በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ጓደኞች እንዲኖሩኝ ምን ላድርግ?

ጥሩ ጓደኞች እንዲኖሩኝ ምን ላድርግ?

ምዕራፍ 8

ጥሩ ጓደኞች እንዲኖሩኝ ምን ላድርግ?

“ስናደድ የተሰማኝን አውጥቼ የምነግረው፣ ሳዝን የሚያጽናናኝ እንዲሁም ደስታዬን የማካፍለው ሰው እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። ያለ ጓደኛ መኖር እንደማልችል ይሰማኛል።”—ብሪታኒ

ትንሽ ልጅ እያለህ አብረውህ የሚጫወቱ ሌሎች ልጆች ትፈልግ ነበር፤ እነዚህን ልጆች የምትፈልጋቸው ብቻህን ላለመሆን ነው። አሁን ግን የሚያስፈልጉህ አብረውህ ጊዜ የሚያሳልፉ ብቻ ሳይሆን የአንተ ዓይነት አመለካከት ያላቸው እውነተኛ ጓደኞች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 17:17) ይህ ዓይነቱ ጓደኝነት ልጅ እያለህ አብረውህ ከሚጫወቱ ልጆች ጋር ከነበረህ ቅርርብ ይበልጥ የጠነከረ ነው።

እውነታው፦ እያደግህ ስትሄድ ከታች የተዘረዘሩትን ብቃቶች የሚያሟሉ ጓደኞች ያስፈልጉሃል፦

1. መልካም ባሕርያት ያሏቸው

2. ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የሚከተሉ

3. በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብህ

ጥያቄ፦ እነዚህን ብቃቶች የሚያሟሉ ጓደኞች ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከት።

የመጀመሪያው ነጥብ፦ መልካም ባሕርያት

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ እንደ ጓደኛ የሚቀርብህ ሰው ሁሉ እውነተኛ ጓደኛ ይሆናል ማለት አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርስ ከመጠፋፋት የማይመለሱ ጓደኛሞች አሉ” ይላል። (ምሳሌ 18:24 NW) ይህ አባባል የተጋነነ ይመስል ይሆናል። ይሁንና እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ጓደኛዬ ብለህ የምታስበው ሰው መጠቀሚያ ሊያደርግህ የሞከረበት ጊዜ አለ? ወይም ደግሞ ሚስጥርህን ለሌሎች አውርቶብህ አሊያም ስለ አንተ መጥፎ ወሬ አናፍሶ ያውቃል? እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከነበረ በዚህ ጓደኛህ ላይ እምነት ለመጣል ትቸገር ይሆናል። * ምንጊዜም ማስታወስ የሚኖርብህ ነገር ቢኖር መጥፎ ባሕርይ ያላቸው ብዙ ጓደኞች ከሚኖሩህ ይልቅ ጥሩ ባሕርይ ያላቸው ጥቂት ጓደኞች ቢኖሩህ የተሻለ መሆኑን ነው!

ምን ማድረግ ትችላለህ? ጥሩ ባሕርይ ያላቸውና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ጓደኛ አድርግ።

“ፊዮና የተባለችውን ጓደኛዬን ሰው ሁሉ በጣም ያደንቃታል። እኔም እንደ እሷ ዓይነት ስም ባተርፍ ደስ ይለኛል። ፊዮና በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ያላት መሆኑ እንዳደንቃት አድርጎኛል።”—ኢቬት፣ 17

ይህን መልመጃ ለመሥራት ሞክር

1. ገላትያ 5:22, 23⁠ን አንብብ።

2. ‘ጓደኞቼ “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች የሆኑትን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

3. በጣም የምትቀርባቸውን ጓደኞችህን ስም ከዚህ በታች ጻፍ። ከዚያም ከእያንዳንዱ ስም ጎን ግለሰቡን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል የምትለውን ባሕርይ ጥቀስ።

ስም

․․․․․

ባሕርይ

․․․․․

ፍንጭ፦ ስለ ጓደኞችህ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው መጥፎ ባሕርያቸው ብቻ ከሆነ የተሻሉ ጓደኞች መፈለግ ይኖርብህ ይሆናል!

ሁለተኛው ነጥብ፦ ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ ጓደኞች ለማግኘት ከመጠን በላይ የምትጓጓ ከሆነ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ልትገጥም ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “የተላሎች ባልንጀራ . . . ጕዳት ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) “ተላሎች” ወይም ሞኞች የሚለው ቃል የማሰብ ችሎታ ማነስን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚሰጣቸውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ችላ በማለት ከሥነ ምግባር አኳያ ማስተዋል የጎደለው አካሄድ የሚከተሉ ሰዎችን የሚያመለክት ነው። እንዲህ ያሉ ጓደኞች ደግሞ አይጠቅሙህም!

ምን ማድረግ ትችላለህ? ካገኘኸው ሁሉ ጋር ጓደኝነት ከመመሥረት ይልቅ በጓደኛ ምርጫህ ረገድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርብሃል። (መዝሙር 26:4) ይህም ሲባል “በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት” ማስተዋል መቻል አለብህ ማለት ነው።—ሚልክያስ 3:18

“እኩዮቼ የሆኑና ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ጓደኞች እንዳገኝ ስለረዱኝ ወላጆቼን አመሰግናቸዋለሁ።”—ክሪስቶፈር፣ 13

የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ፦

ትክክል እንዳልሆነ የማውቀውን ነገር እንድፈጽም ጓደኞቼ ተጽዕኖ ቢያደርጉብኝስ ብዬ እጨነቃለሁ?

□ አዎ

□ አይ

ወላጆቼ፣ ጓደኞቼን ላይወዷቸው እንደሚችሉ በመፍራት ጓደኞቼን ለእነሱ ከማስተዋወቅ ወደኋላ እላለሁ?

□ አዎ

□ አይ

ፍንጭ፦ ከላይ ላሉት ጥያቄዎች የሰጠኸው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የሚከተሉ ሌሎች ጓደኞች መፈለግ ይኖርብሃል ማለት ነው። ታዲያ ጥሩ ክርስቲያን በመሆን ረገድ አርዓያ የሚሆኑ ጓደኞችን ለምን አትፈልግም?

ሦስተኛው ነጥብ፦ በጎ ተጽዕኖ

ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሎረን የተባለች ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “አብረውኝ የሚማሩ ልጆች እንደ ጓደኛቸው አድርገው የሚያዩኝ የሚሉኝን እስካደረግሁ ድረስ ብቻ ነበር። ጓደኛ ስላልነበረኝ ከእነሱ ጋር ለመሆን ስል እነሱ የሚያደርጉትን ነገር ማድረግ ጀመርኩ።” ሎረን ካጋጠማት ነገር መገንዘብ እንደቻለችው አንድ ሰው በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል እነሱ የሚሉትን ሁሉ የሚያደርግ ከሆነ በቼዝ ጨዋታ ላይ እንዳሉት መጫወቻዎች ይሆናል፤ በሌላ አባባል ሌሎች እንደፈለጉ ያሽከረክሩታል። አንተ ደግሞ መጫወቻ መሆን እንደማትፈልግ የታወቀ ነው!

ምን ማድረግ ትችላለህ? ጓደኞችህ እነሱን እንድትመስል ጫና የሚያደርጉብህ ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርብሃል። እርግጥ እንዲህ ካደረግህ ብዙ ጓደኞች አይኖሩህ ይሆናል፤ ያም ቢሆን እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰድህ ለራስህ ያለህ ግምት ከፍ እንዲል የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ የሚችሉ ጥሩ ጓደኞች ለማግኘት አጋጣሚ ይከፍትልሃል።—ሮም 12:2

“ክሊንት የተባለው በጣም የምቀርበው ጓደኛዬ አስተዋይና ለሌሎች ስሜት የሚያስብ ሰው ነው፤ የእሱ ምሳሌነት በጣም ያበረታታኛል።”ጄሰን፣ 21

የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ፦

ጓደኞቼን ለማስደሰት ስል የእነሱን መጥፎ አለባበስ፣ አነጋገር ወይም ድርጊት ለመኮረጅ እሞክራለሁ?

□ አዎ

□ አይ

ለጓደኞቼ ስል ብቻ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ወደማይሄዱባቸው ቦታዎች እሄዳለሁ?

□ አዎ

□ አይ

ፍንጭ፦ ቀደም ሲል ለቀረቡት ጥያቄዎች የሰጠኸው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ የተሻሉ ጓደኞች ለመምረጥ እንዲረዱህ ወላጆችህን ወይም ብስለት ያለውን ሌላ ሰው አማክር። የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ደግሞ ወደ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ቀርበህ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ የሚችሉ ጓደኞችን ለመምረጥ እንዲረዳህ ልትጠይቀው ትችላለህ።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 9 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ጓደኛዬ ብለህ የምታስበው ሰው አሊያም ልብህ መጥፎ ነገር እንድታደርግ ይገፋፋሃል? ይህን ግፊት መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 እርግጥ ነው፣ የማይሳሳት ሰው የለም። (ሮም 3:23) ስለሆነም ጓደኛህ ቢያስቀይምህና ባደረገው ነገር ተጸጽቶ ከልቡ ይቅርታ ቢጠይቅህ “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ።—1 ጴጥሮስ 4:8

ቁልፍ ጥቅስ

“ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።”—ምሳሌ 18:24

ጠቃሚ ምክር

ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ለመከተል የምትጥር ከሆነ በእነዚህ መሥፈርቶች የሚመሩ ሰዎች ከአንተ ጋር ለመቀራረብ መፈለጋቸው አይቀርም። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ጥሩ ጓደኞች ይሆኑሃል!

ይህን ታውቅ ነበር?

አምላክ አያዳላም፤ ሆኖም ‘በድንኳኑ ውስጥ’ በእንግድነት የሚቀበለው ሁሉንም ሰው አይደለም።—መዝሙር 15:1-5

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ጥሩ ጓደኞች ለማግኘት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

በዕድሜ ከሚበልጡኝ መካከል ጓደኛ ላደርጋቸው የምፈልጋቸው ሰዎች ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ጓደኛህ እንዲኖረው የምትፈልጋቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ለምን?

● ለሌሎች ጥሩ ጓደኛ ለመሆን የትኞቹን ባሕርያት ማፍራት ይኖርብሃል?

[በገጽ 60 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወላጆቼ ከአንዳንድ ጓደኞቼ እንድርቅ መከሩኝ። በወቅቱ፣ ጓደኞቼ ሊሆኑ የሚችሉት እነዚህ ልጆች ብቻ እንደሆኑ ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም እነሱ የሰጡኝን ጠቃሚ ምክር ቆም ብዬ ሳስብበት ከእነዚህ ልጆች የተሻሉ ብዙ ጓደኞች ማግኘት እንደምችል ገባኝ።”—ኮል

[በገጽ 61 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እነዚህን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር

የጓደኛ ምርጫን በተመለከተ ወላጆችህን አማክራቸው። ወላጆችህ በአንተ ዕድሜ ላይ በነበሩበት ወቅት ምን ዓይነት ጓደኞች እንደነበሯቸው ጠይቃቸው። የጓደኛ ምርጫቸውን በተመለከተ የሚቆጩበት ነገር አለ? ካለ የሚቆጩት ለምንድን ነው? እነሱ የሠሩትን ስህተት እንዳትደግም ምን ማድረግ እንደምትችል ጠይቃቸው።

ጓደኞችህን ከወላጆችህ ጋር አስተዋውቃቸው። ጓደኞችህን ለማስተዋወቅ የምታመነታ ከሆነ ‘እንዲህ ማድረግ የከበደኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ጓደኞችህ በሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች ወላጆችህ እንደማይደሰቱ ይሰማሃል? ከሆነ በጓደኛ ምርጫህ ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን ሊያስፈልግህ ይችላል።

ጥሩ አድማጭ ሁን። ጓደኞችህ የሚያሳስቧቸውንና የሚያስጨንቋቸውን ነገሮች ሲነግሩህ በትኩረት አዳምጥ።—ፊልጵስዩስ 2:4

ይቅር ባይ ሁን። ከጓደኞችህ ፍጽምና አትጠብቅ። “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።”—ያዕቆብ 3:2

መፈናፈኛ አታሳጣቸው። ጓደኞችህ ላይ ሙጭጭ ማለት ተገቢ አይደለም። እውነተኛ ጓደኞች በሚያስፈልግህ ጊዜ ሁሉ ከጎንህ መሆናቸው አይቀርም።—መክብብ 4:9, 10

[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስትል እነሱ የሚሉትን ሁሉ የምታደርግ ከሆነ በቼዝ ጨዋታ ላይ እንዳሉት መጫወቻዎች እንደፈለጉ ያሽከረክሩሃል