በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃልን?

የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃልን?

ምዕራፍ 18

የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃልን?

1–3. በዓለም ውስጥ ብዙ ሰዎች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ስለመፈጸም እንዴት ይሰማቸዋል?

በዛሬው ጊዜ በብዙ ቦታዎች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ኃይለኛ ግፊት አለ። እንዲያውም ዓለም “የፆታ አብዮት” እየተባለ የሚጠራውን ፈሊጥ ተያይዞታል። በኒው ዮርክ ከተማ የሚታተመው ዴይሊ ኒውስ ጋዜጣ “በአሁኑ ጊዜ ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም በወላጆች፣ በኰሌጆችና ባጠቃላይም በሕዝብ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት አግኝቷል። የፆታ ብልግና ሊቋቋሙት የማይቻልን ድንገት ደራሽ ጐርፍ ለመግታት እንደመሞከር ያህል ከንቱ ልፋት ተደርጐ በመቆጠሩ በዝምታ የሚታለፍ ነገር ሆኗል” በማለት አስረድቷል።

2 ብዙ ሰዎች ከፈለጉት ሰው ጋርና በፈለጉት መንገድ የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ነፃነት እንዲኖራቸው ይጠይቃሉ። እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ ብዙ ግለሰቦችን ግራ የሚያጋባ ሆኖባቸዋል። አንዲት የኰሌጅ ተማሪ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ተቀጣጥራ በወጣችበት ቀን ስላጋጠማት ለየት ያለ ችግር ስትገልጽ “ልጁ ምን አለበት? ይለኛል። እኔም አብረን ከምንውልበት ጊዜ ከፊሉን ስለ ስነ ምግባር አስፈላጊነት ለማስረዳት በመሞከር አሳለፍሁት። ከዚያ በኋላ ግን እኔው ራሴ ምን አለበት? እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርሁ” በማለት ተናግራለች። አንተም “ምን አለበት?” እያልክ ራስህን ጠይቀሃልን? የፆታ ስነ ምግባር በእርግጥ አስፈላጊ መስሎ ይታይሃልን?

3 ወጣቶች የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደሚችሉበት ደረጃ ስለደረሱና “በጣም አስደሳች” ነው ሲባል ስለሚሰሙ ለእነርሱ የሚገባ ነገር እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ለእነርሱ የሚገባ ነገር ነውን? ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ተገቢ ነውን? ሕይወትን አስደሳች ለማድረግስ ይረዳልን?

ውጤቱ ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ?

4–7. (ሀ) ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ከሚመጡት የተለመዱ መዘዞች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? (ለ) ስድ የፆታ ድርጊቶች “አዲስ” ስነ ምግባር እንዳልሆኑ የሚያሳየው ምንድን ነው? (መሳፍንት 19:22–25፤ ይሁዳ 7) (ሐ) በ1 ቆሮንቶስ 6:18 ላይ የተሰጠው ምክር ይህን ያህል ክብደት ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው? (ሥራ 15:28, 29፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3, 7, 8)

4 የፆታ ነፃነት የላቀ የግል ደስታ ያመጣል፤ ደግሞም “በጣም ደስ ይላል” እያሉ የሚናገሩት የአንዳንድ ሰዎች አባባልስ ትክክል ነውን? የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር ጋዜጣ ከጋብቻ በፊት ከብዙ ሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት የፈጸመ አንድ ወጣት ስለደረሰበት ግንዛቤ ሲዘግብ “ይህ ደስታ እንዳላመጣልኝ ተረድቻለሁ” ማለቱን ገልጿል። ወጣት ሴቶችማ ከጋብቻ በፊት ከሚደረግ የፆታ ግንኙነት ደስታ የማግኘታቸው ጉዳይ ይብሱን የማይመስል ነው። አንዲት የኰሌጅ ተማሪ እንዲህ ስለመሰለው ተሞክሮ ስትናገር “በእርግጥ ምንም ዋጋ የለውም። በወቅቱም ደስ የሚል አልነበረም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በጭንቀት ላይ እገኛለሁ” በማለት እንባ እያነቃት ተናግራለች።

5 ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነቱ ጭንቀት በበርካታ ምክንያቶች የተነሳ ተገቢ ነው። አንድ የጤና መኮንን አንዱን ምክንያት በመጠቆም በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ 50 በመቶ የሚሆኑት የዩናይትድ ስቴትስ ወጣቶች በጨብጥ የመለከፍ አደጋ እንደተደቀነባቸው ተናግረዋል! የሕክምና ባለ ሥልጣኖችም ዘመናዊ መድኃኒቶች ዋነኛ የአባለ ዘር በሽታዎች የሆኑትን የጨብጥና የቂጥኝን እድገት በመግታት ረገድ አጥጋቢ ውጤት እንደማያስገኙ ይናገራሉ። ብዙውን ጊዜ በበሽታዎቹ የተያዙት ሰዎች በሰውነታቸው ላይ የሚደርሰውን ከባድና ሊጠገን የማይችል ጉዳት ለማስወገድ ጊዜው እንዳለፈባቸው ይገነዘባሉ። በፆታ ብልግና ምክንያት ዘላቂ ጉዳት፣ ምናልባትም የመታወርን ወይም መካን ሆኖ የመቅረትን ዕጣ መቀበል ምክንያታዊ ነውን?

6 በተጨማሪም ለማርገዝ ያለው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ያላገቡ ልጃገረዶች አርግዘዋል። ከነዚህ ብዙዎቹ ለማስወረድ ሲሞክሩ አደጋና የስሜት መረበሽ ይደርስባቸዋል። ሌሎች ደግሞ አስደሳች ወዳልሆነ ጋብቻ ውስጥ እንዲገቡ ተገደዋል። የተቀሩት ሌሎች ደግሞ ዲቃላ የማሳደግ ረጅምና አሳዛኝ ትግል ያጋጥማቸዋል። በአሥራዎቹ ዓመታት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶችን በቀላሉ ሊያገኟቸው ቢችሉም ከእርግዝና ነፃ ለመሆን “ዋስትና” እንደማይሰጡ ለማየት አያዳግትም።

7 እንደ እውነቱ ከሆነ የፆታ ግንኙነት ስድነት አዲስ ወይም “ዘመናዊ” የሚያሰኘው ምንም ነገር የለም። ከረጅም ጊዜ በፊት የነበረ ነገር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ይፈጽሙት ነበር። የጥንቱን የሮም መንግሥት ታሪክ ብታነብ ዛሬ በሚደረጉት በሁሉም ዓይነት የፆታ ስድነት ተጨማልቆ እንደነበረ ትገነዘባለህ። እንዲያውም ውድቀቱ የመጣው በአብዛኛው በስነ ምግባር መዳከም ምክንያት ነው። “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መስማት በእርግጥ አስተዋይነት ነው። — 1 ቆሮንቶስ 6:18

የፆታ ስነ ምግባር የደካማነት ምልክት ነውን?

8–11. (ሀ) ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም መቆጠብ ጥንካሬን የሚጠይቀው ለምንድን ነው? (ለ) በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ እንደተገለጸው በፆታ ብልግና የወደቀው ወጣት ለመልካም ዓላማ የሚገፋፋ ልብ እንደጐደለው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ሐ) ሱነማይቱ ወጣት ለትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጽናት ያሳየችው እንዴት ነው?

8 ሆኖም ዝሙት እንድትፈጽም ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥምህና እምቢ ካልክ ሌሎቹ ደካማ ነው እያሉ ያወሩብህ ይሆናል። በአንዳንድ ቦታዎች ዝሙት ተቀባይነት ያለው ድርጊት ሆኗል።ሁለት ሐኪሞች ስለ ሰው ፍትወታዊነት የሕክምና አመለካከት በተሰኘ ጽሑፍ ላይ ሲጽፉ “ወጣቶች የፆታ ግንኙነት ግብዣ ቀርቦላቸው እምቢ ሲሉ የጥፋተኛነት ስሜት ሊሰማቸው ጀምሯል። ወጣት ሴቶችም በ25 ዓመታቸው ገና ድንግል መሆናቸውን መናገር እንደሚያሳፍራቸው የገለጹበት ጊዜ አለ” በማለት ጠቅሰዋል። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም እምቢ ማለት የደካማነት ምልክት ነውን? የበለጠ ጥንካሬ የሚጠይቀው የትኛው ነው? ለፍትወት መሸነፍ ወይስ አፍኖ መያዝ?

9 በእውነቱ ማንኛውም ደካማ ሰው ለፍትወት ግፊት እጁን ሊሰጥ ይችላል። ነገር ግን በጋብቻ የትዳር ጓደኛ እስኪገኝ ድረስ የፍትወትን ግፊት ለመቋቋም እውነተኛ “ወንድነትን” (ወይም እውነተኛ “ሴትነትን”) ይጠይቃል። ዓለም አቀፋዊው አዝማሚያ በተቃራኒው አቅጣጫ እያመራ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ጐርፍን እንደመቋቋም ያህል ስለሚሆን የበለጠ ጥንካሬ ይጠይቃል።

10 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ይህንን ነጥብ የሚያጐላ ታሪክ ያቀርብልናል። “አእምሮ [ተሞክሮ አዓት ] ከጐደላቸው” መካከል ለመልካም ዓላማ የሚገፋፋ ልብ የጐደለው አንድ ወጣት ከጋለሞታ ሴት ጋር ወደተገናኘበት ቦታ ያቀናበትን አኳኋን ይተርክልናል። በለዘበ የማግባቢያ አነጋገሯ ተሸንፎ ‘ወዲያውኑ ወደ መታረድ እንደሚነዳ በሬ፣ እንዲሁም ለመቀጣት በእግር ብረት እንደታሠረ ሞኝ ሰው በመሆን ይከተላታል።’ (ምሳሌ 7:6–23) የጋለሞታዋን ማግባቢያ ለመቋቋም የሚያስችል የስነ ምግባር ጥንካሬ አልነበረውም።

11 ነገር ግን ቀደም ብለን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት ልታገባው ላሰበችው ወጣት እረኛ ታማኝ ሆና መገኘትን በመምረጥ የንጉሡን የሰሎሞንን ማባበያ ሁሉ ስለተቋቋመችው ቆንጆይቱ የሱነም ልጃገረድ አንብበን ነበር። አዎን፤ በቀላሉ እንደሚከፈት “በር” በመሆን ፋንታ እንደ “ግንብ” ጽኑ በመሆን ለምትጠብቀው ሰው ድንግልናዋን ለመጠበቅ የቆረጠች መሆንዋን ለታላላቅ ወንድሞቿ አረጋገጠች። — መኃልየ መኃልይ 8:8–10

የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

12–14. (ሀ) የፆታ ግንኙነትን በሚመለከት አምላክ ካወጣቸው ሕግጋት ጋር መስማማት ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ዕብራውያን 13:4 እና 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ስለ ሴሰኞች የወደፊት ዕጣ ምን ይላሉ? ዝሙት ምን ማለት ነው?

12 የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ የሆነበት ዋናው ምክንያት ስለ ሰው ደስታ ከሁሉ የበለጠ በሚያውቀው በይሖዋ አምላክ የተቀየሰ መንገድ በመሆኑ ነው። እስቲ አስበው። ይሖዋ አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ የሰው ሕይወት በፆታ ግንኙነት አማካኝነት እንዲተላለፍ ዝግጅት አድርጓል። ይህም እጅግ ግሩምና ቅዱስ ነገር ነው። ሁላችንም ሕይወት ስላገኘን የዚህ ዝግጅት ተጠቃሚዎች ሆነናል። የጥቅሙ ተካፋዮች ከሆንን ለጠቅላላው አሠራሩ አምላክ ያወጣቸውን ደንቦች የመቀበል ግዴታ አይኖርብንምን? በእርግጥም ይሖዋ አምላክ ሕይወት ሰጪአችን እንደመሆኑ መጠን ሕይወት የማስተላለፍ ኃይል ያላቸውን የፆታ ብልቶቻችንን እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል የሚገልጹ የተግባር ደንቦችን ለማውጣት መብት አለው።

13 አምላክ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካኝነት “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” በማለት ይነግረናል። (ዕብራውያን 13:4) ዝሙት የሚለው ቃል ከማንም ሰው ጋር መልከስከስን ብቻ ሳይሆን ገና ያልተጋቡ ሰዎች ከጋብቻ በፊት የሚፈጽሙትን የፆታ ግንኙነትም ይጨምራል። የተጫጩ ሰዎች ከጋብቻ በፊት የሚፈጽሙትንም የፆታ ግንኙነት ይጨምራል።

14 የአምላክ ቃል ዝሙትንና ሌሎችንም ስድ ጠባዮች በማውገዝ ረገድ አቋሙ በጣም ግልጽ ነው። እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ውስጥ ምንም ድርሻ እንደማይኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ (ግብረ ሰዶማውያን) ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” — 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

15–19. (ሀ) የፆታ ብልግናን መጥላት የሚገባን ለምንድን ነው? (መዝሙር 97:10) (ለ) እንደዚህ ዓይነቱን ተገቢ ጥላቻ ለማሳደግ የሚረዳን ምንድን ነው?

15 ይህ ቁርጥ ያለ የአምላክ ሕግ በእርግጥ ለእኛው ጥቅም የሚበጅ ነው። የፆታ ግፊቶች በጣም ጠንካራ ሊሆኑ ይችላሉ። በአብዛኛዎቹ ሰዎች ሕይወት ውስጥም ተፈታታኝ ግፊት ሲመጣ በቀላሉ የሚሸነፉባቸው ወቅቶች ይመጣሉ። በጉዳዩ ላይ የአምላክ ሕግ የሚናገረው ነገር የተድበሰበሰ ወይም ደካማ ቢሆን ኖሮ እንደነዚህ ያሉት ተፈታታኝ ጊዜያት ሲመጡ ብዙም አይረዳንም ነበር። ነገር ግን የአምላክ ሕግ በጣም ግልጽና ኃይለኛ ስለሆነ ስሜታችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል፣ የስነ ምግባር ብርታታችንን ያጠናክርልናል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መጥፎውን ጎዳና መጥላትን እንድንማር ይረዳናል። አንተስ የፆታ ብልግናን ጐዳና በእርግጥ ትጠላለህን? መጥላት የሚገባህስ ለምንድን ነው?

16 ይህ ጐዳና አንዳንድ ጊዜ ማራኪ መስሎ ቢታይህ ራስህን እንደዚህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የቤተሰቤ አባላት ማለትም ወላጆቼ፣ ወንድሞቼና እኅቶቼ የፆታ ብልግና ቢፈጽሙ ደስ ይለኝ ነበርን? ዲቃላ ቢወልዱስ እደሰት ነበርን? ይህስ ለእነርሱ ያለኝን ፍቅርና አክብሮት ይጨምርልኝ ነበርን?’ ነገሩ እንደዚያ ካልሆነ ታዲያ ይህ ድርጊት ሊጠላ የሚገባው አይደለምን? በፆታ ብልግና አማካኝነት ማንም ወንድ ወይም ሴት እጁን ወይም እጅዋን እንደሚጠርጉበት የምግብ ቤት ፎጣ መሆን እንደማትፈልጉ ጥርጥር የለውም።

17 በእንደዚህ ዓይነቱ የብልግና መንገድ የተወለዱት ልጆችስ? ለምሳሌ ሴት ልጅ ከሆንሽ ዲቃላ ብትወልጂ የሚያሳድገው ማን ነው? እናትና አባትሽ ናቸውን? አንቺ ራስሽ ነሽን? አንቺ ከሆንሽ ታዲያ እንዴት አድርገሽ ታሳድጊዋለሽ? ልጁ ካደገ በኋላስ እንዴት እንደ ተፀነሰ ሲያውቅ ምን ይሰማዋል? ወይም ደግሞ የማሳደጉን ኃላፊነት ለመሸከም እምቢ ብለሽ ልጁን ጒዲፈቻ ብትሰጪው ሌሎች ሰዎች ስለ አንቺ ምን ይሰማቸዋል? አንቺስ ስለ ራስሽ ምን ይሰማሻል? መውለድሽን ለመደበቅ ልትሞክሪና ልጁን ለአሳዳጊ ሰጥተሽ ከዓይንሽ በማራቅ ከሃፍረትና ከኃላፊነት ለመሸሽ ትሞክሪ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከራስሽ መሸሽ አትችይም። ትችያለሽ እንዴ?

18 ወይም ደግሞ ወንድ ከሆንክ ከአንዷ ሴት ዲቃላ ብትወልድ ሕሊናህ ዕረፍት ያገኛልን? በናትየዋና በልጅህ ላይ ስለሚደርሰው ችግርና ሃፍረት እስቲ አስብ። በእርግጥ ይህ ሊርቁት የሚገባ ነገር ነው።

19 እንደ እውነቱ ከሆነ ከፆታ ብልግና ምን ጥሩ ነገር ተገኝቶ ያውቃል? የማይፈለጉ ብዙ ነገሮች፤ ለምሳሌ ያህል አካል አጉዳዮቹ የአባለ ዘር በሽታዎች፣ ውርጃዎች፣ የቅናት አምባጓሮዎች፣ ነፍስ ግድያም እንኳ ሳይቀር ከፆታ ብልግና ጋር ተያይዘው የሚመጡት ለምንድን ነው? ከፍተኛ የፆታ “ነፃነት” በተፈቀደባቸው አገሮች የፍቺ ብዛት በዓለም ካሉት ውስጥ ከፍተኛ ከሆኑት መካከል ሆኖ የሚገኘው ለምንድን ነው? ፍቺ የሚያመለክተው የኑሮ መሳካትን ነው ወይስ ውድቀትን? ፍቺ የእውነተኛ ደስታ ምልክት ነው ወይስ የኀዘንና የትካዜ?

20, 21. ከፆታ ብልግና መራቅ የተሳካ ጋብቻ ለመመሥረት ያለህን ዕድል የተሻለ ሊያደርገው የሚችለው እንዴት ነው?

20 በሌላው በኩል ግን የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ይህን አቋም አጥብቀው የሚከተሉት ሰዎች የተሳካ ጋብቻ ለመመሥረት የተሻለ አጋጣሚ አላቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት የአምላክን ዝግጅትና የወደፊት የትዳር ጓደኛቸውን ስለሚያከብሩ፤ እንዲሁም ሁለቱም ተጋቢዎች ንጹሕ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ያላቸውን የጋራ መብት በማክበር ለጋብቻ ከፍተኛ ቦታ ስለሚሰጡ ነው።

21 እንደ እውነቱ ከሆነ ከስድ ጠባይ ለመራቅ ይበልጥ ጥንቁቅ በሆንክ መጠን ወይም ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለመጠናናት በምትቀራረብበት ጊዜና በመተጫጨት ወቅቶች የፈለግኸውን ላለማድረግ የበለጠ ጥንቃቄ ካደረግህ ጋብቻህ የሰመረ ለመሆን የበለጠ ዕድል ይኖረዋል። እንዲህ ከሆነም አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ ወደ ጋብቻ ያስገባችሁ ምክንያት ‘የፆታ ጉዳይ ይሆን ወይ?’ በሚል ጥርጣሬ አንዳችሁ ለሌላው እውነተኛ ፍቅር ያለው ስለመሆኑ የሚከነክን ጥርጣሬ አይኖራችሁም። ምክንያቱም ከሁሉ በላይ ጋብቻ የሁለት ሰዎች ባሕርያት እንጂ የሁለት አካሎች ውህደት ስላልሆነ ነው። ጋብቻ ዘላቂ ደስታ እንዲያመጣ ከተፈለገ እርስ በርሳችሁ አንዱ ለሌላው ሰው ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር ሊሰጠው ይገባል።

ጥበብ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ

22–24. (ሀ) አንዲት ወጣት ስለ አምኖንና ስለ ትዕማር ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ጠቃሚ ትምህርት ልታገኝ ትችላለች? (ለ) የጶጢፋር ሚስት ያሳየችው ፍትወታዊ ፍቅር ዘላቂ ፍቅር አለመሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

22 በፍትወት ላይ ብቻ የተመሠረተ ፍቅር ዘላቂ አይደለም። ራስ ወዳድነትና ስግብግብነትን የሚያሳይ ፍቅር ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምኖን በተባለው የዳዊት ልጅ ላይ ታይቷል። ውብ በሆነችው ግማሽ እኅቱ በትዕማር ፍቅር ተነደፈ። ከዚያ በኋላም በዘዴ ተጠቅሞ በማታለል ከእርሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድታደርግ አስገደዳት። ከዚያ በኋላስ ምን ሆነ? ዘገባው “ከዚያ በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት። አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ” ይላል። ወደ ውጭ አስወጥቶ አባረራት። (2 ሳሙኤል 13:1–19) እስቲ አንቺ ወጣት ሴት ብትሆኚ አንድ ልጅ የጋለ ፍትወታዊ ፍቅር እንዳለው ቢገልጽልሽና ከአንቺም ጋር ግንኙነት ለማድረግ ቢፈልግ ከልብ ያፈቅረኛል ብለሽ በገርነት ማሰብ ይኖርብሻልን? ልክ እንደ አምኖን ሊሆንብሽ ይችላል።

23 መጽሐፍ ቅዱስ የግብፃዊው ጃንደረባ የጶጢፋር ሚስት በቤታቸው ያገለግል ለነበረው ለዮሴፍ ተመሳሳይ ስሜት አሳይታ እንደነበር ይነግረናል። እርሱን ለማሳሳት ያደረገችውን ሙከራ ሁሉ በተቋቋመ ጊዜ የልቧን እውነተኛ መልክ መግለጥ ጀመረች። ስለ ዮሴፍ ለባልዋ ክፉ ውሸት ተናግራ ያለ ፍትሕ እንዲታሰር አደረገችው። — ዘፍጥረት 39:7–20

24 አዎን፣ የፆታ “ነፃነት” የተባለው ፈሊጥ አስደሳችና ንጹሕ ሊሆን የሚገባውን ነገር ርካሽና አስጸያፊ አድርጎ ይለውጠዋል። ስለዚህ አንተ የምትፈልገው የትኛውን ነው? ከሚያመጣው አደጋና ችግር ሁሉ ጋር ያጭር ጊዜ ሕገ ወጥ የፆታ ደስታን ነው ወይስ ለሁልጊዜው ራስህን ራስህ ማክበር ችለህ በአምላክና በሰዎች ሁሉ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘህ መኖር?

25, 26. በፆታ ብልግና ከመውደቅ ለመዳን ሊረዱን የሚችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ኤፌሶን 5:3, 4፤ ፊልጵስዩስ 4:8)

25 ከፆታ ብልግና ርቀህ ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ ወደዚያ ከሚመሩ ነገሮች ራቅ:- ሁልጊዜ በተቃራኒ ፆታ ላይ ከሚያተኩር ወሬ፣ እንዲሁም አንድ ግብ ብቻ ካላቸው ነገሮች ይኸውም የፆታን ስሜት ለማነሣሣት ከተዘጋጁ ጽሑፎች ወይም ሥዕሎች ራቅ። ዘላቂ ጥቅም የሚያመጡና ምንም ሐፍረት ወይም የልብ ሥቃይ ትተው የማያልፉ ነገሮችን በሚያመጡ ጠቃሚ ግቦች ላይ ለመድረስ አእምሮህ፣ ዓይንህና ምላስህ ንጹሕና ገንቢ በሆኑ ነገሮች እንዲያዙ አድርግ።

26 ከሁሉ በላይ ስለ ፈጣሪህና ስለ መንገዶቹ ትክክለኛነትና ጥበባዊነት ያለህን እውቀትና አድናቆት አጠናክር። ወደርሱ በጸሎት እየቀረብክ ለሚያገለግሉት ሰዎች ቃል በገባላቸው ነገሮች ላይ ልብህን ትከል። ይሖዋ አምላክና ልጁ የሚያስፈልግህን ኃይል ስለሚሰጡህ አንተ ከልብ የምትፈልግ ከሆነ በፆታ ስነ ምግባር ጐዳና ልትጸና ትችላለህ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]