አባቴና እናቴ የተለያዩት ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 4
አባቴና እናቴ የተለያዩት ለምንድን ነው?
“አባቴ ጥሎን የሄደበትን ቀን አስታውሳለሁ። ምን ችግር እንደተፈጠረ አላወቅንም ነበር። እናታችን ሥራ መሄድ ስላለባት ሁልጊዜ ብቻችንን ትታን ትሄዳለች። አንዳንድ ጊዜ በመስኮቱ አጠገብ ቁጭ ብለን እሷም ጥላን ሄዳ ይሆን? ብለን እናስባለን። . . .”—ወላጆቿ የተፋቱባት አንዲት ልጃገረድ የተናገረችው
የወላጆች መፋታት በልጆች ላይ ዘላለማዊ ችግር የሚያመጣ መዓትና የዓለም ፍጻሜ ሊመስል ይችላል። ይህ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ የኀፍረት፣ የንዴት፣ የጭንቀት፣ ፈላጊ የማጣት፣ የጥፋተኛነት፣ የትካዜና የጥቃት ስሜት፣ እንዲያውም የመበቀል ስሜት ሊያሳድር ይችላል።
ወላጆቻችሁ በቅርቡ ተለያይተው ከሆነ እናንተም እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቷችሁ ይሆናል። ለነገሩማ የፈጣሪያችን ዓላማም አባትና እናት ሁለቱም አንድ ላይ ሆነው እንዲያሳድጓችሁ ነበር። (ኤፌሶን 6:1–3) አሁን ግን ከምትወዷቸው ወላጆቻችሁ አንዱን በየዕለቱ የማየት መብት ተነፍጋችኋል። “አባቴን በእውነት አከብረውና ከእርሱም ጋር መሆን እፈልግ ነበር” በማለት የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ የተለያዩበት ፖል የተሰማውን ሐዘን ገልጿል። “እኛን የማሳደግ መብት የተሰጣት ግን እናታችን ናት።”
ወላጆች የሚለያዩበት ምክንያት
ወላጆች ብዙውን ጊዜ ችግራቸውን ደብቀው ይይዛሉ። ሕፃን ልጅ ሳለች ወላጆቿ የተፋቱባት ሊን “ወላጆቼ ሲጣሉ ያየሁበትን ጊዜ አላስታውስም” ትላለች። “ተስማምተው የሚኖሩ ይመስለኝ ነበር።” ወላጆች የሚጨቃጨቁ ቢሆንም እንኳን መለያየታቸው ዱብ ዕዳ ሊሆን ይችላል!
ብዙውን ጊዜ ለመለያየት ምክንያት የሚሆነው አንደኛው ወላጅ የፆታ ውስልትና በመፈጸም መበደሉ ነው። ንጹሕ የሆነው ማቴዎስ 19:9) ‘ቁጣ፣ ጩኸትና ስድብ’ ወደ መደባደብ በማምራቱ ምክንያት አንደኛው ወላጅና ልጆቹ አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመፍራት ምክንያት ወላጆች የሚለያዩበት ጊዜም አለ።— ኤፌሶን 4:31
የትዳር ጓደኛ ፍቺ እንዲያገኝ አምላክ ይፈቅዳል። (በእርግጥ አንዳንድ ፍቺዎች የሚፈጸሙት ደካማ በሆኑ ጥቃቅን ምክንያቶች ነው። አንዳንድ ባለትዳሮች ችግሮቻቸውን ለመፍታት በመ ጣር ፈንታ ‘አልተደሰትኩም’ ወይም ‘ፍቅሬ አልቋል’ በማለት በራስ ወዳድነት ይፋታሉ። ይህም “መፋታትን እጠላለሁ” ያለውን አምላክ ያሳዝነዋል። (ሚልክያስ 2:16) አንዳንዶች ደግሞ የትዳር ጓደኞቻቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ምክንያት ትዳራቸውን እንደሚያፈርሱ ኢየሱስ አመልክቷል።— ማቴዎስ 10:34–36
ያም ሆነ ይህ ወላጆቻችሁ የተፋቱበትን ምክንያት ላለመንገር ወይም አድበስብሰው ለማለፍ የመረጡት ስለማይወዷችሁ አይደለም። * ወላጆቻችሁ ፍቺው ባደረሰባቸው የስሜት ቁስል በመዋጣቸው ምክንያት ስለ ፍቺው መናገር ከባድ ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 24:10) የትዳራቸውን አለመሳካት መቀበል የሚያሳፍርና የሚያሸማቅቅ ሆኖባቸው ይሆናል።
ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?
ስለሚያሳስባችሁ ነገር ከወላጆቻችሁ ጋር ረጋ ብላችሁ ለመወያየት የምትችሉበትን አመቺ ጊዜ ለይታችሁ ለማወቅ ጣሩ። (ምሳሌ 25:11) በፍቺው ምክንያት ምን ያህል እንዳዘናችሁና ግራ እንደተጋባችሁ እንዲያውቁ አድርጉ። ምናልባት በቂ ማብራሪያ ይሰጧችሁ ይሆናል። ካልሆነም ተስፋ አትቁረጡ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሊገባቸው አይችልም ብሎ ያሰበውን ነገር ከመናገር ተቆጥቦ አልነበረምን? (ዮሐንስ 16:12) ታዲያ የእናንተ ወላጆችስ የግል ምሥጢር ሊኖራቸው መብት የላቸውምን?
በመጨረሻም የፍቺው ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ጠቡ የተፈጠረው በወላጆቻችሁ መካከል እንጂ ከእናንተ ጋር አለመሆኑን ተገንዘቡ! ዎለርስቴይን እና ኬሊ በ60 የተፋቱ ቤተሰቦች ላይ ባደረጉት ጥናት ባልና ሚስቱ ለፍቺው ምክንያት ያደረጉት ራሳቸውን፣ አሠሪዎቻቸውን፣ የቤተሰቦቻቸውን አባሎችና ጓደኞቻቸውን መሆኑን ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎቹ “አንዳቸውም እንኳን ልጆቻቸውን ምክንያት አላደረጉም” በማለት ገልጸዋል። ወላጆቻችሁ ለእናንተ ያላቸው ስሜት አልተለወጠም።
የጊዜ ፈዋሽነት
“ለመፈወስም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:3) አካላዊ ቁስልና የተሰበረ አጥንት ሙሉ በሙሉ ለመዳን ሳምንታት ወይም ወራት እንደሚፈጅ ሁሉ ስሜታዊ ቁስልም እስኪፈወስ ድረስ ጊዜ ይወስዳል።
የፍቺ ተመራማሪዎች የሆኑት ዎለርስቴይን እና ኬሊ “ፍቺው የሚያስከትለው ፍርሃት፣ ኀዘን፣ ፍቺው እውነት መፈጸሙን ለማመን ያለመቻልና የመደናገጥ ስሜት . . . ፍቺው ከተፈጸመ ከሁለት ዓመት በኋላ መደብዘዙን ወይም ጨርሶ መጥፋቱን” ደርሰውበታል። አንዳንድ ጠበብት እንዲህ ዓይነቶቹ የፍቺ መዘዞች ግፋ ቢል እስከ ሦስት ዓመት እንጂ ከዚያ በላይ እንደማይቆዩ ያምናሉ። ይህ ረዥም ጊዜ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ቢሆንም ሕይወታችሁ ተስተካክሎ ፈር ለመያዝ እንዲችል ብዙ መደረግ ያለበት ነገር አለ።
ከሁሉ በፊት በፍቺው ምክንያት የተፋለሰው የቤተሰቡ የተለመደ ዕለታዊ አኗኗር እንደገና መደራጀት አለበት። የወላጆቻችሁም ስሜት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ እስኪመለስ ጊዜ ይፈጃል። ለእናንተ አስፈላጊውን የስሜት ድጋፍ ሊሰጧችሁ የሚችሉት ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል። ሕይወታችሁ ወደ ወትሮው ሁኔታ መመለስ ሲጀምር ደህና ስሜት ሊሰማችሁ ይጀምራል።
ይሁን እንጂ ሰሎሞን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።” (መክብብ 7:10) ስለ ቀድሞው ኑሮ ማብሰልሰሉ አሁን ባላችሁ ኑሮ እንዳትደሰቱ ሊጋርድባችሁ ይችላል። ወላጆቻችሁ ከመፋታታቸው በፊት የቤተሰባችሁ ኑሮ ምን ይመስል ነበር? “ሁልጊዜ መጣላት፣ መጯጯህና መሰዳደብ ነበረ” በማለት አኔት ተናግራለች። በቤት ውስጥ ሰላም ያገኛችሁት ገና አሁን እንደሆነስ?
‘አስታርቃቸዋለሁ’
አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ስለማስታረቅ ያልማሉ። አንዳንዶቹማ ወላጆቻቸው ሌላ የትዳር ጓደኛ ካገቡ በኋላም እንኳን ሳይቀር ከእንዲህ ዓይነቱ ቅዠት አይላቀቁም!
ይሁን እንጂ ፍቺውን አለመቀበሉ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ምንም ያህል እንባ ብታፈሱ፣ ምንም ዓይነት ልመና ብታቀርቡና ማንኛውንም ዘዴ ብትጠቀሙ ወላጆቻችሁ እንደገና ላይታረቁ ይችላሉ። ስለዚህ የማይሆን ነገር በማብሰልሰል ራሳችሁን ለምን ታሠቃያላችሁ? (ምሳሌ 13:12) ሰሎሞን “እርግፍ አድርጎ ለመተው ጊዜ አለው” ብሏል። (መክብብ 3:6 አዓት ) ስለዚህ ያለውን እውነታና የፍቺውን እርግጠኝነት ተቀበሉ። ይህም በፍቺው ምክንያት የደረሰባችሁን ችግር ለማሸነፍ የሚረዳችሁ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው።
ከወላጆቻችሁ ጋር መስማማት
ወላጆቻችሁ በመፋታታቸው ምክንያት ሕይወታችሁን በማፋለሳቸው ብትናደዱ አይፈረድባችሁም። አንድ ወጣት በምሬት እንደገለጸው “ወላጆቼ ራስ ወዳዶች ነበሩ። በእውነቱ ከሆነ ስለ እኛና መፋታታቸው ስለሚያስከትልብን ውጤት አላሰቡም። ተሽቀዳድመው የራሳቸውን አሳብ ብቻ ፈጸሙ።” ይህ ትክክል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የንዴትንና የምሬትን ሸክም ይዛችሁ ራሳችሁን ሳትጎዱ በሕይወት መቀጠል ትችላላችሁን?
መጽሐፍ ቅዱስ “መራርነትና ንዴት . . . ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” በማለት ይመክራል። (ኤፌሶን 4:31, 32) በጣም ያስቀየማችሁን ሰው ይቅር ልትሉ የምትችሉት እንዴት ነው? ስለ ወላጆቻችሁ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራችሁ ጣሩ፤ የሚሳሳቱና ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች እንደሆኑ ተገንዘቡ። አዎን፣ ወላጆችም ሳይቀሩ ‘ኃጢአትን ሠርተዋል፣ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል።’ (ሮሜ 3:23) ይህን መገንዘባችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር እንድትስማሙ ሊረዳችሁ ይችላል።
ስሜታችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ
ቃለ መጠይቅ ያደረግንለት አንድ ወጣት “ስለ ወላጆቼ መፋታት የተሰማኝን ስሜት ተናግሬ አላውቅም” ብሏል። ወጣቱ መጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት የስሜት መረበሽ ያልታየበት ቢሆንም ስለወላጆቹ መፋታት መናገር ሲጀምር ስሜቱ ተረብሾ እስከ ማልቀስ ደረሰ። ረዘም ላለ ጊዜ አምቆ የያዘው ስሜቱ ገንፍሎ ወጣ። እርሱም በዚህ ሁኔታው በመገረም “ስሜቴን አውጥቼ መናገሬ በእርግጥ ረድቶኛል” በማለት እውነቱን ተናግሯል።
እናንተም ከሰው ከመራቅ ይልቅ ለአንድ ሰው ስሜታችሁን ገልጣችሁ ብትናገሩ ጠቃሚ ሆኖ ታገኙት ይሆናል። ለወላጆቻችሁም በመፋታታቸው ምን እንደሚሰማችሁ፣ ስጋታችሁንና የሚያስጨንቃችሁን ነገር አሳውቋቸው። (ከምሳሌ 23:26 ጋር አወዳድሩ።) በተጨማሪም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሊረዷችሁ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ኪት በፍቺ ከተበታተኑት ቤተሰቦቹ ምንም ያህል ድጋፍ አላገኘም ነበር። ሆኖም ከሌላ አቅጣጫ እርዳታ አግኝቷል። ኪት “የክርስቲያን ጉባኤ ቤተሰቤ ሆነልኝ” ብሏል።
ከሁሉ በላይ ‘ጸሎት ሰሚ’ በሆነው በሰማያዊው አባታችሁ ዘንድ ተደማጭነት ልታገኙ ትችላላችሁ። (መዝሙር 65:2) ፖል የተባለ ወጣት በወላጆቹ መፋታት ምክንያት የደረሰበትን የስሜት መረበሽ እንዲያሸንፍ የረዳው ምን እንደሆነ ሲናገር “በማንኛውም ጊዜ እጸልይና ይሖዋ በእርግጥ እውን የሆነ አካል እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” ብሏል።
የራሳችሁን ኑሮ መምራት
ወላጆች ከተፋቱ በኋላ ነገሮች እንደቀድሞው ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ሕይወታችሁ ፍሬያማና ደስተኛ ሊሆን አይችልም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ” በማለት ይመክራል። (ሮሜ 12:11) አዎን፣ በኀዘን፣ በቂም ወይም በንዴት ስሜት ተሳስራችሁ ከመቀመጥ ይልቅ ኑሯችሁን መምራት ጀምሩ! በትምህርት ቤት ሥራችሁ ተዋጡ። ትርፍ ጊዜያችሁን የምትደሰቱበትን ነገር በመሥራት አሳልፉ። “የጌታም ሥራ . . . የሚበዛላችሁ ሁኑ።”— 1 ቆሮንቶስ 15:58
ይህን ማድረግ ጥረት፣ ቆራጥነትና ጊዜ ይጠይቃል፤ ቢሆንም ቀስ በቀስ የወላጆቻችሁ ትዳር መፍረስ በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቅ ጉዳይ የማይሆንበት ጊዜ ይመጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.10 ዎለርስቴይን እና ኬሊ የተባሉ ተመራማሪዎች “ጥናት ከተደረገባቸው [ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው] ሕፃናት ልጆች ውስጥ ከአምስቱ እጅ አራቱ ስለሁኔታው በቂ ማብራሪያና የሚደረግላቸው እንክብካቤ እንደማያቋርጥባቸው ዋስትና አልተሰጣቸውም። አንድ ቀን ጧት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ከወላጆቻቸው አንዱ መሄዱን እንደተገነዘቡ” ደርሰውበታል።
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ወላጆች የሚለያዩባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
◻ ወላጆቻችሁ ስለተለያዩበት ምክንያት መናገር ከባድ ሊሆንባቸው የሚችለው ለምንድን ነው? ለመናገር የማይፈልጉ ከሆኑ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?
◻ ያለፈውን ነገር ማብሰልሰል ወይም ወላጆችን ለማስታረቅ ማለም ጥቅም የማይኖረው ለምንድን ነው?
◻ ፍቺው ያስከተለባችሁን ችግር ለመርሳት ልታደርጓቸው የምትችሏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ በወላጆቻችሁ ላይ የሚሰማችሁን የቁጣ ስሜት ልትቋቋሙ የምትችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 36, 37 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘የወላጆቼ መፋታት ሕይወቴን ያበላሽብኝ ይሆን?’
አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው በተፋቱ ማግስት የራሳቸውን ሕይወት ማበላሸት ይጀምራሉ። አንዳንዶቹ ትምህርታቸውን መተውን የመሰለ የችኩልነት ውሳኔ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ የተፋቱ ወላጆቻቸውን ለመበቀል በማሰብ ብስጭታቸውንና ንዴታቸውን ለመወጣት መጥፎ ድርጊት ይፈጽማሉ። ዴኒ እንዲህ ይላል:- “ወላጆቼ ከተፋቱ በኋላ በጣም ማዘንና መተከዝ ጀመርኩ። በትምህርት ቤትም ችግር ያጋጥመኝ ጀመር። አንድ ዓመትም ወደቅሁ። ከዚያ በኋላ . . . በክፍል ውስጥ ረባሽና ተደባዳቢ ሆንኩ።”
አስደንጋጭ ጠባይ ማሳየት የወላጆችን ትኩረት ይስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የተበላሸውን ሁኔታ ይበልጥ ከማባባስ በቀር ምን የሚፈይደው ነገር ይኖራል? በእርግጥም በመጥፎ ሥራው ቅጣት የሚደርስበት ድርጊቱን የፈጸመው ሰው ብቻ ነው። (ገላትያ 6:7) ወላጆቻችሁም እየተሠቃዩ መሆናቸውንና ችላ ያሏችሁ መስሎ ቢታያችሁም ለክፋት ብለው እንዳላደረጉት ለመረዳት ሞክሩ። የዴኒ እናት “ልጆቼን በእርግጥ ችላ ብያቸዋለሁ። ከፍቺው በኋላ እኔ ራሴ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ስለነበርኩ ልረዳቸው አልቻልኩም” በማለት ጥፋቷን አምናለች።
መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 12:13 ላይ “ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፣ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ” በማለት ይመክራል። የወላጅ ማሠልጠኛ የማይሰጣችሁ ቢሆንም እንኳን ይህ ምግባረ ብልሹ ለመሆን ሰበብ ሊሆናችሁ አይችልም። (ያዕቆብ 4:17) ራሳችሁ ለምታደርጉት ማንኛውም ድርጊት ኃላፊነት በመውሰድ ራሳችሁን በራሳችሁ ተቆጣጠሩ።— 1 ቆሮንቶስ 9:27
በተጨማሪም ከቤት መኮብለልን የመሰለ የችኮላ ውሳኔ ከማድረግ ተቆጠቡ። “ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።” (ምሳሌ 14:15) በዚህ ወቅት ወላጆቻችሁ ሐሳባቸው በመበታተኑ ምክንያት የእናንተን ችግር ለማዳመጥ የማይችሉ መስሎ ከታያችሁ ለምን ትልቅ ሰው ከሆነ ወዳጃችሁ ጋር ስለ ውሳኔያችሁ አትነጋገሩም?
ያም ሆኖ ስለ ወደፊቱ ሕይወታችሁ የሚያሳስቧችሁ በርካታ ነገሮች ይኖሩ ይሆናል። የወላጆቻችሁ ጋብቻ በመፍረሱ እናንተም ለወደፊቱ የተሳካ ጋብቻ ሊኖራችሁ የመቻሉ ጉዳይ ሊያስጨንቃችሁ እንደሚችል ለመረዳት አያዳግትም። ደስ የሚለው ነገር በጋብቻ አለመደሰት ከወላጆች የሚወረስ አለመሆኑ ነው። እናንተ ከማንኛውም ሰው የተለያችሁ ግለሰቦች በመሆናችሁ ወደፊት የምትፈጽሙት ጋብቻ
መሳካቱና አለመሳካቱ የሚመካው በወላጆቻችሁ ጋብቻ አለመሳካት ላይ ሳይሆን እናንተና የትዳር ጓደኛችሁ የአምላክን ቃል ሥራ ላይ በምታውሉበት መጠን ላይ ነው።ከዚህ በፊት ምንም ሳትጨነቁ ታገኟቸው የነበሩትን እንደ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ ገንዘብ የመሳሰሉ ነገሮች እንዴት እንደምታገኙ ትጨነቁ ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ከተፋቱ በኋላ እናት ሥራ ፈልጋ መቀጠር ቢኖርባትም እንኳን ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩበትን መንገድ ይተልማሉ። የሆነ ሆኖ ሰርቫይቪንግ ዘ ብሬክ አፕ የተባለው መጽሐፍ “ባንድ ወቅት አንድ ቤተሰብ ብቻ ያስተዳድር የነበረው ገቢ አሁን ሁለት ቤተሰብ ማስተዳደር ስላለበት እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ከነበረው የኑሮ ደረጃ ዝቅ እንዲል ያስገድደዋል” በማለት ያስጠነቅቃል።
ስለዚህ በፊት እንደልብ ታገኟቸው የነበሩትን አዲስ ልብስ እንደመግዛት ያሉትን ነገሮች ማጣትን መልመድ ይኖርባችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” በማለት ያሳስበናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) ምናልባት አዲስ የቤተሰብ ባጀት በማውጣት ረገድ ለመርዳት ትችሉ ይሆናል። በተጨማሪም ይሖዋ “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት” መሆኑንም አስታውሱ። (መዝሙር 68:5 የ1980 ትርጉም ) ስለሚያስፈልጓችሁ ነገሮች በጥልቅ እንደሚያስብ እርግጠኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ።
ነቢዩ ኤርምያስ “ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው” በማለት ተናግሯል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27) እርግጥ ወላጆች ሲለያዩ ማየት ጥሩ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ይህን መጥፎ አጋጣሚም እንኳን ወደሚጠቅም ሁኔታ መለወጥ ይቻላል።
በፍቺ ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱ ጁዲት ዎለርስታይን የተባሉ ሴት “በቤተሰብ መፍረስ ምክንያት የሚፋጠነው [ወላጆቻቸው በተፋቱባቸው ልጆች መካከል የሚታይ] የስሜትና የአእምሮ እድገት አስደናቂና አንዳንድ ጊዜም ስሜትን የሚነካ ነው። ወጣቶቹ . . . የወላጆቻቸውን ተሞክሮ በእርጋታ ካመዛዘኑ በኋላ ለራሳቸው የወደፊት ሕይወት የአስተዋይነት ውሳኔ ያደርጋሉ። ወላጆቻቸው የሠሩትን ስህተት የሚያስወግዱበትን መንገድ ስለመፈለግ አጥብቀው ያስባሉ” ብለዋል።
የወላጆቻችሁ መፋታት በሕይወታችሁ ላይ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ መሆኑ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ያ ምልክት እየለቀቀ የሚሄድ ጠባሳ ወይም የሚያመረቅዝ ቁስል መሆኑ በእጅጉ የሚመካው በእናንተው ላይ ነው።
[በገጽ 35 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሊያጋጥሙ ከሚችሉ መጥፎ ተሞክሮዎች ሁሉ የሚከፋው የወላጆቻችሁ ትዳር ሲፈርስ ማየት ነው
[በገጽ 38 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቻችሁ ከመፋታታቸው በፊት እንዴት ትኖሩ እንደነበረ ማብሰልሰሉ ከማስተከዝ በቀር ምንም አይጠቅማችሁም