በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደፊት የሚጠብቅህ ታላቅ ተስፋ

ወደፊት የሚጠብቅህ ታላቅ ተስፋ

ምዕራፍ 24

ወደፊት የሚጠብቅህ ታላቅ ተስፋ

1–3. (ሀ) የምንኖረው በሰው ታሪክ ውስጥ በጣም በታደለ ዘመን ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ለጥቅማችን ሲል ምን ለውጦች ሊያመጣ ነው?

በብዙ መንገዶች ሲታይ በሰው ታሪክ ውስጥ በጣም በታደለ ዘመን ላይ ትኖራለህ። ይህ ሊባል የሚቻለው ዛሬ የዓለም ሁኔታዎች ጥሩ ስለሆኑ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከፊታችን ያለው ቅርብ ጊዜ ስለሚያመጣው ነገር በሚገልጸው ምክንያት ነው።

2 ይሖዋ አምላክ በዚህች ፕላኔት፣ በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ለውጥ፣ አዎ፣ ትልቅ ለውጥ ማምጣት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃል። ይህንንም ለውጥ ለማምጣት የሚችለው እርሱ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ዓለም በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ የሰውን ዘር ለዘመናት ሲያስቸግሩ የኖሩትን እነዚያኑ የቆዩ ችግሮች ማለትም ጦርነትን፣ ረሀብን፣ የቤት እጦትን፣ የፍትሕ መዛባትንና የምጣኔ ሀብት ችግሮችን አሁንም እየታገለ ነው።

3 በዛሬው የዓለም ሥርዓት ውስጥ ሊስተካከሉ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች በእርግጥም ለቁጥር ያታክታሉ። ከዚህ የተሻለ ነገር ሊኖር ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስም ይሖዋ አምላክ እርሱን ለሚወዱትና ለሚያገለግሉት ሰዎች ከዚህ በጣም የተሻለ ነገር እንዳስቀመጠላቸው ይገልጻል። እንዲያውም ፈጽሞ አዲስ የሆነ ሥርዓት፣ የደስታ ገነት ለማምጣት ያለውን ዓላማ ስድስት ሺህ ዓመታት በፈጀ ጊዜ ውስጥ ደረጃ በደረጃ ሲያስታውቅ ቆይቷል። የሕይወትን ደስታ የሚቀንሱትን ብልሹ የሆኑ እንዲሁም ጭካኔና ስግብግብነት ያለባቸውን ሁኔታዎች በዚያ አዲስና አስደሳች የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ለአንዴና ለሁልጊዜ ለማጥፋት ቃል ገብቷል።

ለውጥ እንዴትና መቼ ይመጣል?

4–8. (ሀ) ይሖዋ ተፈላጊውን ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው? (ለ) ይህ የሚሆንበት ጊዜስ በጣም ቅርብ እንደሆነ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ማቴዎስ 24:7, 8, 32, 33)

4 አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በአሁኑ ጊዜ ባሉት በመቶ በሚቆጠሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ተከፋፍሎ ምድርን እየገዛ ያለውን የተመሰቃቀለና ውጤት አልባ የሆነ አገዛዝ በማስወገድ ነው። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራ ራሱ ባዘጋጀው አንድ ብቸኛ መንግሥት እነርሱን ለመተካት ያለውን ዓላማውን ተናግሯል። አምላክ ነቢዩ ዳንኤልን እንደሚከተለው በማለት ትንቢት እንዲናገር አድርጎታል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፤ ለዘላለምም ትቆማለች።” (ዳንኤል 2:44) ይህ የሚፈጸመው መቼ ነው? የሚፈጸምበት ጊዜ እንደቀረበ የሚታወቅበት መንገድ አለ።

5 በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ የሚኖር ሰው የዛፍ ቅጠሎች ቀለም ወደ ቡና ዓይነት ሲለወጥና ሲረግፉ ቢያይ፣ ሰማዩም ከቀን ወደ ቀን እየከበደና አየሩም ደረቅና ቀዝቃዛ እየሆነ እንደመጣ ቢሰማው፣ የወፎች ጋጋታም ወደ ሞቃቱ የምድር ክፍል ሲበርሩ ቢመለከት የቀን መቁጠሪያ ሳያይ የበረዶው ወራት እየቀረበ መሆኑን ያውቃል፤ አይደለም እንዴ? እንደዚያ ብሎ ለመደምደም የሚያበቃው ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱም በበጋም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ሰማዩ ሊከብድ፤ ዛፎችም አንዳንድ ጊዜ በሽታ ሲያጠቃቸው ቅጠላቸው ሊረግፍ ይችላል። ነገር ግን እነዚያ ሁሉ ነገሮች በአንድነት ተዳምረው ክረምት ለመቅረቡ የማያሳስቱ ምልክቶች ይሆናሉ።

6 በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ብዙ ገጽታዎችን ያካተተ “ምልክት” አለ። ይህም ምልክት በክርስቶስ ኢየሱስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት የምድርን ቁጥጥር የምትረከብበት ጊዜ እንደቀረበ ይነግረናል። ዛሬ ይህን ምልክት ጋዜጣ በማንበብ ወይም የሬድዮና የቴሌቪዥን ዜና ፕሮግራሞችን በማዳመጥና በመመልከት ብቻ ልታየው ትችላለህ። ምልክቱ ምንድን ነው?

7 ኢየሱስ በአንድ የተወሰነ ትውልድ ውስጥ በምድር ላይ የሚመጣውን ነገር ባለማወቅ ከመጨነቅና ግራ ከመጋባት ጋራ አብረው የሚመጡ ጦርነቶች፣ ረሀብ፣ በሽታና የመሬት መናወጥ የሚደራረቡበት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮአል። ባሁኑ ጊዜ በዜና ምንጮች አማካይነት ያለማቋረጥ የምናየውና የምንሰማው እነዚህን ነገሮች አይደለምን? ከ1914 ወዲህ ያለውን ትውልድ ያህል እነዚህ ነገሮች በዚህ መጠን ሲፈጸሙ ያየ ሌላ ትውልድ በሰው ታሪክ ውስጥ አልነበረም። ታሪክ ጸሐፊዎች 1914⁠ን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ “አቅጣጫ ለዋጭ” ብለው የጠሩት ለዚህ ነው።

8 ኢየሱስ ይህን “ምልክት” ስለሚያየው ትውልድ ሲናገር “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ብሏል። (ሉቃስ 21:31, 32) ይህም የአምላክ አዲስ ሥርዓት ቀርቧል ማለት ነው። የአምላክ አዲስ ሥርዓት ምን ለውጦችን ያመጣ ይሆን?

አምላክ ለሰብዓዊው ቤተሰብ እንደሚያመጣላቸው ቃል የገባላቸው ለውጦች

9–13. (ሀ) በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለሰው ልጆች ሁሉ ምን ሁኔታዎች ይፈጠሩላቸዋል? (ለ) እነዚህ ነገሮች በእርግጥ ሊፈጸሙ እንደሚችሉና እንደሚፈጸሙም የሚያሳምንህ ምንድን ነው? (ራእይ 21:5)

9 አምላክ ይህችን ፕላኔትና ነዋሪዎቿን ከሰማይ በሚመራ አንድ ፍጹም መንግሥት አገዛዝ ሥር በማድረግ የዓለምን ሀብት የሚያባክነውን የፖለቲካ ጭቅጭቅና ውጊያ ለሁልጊዜው ለማስቀረት ቃል ገብቷል። ይህም ማለት የየአገሩን ወጣቶች አፍላ ጉልበት ከወሰዱ በኋላ ብዙ ቁጥር ያላቸው አካለ ጐደሎዎች ሆነው፣ እጃቸው፣ ክንዳቸው ወይም እግራቸው ተቆርጦ፣ ምናልባትም ታውረው ወይም ከዚህ የከፋ ሞተው ሬሳቸው ብቻ እንዲቀር የሚያደርጉት ጦርነቶች ፍጻሜ ይሆናል ማለት ነው። በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ወስጥ የሚኖሩ ሁሉ በኢሳይያስ 2:4 ላይ የሚገኘውን “ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፣ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም (ጦርነትም) ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የፈጸሙ ሰላም ወዳድ ሰዎች ይሆናሉ። ሰላም በመላው ምድር ሲሰፍን በሁሉም ሥፍራ ለሚኖሩ ሰዎች የሚጠቅሙ አስደናቂ ነገሮች ሊከናወኑ ይችላሉ።

10 የሚያከትሙት ፖለቲካዊ የሥልጣን ብልግናና አባካኝነት ብቻ አይደሉም። የግዙፎቹ የንግድ ሥርዓቶች ስግብግብነትም እንዲቆም ይደረጋል። ግዙፍ የሆኑት ብዙዎቹ የንግድ ሥርዓቶች አየሩን፣ ውኃውንና አፈሩን በመበከል የዱር አራዊትን ገድለው ከምድር ላይ በመጨረስ ምድሪቱን እያቆሸሹ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በራእይ 11:18 ላይ አምላክ “ምድርን የሚያጠፉትን ሊያጠፋ” እንደሆነ ይነግረናል። ከዚያ በኋላ ምድር የጫካዎቿ ውበት፣ የወንዞቿና የሐይቆቿ አንጸባራቂ ጥራት፣ ከብክለት የፀዳው የአየሯ ንጽሕናና መዓዛ፣ የወፎቿ፣ የዓሦቿና የዱር አራዊቷ ብዛትና ዓይነት እንደገና ይመለስላታል። አንተም አምላክ በቃሉ ላይ እምነት ለሚጥሉ ሰዎች ያዘጋጀላቸውን ታላቅ ተስፋ ወደፊት ከሚያገኙት ሰዎች አንዱ ለመሆን ትችላለህ።

11 ፈጣሪያችን በአዲስ ሥርዓቱ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ባሉበት ሥፍራ የመሬትን የተትረፈረፈ ምርት እንደሚያገኙና እንደሚደሰቱበት ቃል ገብቷል። ከዚያ በኋላ ዛሬ በምድር ላይ በብዙ አገሮች እንደሚታየው ሆዳቸው የተነፋና ክንዳቸው የሰለለ ራብተኛ ልጆች አታይም። አምላክ በኢሳይያስ 25:6, 8 የሚከተለው ትንቢት እንዲጻፍ አድርጓል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ለሕዝብ ሁሉ . . . ታላቅ የሰባ ግብዣ . . . ያደርጋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”

12 አዎ፤ ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለታዛዥ የሰው ልጆች ፍጹም ጤንነት እንደሚመልስ ማመልከቱ ነው። የልጁ መንግሥት የሰው ልጆችን ሕመምና አለፍጽምና በሚፈውስበት ጊዜ በሽታ፣ ሥቃይና ሞት ያመጡት ኃዘንና መከራ በሙሉ ይወገዳል። ራእይ 21:4 “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ” በማለት ይናገራል።

13 ይህም ማለት የሰው አለፍጽምና ያስከተለው እርጅና የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣል ማለት ነው። አምላካችን የፊት መጨማደድ፣ የጠጉር መሸበት ወይም ራሰ በራነት፣ የአጥንት በቀላሉ ተሰባሪ መሆን፣ የጡንቻ መላላት፣ የትንፋሽ ማጠርና ዛሬ በእርጅና ምክንያት የሚመጡ ሌሎች ነገሮችም ሁሉ የሚወገዱበት ጊዜ ማዘጋጀቱ እንዴት አፍቃሪ ቢሆን ነው! አዎ፤ አምላክ ከዚያ በኋላ ኢዮብ 33:25 የሚገልጸውን ላረጁት ሰዎች ሊፈጽምላቸው ይችላል:- “ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል ወደ ጉብዝናውም ዘመን ይመለሳል።” አዎ፤ በአሁኑ ጊዜ ወጣቶችም እንኳን ሳይቀሩ ሊታመሙና አንዳንዶቹም ሳይታሰብ በአፍላ ዕድሜያቸው በሞት ሊቀጩ ስለሚችሉ ይሖዋ አምላክ ዛሬ ወጣትነት ከሚሰጠው የተሻለ ጤናና ብርታት ለማምጣት ይችላል።

በመጪው ጊዜ እንዴት መደሰት እንደምትችል

14–16. ይህን ታላቅ የወደፊት ተስፋ ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልግሃል?

14 መጽሐፍ ቅዱስ “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፣ [በእርጅና የሚሠቃዩ ሰዎች እንደሚሉት] ደስ አያሰኙም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ” የሚለውን የምትፈጽም ከሆነ ያን ታላቅ ተስፋ ልትጨብጥ ትችላለህ። — መክብብ 12:1

15 ይህም ስለ ፈጣሪህ አልፎ አልፎ የማሰብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። እርሱን በሚያስደስተውና በአዲስ ሥርዓቱ ውስጥ ከሚያኖራቸው ሰዎች መካከል እንድትገኝ እንዲፈልግ በሚያደርገው መንገድ ለመኖር በመጣር በየዕለቱና ቀኑን ሙሉ እርሱን የማስታወስ ጉዳይ ነው። ይህን እንድታደርግ አያስገድድህም። በራስህ ምርጫና ፍላጐት ተነሳስተህ ልታደርገው ይገባሃል። ወላጆችህ ስላስገደዱህ ብቻ ያዘዙህን ነገር ስትሠራ ቢያዩህ አድራጎትህ ደስታ እንደማያመጣላቸው ታውቃለህ። እነርሱን ደስ እንደሚያሰኛቸው በማወቅ በፈቃደኝነትና በደስታብታደርገው ግን ብዙ ደስታ ታመጣላቸዋለህ። እንደዚሁም ደግሞ ይሖዋ በቃሉ “ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት ይናገራል። — ምሳሌ 27:11

16 አዎን፣ የሕይወትህ የጸደይ ወራት በሆነው በወጣትነትህ ተደሰት። ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት። አሁንም ሆነ ወደፊት ከሁሉ የበለጠ ደስታ የሚያመጡልህን ባሕርያት ገንባ። ወጣትነትህን በሕይወት ጐዳና ላይ በጥሩ ሁኔታ ለመጀመር ተጠቀምበት። ይህም ሕይወት ሟችና በስባሽ በሆነው በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የሚገኘው አጭር ሕይወት ሳይሆን አምላክ በሚያዘጋጃት ገነት የሆነች ምድር ላይ የወጣትነት ትኩስ ብርታት ይዞ ለዘላለም መኖር ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]