ምን ዓይነት የሥራ መስክ መምረጥ ይሻለኛል?
ምዕራፍ 22
ምን ዓይነት የሥራ መስክ መምረጥ ይሻለኛል?
ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ‘በቀረው የሕይወት ዘመኔ ምን ዓይነት ሥራ ልሥራ?’ የሚለው ፈታኝ ጥያቄ ይገጥማችኋል። ግራ የሚያጋቡ ብዙ ምርጫዎች ይቀርቡላችኋል። ከእነዚህም ውስጥ ሕክምና፣ የንግድ ሥራ፣ ኪነ ጥበብ፣ ትምህርት፣ የኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ምሕንድስና እና የእጅ ሥራ ይገኙበታል። ምናልባትም “እንደተሳካልኝ የምቆጥረው . . . ባደግሁበት ዓይነት ምቾት መኖር ከቻልኩ ነው” እንዳለው ወጣት ይሰማችሁ ይሆናል። ወይም እንደ አንዳንድ ወጣቶች በርካታ ገንዘብ ለማካበት ታልሙ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ቁሳዊ ሀብት ከማግኘት የተለየ የኑሮ መሳካት የሚለካበት መንገድ አለን? ማንኛውም ዓይነት ዓለማዊ ሥራ እውነተኛ እርካታ ሊያመጣላችሁ ይችላልን?
‘ምንም ፋይዳ የለውም’
ተንቀሳቃሽ ፊልሞች፣ ቴሌቪዥንና መጻሕፍት አንዳንድ ዓለማዊ ሥራዎችን የሚያጓጓ፣ የሚያስደስት፣ የሚያበላ! ብለው ይገልጿቸዋል። ይሁን እንጂ የሥራን መሰላል የሚወጣጡ ሰዎች የተሳካ ኑሮ ተብሎ ወደሚጠራው ደረጃ ለመድረስ የሚያስችል ታዋቂነት ለማግኘት ብዙውን ጊዜ የሞትና የሽረት ትግል እስከማድረግ ድረስ እርስ በርሳቸው መፎካከር አለባቸው። “ፈጣን እድገት በሚገኝባቸው የከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሥራ መስኮች ከተሰለፉ ወጣቶች” ብዙዎቹ “እርካታ እንደሌላቸው፣ እንደሚጨነቁ፣ ትካዜና ባዶነት እንደሚሰማቸው፣ ሰዎችን አለበቂ ምክንያት የመጠራጠር ችግር እንዳለባቸውና እንዲሁም መላ ሰውነታቸውን የሚያብሰከስክ ጤና ማጣት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ” በማለት ዶክተር ዳግላስ ላቢር ይገልጻሉ።
ከረዥም ጊዜ በፊት ንጉሡ ሰሎሞን ዓለማዊ ሀብት ማትረፍ ብቻውን ከንቱ መሆኑን አጋልጧል። ሰሎሞን ቁጥር ሥፍር በሌለው ሀብት ታግዞ አስገራሚ የሆኑ ሥራዎችን አከናውኗል። (መክብብ 2:4–10ን አንብቡ።) ሆኖም ሰሎሞን “ይህን ሁሉ ካደረግሁ በኋላ ያንን የሠራሁትን ነገር ሁሉ ምን ያህል እንደደከምኩበት ስመለከት ከቁጥር የማይገባ ዋጋቢስ መሆኑን ተረዳሁ፤ እንዲያውም ምንም የማይጠቅምና [“ምንም ፋይዳ የሌለው” ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን] ነፋስን እንደመጨበጥ የሚያስቆጥር ሆኖ አገኘሁት” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።— መክብብ 2:11 የ1980 ትርጉም
አንድ ሥራ ሀብትና ታዋቂነት ሊያስገኝ ቢችልም አንድ ሰው ‘የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ ነገሮች’ ሊያሟላ አይችልም። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) በመሆኑም ሕይወታቸውን ዓለማዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ብቻ የሚመሠርቱ ሰዎች እርካታ አያገኙም።
የሚያረካ ሥራ
ንጉሥ ሰሎሞን “እነሆ ሁሉ ነገር ተነግሮአል፤ የሁሉ ነገር መደምደሚያ ይህ ነው፣ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዙንም ጠብቅ፤ ምክንያቱም ይህ የሰው ዋና ተግባሩ ነው” በማለት ይመክራል። (መክብብ 12:13 የ1980 ትርጉም) በአሁኑ ጊዜም የክርስቲያኖች ዋና ተግባር የመንግሥቱን መልእክት መስበክ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በአምላክ ፊት ያለባቸውን ግዴታ አክብደው የሚመለከቱ ወጣቶች ደግሞ ለመስበክ የተፈጥሮ ዝንባሌ ባይኖራቸውም የቻሉትን ያህል በዚህ ሥራ ሙሉ ድርሻ እንዲኖራቸው ይገፋፋሉ። (ከ2 ቆሮንቶስ 5:14 ጋር አወዳድሩ።) በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ ዓለማዊ ሥራ በማሳደድ ፋንታ የሙሉ ጊዜ አቅኚ ወንጌላውያን ሆነው ማገልገልን መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ የትውልድ ቦታቸው ባልሆኑ አገሮች በሚስዮናዊነት ወይም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች ያገለግላሉ።
አቅኚ ለመሆን ብላ የነበራትን የሥራ አስኪያጅ ጸሐፊነት ሥራ የተወችው ኤሚሊ “ለዚህ ሥራ [ለአቅኚነት] እውነተኛ ፍቅር አድሮብኛል” ትላለች። አዎን፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሰው ሊያገኘው ከሚችለው ሁሉ የበለጠ አርኪና አስደሳች ሥራ ነው! አንድ ሰው ‘ከአምላክ ጋር አብሮ ሠራተኛ’ ከመሆን የበለጠ ምን መብት ሊያገኝ ይችላል?— 1 ቆሮንቶስ 3:9
የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጠቃሚ ነውን?
ብዙ አቅኚ አገልጋዮች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩት በትርፍ ሰዓት ሥራ ነው። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ቤተሰብ ማስተዳደር ቢያስፈልጋችሁስ? በእርግጥ አንድ ሰው የወጣትነት ዕድሜውን ለአምላክ አገልግሎት በማዋሉ ፈጽሞ አይጸጸትም! ሆኖም አንድ ወጣት መጀመሪያ
የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ቢይዝና ምናልባትም ከዚያ በኋላ አገልግሎቱን ቢሞክር አስተዋይነት አይሆንምን?እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወጣት ምን ያህል ዓመታት በትምህርት ላይ ማሳለፍ እንዳለበት ገደብ አያበጅም። ወይም ደግሞ ትምህርትን አያወግዝም። “ታላቅ አስተማሪ” የሆነው ይሖዋ ሕዝቦቹ በጥሩ ሁኔታ ማንበብና ሐሳባቸውን አሳክተው የመግለጽ ችሎታ እንዲኖራቸው ያበረታታል። (ኢሳይያስ 30:20 አዓት፤ መዝሙር 1:2፤ ዕብራውያን 5:12) ከዚህም በላይ ትምህርት ስለ ሕዝቦችና ስለምንኖርበት ዓለም ያለንን ግንዛቤ ሊያሰፋልን ይችላል።
ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ሁልጊዜ ያን ያህል ጊዜና ገንዘብ ሊፈስለት የሚገባ አስፈላጊ ነገር ነውን? * የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምሩቃን የሚበልጥ ደመወዝ እንደሚያገኙና በሥራ አጥነትም የእነርሱን ያህል እንደማይጠቁ የስታቲስቲክስ ዘገባዎች ቢያመለክቱም ፕላኒንግ ዩር ኮሌጅ ኤዱኬሽን የተሰኘው መጽሐፍ እነዚህ ስታቲስቲኮች አማካዩን ሁኔታ ብቻ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ያሳያል። በእርግጥ በጣም ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኙት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በቁጥር አነስተኛ ናቸው። የተቀሩት ዝቅተኛ ደመወዝ የሚያገኙ ናቸው። ከዚህም ሌላ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ምክንያት የተገኘ ነው ተብሎ የሚታሰበው ከፍተኛ ገቢ “ለየት ባለ ችሎታ፣ በሥራ ፍላጎት፣ ጥሩ የሥራ አጋጣሚ በማግኘት . . . ልዩ በሆነ ተሰጥኦና” በመሳሰሉት ምክንያቶች የተገኘ ሊሆን ይችላል።
“[የዩኒቨርሲቲ] ዲግሪ መያዝ በሥራ ዓለም ጥሩ ዕድል ለማግኘት ዋስትና መሆኑ ቀርቷል” ይላሉ የዩናይትድ ስቴትስ የሠራተኞች ሚኒስቴር። “በፕሮፌሽናል፣ በቴክኒክና በአስተዳደራዊ ሥራዎች የሚቀጠሩት [የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን] ቁጥር . . . እነዚህ ሥራዎች እያደገ የመጣውን የምሩቃን አቅርቦት ሊቀበሉ በሚያስችላቸው መጠን ባለማደጋቸው ምክንያት እየቀነሰ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ከ1970 እስከ 1984 ባሉት ዓመታት ወደ ሥራ ዓለም ከገቡት 5 የሚሆኑ [የዩኒቨርሲቲ] ምሩቃን አንዱ ያገኘው ሥራ ዲግሪ መያዝ የማይጠይቅ ነበር። ይህ የምሩቃን መብዛት እስከ 1990ዎቹ አጋማሽም የሚቀጥል ይመስላል።”
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች
የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ መያዛችሁ ሥራ የማግኘት አጋጣሚያችሁን ሊያሻሽለውም ኤፌሶን 5:16
ላያሻሽለውም ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ የማያሻማ ሐቅ አለ:- “የቀረው ጊዜ አጭር ነው”! (1 ቆሮንቶስ 7:29 አዓት) የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ያስገኛል የሚባለው ጥቅም በሙሉ ሲመዘን አራት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ዓመታት ለዚህ ዓይነቱ ትምህርት ማዋል ለቀረው ጊዜ ከሁሉ የተሻለ አጠቃቀም ሊሆን ይችላልን?—የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ወደ መንፈሳዊ ግቦቻችሁ ለመድረስ የምታደርጉትን ጥረት ያፋጥንላችኋል ወይስ ከግባችሁ ያርቃችኋል? ከፍተኛ ገቢ ማግኘት አንድ ክርስቲያን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚያስፈልግ ነገር እንዳልሆነ አስታውሱ። (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) ሆኖም የዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲ አስተዳዳሪዎች ያደረጉት ጥናት የአሁኑን ጊዜ ተማሪዎች ‘በሥራ መስካቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚፈልጉ፣ ቁሳዊ ሀብት በማካበት ረገድ የተሳካላቸው መሆናቸው የሚያሳስባቸው፣ ስለ ራሳቸው ብቻ የሚጨነቁ ናቸው’ በማለት ገልጿቸዋል። አንድ የተማሪዎች ቡድን ሲናገር “ገንዘብ። የምንነጋገረው ሁሉ ስለ ገንዘብ ብቻ ይመስላል” ብሏል። የጋለ ፉክክርና ራስ ወዳድነት የተቆራኘው ፍቅረ ንዋይ በሰፈነበት አካባቢ መዘፈቅ እናንተን እንዴት የሚነካችሁ ይመስላችኋል?
ዩኒቨርሲቲዎች በ1960ዎቹ ዓመታት የነበረው ዓይነት ረብሻ የሚታይባቸው ቦታዎች ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲ ረብሻ መቀነሱ በግቢው ውስጥ ያለው መንፈስ ጤናማ ነው ማለት አይደለም። በዩኒቨርሲቲ ግቢ ኑሮ ላይ የተደረገ አንድ ጥናት “አሁንም ቢሆን ተማሪዎች በግልም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች ገደብ የሌለው ነፃነት አላቸው ሊባል ይቻላል” ብሏል። አደንዛዥ ዕፆችና የአልኮል መጠጦች ያለአንዳች ቁጥጥር ይወሰዳሉ። ዝሙትም እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁሉም የሚፈጽመው ነገር ሆኗል። በአገራችሁ ያለው የዩኒቨርሲቲ ሁኔታ እንዲህ ከሆነ በዩኒቨርሲቲ መኖራችሁ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ለመቆየት የምታደርጉትን ጥረት ሊያጨናግፍባችሁ አይችልምን?— 1 ቆሮንቶስ 6:18
ሌላው አሳሳቢ ነገር ለከፍተኛ ትምህርት መጋለጥ “ሃይማኖታዊ ትምህርት ለያዛቸው ፍሬ ነገሮች የሚሰጠው ግምት” ከመቀነሱ ጋር ያለው በማስረጃ የተረጋገጠ ግንኙነት ነው። (ዘ ሴክረድ ኢን ኤ ሴኩላር ኤጅ) አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ከፍተኛ ማርክ ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት የሚያስከትልባቸው የሥራ ጫና መንፈሳዊ ጉዳዮችን ችላ እንዲሉና ብሎም በዩኒቨርሲቲዎች ለሚስፋፋው ዓለማዊ አስተሳሰብ ኃይለኛ ጥቃት የተጋለጡ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አንዳንዶች በእምነታቸው ቆላስይስ 2:8
ረገድ የመርከብ መስጠም አደጋ ደርሶባቸዋል።—በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ምትክ ሊወሰዱ የሚችሉ አማራጮች
ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች እነዚህን የተመለከትናቸውን ሁኔታዎች በማገናዘብ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አያስፈልገንም ብለው ወስነዋል። ብዙዎቹ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠው ሥልጠና፣ በተለይም ሳምንታዊው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሥራ በማግኘት ረገድ ከሌሎች ወጣቶች የበለጠ አጋጣሚ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተገንዝበዋል። እነዚህ ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ባይኖራቸውም የተረጋጋ መንፈስ፣ ሐሳባቸውን የመግለጽ ችሎታና ከፍ ያለ ኃላፊነት የመሸከም ብቃት እንዲኖራቸው ሰልጥነዋል። በተጨማሪም አንዳንዶቹ ገና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ የመኪና ጽሕፈት፣ የኮምፒዩተር ፕሮግራም አሠራር፣ የመኪና ጥገና፣ የማሽን ሾፕ ሥራና የመሳሰሉትን ትምህርቶች ይማራሉ። እንዲህ ያሉት ችሎታዎች የትርፍ ሰዓት ሥራ ለማግኘት የሚያመቹና ብዙውን ጊዜም ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ናቸው። ብዙ ወጣቶች ‘በእጃቸው መሥራትን’ በንቀት የሚመለከቱ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‘በትጋት ለመሥራት’ ከፍተኛ አክብሮት ይሰጣል። (ኤፌሶን 4:28፤ ከምሳሌ 22:29 አዓት ጋር አወዳድሩ።) ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱም እንኳን “ጸራቢው” ተብሎ ለመጠራት ያበቃው የእጅ ሥራ ተምሮ ነበር!— ማርቆስ 6:3
እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ አገሮች የሥራው ዓለም በዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ከመጥለቅለቁ የተነሳ ያለ አንድ ዓይነት ተጨማሪ የሥራ ሥልጠና ተራ ሥራ እንኳን ማግኘት ከባድ ሆኗል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የሥራ ልምምድ ፕሮግራሞች፣ የሞያ ወይም የቴክኒክ ትምህርት ቤቶችና ሥራ ሊያስገኙ የሚችሉ ሙያዎችን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ክፍያ የሚያስተምሩ የአጭር ጊዜ የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ፕሮግራሞች አሉ። በተጨማሪም የሥራ ስታቲስቲኮች ከግምት የማያስገቡት አንድ ነገር አለ። ይኸውም ለመንፈሳዊ ፍላጎቶች ቅድሚያ ለሚሰጡ ሰዎች አምላክ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያቀርብላቸው ተስፋ የሰጠ መሆኑን ፈጽሞ አትርሱ።— ማቴዎስ 6:33
የሥራ አጋጣሚዎችና ሥርዓተ ትምህርቶች ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። ወጣቶች የተለያዩ ችሎታዎችና ዝንባሌዎች አሏቸው። በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሥራ መሠማራት ጠቃሚ መሆኑ ቢገለጽም በግል ምርጫ የሚወሰን ጉዳይ ነው። በመሆኑም ምን ያህል ትምህርት እንደሚያስፈልጋችሁ በመወሰን ረገድ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸውን ነገሮች ሁሉ እናንተና ወላጆቻችሁ በጥንቃቄ መመዘን አለባችሁ። እንዲህ ዓይነቱን ገላትያ 6:5
ውሳኔ በማድረግ ረገድ ‘እያንዳንዱ የራሱን ሸክም መሸከም አለበት።’—ለምሳሌ ያህል ወላጆቻችሁ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መከታተል አለባችሁ ብለው ቢያስገድዷችሁ በእነርሱ ቁጥጥር ሥር የምትኖሩ እስከሆናችሁ ድረስ ከመታዘዝ በቀር ምንም ምርጫ አይኖራችሁም። * (ኤፌሶን 6:1–3) ምናልባትም እቤታችሁ እያደራችሁ ልትማሩና በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በሚካሄደው መጥፎ አካሄድ ከመለከፍ ራሳችሁን ልትጠብቁ ትችሉ ይሆናል። በትምህርት አመራረጣችሁ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ። ለምሳሌ ዓለማዊ ፍልስፍናዎችን ከመማር ይልቅ አንዳንድ ሞያዎችን በመማር ላይ አተኩሩ። ጓደኛ አድርጋችሁ ስለምትመርጧቸው ወጣቶችም ጥንቃቄ አድርጉ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በስብሰባዎች አዘውትራችሁ በመገኘት፣ በመስክ አገልግሎትና በግል ጥናት አማካኝነት ራሳችሁን በመንፈሳዊ ጠንካሮች አድርጋችሁ ጠብቁ። እንዲያውም የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲከታተሉ የተገደዱ አንዳንድ ወጣቶች አቅኚ ሆነው ለማገልገል የሚያስችሏቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች በመምረጥ አቅኚ ለመሆን ችለዋል።
የምትሠማሩበት የሥራ መስክ የግል ደስታ ብቻ ሳይሆን ‘በሰማይ መዝገብ ለማከማቸት’ የሚያስችላችሁ እንዲሆን በጥንቃቄና በጸሎት ምረጡ።— ማቴዎስ 6:20
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.15 በዩናይትድ ስቴትስ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት የሚወጣው ወጪ በአንድ ዓመት በአማካይ ከ10,000 ዶላር ይበልጣል! ተማሪዎቹ ብዙውን ጊዜ ዕዳቸውን ከፍለው ለመጨረስ ብዙ ዓመታት ይፈጅባቸዋል።
^ አን.26 ወላጆቻችሁን ለማስደሰት የአራት ዓመት ትምህርት የሚያስፈልገው ዲግሪ ማግኘት የግድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ በብዙ ፕሮፌሽናልና አገልግሎት ነክ መስኮች ተቀባይነት ያለውና በሁለት ዓመት ሊገኝ የሚችል ተጓዳኝ ዲግሪ የሚባል ዲግሪ አለ።
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ዓለማዊ ሥራዎች ብዙውን ጊዜ የግል ደስታ ሊያስገኙ የማይችሉት ለምንድን ነው?
◻ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት የሥራ መስክ ስለመሠማራት ሊያስቡ የሚገባቸው ለምንድን ነው?
◻ ከፍተኛ ትምህርት ያስገኛል ከሚባሉት ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ይህስ አባባል ሁልጊዜ እውነት ነውን?
◻ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ምን አደጋዎች ሊያመጣ ይችላል?
◻ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ፈንታ አንድ ወጣት ሊያስብባቸው የሚችል ምን አማራጮች አሉ?
[በገጽ 175 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ ሥራ ሀብትና ታዋቂነት ሊያስገኝ ቢችልም እንኳን አንድ ሰው ‘የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ ነገሮች’ ሊያሟላ አይችልም
[በገጽ 177 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሥራ ዓለም ጥሩ ዕድል ለማግኘት [የዩኒቨርሲቲ] ዲግሪ መያዝ ዋስትና መሆኑ ቀርቷል”