ከአስተማሪዬ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?
ምዕራፍ 20
ከአስተማሪዬ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?
የምትወደውን አስተማሪ ስም ጻፍ። ․․․․․
ይህን አስተማሪ የምትወደው ለምንድን ነው? ․․․․․
የማትወደውን አስተማሪ ስም ጻፍ። ․․․․․
ጓደኞችህን መምረጥ ትችላለህ፤ በሌላ በኩል ግን በትምህርት ቤት በምታሳልፋቸው አብዛኞቹ ዓመታት አስተማሪዎችህ እነማን እንደሚሆኑ መምረጥ አትችልም። ምናልባት አንተ ሁሉንም አስተማሪዎችህን ትወዳቸው ይሆናል። የ18 ዓመቱ ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ከአስተማሪዎቼ ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሞኝ አያውቅም። እኔ የማከብራቸው ሲሆን እነሱም ይወዱኛል።”
በሌላ በኩል ግን የ11 ዓመቷ ሣራ ያጋጠማት ዓይነት አስተማሪ ይኖርህ ይሆናል። ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “አስተማሪያችን በጣም ክፉ ናት፤ የምታስተምረው ነገር ገብቶኝ አያውቅም። ወይ ትምህርቱን ታደበሰብሰዋለች ወይም ደግሞ በጣም ታንዛዛዋለች።” ከአስተማሪህ ጋር ለመስማማት እንድትችል በመጀመሪያ ለዚህ እንቅፋት እንደሆነ የሚሰማህን ችግር መለየት ያስፈልግሃል። ችግሩ ምን እንደሆነ መለየት
ከቻልክ መፍትሔ ማግኘት ቀላል ይሆንልሃል። ከታች ከቀረቡት መካከል የአንተን ስሜት በሚገልጹት ላይ ✔ አድርግ፤ ወይም የራስህን ምክንያት ጻፍ።□ አስተማሪው ምን እንደሚል አይገባኝም
□ የሠራሁትን ያህል ጥሩ ውጤት አልሰጠኝም
□ ለሌሎች ተማሪዎች ያዳላል
□ ከልክ በላይ ይቀጣኛል
□ እኔን አይወደኝም
□ ሌላ ․․․․․
ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ማድረግ ትችላለህ? በመጀመሪያ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር። ጴጥሮስ “ሁላችሁም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ፣ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 3:8) “ክፉ” የሆነብህን አስተማሪ ስሜት ለመረዳት ጥረት እንድታደርግ ሊረዳህ የሚችለው ምንድን ነው? ከአስተማሪዎች ጋር በተያያዘ ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች ልብ በል።
አስተማሪዎችም ሊሳሳቱ ይችላሉ። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ አስተማሪዎችም የራሳቸው ድክመቶች ሊኖሯቸውና የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ሌላው ቀርቶ አንዱን ከአንዱ የማስበለጥ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱን ጭምር መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 3:2) የ19 ዓመቷ ብሪያና እንዲህ ብላለች፦ “የሒሳብ አስተማሪያችን ትዕግሥት የሚባል ነገር የላትም፤ ሁልጊዜ ትጮኽብናለች። በዚህ ምክንያት እሷን ማክበር ከብዶን ነበር።” አስተማሪዋ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንዲኖራት አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? ብሪያና እንዲህ ብላለች፦ “ክፍላችን ሁልጊዜ እንደተረበሸ ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ተማሪዎቹ እሷን የበለጠ ለማበሳጨት ክፍሉን ቀውጢ ያደርጉታል።”
አስተማሪህ ስህተት ባይለቃቅምብህ እንደምትደሰት የታወቀ ነው፤ በተለይ ደግሞ ውጥረት ውስጥ ሆነህ የምትሠራቸውን ስህተቶች እንዲሁ እንዲያልፍልህ ትፈልጋለህ። አንተስ ከአስተማሪህ ጋር በተያያዘ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ? በቅርቡ
ትምህርት ቤት ያጋጠመህን አስተማሪህ እንዲበሳጭ ያደረገ አንድ ሁኔታ ጥቀስ፤ አስተማሪህን ያበሳጨው ምን ይመስልሃል?․․․․․
አስተማሪዎች አንዳንድ ተማሪዎችን ከሌሎች አስበልጠው ሊወዱ ይችላሉ። አስተማሪዎችህ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እስቲ ለማሰብ ሞክር፦ አብረውህ ከሚማሩት ልጆች መካከል ክፍል ገብተው መማር የሚፈልጉት ስንቶቹ ናቸው? የመማር ፍላጎት ካላቸው መካከልም እንኳ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ትምህርት ሲሰጥ ለግማሽ ሰዓት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ደስ ብሏቸው በትኩረት መከታተል የሚችሉት ምን ያህል ናቸው? የተበሳጩበት ምክንያት ሌላ ቢሆንም ንዴታቸውን በአስተማሪዎቻቸው ላይ የሚወጡት ተማሪዎችስ ምን ያህል ናቸው? ከእኩዮችህ መካከል 20፣ 30 ወይም ከዚያ የሚበልጡትን ማስተማር ቢኖርብህና የምታስተምረውን ርዕስ የሚወዱት ጥቂቶቹ ብቻ ቢሆኑ ምን እንደሚሰማህ አስብ። ትምህርቱን በደንብ ለሚያዳምጡህ ተማሪዎች የተለየ ትኩረት ለመስጠት አትፈልግም?
እርግጥ ነው፣ አስተማሪህ ዓይን ያወጣ መድልዎ እንዳደረገ ሲሰማህ ልትበሳጭ ትችላለህ። ናታሻ ስለ አንድ አስተማሪዋ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አስተማሪያችን የምንሠራው ነገር ሲሰጠን እንድናስረክብ ከነገረን ቀን እንድናሳልፍ አይፈቅድልንም፤ እግር ኳስ ለሚጫወቱት ልጆች ግን ሁልጊዜ የተለየ አስተያየት ያደርግላቸው ነበር። ለነገሩ ይህ ብዙም አይገርመኝም፤ አስተማሪው የእግር ኳስ ቡድኑ ረዳት አሠልጣኝ ነበር።” አንተም ተመሳሳይ ነገር ካጋጠመህ ‘አስተማሪው መማር የሚገባኝን ነገር አስቀርቶብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ካልሆነ ለሌሎች አድልዎ በማድረጉ ምን አበሳጨህ?
ትምህርቱን በትኩረት እንደምትከታተል ለአስተማሪህ በግልጽ ማሳየት የምትችልበትን መንገድ ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።
․․․․․
አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን በተሳሳተ መንገድ ሊረዷቸው ይችላሉ። አስተማሪህ ለአንተ ጥሩ አመለካከት የሌለው ባሕርያችሁ ስላልተጣጣመ ወይም ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ስለተረዳህ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ጥያቄ ስታበዛበት ዓመፀኛ እንደሆንክ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ለቀልድ ብለህ የተናገርከው ነገር ለእሱ አክብሮት እንደሌለህ ወይም ቁም ነገረኛ እንዳልሆንክ እንዲሰማው አድርጎት ይሆናል።
አስተማሪህ በተሳሳተ መንገድ ተረድቶህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” ይላል። (ሮም 12:17, 18) ስለዚህ ሆን ብለህ አስተማሪህን ለማበሳጨት አትሞክር። አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ አትግባ። አስተማሪህ ሰበብ እንዲያገኝብህ አታድርግ። እንዲያውም ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ለማድረግ ጣር። ‘ጭራሽ ከእሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አዎ፣ ለአስተማሪህ አክብሮት በተሞላበት መልኩ ሰላምታ በመስጠት እንደምታከብረው አሳይ። ምንጊዜም ትሑት መሆንህና አልፎ አልፎ በፈገግታ ሰላምታ መስጠትህ ለአንተ ያለው አመለካከት እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል።—ሮም 12:20, 21
ኬን የተባለውን ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኬን ብዙውን ጊዜ አስተማሪዎቹ በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። ኬን “በጣም ዓይን አፋር ስለሆንኩ አስተማሪዎቼን ቀርቤ
ማናገር ፈጽሞ አልችልም” ብሏል። ታዲያ ሁኔታውን ለማሻሻል ምን አደረገ? ኬን እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ የአስተማሪዎቼ ፍላጎት እኔን መርዳት እንደሆነ እያደር ተገነዘብኩ። ስለዚህ ሁሉንም አስተማሪዎቼን ለመቅረብ ግብ አወጣሁ። ይህን ሳደርግ ደግሞ ውጤቴ በጣም ተሻሻለ።”እርግጥ ነው፣ ከአስተማሪህ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርህ ጥረት ማድረግህ እንዲሁም እሱን ቀርበህ ማነጋገርህ በእሱ ዘንድ ተወዳጅነት እንድታተርፍ የሚረዳህ ሁልጊዜ አይደለም። ያም ቢሆን ትዕግሥተኛ ሁን። ንጉሥ ሰለሞን “ትዕግሥት በማሳየትና ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ በመናገር ገዥን [ወይም አስተማሪን] ማሳመን እንዲሁም ማንኛውንም ችግር መወጣት ይቻላል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 25:15 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን) አስተማሪህ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግብህ ሳትቆጣ በእርጋታ አነጋግረው። እንዲህ ማድረግህ ለአንተ ያለውን አመለካከት እንዲለውጥ ያደርገው ይሆናል።—ምሳሌ 15:1
አስተማሪህ በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳህ ወይም መድልዎ እንዳደረገብህ ሲሰማህ ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ የምትወስደው እርምጃ ምንድን ነው?
․․․․․
የተሻለ የሚሆነው ምን ብታደርግ ነው?
․․․․․
ለችግሮችህ መፍትሔ ማግኘት
አስተማሪህ አንድ ነገር ያደረገበትን ምክንያት ለመረዳት መሞከር ከእሱ ጋር ለመስማማት እንድትችል ልትወስደው የሚገባ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ይሁንና ላጋጠመህ ችግር መፍትሔ ለማግኘት ምን ሌላ እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? ለምሳሌ ያህል፣ እንደሚከተሉት ያሉ ቅሬታዎች ቢኖሩህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
የተሰጠኝ ውጤት ያንሰኛል። ካትሪና እንዲህ ብላለች፦ “ሁልጊዜ የማገኘው ከፍተኛ ውጤት ነው። በአንድ ወቅት ግን የሳይንስ አስተማሪዬ ጣለኝ። ከዚህ የተሻለ ውጤት ሊሰጠኝ ይገባ ነበር። በመሆኑም ወላጆቼ ርዕሰ መምህሩን አነጋገሩት። እንደዚያም ሆኖ ያገኘሁት ማለፊያውን ነጥብ ብቻ ነው፤ ይህም የበለጠ አበሳጨኝ።” 2 ሳሙኤል 12:1-7
አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠመህ አስተማሪህን ለመንቀፍ አትቸኩል። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የናታንን ምሳሌ ተከተል። ናታን አንድ አስቸጋሪ ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር፤ ይህ ነቢይ፣ ንጉሥ ዳዊት የሠራውን ከባድ ስህተት እንዲነግረው ተልኮ ነበር። ናታን ልክ ቤተ መንግሥት እንደደረሰ የዳዊትን ስህተቶች አልደረደረለትም፤ ከዚህ ይልቅ ዳዊት የሠራውን ስህተት በዘዴ ነግሮታል።—አንተም በተመሳሳይ አስተማሪህን ቀርበህ በትሕትና እና በተረጋጋ መንፈስ አነጋግረው። በቁጣ ገንፍለህ በመናገር፣ አስተማሪህ ሥራውን በአግባቡ እንዳላከናወነ በመግለጽ ወይም ሌላ የከፋ ነገር በማድረግ የምታተርፈው ነገር የለም። ነገሩን ብስለት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመያዝ ሞክር። ለምሳሌ፣ ውጤት ለመስጠት የተጠቀመባቸውን መመዘኛዎች እንዲያስረዳህ አስተማሪህን ልትጠይቀው ትችላለህ። ሰለሞን “መልስ ከመስጠትህ በፊት አዳምጥ፤ አለበለዚያ ሞኝና የተናቅህ መሆንህን ታሳያለህ” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 18:13 የ1980 ትርጉም) አስተማሪህ የሚሰጥህን ማብራሪያ ከሰማህ በኋላ ስህተት ነው ብለህ የምታስበውን ነገር መግለጽ ትችላለህ። ውጤትህ ባይስተካከልም እንኳ አስተማሪህ ሁኔታውን ብስለት በሚንጸባረቅበት መንገድ መያዝህን ማድነቁ አይቀርም።
አስተማሪዬ ይጠላኛል። ሬቸል ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ሬቸል ምንጊዜም ከፍተኛ ውጤት ታገኝ ነበር። ሰባተኛ ክፍል ስትደርስ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ።
ሬቸል “ከአስተማሪዎቼ አንዱ እኔን ለመጣል የማያደርገው ነገር አልነበረም” ብላለች። ችግሩ ምን ነበር? አስተማሪው የሬቸልንም ሆነ የእናቷን ሃይማኖት እንደሚጠላው በግልጽ ይታይ ነበር።ታዲያ ሬቸል ምን አደረገች? እንዲህ ብላለች፦ “አስተማሪዬ ውጤቴን የሚያበላሸው እኛን በእምነታችን ስለሚጠላን እንደሆነ በሚሰማን ጊዜ እናቴ መጥታ ታነጋግረዋለች። ውሎ አድሮ ይህን ማድረጉን አቆመ።” አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠመህ ጉዳዩን ለወላጆችህ ከመናገር ወደኋላ አትበል። ወላጆችህ ለጉዳዩ መፍትሔ ለማግኘት ከአስተማሪህ እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸው አይቀርም።
ነገሮችን ሰፋ አድርገህ ተመልከት
እርግጥ ነው፣ ሁሉም ዓይነት ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ ያገኛሉ ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታውን ችሎ ከመኖር ሌላ አማራጭ አይኖርህ ይሆናል። ታንያ እንዲህ ብላለች፦ “አንደኛው አስተማሪያችን ለተማሪዎቹ ጥሩ አመለካከት አልነበረውም። ብዙውን ጊዜ ‘ደደቦች’ እያለ ይሰድበን ነበር። መጀመሪያ ላይ አስተማሪያችን ሲሰድበን አለቅስ ነበር፤ እያደር ግን ችግሩ ከእኔ ጋር ብቻ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ትምህርቴ ላይ ትኩረት ለማድረግ መጣር ጀመርኩ። በመሆኑም የሚናገረው ነገር ያን ያህል አይረብሸኝም፤ እንዲያውም በእሱ ትምህርት ጥሩ ውጤት ካመጡት ጥቂት ተማሪዎች መካከል አንዷ መሆን ቻልኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ አስተማሪው ተባረረ።”
አስቸጋሪ ከሆነ አስተማሪ ጋር እንዴት መስማማት እንደምትችል ማወቅህ ጥሩ ሥልጠና ይሰጥሃል፤ ወደፊት እንዲህ ያለ ባሕርይ ያለው አሠሪ ቢያጋጥምህ እንዴት ልትይዘው እንደሚገባ ታውቃለህ። ከዚህም በላይ ጥሩ አስተማሪዎች ሲገጥሙህ ይበልጥ ታደንቃቸዋለህ።
ጊዜህን ማብቃቃት አቅቶሃል? ከሆነ ጊዜህን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ማድረግ ትችላለህ?
ቁልፍ ጥቅስ
“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12
ጠቃሚ ምክር
አስተማሪህ የሚያስተምርበት መንገድ አሰልቺ ከሆነብህ በእሱ ላይ ሳይሆን በትምህርቱ ላይ ትኩረት ለማድረግ ሞክር። ማስታወሻ ያዝ፤ ጥያቄ ሲኖርህ በአክብሮት ጠይቅ፤ እንዲሁም ትምህርቱን በጉጉት ለመከታተል ጥረት አድርግ። አንተ ለትምህርቱ ያለህ ጉጉት ሌሎችም ተመሳሳይ ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ይህን ታውቅ ነበር?
አስተማሪህ አንድን የትምህርት ዓይነት ለተለያዩ ተማሪዎች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት አስተምሮ ይሆናል። ስለዚህ መጀመሪያ ሲያስተምር ያደርግ እንደነበረው ትምህርቱን በግለት ማቅረብ ፈታኝ ሊሆንበት ይችላል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
አንድ የትምህርት ዓይነት ቢደብረኝ ትምህርቱን መውደድ እንድችል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
አስተማሪዬ መድልዎ እንዳደረገብኝ ከተሰማኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● በአስተማሪው ላይ ሳይሆን በትምህርቱ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
● አንተ ስለ አንድ ትምህርት ያለህ አመለካከት አስተማሪህ ስለ አንተ ባለው አመለካከት ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?
[በገጽ 146 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ከሁሉም አስተማሪዎቼ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረኝ ለማድረግ እጥር ነበር። የሁሉንም ስም አውቃለሁ፤ መንገድ ላይ ሳገኛቸው ቆም ብዬ አዋራቸዋለሁ።”—ካርመን
[በገጽ 145 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስተማሪዎች፣ ውኃ ላይ እንዳሉ የመሸጋገሪያ ድንጋዮች ካለማወቅ ወደ ማወቅ እንድትሸጋገር ይረዱሃል፤ መሸጋገሪያውን መጠቀም ግን የአንተ ድርሻ ነው