የብቸኝነት ስሜት እንዲለቀኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
ምዕራፍ 14
የብቸኝነት ስሜት እንዲለቀኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
ዕለቱ ቅዳሜ ማታ ነው። ወጣቱ በክፍሉ ውስጥ ብቻውን ተቀምጧል።
“ቅዳሜና እሁዶችን እጠላቸዋለሁ!” ብሎ ጮኸ። ነገር ግን በክፍሉ ውስጥ መልስ የሚሰጥ ሰው አልነበረም። አንድ መጽሔት አነሳና ወጣቶች በቡድን ሆነው በባሕር ዳር የተነሱትን ፎቶግራፍ ተመለከተ። መጽሔቱን ወደ ግድግዳው ወረወረው። እንባው መጣበት። ከንፈሩን ነከሰ። እንባውን ግን ሊገታ አልቻለም። እንባውን ለመቋቋም ባለመቻሉ አልጋው ላይ ወደቀና እየተንሰቀሰቀ “ሁልጊዜ ሰዎች ነጥለው የሚተዉኝ ለምንድን ነው?” አለ።
እናንተም አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ይሰማችኋልን? ከመላው ዓለም የተነጠላችሁ፣ ብቸኞች፣ ዋጋ ቢሶችና ባዶ እንደሆናችሁ ይሰማችኋልን? እንዲህ የሚሰማችሁ ከሆነ ተስፋ አትቁረጡ። የብቸኝነት ስሜት የሚያስደስት ባይሆንም የሚገድል በሽታ አይደለም። ባጭር አነጋገር የብቸኝነት ስሜት የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው። ረሀብ ምግብ መብላት እንዳለባችሁ ይነግራችኋል። የብቸኝነት ስሜት ደግሞ ከሰው ጋር መወዳጀት፣ መቀራረብና የቅርብ ወዳጅ እንደሚያስፈልጋችሁ ያስታውቃችኋል። ደህና ሆነን ሥራችንን ለማከናወን ምግብ ያስፈልገናል። በተመሳሳይም ደህና ስሜት እንዲኖረን ከሰዎች ጋር መጎዳኘት ያስፈልገናል።
የከሰል ፍም የሚነድበት ምድጃ ተመልክታችሁ ታውቃላችሁን?
አንዱን ከሰል ብቻ ነጥላችሁ ከምድጃው ላይ ብታነሱት የዚህ ነጠላ ከሰል ፍም እየጠፋ ይሄዳል። ይህን ነጠላ ከሰል ወደምድጃው ብትመልሱት ግን እንደገና መፋም ይጀምራል! እኛ ሰዎችም ከሌሎች ሰዎች ከተነጠልን ረዘም ላለ ጊዜ “ልንፍም” ወይም በጥሩ ሁኔታ ተግባራችንን ልናከናውን አንችልም። ከሰው ጋር የመጎዳኘት ፍላጎት በተፈጥሮ በውስጣችን የተቀረጸ ባሕርይ ነው።ለብቻ ሆኖ ብቸኛ አለመሆን
ደራሲው ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ “ብቸኛ የመሆንን ያህል ሊጎዳኙት የሚገባ ጓደኛ አላገኘሁም” በማለት ጽፈዋል። እናንተስ በዚህ አባባል ትስማማላችሁን? “አዎን” ይላል የ20 ዓመቱ ቢል። “ተፈጥሮን እወዳለሁ። አንዳንድ ጊዜ በትንሿ ጀልባዬ ላይ ሆኜ በሐይቅ ላይ እጓዛለሁ። እዚያም ብቻዬን ለብዙ ሰዓቶች እቀመጣለሁ። በሕይወቴ ምን እየሠራሁበት እንዳለሁ እንድመረምር የሚያስችለኝ ጊዜ አገኛለሁ። ይህ በእርግጥ ትልቅ ነገር ነው።” የሀያ አንድ ዓመቱ ስቴቨንም ከቢል ጋር የሚስማማ ሐሳብ አለው። “የምኖረው በአንድ ትልቅ አፓርታማ ሕንፃ ውስጥ ነው” ይላል። “ታዲያ አንዳንድ ጊዜ ብቻዬን ለመሆን ብዬ ወደ ሕንፃው ጣራ እወጣለሁ። እዚያም ሆኜ አንዳንድ ነገሮችን አስባለሁ፤ እጸልያለሁ። ይህም አእምሮዬን ያድስልኛል።”
አዎን፣ ብቻችንን የምንሆንባቸው ጊዜያት በሚገባ ከተጠቀምንባቸው ጥልቅ እርካታ ሊሰጡን ይችላሉ። ኢየሱስም ለብቻው በሚሆንባቸው ጊዜያት ይደሰት ነበር:- “[ኢየሱስ] ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ።” (ማርቆስ 1:35) ይሖዋ ‘ሰው አልፎ አልፎ ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም’ ብሎ እንዳልተናገረ አስታውሱ። ከዚህ ይልቅ አምላክ የተናገረው ሰው “ብቻውን መኖሩ” መልካም አይደለም ብሎ ነው። (ዘፍጥረት 2:18–23 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርገው ለረዥም ጊዜ ከሰው ተነጥሎ መኖር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ራሱን የሚነጥል የራሱን የራስ ወዳድነት ምኞት ይከተላል፤ ተግባራዊ የሆነ ጥበብን ሁሉ ይጥሳል” በማለት ያስጠነቅቃል።— ምሳሌ 18:1 አዓት
ጊዜያዊ ብቸኝነት
አንዳንድ ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ወደ አዲስ ሥፍራ በመዛወራችን ምክንያት ከቅርብ ወዳጆቻችን በመራቃችንና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከቁጥጥራችን ውጭ በሆነ ሁኔታ ሳንወድ በግድ ይመጣብናል። ስቴቨን ሲናገር “በትውልድ ሥፍራዬ ሳለሁ ጄምስና እኔ ከወንድማማች የጠበቀ ጓደኝነት ነበረን። እኔ ከዚያ ስለቅ እንደምናፍቀው አውቅ ነበር” ብሏል። ስቴቨን ከጓደኛው የተለየበት ጊዜ በዓይነ ሕሊናው እየታየው ንግግሩን ቆም አድርጎ ላንዳፍታ በሐሳብ ተዋጠ። “በአውሮፕላን ላይ ልሳፈር ስል እንባ አነቀኝ። ተቃቀፍንና ከዚያም ጥየው ሄድኩ። አንድ ውድ የሆነ ነገር እንዳጣሁ ተሰምቶኝ ነበር።”
ስቴቨን አዲሱን አካባቢውን እንዴት አገኘው? “በጣም አስቸጋሪ ነበር” ይላል። “በአገሬ ሳለሁ ጓደኞቼ ሁሉ ይወዱኝ ነበር። እዚህ ግን የሥራ ባልደረቦቼ ከሆኑት አንዳንዶቹ ለምንም የማልረባ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገውኛል። ሰዓቱን እየተመለከትሁ አራት ሰዓት ወደኋላ እቆጥርና (ስቴቨን ባለበት አዲስ አካባቢና በትውልድ አገሩ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት አራት ሰዓት ስለሆነ ነው) አሁን ይኼኔ ጄምስና እኔ ምን እንሠራ ነበር እያልኩ አስብ የነበረበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። በጣም ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር።”
ነገሮች አልሰምር ሲሉ ባለፈው ጊዜ ባሳለፍነው ጥሩ ዘመን ትዝታ መኖር እናዘወትራለን። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ ብለህ አትናገር” ይላል። (መክብብ 7:10) ይህ ምክር የተሰጠው ለምንድን ነው?
መጀመሪያ ነገር ሁኔታዎች ሊሻሻሉ ስለሚችሉ ነው። ብዙውን ጊዜ ስለ ጉዳዩ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች “ጊዜያዊ ብቸኝነት” የሚሉት ለዚህ ነው። ስቴቨን የብቸኝነት ስሜቱን ሊያሸንፍ የቻለው ለዚህ ነው።
እንዴት ሊያሸንፍ ቻለ? “ስለሚሰማኝ ነገር ለሚያስብልኝ ሰው መናገሬ በጅቶኛል። ላለፈው ጊዜ መኖር አይቻልም። ከሌሎች ሰዎች ጋር ለመገናኘትና ለእነርሱም ሞቅ ያለ ስሜት ለማሳየት ራሴን አስገደድኩ። ይህም ጠቅሞኛል። አዲስ ጓደኞች አገኘሁ።” ጄምስስ? ‘ተሳስቼአለሁ። በቦታ መለያየታችን ወዳጅነታችንን አላጠፋውም። በቀደም ደወልኩለትና ለአንድ ሰዓት ከ15 ደቂቃ ያህል አወራን።’ሥር የሰደደ የብቸኝነት ስሜት
ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የሚያብከነክን የብቸኝነት ስሜት አልለቅ ሊለንና መፍትሔ የሌለው ሊመስል ይችላል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነው ሮኒ “በዚህ ቀበሌ ለስምንት ዓመት ያህል እየተመላለስኩ ተምሬያለሁ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን አንድም ጓደኛ አላፈራሁም! . . . ምን እንደሚሰማኝ የሚያውቅም ሆነ ለማወቅ ደንታ ያለው ሰው የለም። አንዳንድ ጊዜ ልታገሠው ከምችለው በላይ ይሆንብኛል!” በማለት ተናግሯል።
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ልክ እንደ ሮኒ ሥር የሰደደ ከባድ የብቸኝነት ስሜት ያጋጥማቸዋል። ይህም ከጊዜያዊ ብቸኝነት ይበልጥ ከባድ ነው። እንዲያውም ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሁለቱ ማለትም ጊዜያዊውና ሥር የሰደደው የብቸኝነት ስሜት “የተራ ጉንፋንና የሳምባ ምችን ያህል የተለያዩ ናቸው።” ይሁን እንጂ የሳምባ ምች ሊድን እንደሚችል ሁሉ ሥር የሰደደ የብቸኝነት ስሜትንም ማሸነፍ ይቻላል። ለዚህም የመጀመሪያው እርምጃ ምክንያቱን መረዳት ነው። (ምሳሌ 1:5) የ16 ዓመቷ ሮንዳ ሥር ለሰደደ የብቸኝነት ስሜት ዋና መንስኤ የሆነውን ነገር ስትገልጽ “የብቸኝነት ስሜት በጣም ሊያጠቃኝ የቻለበት ምክንያት ስለ ራሴ መጥፎ ግምት ስላለኝና በዚህም ምክንያት ጓደኛ ማፍራት ስላልቻልኩ ይመስለኛል። ራሴን እምብዛም የምወደው አይመስለኝም” ብላለች።— ሎንሊ ኢን አሜሪካ
የሮንዳ የብቸኝነት ስሜት ከውስጥ የመጣ ነው። ለራሷ ያላት ዝቅተኛ ቆላስይስ 3:9–12
ግምት ራሷን ለሌሎች አስተዋውቃ ጓደኝነት እንዳትመሠርት እንቅፋት ሆኖባታል። አንድ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል:- “ሥር የሰደደ የብቸኝነት ስሜት ባጠቃቸው ሰዎች መካከል ‘አላምርም’ ‘አልረባም’ ብሎ ማሰብ የተለመደ ነገር ነው።” የብቸኝነት ስሜታችሁን ለማሸነፍ ዋናው አስፈላጊ ነገር ለራሳችሁ ያላችሁን ግምት በማሳደግ ላይ የተመካ ነገር ነው። (ምዕራፍ 12ን ተመልከቱ።) በደግነት፣ በትሕትናና በገርነት ተለይቶ የሚታወቀውን መጽሐፍ ቅዱስ “አዲሱ ሰው” በማለት የሚጠራውን ባሕርይ ስታሳድጉ ለራሳችሁ የሚኖራችሁ ግምት እንደሚያድግ የተረጋገጠ ነገር ነው!—በተጨማሪም ራሳችሁን መውደድ እየተማራችሁ ስትሄዱ ሌሎች ሰዎች ማራኪ በሆኑት ጠባዮቻችሁ መሳብ ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ የአንድን አበባ ሙሉ የቀለም ድምቀት ማየት የምትችሉት ከፈካ በኋላ እንደሆነ ሁሉ ሌሎችም ጠባዮቻችሁን ሙሉ በሙሉ ሊያደንቁላችሁ የሚችሉት ራሳችሁን ለሌሎች ግልጽ ስታደርጉ ብቻ ነው።
ጭውውት መጀመር የሚቻለው እንዴት ነው?
‘የብቸኝነት ስሜት ላጠቃው ሰው መሰጠት ያለበት ከሁሉ የተሻለው ምክር’ ይላል በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜንታል ሄልዝ ያቀረበው ጽሑፍ ‘ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘትና መነጋገር’ ነው። ይህ ምክር መጽሐፍ ቅዱስ ‘ልባችንን እንድናሰፋ’ ወይም የሌላውን ሰው ችግር እንደራሳችን ችግር አድርገን እንድንመለከት ከሚሰጠው ምክር ጋር ይስማማል። (2 ቆሮንቶስ 6:11–13፤ 1 ጴጥሮስ 3:8) የተፈለገውን ውጤት የሚያስገኝ ምክር ነው። ለሌሎች ማሰብ አእምሯችሁን ከራሳችሁ የብቸኝነት ስሜት ከማላቀቁም በላይ ሌሎች ለእናንተ ሞቅ ያለ ስሜት እንዲኖራቸው ያነሳሳቸዋል።
በመሆኑም የአሥራ ዘጠኝ ዓመቷ ናታሊ ሌሎች ሰዎች ሰላምታ እስኪሰጧት ቁጭ ብላ ከመጠበቅ የበለጠ ነገር ለማድረግ ወሰነች። ‘እኔም የወዳጅነት ስሜት ማሳየት አለብኝ’ ትላለች። ‘አለበለዚያ ሰዎች ኩራተኛ የሆንኩ ይመስላቸዋል።’ ስለዚህ ፈገግ በማለት ጀምሩ። ሌላው ሰውም ፈገግታችሁን በማየት አጸፋውን ይመልስላችኋል።
ምሳሌ 11:25 አዓት
ቀጥሎም ጭውውት ጀምሩ። 15 ዓመት የሆናት ሊሊያን “ለመጀመሪያ ጊዜ እንግዳ የሆኑ ሰዎችን ቀርቦ ማነጋገር በጣም ያስፈራኝ ነበር። አይፈልጉኝ ይሆናል ብዬ እፈራ ነበር” ስትል ገልጻለች። ታዲያ ሊሊያን ጭውውት የምትጀምረው እንዴት ነው? እንዲህ ትላለች:- “‘ከየት መጣሽ?’ ‘እገሊትን ታውቂያታለሽ?’ የሚሉትን የመሳሰሉ ቀላል ጥያቄዎችን እጠይቃለሁ። የጠየቅኳትን ልጅ እርሷም ልታውቃት ትችላለች። በዚህ መንገድ ብዙም ሳንቆይ ሞቅ ያለ ጨዋታ እንጀምራለን።” ደግነትን የሚያሳዩ ነገሮችን ማድረግና የለጋስነት መንፈስ ማሳየት ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ሊረዳችሁ ይችላል።—ከዚህም ሌላ በማንኛውም ጊዜ የማይተዋችሁ ጓደኛ ሊኖራችሁ እንደሚችል አስታውሱ። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም” በማለት ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 16:32) ለእናንተም ቢሆን ይሖዋ ከማንም የበለጠ የቅርብ ወዳጃችሁ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ፍጥረቶቹን አስተውላችሁ በመመልከት ባሕርዮቹን ለማወቅ ጣሩ። በጸሎት አማካኝነት ከእርሱ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጠንክሩ። ከይሖዋ አምላክ ጋር የምትመሠርቱት ወዳጅነት የኋላ ኋላ ለብቸኝነት ስሜታችሁ ከሁሉ የበለጠ መፍትሔ ይሆናል።
አሁንም አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት የሚያጠቃችሁ ከሆነ አትጨነቁ። ይህ ዓይነቱ ስሜት የተለመደ ነው። ይሁንና ከመጠን በላይ የሆነ ዓይን አፋርነት ጓደኞች እንዳታፈሩና ከሌሎች ጋር እንዳትወዳጁ ቢያደርጋችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ ለብቻ መሆን ሁልጊዜ መጥፎ ነው ሊባል ይቻላልን? ለብቻ ከመሆን የሚገኙ ጥቅሞች አሉን?
◻ አብዛኛው የብቸኝነት ስሜት ጊዜያዊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ በእናንተ ላይ ደርሷልን?
◻ ሥር የሰደደ የብቸኝነት ስሜት ምንድን ነው? እርሱንስ ልትዋጉ የምትችሉት እንዴት ነው?
◻ ከሌሎች ጋር ‘ጭውውት ለመጀመር’ የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? እናንተንስ የረዳችሁ ምን ነበር?
[በገጽ 119 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘የብቸኝነት ስሜት ላጠቃው ሰው መሰጠት ያለበት ከሁሉ የተሻለው ምክር’ ይላል የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜንታል ሄልዝ ያቀረበው ጽሑፍ ‘ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘትና መነጋገር’ ነው
[በገጽ 116, 117 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጓደኛሞች ተራርቀው ቢኖሩም ግንኙነታቸው እንዳይቋረጥ ማድረግ ይችላሉ
[በገጽ 118 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብቻችንን የምንሆንባቸው ጊዜያት አስደሳች ሊሆኑ ይችላሉ