንድ ሰው “ቃል ስገባ ምን ውስጥ እየገባሁ እንዳለሁ አላወቅኩም ነበር!” ይል ይሆናል። እዚህ ላይ የሚነሳው ዋና ጥያቄ:- ስሕተቱ የማን ነው? የሚል ነው። ሌላው ሰው ዋሽቶሃል ወይም አታሎሃልን? ካልሆነ ቃልህን ለመጠበቅ የሚጠይቅብህን ማንኛውንም ዓይነት ችግር ለመቻል በመምረጥህ ጠቃሚ ትምህርት ታገኛለህ። ይኸውም:- ከመናገርህና ቃል ከመግባትህ በፊት አስብ ። ከዚያ በኋላ ከተናገርክ ግን ቃልህን አክብር የሚለው ነው።

19 አንድን ሰው ለማስደሰት ብለህ የሚያስከትለውን ነገር አስቀድመህ ሳታስብ “እሺ” ብትል ችግር ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። ባንፃሩ ግን ቃል ስለ መግባት ጠንቃቃ ከሆንክ፣ የገባኸውን ቃል መጪ ሕይወትህን እንዴት እንደሚነካው ጉዳዩን በደንብ ከመረመርከውና ካሰብክበት ከዚያ በኋላ ቃል የገባህበትን ነገር መጠበቅ በጣም ቀላል ይሆንልሃል። ቃልህን ለማክበር ልብህንና አእምሮህን አዘጋጅተሃል ማለት ነው። ኢየሱስ “አዎን ያላችሁት ቃላችሁ አዎን ማለት ይሁን” ሲል ተናግሯል። — ማቴዎስ 5:37

እውነተኝነት ዋጋ አለው የምንልበት ዋነኛው ምክንያት

20–22. (ሀ) በማንኛውም ጊዜ እውነተኛ መሆን አስፈላጊ የሆነበት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? (መዝሙር 15:1–4) (ለ) ቃሉን በመጠበቅ ረገድ አምላክ ምን ጥሩ አርዓያ ትቶልናል? የእርሱን አርዓያ እንድንከተል ምን ሊረዳን ይችላል?

20 እውነተኛ መሆን ዋጋ ሊኖረው የቻለበት ዋናው ምክንያት ይሖዋ አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጐ የሚቆጥራቸው እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ብቻ ስለሆነ ነው። ለምን? ምክንያቱም እርሱ ራሱ በምንም ዓይነት መንገድ ቃሉን ከመጠበቅ ወደኋላ የማይል አምላክ ነው። ኢያሱ ለእስራኤል ሕዝብ የሚከተለውን ለመናገር የቻለውም ለዚህ ነው:- “እናንተም እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላካችሁ ሰለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ ሁሉም ደርሶላችኋል ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።” (ኢያሱ 23:14) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ቃሉን በመጠበቅ የፈጸማቸውን ተስፋዎች በብዛት የተመዘገቡበት መጽሐፍ ነው። ባለፉት ጊዜያት እውነተኛ ሆኖ መገኘቱ ወደፊት ይመጣሉ ሲል ቃል የገባልን በረከቶችም እንደሚመጡ በሙሉ ልባችን እንድናምን ያደርገናል።

21 የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ እርሱ ሞገሱን የሚሰጠው “በመንፈስና በእውነት” ለሚያመልኩት ብቻ መሆኑን አስታውስ። (ዮሐንስ 4:23) ውሸትን በማንኛውም ዓይነት መልኩ ማለትም ማታለልን፣ ጉረኛነትን፣ ስም አጥፊነትን፣ ማጭበርበርን እንደሚጸየፍ አስታውስ። ምክንያቱም መዋሸት የሚመነጨው ከራስ ወዳድነት፣ ከስስትና ለሌሎች ጥቅም ደንታቢስ ከመሆን ስለሆነ ነው። የሰው ልጅ መከራና ሥቃይ በሙሉ የመጣው የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነው “የሐሰት አባት” እርሱም ሰይጣን በመዋሸቱ ምክንያት መሆኑን ይሖዋ ያውቃል። — ዮሐንስ 8:44

22 የእውነተኝነትን ጐዳና አጥብቀህ ለመያዝ ከልብህ ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ ለዚህ የሚያስፈልግህን ግፊት ሊሰጥህ የሚችለው ለፈጣሪህና ለጐረቤትህ ያለህ እውነተኛ ፍቅር ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብሃል። ስለሚያመጣው ጥቅም እውነትን ከልብ መውደድና ውሸት ደግሞ ስለሚያስከትለው ጉዳት የዚያኑ ያህል አጥብቀህ ልትጠላው ይገባል። በተጨማሪም የሰውን ሞገስ ከማግኘት የአምላክን ሞገስ ማግኘት ልቆ ሊታይህ ይገባል። አስታውስ፣ በአምላክ እውነተኛ ተስፋና በተረጋገጠው የቃሉ አስተማማኝነት ላይ ተመሥርተን ለወደፊቱ ጽኑ ተስፋ ሊኖረን የቻለው እርሱ ራሱ እውነትን ስለሚያፈቅርና መዋሸትን ስለሚጠላ ብቻ ነው። ስለዚህ እርሱን ለመምሰል ተጣጣር። ‘የእውነት ከንፈር ለዘላለም እንደምትቆም፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት’ መሆኑን አስታውስ። — ምሳሌ 12:19

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 174 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብትሰርቂ በእርግጥ ትጠቀሚያለሽን?