ትምህርቴን ማቋረጥ ይኖርብኛልን?
ምዕራፍ 17
ትምህርቴን ማቋረጥ ይኖርብኛልን?
ጃክ ከ25 ዓመታት በላይ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የስም ጥሪ ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል። ስለዚህ አለፈቃድ ከትምህርት ቤት የቀረ ወጣት ስለቀረበት ምክንያት ጃክ ሰምቶት የማያውቀው ሰበብ ለማቅረብ አይችልም ነበር። “ልጆቹ ‘የሚያመኝ መስሎኝ ነበር’ . . . ‘አላስካ የሚኖረው አያቴ ሞቶ ነበር’ የሚሉና የመሳሰሉትን ምክንያቶች ሁሉ ሲነግሩኝ ኖረዋል” ይላል። ታዲያ ከሁሉ በላይ ጃክን ያስደነቀው ሰበብ የቱ ይሆን? ሦስት ልጆች “በጣም ጭጋጋማ ቀን በመሆኑ ትምህርት ቤቱን ለማግኘት አልቻልንም” በማለት የነገሩት ምክንያት ነበር።
እነዚህ አሳፋሪ የሆኑ ተልካሻ ሰበቦች ብዙ ወጣቶች ለትምህርት ቤት ያላቸውን ጥላቻ የሚያሳዩ ሲሆኑ የጥላቻቸው ደረጃም ከግዴለሽነት (“ደህና ነው፣ አይከፋም ብዬ እገምታለሁ” ከማለት) እስከ መራራ ጥላቻ (“ግም የሆነ ትምህርት ቤት! በጣም ያስጠላኛል” እስከ ማለት) ይለያያል። ለምሳሌ ያህል ጋሪ ትምህርት ቤት ለመሄድ ሲነሳ ወዲያውኑ ሆዱን ያመዋል። እንዲህ ይላል፦ “ገና ወደ ትምህርት ቤቱ ስቃረብ በጣም ያልበኛል፣ ጭንቅ ጭንቅ ይለኛል። . . . ወደ ቤቴ ለመመለስ እገደዳለሁ።” በተመሳሳይ ብዙ ወጣቶች ትምህርት ቤትን ከልክ በላይ በመፍራት ይሠቃያሉ። ሐኪሞች ይህን ፍርሃት ስኩል ፎቢያ ብለው ይጠሩታል። አብዛኛውን ጊዜ ለትምህርት ቤት ፍርሃት ምክንያት የሚሆነው በትምህርት ቤት የሚፈጸመው ዓመፅ፣ የእኩዮች ጭካኔና ጥሩ ውጤት እንዲያገኙ የሚደረግባቸው ግፊት ነው። እንደዚህ ያሉት ወጣቶች (በወላጆቻቸው ተገፋፍተው) ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፤ ይሁን እንጂ የማያቋርጥ የመረበሽ ስሜት፣ አልፎ ተርፎም አካላዊ ጭንቀት ያሠቃያቸዋል።
ቁጥራቸው በጣም ከፍተኛ የሆኑ ወጣቶች እስከነጭራሹ ትምህርት ቤት ባይሄዱ የሚመርጡ መሆናቸው አያስደንቅም። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሁለት ሚልዮን ተኩል የሚያህሉ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየቀኑ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ! በኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚገልጸው በኒው ዮርክ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ
በጣም ብዙ ተማሪዎች (አንድ ሦስተኛ ያህሉ) “ልማደኛ ቀሪዎች” ከመሆናቸው የተነሳ “እነርሱን ማስተማር አይቻልም ለማለት የሚያስደፍር ሆኗል።”ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ከዚህም የባሰ ከባድ እርምጃ ወስደዋል። ዋልተር የሚባል ወጣት ሲናገር “ትምህርት ቤት በጣም አሰልቺና ጥብቅ ቁጥጥር ያለበት ነው” ብሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ትቶ ወጣ። አንቶኒያ የተባለች ልጃገረድም እንዲሁ አድርጋለች። የትምህርት ቤት ሥራዋን ማከናወን አዳጋች ሆኖባት ነበር። “የማነበውን ካልተረዳሁት እንዴት ልሠራው እችላለሁ?” ብላ ጠይቃለች። “እዚያ ተጎልቼ የባሰ እየደደብኩ እንደምሄድ ስለ ተሰማኝ ጥዬ ወጣሁ።”
በዓለም ዙሪያ ያሉት የትምህርት ቤት ሥርዓቶች በከባድ ችግሮች በመዋጥ ላይ መሆናቸው አይካድም። ታዲያ እንዲህ መሆኑ የትምህርት ፍላጎታችንን አጥተን ትተን እንድንወጣ ለማድረግ የሚያበቃ በቂ ምክንያት ነውን? ትምህርታችሁን ትታችሁ መውጣታችሁ የኋላ ኋላ በሕይወታችሁ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል? ትምህርታችሁን እስከምትጨርሱ ድረስ በትምህርት ቤት ለመቆየት የምትችሉባቸው በቂ ምክንያቶች አሉን?
የመማር ጥቅም
ማይክል ከሁለተኛ ደረጃ መመረቂያ ጋር እኩል የሆነ ዲፕሎማ ለማግኘት ወደ ትምህርት ቤት ተመልሷል። ለምን ወደ ትምህርት ቤት እንደተመለሰ ሲጠየቅ “ትምህርት እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ” ብሏል። ይሁን እንጂ “ትምህርት” ምንድን ነው? ብዙ አስደናቂ እውቀቶችን በቃል ለመውጣት መቻል ነውን? የጡቦች ክምር ብቻውን ቤት ሊሆን እንደማይችል ሁሉ እውቀት መሰብሰብ ብቻውን ትምህርት ማግኘት አይሆንም።
ትምህርት ስታድጉ የተሳካ ኑሮ እንድትኖሩ ያስችላችኋል። ለ18 ዓመታት የአንድ ትምህርት ቤት ዲን ሆነው ያገለገሉት አለን ኦስቲል “ትምህርት እንዴት ማሰብ እንዳለባችሁ፣ ችግሮችን እንዴት እንደምትፈቱ፣ ምክንያታዊ የሆነውንና ያልሆነውን ነገር እንዴት እንደምትለዩ፣ በግልጽ የማሰብን መሠረታዊ ችሎታ፣ የመረጃዎች ስብስብ ምን እንደሆነ ማወቅንና በአንድ ነገር ክፍልና በሙሉው መካከል ያለውን ግንኙነት ለማወቅ ያስችላል። እነዚህን ነገሮች ማመዛዘንና ለመለየት መቻልን፣ የመማር ዘዴን ያስተምራል” ሲሉ ትምህርት ስለሚሰጠው ጥቅም ተናግረዋል።
ምሳሌ 1:1–4 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ የእውቀት (የተሞክሮ) ጉድለት ከወጣትነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ትምህርት ቤት የማሰብ ችሎታችሁን እንድታሳድጉና እንድትኮተኩቱ ሊረዳችሁ ይችላል። ይህም የተማሩትን በቃል ለመድገም መቻል ብቻ ሳይሆን የተሰጠውን ትምህርት ለማመዛዘንና ከእርሱም ውጤታማ የሆኑ ሐሳቦችን ለማፍለቅ መቻል ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች የአንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ትምህርት አሰጣጥ ቢነቅፉም ትምህርት በእርግጥ በአእምሯችሁ እንድትጠቀሙ ያስገድዳችኋል። እውነት ነው፣ የጂኦሜትሪ ጥያቄዎችን መሥራት ወይም የታሪክ ዓመታትን መሸምደድ ለወደፊቱ ኑሯችሁ የሚኖረው አስፈላጊነት ለጊዜው አይታያችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ባርባራ ሜዬር ዘ ሃይ ስኩል ሰርቫይቫል ጋይድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንዳሠፈሩት “ሁሉም ተማሪዎች መምህራን በፈተና ላይ ሊያመጧቸው የሚፈልጓቸውን ፍሬ ነገሮችና ጥቃቅን እውቀቶች ላያስታውሱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የአጠናንና የዕቅድ አወጣጥ ዘዴዎችን የመሰሉት ጥሩ ችሎታዎች ፈጽሞ አይረሱም።”
ታዲያ በዚህ ረገድ ትምህርት ቤት ምን ቦታ ይኖረዋል? ንጉሥ ሰሎሞን ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት “ዕውቀት የጎደላቸው ሰዎች ማስተዋልን፣ ወጣቶችም ዕውቀትን እንዲያገኙ” ምሳሌ ጽፎ ነበር። (ትምህርት የሚያመጣቸው ዘላቂ ውጤቶችን ያጠኑ ሦስት ፕሮፌሰሮችም በተመሳሳይ “ሰፋ ያለ ትምህርት ያላቸው ሰዎች በመጻሕፍት ላይ የሰፈሩ ደረቅ መረጃዎችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው ያለውን ዓለም በስፋትና በጥልቀት ለማወቅ፣ እውቀት ለመሻትና ከመረጃ ምንጮች ጋር ለመላመድ ቀና ይሆንላቸዋል። . . . እነዚህ ልዩነቶች በእርጅናና ለብዙ ዓመታት ከትምህርት በመገለል ሊጠፉ አለመቻላቸው ተደርሶበታል” በማለት ደምድመዋል። — ዘ ኢንድዩሪንግ ኢፌክትስ ኦቭ ኤዱኬሽን
ከሁሉ በላይ ደግሞ ትምህርት ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችሁን እንድትወጡ ያዘጋጃችኋል። ጥሩ የአጠናን ልማድ ካዳበራችሁና የተጣራ የንባብ ችሎታ ካላችሁ የአምላክን ቃል በቀላሉ ልታጠኑ ትችላላችሁ። (መዝሙር 1:2) በትምህርት ቤት ሳላችሁ ሐሳባችሁን እንዴት እንደምትገልጹ ከተማራችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ሰዎች በቀላሉ ልታስተምሩ ትችላላችሁ። የታሪክ፣ የጂኦግራፊና የሒሳብ እውቀት የተለያየ አስተዳደግ፣ ፍላጎትና እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ለመነጋገር ይረዳችኋል።
ትምህርትና ሥራ
ትምህርት ወደፊት በሚኖራችሁ ሥራ የማግኘት አጋጣሚ ላይም ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። እንዴት?
ምሳሌ 22:29) ዛሬም ቢሆን ያው ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የሥራ ሚኒስቴር ባልደረባ የሆኑት ኧርነስት ግሪን “ችሎታ ከሌላችሁ በብዙ ነገሮች ወደ ኋላ ትቀራላችሁ” ብለዋል።
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ጥሩ ችሎታ ስላለው ሠራተኛ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “በነገሥታት ፊት ይቆማል፤ በተዋረዱም ሰዎች ፊት አይቆምም።” (እንግዲያውስ ትምህርታቸውን ለሚያቋርጡ ወጣቶች ሥራ የማግኘት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። ዋልተር (ቀደም ሲል የጠቀስነው ተማሪ) ይህን የተገነዘበው ችግሩ ከደረሰበት በኋላ ነው። “ብዙ ጊዜ ሥራ ለመቀጠር ማመልከቻ አቅርቤ ዲፕሎማ ስላልነበረኝ ላገኝ አልቻልኩም።” በተጨማሪም “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የማልረዳቸውን ቃላት ሲናገሩ ስሰማ ምንም የማላውቅ ደደብ እንደሆንኩ ይሰማኛል” በማለት ሳይደብቅ ተናግሯል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው ከወጡት ከ16 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ወጣቶች መካከል ሥራ የሌላቸው ቁጥር “ትምህርታቸውን ከጨረሱት እኩዮቻቸው እጥፍ ሲሆን ከጠቅላላው የሥራ አጦች ቁጥር ጋር ሲወዳደር ደግሞ ሦስት እጥፍ ያህል ነው።” (ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ) “ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች የዕድላቸውን በር ይዘጋሉ” በማለት ደራሲው ኤፍ ፊሊፕ ራይስ ዘ አዶለሰንት በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ አክለዋል። ትምህርቱን ያቋረጠ ሰው በጣም ቀላል የሆነ ሥራ የሚጠይቀውን መሠረታዊ ችሎታ ጠንቅቆ ላያውቅ ይችላል።
ፖል ኮፐርማን ዘ ሊተረሲ ሆክስ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “የወጥ ቤትነት ሥራ ለመሥራት በግምት የሰባተኛ ክፍል የንባብ ችሎታ፣ የመካኒክነት ሥራ ለመሥራት የስምንተኛ ክፍል ደረጃ፣ የዕቃ ሻጭነት ሥራ ለመሥራት ደግሞ የዘጠነኛ ወይም የአሥረኛ ክፍል ደረጃ እንደሚያስፈልግ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት ያመለክታል።” ቀጥለውም “የአስተማሪነት፣ የነርስነት፣ የሒሳብ ሠራተኛነት ወይም የመሐንዲስነት ሥራ ከዚህ በጣም ከፍ ያለ የንባብ ችሎታ የሚጠይቅ መሆኑ ምክንያታዊ እንደሆነ አምናለሁ” ብለዋል።
እንግዲያውስ ንባብን የመሳሰሉትን መሠረታዊ ችሎታዎች ለመማር በእርግጥ ጥረት የሚያደርጉ ተማሪዎች በጣም የተሻለ የሥራ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ይሁን እንጂ ትምህርት ቤት ገብታችሁ ከመማር ሊገኝ የሚችል ሌላው የዕድሜ ልክ ጥቅም ምንድን ነው?
የተሻላችሁ ሰዎች መሆን
ይህ የዕድሜ ልክ ጥቅም ጥንካሬያችሁንና ድክመታችሁን ማወቅ ነው። በኮምፒዩተር መስክ በቅርቡ ሥራ የያዘችው ሚሼል “ትምህርት ቤት ሳለሁ እንዴት ውጥረት ባለበት ሁኔታ መሥራት እንደሚቻል፣ እንዴት ፈተና እንደምፈተንና ሐሳቤን እንዴት መግለጽ እንደምችል ተምሬያለሁ” ብላለች።
‘ትምህርት ቤት የነገሮችን አለመሳካት እንዴት መመልከት እንደሚኖርብኝ አስተምሮኛል’ ትላለች ሌላዋ ወጣት። ለሚያጋጥማት መሰናክል ምክንያቱ ራሷ ሳትሆን ሌሎች እንደሆኑ አድርጋ የመመልከት ዝንባሌ ነበራት። ሌሎች ደግሞ ሥነ ሥርዓት አክባሪነትን ከሚጠይቀው የትምህርት ቤት ሥራ ጥቅም አግኝተዋል። ብዙ ሰዎች ይህ ሥርዓት አክባሪ የመሆን ግዴታ የወጣቶችን አእምሮ ያስጨንቃል በማለት ትምህርት ቤቶችን ይነቅፋሉ። ሆኖም ወጣቶች ‘ጥበብንና ተግሣጽን እንዲያውቁ’ ሰሎሞን አበረታቷቸዋል። (ምሳሌ 1:2) ሥነ ሥርዓት የማስከበር ቁጥጥር የሚበዛባቸው ትምህርት ቤቶች ብዙ የታረሙና የፈጠራ ችሎታ ያላቸው አእምሮዎችን አፍርተዋል።
በዚህ ምክንያት በትምህርት ቤት የምታሳልፏቸውን ዓመታት ሙሉ በሙሉ ብትጠቀሙባቸው አስተዋይነት ይሆናል። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? እስቲ በትምህርት ቤት ሥራችሁ እንጀምር።
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ብዙ ወጣቶች ስለ ትምህርት ቤት አፍራሽ አመለካከት ያላቸው ለምንድን ነው? እናንተስ ስለ ጉዳዩ እንዴት ይሰማችኋል?
◻ ትምህርት ቤት አንድ ሰው የማሰብ ችሎታውን እንዲያዳብር የሚረዳው እንዴት ነው?
◻ ትምህርት ማቋረጥ ወደፊት ሥራ የማግኘት አጋጣሚያችሁን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው? ለምንስ?
◻ ትምህርት አጠናቅቆ ከመጨረስ ሊገኙ የሚችሉ ሌሎች ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 135 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እዚያ ተጎልቼ የባሰ እየደደብኩ እንደምሄድ ስለ ተሰማኝ ጥዬ ወጣሁ”
[በገጽ 138 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የወጥ ቤትነት ሥራ ለመሥራት በግምት የሰባተኛ ክፍል የንባብ ችሎታ፣ የመካኒክነት ሥራ ለመሥራት የስምንተኛ ክፍል ደረጃ፣ የዕቃ ሻጭነት ሥራ ለመሥራት ደግሞ የዘጠነኛ ወይም የአሥረኛ ክፍል ደረጃ እንደሚያስፈልግ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት ያመለክታል”
[በገጽ 136 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በትምህርት ቤት የምትማሩት ሥርዓት አክባሪነት ለቀሪው ሕይወታችሁ ሊጠቅማችሁ ይችላል
[በገጽ 137 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትምህርት ቤት የሚሰጡትን መሠረታዊ ችሎታዎች አጣርተው የማያውቁ ወጣቶች ሥራ የማግኘት ዕድላቸው በጣም የመነመነ ይሆናል