‘ወላጆቼን ማክበር’ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 1
‘ወላጆቼን ማክበር’ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?
“አባትህንና እናትህን አክብር።” ይህ አባባል ለብዙ ወጣቶች ዘመን ያለፈበት፣ ለጨለማው ዘመን ብቻ የሚያገለግል ምክር ይመስላ ቸዋል።
ቬዳ የተባለች ወጣት አደንዛዥ ዕፅና ከአግባባ ውጭ የአልኮል መጠጥ ከሚወስድ ወጣት ጋር አብራ በመውጣት በአባቷ ፈቃድ ላይ በይፋ ዓመፀች። ይባስ ብላም ጎሕ እስኪቀድ ድረስ ከልጁ ጋር ስትደንስ ታድር ነበር። “አባቴ ከሚገባ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” በማለት ገለጸች። “ዕድሜዬ 18 ዓመት ስለሆነ ሁሉንም ነገር ያወቅሁ መስሎኝ ነበር። አባቴ ክፉ እንደሆነና እንድዝናና እንደማይፈልግ ስለ ተሰማኝ ብቻ አሻፈረኝ ብዬ በመሄድ የፈለግሁትን ነገር ሁሉ አደረግሁ።”
ብዙ ወጣቶች የቬዳን አድራጎት ይቃወሙ ይሆናል። ሆኖም የመኝታ ክፍላቸውን እንዲያጸዱ፣ የቤት ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ወይም በተወሰነ ሰዓት እቤት እንዲገቡ ወላጆቻቸው ሲያዟቸው ብዙዎቹ ይበሽቁ ይሆናል፣ ወይም ደግሞ ከዚያም አልፈው የወላጆቻቸውን ትእዛዝ በግልጽ ይጥሱ ይሆናል! ይሁንና አንድ ወጣት ለወላጆቹ ያለው አመለካከት በቤት ውስጥ ሰላም ወይም ጥል በማምጣት የሚያበቃ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አልፎ ተርፎ ሕይወቱን የሚነካ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ‘ወላጆቻችሁን እንድታከብሩ’ የሚጠይቀው ትእዛዝ የመጣው ከአምላክ ስለሆነ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” በማለት ይህን ትእዛዝ እንድታከብሩ የሚገፋፋችሁን ምክንያት አብሮ ሰጥቷል። (ኤፌሶን 6:2, 3) ይህን ትእዛዝ መታዘዝ የሚያመጣው ጥቅም ወይም አለመታዘዝ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ስለዚህ አባታችሁንና እናታችሁን ማክበር ማለት በእርግጥ ምን ማለት እንደሆነ እንደ አዲስ እንመርምር።
ወላጆችን ‘ማክበር’ ማለት ምን ማለት ነው?
“ማክበር” ሕጋዊ ሥልጣንን መቀበል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች “ንጉሥን አክብሩ” ተብለው ታዘዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ከአንድ ብሔራዊ መሪ ጋር የማትስማሙበት ነገር ቢኖርም ሥልጣኑ ወይም መንበሩ መከበር ይኖርበታል። በተመሳሳይም አምላክ ቤተሰብን ስለሚመለከቱ አንዳንድ ጉዳዮች ለወላጆች ሥልጣን ሰጥቷል። ስለዚህ ወላጆቻችሁ እናንተን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች አንዳንድ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን ከአምላክ እንደተሰጣቸው መገንዘብ አለባችሁ ማለት ነው። እርግጥ፣ የእናንተ ወላጆች ከሌሎቹ ወላጆች ይበልጥ ጥብቅ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ወላጆቻችሁ ከሁሉ ይበልጥ የሚበጃችሁን የመወሰን ግዴታ አለባቸው። በተጨማሪም ቤተሰቦች ባላቸው የአቋም ደረጃ ረገድ አንዳቸው ከሌላው የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ።
ከዚህም በላይ በጣም ጥሩ ናቸው የሚባሉ ወላጆች እንኳን ሚዛናዊነትና ፍትሕ የጎደላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በምሳሌ 7:1, 2 ላይ አንድ ጠቢብ ወላጅ “ልጄ ሆይ፣ . . . ትእዛዜን ጠብቅ [ጠብቂ] በሕይወትም ትኖራለህ [ትኖሪያለሽ]” ብሏል። የእናንተም ወላጆች የሚያወጡላችሁ ደንቦች ወይም ‘ትእዛዞች’ አብዛኛውን ጊዜ ለእናንተው ጥቅም ታስበው የተሰጡና የእውነተኛ ፍቅራቸውና አሳቢነታቸው መግለጫዎች ናቸው።
ለምሳሌ ያህል ጆን በቤታቸው አጠገብ በሚገኘው ባለ ስድስት ረድፍ መንገድ ላይ ሲሄድ ለእግረኞች በተወሰነው መንገድ ላይ ብቻ መሄድ እንዳለበት እናቱ ደጋግማ ትነግረው ነበር። አንድ ቀን የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሆኑ ሁለት ልጃገረዶች ለተሽከርካሪዎች በተወሰነው መንገድ አቋርጦ እንዲሻገር አደፋፈሩት። ጆን “ፈሪ!” እያሉ የሚስቁበትን ልጃገረዶች ከቁም ነገር ሳይቆጥር ለእግረኞች በተዘጋጀው ማቋረጫ መንገድ ተሻገረ። ጆን መንገዱን አቋርጦ ሳይጨርስ ሲጥጥ የሚል የጎማ ድምፅ ሰማ። ዞር ብሎ ሲመለከት ሁለቱ ልጃገረዶች በሚዘገንን ሁኔታ ተገጭተው ወደ አየር ሲወረወሩ አየ! ወላጆቻችሁን መታዘዛችሁና አለመታዘዛችሁ ይህን የመሰለ የሕይወትና የሞትን ያህል ልዩነት የሚያመጣ ውጤት ላያስከትልባችሁ ይችላል። ቢሆንም በማንኛውም ጊዜ ታዛዥ መሆናችሁ ጥቅም ያስገኝላችኋል።
በተጨማሪም ‘ወላጆቻችሁን ማክበር’ እርማት በሚሰጣችሁ ጊዜ ሳታኮርፉ ወይም ሳትበሳጩ እርማቱን መቀበል ማለትም ነው። ምሳሌ 15:5 እንደሚለው ‘የአባቱን ተግሣጽ የሚንቅ’ ሞኝ ብቻ ነው።
በመጨረሻም አክብሮት ማሳየት ለይስሙላ ብቻ አክብሮት በማሳየት ወይም እያጉረመረሙ በመታዘዝ ተወስኖ የሚቀር ነገር አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አክብር” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያ የግሪክኛ ቃል አንድን ሰው ትልቅ ግምት የሚሰጠው እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ማለት ነው። በመሆኑም ወላጆች ክቡር እንደሆኑ፣ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው እንደሆኑና ለእናንተም ውድ እንደሆኑ ተደርገው መታየት አለባቸው። ይህም ለእነርሱ ሞቅ ያለና የአድናቆት ስሜት ማሳደርን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ወጣቶች ለወላጆቻቸው ሞቅ ያለ የመውደድ ስሜት የላቸውም።
አስቸጋሪ ወላጆች ክብር ሊሰጣቸው ይገባልን?
ጂና የተባለች ወጣት “አባቴ ሰክሮ ስለሚገባ በወላጆቼ መካከል በሚነሳው ጭቅጭቅና መጯጯህ ምክንያት መተኛት አልችልም ነበር። አልጋዬ ላይ ሆኜ አለቅሳለሁ። እናቴ ትመታኝ ይሆናል ብዬ ስለምፈራ ምን እንደሚሰማኝ ልነግራቸው አልቻልኩም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አባትህን አክብር’ ይላል፤ እኔ ግን ላከብረው አልቻልኩም” ስትል ጽፋለች።
ምሳሌ 30:17) በተጨማሪም ምሳሌ 23:22 ‘የወለዷችሁ’ ወላጆቻችሁ እንደሆኑ ያሳስባችኋል። የወለዷችሁ መሆናቸው ብቻ እንኳን እንድታከብሯቸው የሚያስገድዳችሁ ምክንያት ነው። ባንድ ወቅት ወላጆቹን በጣም ያቃልል የነበረ ግሪጎሪ የሚባል ወጣት አሁን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “[እናቴ] ስላላስወረደችኝ ወይም ከወለደችኝ በኋላ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ስላልጣለችኝ ይሖዋ አምላክን በጣም አመሰግነዋለሁ። እኛን ስድስት ልጆችዋን ያሳደገችው ብቻዋን ባል ሳይኖራት ነው። ይህም ምን ያህል አስቸግሯት እንደነበረ አውቃለሁ።”
ሰካራሞች ወይም እርስ በርሳቸው የሚጨቃጨቁ፣ ግልፍተኛ ወይም በሥነ ምግባር ባለጌ የሆኑ ወላጆች በእርግጥ ክብር ሊሰጣቸው ይገባልን? አዎን፣ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆችን ‘በንቀት’ መመልከትን ያወግዛል። (ወላጆቻችሁ በአንዳንድ ሁኔታዎች ፍጹም ሆነው ባይገኙም ለእናንተ
ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ግሪጎሪ በመቀጠል ሲናገር “ባንድ ወቅት በቤት ውስጥ የነበረን ምግብ አንድ ጣሳ በቆሎና ጥቂት ጥራጥሬ ብቻ ነበር” ይላል። “እናቴ ይህንኑ ጥራጥሬ ለእኛ ለልጆችዋ አዘጋጅታ ሰጠችን፤ እርስዋ ግን ምንም አልበላችም። እኔ ጠግቤ ተኛሁ፣ እናቴ ግን ለምን እንዳልበላች አልገባኝም ነበር። አሁን ግን የራሴ ቤተሰቦች ያሉኝ በመሆኔ እናታችን ለእኛ ስትል ድርሻዋን ትታ እንደነበረ ለመገንዘብ ችያለሁ።” (አንድን ልጅ እስከ 18 ዓመት ዕድሜው ድረስ ለማሳደግ 66, 400 የአሜሪካ ዶላር እንደሚፈጅ አንድ ጥናት ያመለክታል።)በተጨማሪም አንድ ወላጅ ጥሩ ምሳሌ ስላልሆነ ብቻ የሚነግራችሁ ወይም የምትነግራችሁ ነገር ሁሉ ስህተት እንደማይሆን ተረዱ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ምግባረ ብልሹዎች ነበሩ። ሆኖም ኢየሱስ ለሕዝቡ “ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፣ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 23:1–3, 25, 26) ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ወላጆችም ላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይችልምን?
የቅሬታ ስሜቶችን መቋቋም
አንድ ወላጅ በከባድ ሁኔታ በሥልጣኑ ወይም በሥልጣኗ ያለ አግባብ የሚጠቀም ወይም የምትጠቀም መስሎ ቢሰማችሁ ምን ማድረግ አለባችሁ? * ረጋ በሉ። ማመፅም ሆነ እልከኛ መሆን ወይም የጥላቻ ስሜት ማሳየት ለምንም ነገር አይበጅም። (መክብብ 8:3, 4፤ ከመክብብ 10:4 ጋር አወዳድሩ።) አንዲት የ17 ዓመት ልጃገረድ ወላጆቿ በራሳቸው ጭቅጭቅ ብቻ በመጠመዳቸው ምክንያት ስለ እርስዋ ምንም ደንታ የሌላቸው መስሎ ስለታያት በወላጆችዋ ላይ ቅሬታ አደረባት። በእነርሱ ላይ የነበራት ቅሬታ እነርሱ ሊያስተምሯት ይጥሩ በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ላይም ቅር ወደመሰኘት አደረሳት። በእልህ ብቻ ተገፋፍታ የጾታ ብልግና ፈጸመች፣ አደንዛዥ ዕፆችንም መውሰድ ጀመረች። “ወላጆቼን የጎዳሁ መስሎኝ ነበር” ብላ በምሬት ገለጸች። ሆኖም እልከኛ በመሆን የጎዳችው ራሷን ብቻ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣ ለእልህ [ድርጊት] እንዳያታልልህ ተጠንቀቅ። . . . ጎጂ ወደ ሆነው ነገር እንዳትመለስ ተጠንቀቅ” በማለት ያስጠነቅቃል። (ኢዮብ 36:18–21 አዓት ) ወላጆች ለሚያሳዩት ማንኛውም መጥፎ ጠባይ ይሖዋ እንደሚጠይቃቸውና ስለሚፈጽሙትም ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ለይሖዋ መልስ እንደሚሰጡ ተገንዘቡ።— ቆላስይስ 3:25
ምሳሌ 19:11 “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል፣ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል” ይላል። አንዳንድ ጊዜ ወላጅ የፈጸመውን ጎጂ አድራጎት ይቅር ማለትና መርሳት የተሻለ ይሆናል። የወላጃችሁን ጉድለት ከመከታተል ይልቅ ጥሩዎቹን ባሕርያቱን ተመልከቱ። ለምሳሌ ያህል ዶዲ የምትባል ልጃገረድ ስሜት የሌላት እናትና ሰካራም የእንጀራ አባት ነበራት። የወላጆችዋን ድክመቶች መረዳቷ ምሬቷን እንዴት እንዳጠፋላት ተመልከቱ። እንዲህ ትላለች:- “እናቴ ፍቅር አሳይታን የማታውቀው ምናልባት ተጎሳቁላ ስላደገችና ፍቅር አግኝታ ስላላወቀች ሊሆን ይችላል። የእንጀራ አባቴ በማይሰክርበት ጊዜ ስለምናደርጋቸው ነገሮች ለማወቅ ይፈልጋል። የማይሰክርባቸው ጊዜያት ግን በጣም ጥቂት ናቸው። ሆኖም እህቴና እኔ ራሳችንን የምናስጠልልበት ቤትና የምንበላው ምግብ አጥተን አናውቅም።”
ደግነቱ አስቸጋሪ የሆኑ ወይም ልጆቻቸውን ችላ የሚሉ ወላጆች ጥቂቶች ናቸው። የእናንተም ወላጆች እንደሚያስቡላችሁና ጥሩ አርዓያ ሊሆኗችሁ እንደሚጥሩ እናምናለን። ያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ በእነርሱ ላይ ቅሬታ ይሰማችሁ ይሆናል። ሮጀር የተባለ አንድ ወጣት “አንዳንድ ጊዜ ከእናቴ ጋር ስለ አንድ ችግር ስወያይ የምነግራትን መረዳት ሲያቅታት እናደድና እርሷን ለማበሳጨት ስል በእልህ የሚያስከፋትን አንድ ነገር እናገራት ነበር። እርሷን የምበቀለው በዚህ መንገድ ነበር። ትቻት ከሄድኩ በኋላ ግን በጣም አዝናለሁ። እርሷም ብትሆን በዚህ ጠባዬ እንደማትደሰት አውቃለሁ” ብሏል።
አሳቢነት የጎደላቸው ቃላት ‘ሊወጉ’ እና ‘ሥቃይ ሊያስከትሉ’ ይችላሉ፤ ለችግራችሁ ግን ምንም ዓይነት መፍትሔ አያስገኙም። “የጠቢብ ምላስ ፈዋሽ ነው።” (ምሳሌ 12:18 አዓት፤ 15:1) ሮጀር “ከባድ ቢሆንብኝም ተመልሼ ሄጄ ይቅርታ እጠይቃታለሁ። ከዚያ በኋላ ስለችግሩ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ረጋ ብዬ እነጋገርና መፍትሔ እናገኝለታለን” ብሏል።
‘አባቴ የተናገረው ትክክል ነበር’
አንዳንድ ወጣቶች የወላጆቻቸውን መመሪያዎች በመቃወም ራሳቸውን ከጎዱና ወላጆቻቸውን ካስመረሩ በኋላ ወላጆቻቸው ትክክል እንደነበሩ የኋላ ኋላ ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል (በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችውን) ቬዳን እንመልከት። አንድ ቀን ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ሆና በመኪና ወጣች። ጓደኛዋ ማሪዋናና ቢራ ወስዶ ሞቅ ብሎት ነበር። በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ትበርር የነበረችው መኪና ከቁጥጥሩ ውጭ ሆና ከአንድ የመብራት ምሰሶ ጋር ተጋጨች። ቬዳ ግምባሯ ላይ በከባድ ሁኔታ ቆሰለች፤ ግን ከሞት ተረፈች። የወንድ ጓደኛዋ ግን ከአካባቢው ከመጥፋቱም ሌላ እሷን ለመርዳት ወደ ሆስፒታል ብቅ እንኳን አላለም።
“ወላጆቼ ሆስፒታል ሲደርሱ” ትላለች ቬዳ ጥፋቷን በማመን “አባቴ የተናገረው ሁሉ ትክክል እንደነበረና ቀድሞውኑም መስማት እንደነበረብኝ ነገርኳቸው። . . . ትልቅ ስህተት ሠርቻለሁ፤ አለመስማቴም ሕይወቴን ሊያሳጣኝ ተቃርቦ ነበር።” ከዚህ በኋላ ቬዳ ለወላጆቿ ባላት አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ አደረገች።
ምናልባት እናንተም አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ይገባችሁ ይሆናል። ‘ወላጆቻችሁን ማክበር’ በእርግጥ ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ወላጆችን ማክበር አዋቂነት ብቻ ሳይሆን በአምላክ ዓይንም ትክክለኛ የሆነ ነገር ነው። ሆኖም ለወላጆቻችሁ አክብሮት ለማሳየት ፈልጋችሁ ስሜታችሁን ያልተረዱላችሁ ቢመስላችሁ ወይም እገዳ ቢያበዙባችሁ ምን ታደርጋላችሁ? በእንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ሥር የሚደርስባችሁን ችግር እንዴት ልታሻሽሉ እንደምትችሉ እስቲ እንመርምር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.18 እዚህ ላይ ለመጥቀስ የፈለግነው ወጣቶቹ ከቤት ውጭ የባለሞያ እርዳታ ሊጠይቁ ስለሚያስፈልጋቸው በአካል ላይ ወይም በጾታ ረገድ ስለሚፈጸምባቸው ተገቢ ያልሆነ አድራጎት አይደለም።
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ወላጆችን ማክበር ምን ማለት ነው?
◻ ወላጆች ብዙ ሕጎችን የሚያወጡት ለምንድን ነው? እነዚህ ሕጎች ሊጠቅሟችሁ ይችላሉን?
◻ ወላጆቻችሁ በጠባያቸው ተነቃፊ ቢሆኑም ልታከብሯቸው ይገባችኋልን? ለምን?
◻ አልፎ አልፎ በወላጆቻችሁ ላይ የሚሰማችሁን ቅሬታ ልትቋቋሙ የምትችሉባቸው አንዳንድ ውጤታማ መንገዶች ምንድን ናቸው? አንዳንድ የሞኝነት መንገዶችስ ምንድን ናቸው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“አባቴ ክፉ እንደሆነና እንድደሰት እንደማይፈልግ ብቻ ስለተሰማኝ አሻፈረኝ ብዬ በመሄድ የፈለግሁትን ሁሉ አደረግሁ”
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የወላጆቻችሁን ሕጎች እንዴት መመልከት ይኖርባችኋል?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጠባያቸው ተነቃፊ የሆኑ ወላጆቻችሁን ማክበር አለባችሁን?