የዛሬውንና የነገውን እያሰቡ መኖር
ምዕራፍ 1
የዛሬውንና የነገውን እያሰቡ መኖር
1–5. ወጣትነት የደስታ ጊዜ መሆን የሚኖርበት ለምንድን ነው? ሆኖም ፈታኝ የሚያደርገው ምንድን ነው?
የወጣትነትህ ጊዜ ከሕይወትህ ዘመን ሁሉ በጣም ድንቅ የሆነው ወቅት መሆን ይኖርበታል። ይህ ወቅት ከዓመቱ የጸደይ ወራት ጋር የሚመሳሰል ነው። ወጣትነት የትኩስ ኃይል ጊዜ ነው። ሰውነትህ እየጠነከረ ይሄዳል። አእምሮህም እያደገ ነው። ልዩ ልዩ ነገሮችን ለመማርና ለመሥራት ብዙ አጋጣሚዎች እየተከፈቱልህ ነው። ስለዚህ የወጣትነት ጊዜ አስደሳችና አስደናቂ የሚሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ።
2 ሆኖም የወጣትነትህ ጊዜ ለአንተ አሁንም ሆነ ወደፊት አስደሳችና አስደናቂ ይሆንልሃልን? በዚህ ረገድ ሊረዱህ ወይም እንቅፋት ሊሆኑብህ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ነገሮች አንዳንዶቹን ልትለውጣቸው አትችልም። አብዛኞቹን ግን ልትቆጣጠራቸው ትችላለህ። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው ከወጣትነት ጊዜህ ከሁሉ የተሻለውንና ለዘለቄታ ጥቅምህ የሚበጀውን ለማግኘት እንድትችል አንተን እንደሚረዳህ ተስፋ በማድረግ ነው።
3 የወጣትነት ዘመን ተፈታታኝ የሆነ የትግል ጊዜ ነው። ዛሬ የሕይወት ጐዳና ብዙ ውጣ ውረድ የሞላበት መሆኑን ሳትገነዘበው አትቀርም። እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም ድፍረትን የሚጠይቅ ነው። ሆኖም ውጣ ውረዱን እንዴት ማሸነፍ እንደምትችል ገና ከጅምሩ ከተለማመድህ ቀሪው መንገድ ቀላል ይሆንልሃል። አንድን ችግር ባሸነፍህ ቁጥር ሌላውንም እንደምታሸንፍ ያለህ እምነት ያድጋል።
4 የኑሮ ውጣ ውረድ፣ ተጽዕኖዎችና ችግሮቹ አቅጣጫህን እንዲያስለውጡህ ከመፍቀድ ይልቅ የወጣትነት ፈተናን መቋቋሙ እንዴት የተሻለ ነው። እርግጥ ነው፤ በሕይወት ውስጥ የሌለውን ነገር እንዳለ አድርጎ በማሰብ ራስን እያታለሉ መኖር ቀላል ነው።
ይሁን እንጂ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ደስ የማይለው ሐቅ ከፊታቸው እንደሚደቀን አያጠራጥርም። ከዚያ በኋላ ለማንሠራራትና ወደፊት ለመራመድ አዳጋች ሊሆን ይችላል። ከፍተኛ ዋጋ ያለው ጊዜ በዚህ መንገድ በከንቱ ያልፋል፤ ምክንያቱም ሰዎችም እንደሚሉት ወጣትነት ተመልሶ አይመጣም።5 አሁን በሽግግር ጊዜ ማለትም በለውጥ ወቅት ላይ ትገኛለህ። ለምሳሌ ሰውነትህ አካላዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ እየተለወጠ ይሄዳል። ቢሆንም ከሃያ እስከ ሃያ ሦስት ዓመት ዕድሜ ላይ ሳትደርስ ወደዚያ ደረጃ አይደርስም። ወደ ስሜታዊ ብስለት ለመድረስ ግን ከዚያ የበለጠ ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። በውስጥህ የሚካሄዱት አንዳንድ ለውጦች ግራ ሊያጋቡህ ወይም ራስህን እንድትጠራጠር ሊያደርጉህ ይችላሉ። በውስጥህ አዳዲስ ግፊቶች እያየሉ እንደመጡ ሲሰማህ ምን ታደርጋለህ? ይህ መጽሐፍ በወጣትነት ጊዜ ስለሚከሰቱት ስለነዚህ ለውጦችና እነርሱን ታግለህ እንዴት በተሳካ ሁኔታ ልትቋቋማቸው እንደምትችል ያብራራል። እንዲያውም ለውጦቹ የሚያመጧቸውን የሚያታግሉ ሁኔታዎች በደስታ ልትቀበላቸው ትችላለህ፤ ምክንያቱም ከሌላው ሰው ሁሉ የተለየህ ግለሰብ የሚያደርግህ ወይም አንተነትህን የሚወስነው አስደናቂ የሕይወት ተሞክሮ ክፍል ናቸው።
መንገድህን ለመቀየስ የሚረዱህ ነገሮች
6–9. ሌሎች ሰዎች ካደረጓቸው ነገሮች በመማር ለመጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
6 አንዳንድ ጊዜ ሕይወትህ ‘ይህን አድርግ፤ ያን አታድርግ’ በሚሉ ዕገዳዎች የተሞላ መስሎ ይታይህ ይሆናል። ሆኖም ነገሩን ከሌላ አቅጣጫ ብትመለከተው በወጣትነትህ ጊዜ በኋላ የማታገኘው ዓይነት ነፃነት አለህ። ትልልቅ ሰዎች ያሏቸው ኃላፊነቶች የተጫኑብህ ስላልሆንክ እውቀት ለመሰብሰብና ችሎታዎችህንና የሙያ ተሰጥኦዎችህን ለማሳደግ ልታውል የምትችልበት ብዙ ጊዜ አለህ። ሌሎች ሰዎች ከዚህ በፊት የሠሩትን ወይም አሁን በመሥራት ላይ ያሉትን ነገር ለመማርና ስለ እርሱም ለማሰብ የሚያስችል በጣም ብዙ ጊዜ አለህ። የተሳካላቸውንና ያልተሳካላቸውን ነገር በማየት ብዙ ትምህርት ልታገኝ እንዲሁም የጥበብ ምርጫ ያደረጉበትን ወይም የሞኝነት ስህተቶችን የፈጸሙበትን ጉዳይ
ለማስተዋል ትችላለህ። ይህም በሕይወት ጎዳና የትኛውን አቅጣጫ መያዝ እንዳለብህ ለማወቅ ይረዳሃል።7 ታዲያ በዚህ ረገድ ያለ ማንም እርዳታ ብቻህን በየትኛው አቅጣጫ እንደምትጓዝ ውሳኔ ለማድረግ ትችላለህን? እንዲህ ለማድረግ መሞከርህ ምን ያህል ብልህነት ይሆናል? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት:-
8 የመኪና ሞተር ለመገጣጠም ትፈልጋለህ እንበል። አስቀድመህ ልምድ ካላቸው መካኒኮች ሳትማር በቀጥታ ብቻህን መሥራት ትጀምራለህን? እንደዚያ ብታደርግ ሞተሩ ምን ይሆናል? ወይም ሴት ብትሆኚ ሌላ ሰው ልብስ ሲሰፋ ሳታዪ ወይም ሞዴል ሳይኖርሽ በግብዣ ጊዜ የሚለበስ ልብስ ለመስፋት ትሞክሪያለሽን? እንዲህ ብታደርጊ ልብሱ ምን ሊመስል እንደሚችል ልትገምቺ ትችያለሸ።
9 የሰዎች ኑሮ ከመኪና ሞተር ወይም ከግብዣ ልብስ የበለጠ የተወሳሰበ መሆኑ የማያጠያይቅ እንደሆነ የታወቀ አይደለምን?
ከሌሎች ጋር ያላችሁ የአሳብ መገናኛ መስመር አይቋረጥ
10–16. (ሀ) አንዳንድ ወጣቶች በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ለመማር እንደማይችሉ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል? (ለ) በዕድሜ የገፉትን ሰዎች ከመስማት በተጨማሪ ስለ ሕይወት ሌላ የዕውቀት ምንጭ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
10 ሁላችንም ዕውቀታችንን የምንገነባው ከእኛ በፊት የኖሩ ሌሎች ሰዎች ባገኙት ዕውቀትና ልምድ ላይ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ይሁን እንጂ ከሌሎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት ሳታደርግ ይህን ማድረግ አትችልም። ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ሳታደርግ ማለትም ሳትነጋገር፣ የጻፉትን ሳታነብ፣ ወይም ትምህርት ማግኘትን ዓላማህ በማድረግ ሲሠሩ ሳትመለከት ሌሎች ያገኙትን እውቀትና ልምድ ልትቀስም አትችልም።
11 ከወጣትነትህ ዘመን ከሁሉ የላቀውን ውጤት ለማግኘት ሌሎች ያገኙትን ትምህርት በመቅሰም መጠቀም አለብህ። ይህም ሰውነትህን በተሻለ ሁኔታ ስለመያዝ፣ እውነተኛና ጥሩ ወዳጆችን ስለማፍራትና ያንን ወዳጅነት አጥብቀህ ስለመያዝ፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር በቀጠሮ ተገናኝቶ መጫወትንና ለመጋባት አስቦ መቀራረብን በሚመለከት ጠቃሚ መመሪያዎችን ስለማግኘት፣ ስለ ጋብቻ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት፣ ስለ ፆታ ግንኙነትና የአልኮል
መጠጦችን ወይም አደንዛዥ ዕፆችን ስለመውሰድ የመሳሰሉትን ነገሮች ይጨምራል። እነዚህ ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተተንትነዋል።12 ይሁን እንጂ ዛሬ በዙሪያህ ባለው ዓለም ውስጥ ስለምታየው ነገር እያሰብህ ሊሆን ይችላል። ራስ ወዳድነት በብዛት ይታያል። ብዙ ሰዎች በደል ይደርስባቸዋል። በተጨማሪም ብዙ ማታለል፣ የአካባቢ መበከል፣ ወንጀል፣ ጦርነት፣ ውሸትና ግብዝነት አለ። ‘ታዲያ ትልልቅ ሰዎች ነገሮችን እንዲህ ካመሰቃቀሉ እኔ ከእነርሱ ምን መማር እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
13 እውነት ነው፤ ዛሬ ካሉት ትልልቅ ሰዎች ለእነዚህ ሁኔታዎች ተጠያቂ የሆኑ ብዙዎች አሉ። እነርሱ አንድም የበደሎቹ ተካፋይ ነበሩ፤ አለዚያም እነዚህን ሁኔታዎች ከፈጠሩት ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው የኖሩና የደገፉ ናቸው።
14 ይሁን እንጂ በሌላም በኩል ነገሮች እንደዚህ ተበላሽተው በማየታቸው እንደ አንተው የሚያዝኑ ብዙ ትልልቅ ሰዎችም እኮ አሉ። አይደለም እንዴ? ደግሞም እነዚህ ነገሮች መከሰት የጀመሩት በአንድ ትውልድ ውስጥ አይደለም። ወላጆችህ አሁን አንተ ባለህበት ዕድሜ ላይ ሳሉ እነርሱም የዓለምን መልክ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ አግኝተውት ነበር። እንዲያውም ላለፈው ግማሽ መቶ ዘመን በተለይም ከ1914 እስከ 1918 ከተካሄደው አንደኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ሰዎች ከአንዱ ውዝግብ ወደ ሌላው ሲገለባበጡ ቆይተዋል። አንዱ ውዝግብ ሲያልፍ ሌላ የባሰ ውዝግብ ሲመጣ ታይቷል።
15 በዕድሜ ትልቅ መሆን ወይም ብዙ ልምድ ማካበት ብቻ ለሁሉም የሕይወት ችግሮች መፍትሔ እንደማያስገኝ የታወቀ ነው። ይህ ቢሆን ኖሮ በየትም ቦታ ያሉ ሁኔታዎች ሁልጊዜ እየተሻሻሉ በሄዱ ነበር። ግን እየተሻሻሉ አልሄዱም። ታዲያ ከሌሎች መማር ከምትችለው ልምድ በተጨማሪ አንተ ልትቀዳው የምትችል ሌላ እንዲያውም የተሻለ የዕውቀትና የእርዳታ ምንጭ አለን?
16 አዎን አለ። ቀጥለን ስለዚህ የዕውቀትና የእርዳታ ምንጭ እንነጋገራለን።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]